ምሳሌ 15:1-9
ምሳሌ 15:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ቍጣ ጥበበኞችን ታጠፋለች፤ የለዘበ ቃል ቍጣን ይመልሳል፥ ሻካራ ቃል ግን ጠብን ያነሣሣል። የጠቢባን ምላስ መልካም ነገርን ታውቃለች፤ የአላዋቂዎች አፍ ግን ክፋትን ይናገራል። የእግዚአብሔር ዐይኖች በሁሉ ቦታ ናቸው፤ ክፉዎችንና ደጎችንም ይመለከታሉ። ፈዋሽ ምላስ የሕይወት ዛፍ ነው፤ የሚጠብቀው ግን የዕውቀት መንፈስን ይሞላል። አላዋቂ ልጅ የአባቱን ተግሥጽ ያቃልላል፤ ተግሣጽን የሚጠብቅ ግን ዐዋቂ ነው። እውነት ከበዛ ዘንድ ብዙ ኀይል አለ፥ ኀጢአተኞች ግን ከምድር ገጽ ይጠፋሉ፥ በጻድቃን ቤቶች ብዙ ኀይል አለ፥ የኀጢአተኞች ፍሬ ግን ይጠፋል። የጠቢባን ከንፈሮች በዕውቀት የታሰሩ ናቸው፤ የሰነፎች ልብ ግን የጸና አይደለም። የክፉዎች መሥዋዕት በእግዚአብሔር ዘንድ የረከሰ ነው፤ የቅኖች ጸሎት ግን በእርሱ ዘንድ የተወደደ ነው። የክፉዎች መንገድ በእግዚአብሔር ዘንድ የረከሰ ነው፤ ጽድቅን የሚከተሉትን ግን እግዚአብሔር ይወድዳቸዋል።
ምሳሌ 15:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የለዘበ መልስ ቍጣን ያበርዳል፤ ክፉ ቃል ግን ቍጣን ይጭራል። የጠቢብ አንደበት ዕውቀትን ታወድሳለች፤ የተላሎች አንደበት ግን ቂልነትን ያፈልቃል። የእግዚአብሔር ዐይኖች በሁሉም ስፍራ ናቸው፤ ክፉዎችንም ደጎችንም ነቅተው ይመለከታሉ። ፈውስ የምታመጣ ምላስ የሕይወት ዛፍ ናት፤ አታላይ ምላስ ግን መንፈስን ትሰብራለች። ተላላ የአባቱን ምክር ይንቃል፤ መታረምን የሚቀበል ግን አስተዋይነቱን ያሳያል። የጻድቃን ቤት በብዙ ሀብት የተሞላ ነው፤ የክፉዎች ገቢ ግን መከራን ታመጣባቸዋለች። የጠቢባን ከንፈር ዕውቀትን ታስፋፋለች፤ የተላሎች ልብ ግን እንዲህ አይደለም። እግዚአብሔር የክፉዎችን መሥዋዕት ይጸየፋል፤ የቅኖች ጸሎት ግን ደስ ያሰኘዋል። እግዚአብሔር የክፉዎችን መንገድ ይጸየፋል፤ ጽድቅን የሚከታተሉትን ግን ይወድዳቸዋል።
ምሳሌ 15:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ልዝብ አነጋገር ቊጣን ያስታግሣል፤ የቊጣ አነጋገር ግን ቊጣን ያባብሳል። የጠቢባን አንደበት ዕውቀትን ያፈልቃል። የሞኞች አፍ ግን ሞኝነትን ይለፈልፋል። እግዚአብሔር በየቦታው የሚደረገውን ነገር ሁሉ ያያል። መልካምም ሆነ ክፉ ድርጊትን ይመለከታል። ለስላሳ አነጋገር ሕይወትን ይሰጣል። ተንኰል የተሞላበት አነጋገር ግን መንፈስን ይሰብራል። ሞኝ የአባቱን ምክር ይንቃል፤ ተግሣጽን የሚቀበል ግን አስተዋይ ነው። የደጋግ ሰዎች ቤት በብዙ ሀብት የተሞላ ይሆናል፤ የክፉ ሰዎች ገቢ ግን ችግርን ያመጣባቸዋል። ዕውቀት የሚስፋፋው በብልኆች እንጂ በሞኞች አይደለም። እግዚአብሔር ኃጢአተኞች የሚያቀርቡለትን መሥዋዕት ይጸየፋል፤ የልበ ቅኖች ጸሎት ግን ደስ ያሰኘዋል። እግዚአብሔር የክፉ ሰዎችን መንገድ ይጠላል፤ ቅን አድራጊዎችን ግን ይወዳል።
ምሳሌ 15:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የለዘበች መልስ ቁጣን ትመልሳለች፥ ሸካራ ቃል ግን ቁጣን ታስነሣለች። የጠቢባን ምላስ እውቀትን ያሳምራል፥ የሰነፎች አፍ ግን ስንፍናን ያፈልቃል። የጌታ ዐይኖች በስፍራ ሁሉ ናቸው፥ ክፉዎችንና ደጎችን ይመለከታሉ። ፈዋሽ ምላስ የሕይወት ዛፍ ነው፥ የጠማማ ምላስ ግን ነፍስን ይሰብራል። ሰነፍ የአባቱን ተግሣጽ ይንቃል፥ ዘለፋን የሚቀበል ግን አእምሮው የበዛ ነው። በጻድቅ ሰው ቤት ብዙ ኃይል አለ፥ የኀጥእ ሰው መዝገብ ግን ሁከት ነው። የጠቢባን ከንፈር እውቀትን ትዘራለች፥ የሰነፎች ልብ ግን እንዲህ አይደለም። የኀጥኣን መሥዋዕት በጌታ ዘንድ አስጸያፊ ነው፥ የቅኖች ጸሎት ግን በእርሱ ዘንድ የተወደደ ነው። የኀጥኣን መንገድ በጌታ ዘንድ አስጸያፊ ነው፥ እርሱ ግን ጽድቅን የሚከተል ይወድዳል።