የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ምሳሌ 15:1-9

መጽሐፈ ምሳሌ 15:1-9 አማ2000

ቍጣ ጥበበኞችን ታጠፋለች፤ የለዘበ ቃል ቍጣን ይመልሳል፥ ሻካራ ቃል ግን ጠብን ያነሣሣል። የጠቢባን ምላስ መልካም ነገርን ታውቃለች፤ የአላዋቂዎች አፍ ግን ክፋትን ይናገራል። የእግዚአብሔር ዐይኖች በሁሉ ቦታ ናቸው፤ ክፉዎችንና ደጎችንም ይመለከታሉ። ፈዋሽ ምላስ የሕይወት ዛፍ ነው፤ የሚጠብቀው ግን የዕውቀት መንፈስን ይሞላል። አላዋቂ ልጅ የአባቱን ተግሥጽ ያቃልላል፤ ተግሣጽን የሚጠብቅ ግን ዐዋቂ ነው። እውነት ከበዛ ዘንድ ብዙ ኀይል አለ፥ ኀጢአተኞች ግን ከምድር ገጽ ይጠፋሉ፥ በጻድቃን ቤቶች ብዙ ኀይል አለ፥ የኀጢአተኞች ፍሬ ግን ይጠፋል። የጠቢባን ከንፈሮች በዕውቀት የታሰሩ ናቸው፤ የሰነፎች ልብ ግን የጸና አይደለም። የክፉዎች መሥዋዕት በእግዚአብሔር ዘንድ የረከሰ ነው፤ የቅኖች ጸሎት ግን በእርሱ ዘንድ የተወደደ ነው። የክፉዎች መንገድ በእግዚአብሔር ዘንድ የረከሰ ነው፤ ጽድቅን የሚከተሉትን ግን እግዚአብሔር ይወድዳቸዋል።