የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ምሳሌ 15

15
1ልዝብ አነጋገር ቊጣን ያስታግሣል፤
የቊጣ አነጋገር ግን ቊጣን ያባብሳል።
2የጠቢባን አንደበት ዕውቀትን ያፈልቃል።
የሞኞች አፍ ግን ሞኝነትን ይለፈልፋል።
3እግዚአብሔር በየቦታው የሚደረገውን ነገር ሁሉ ያያል።
መልካምም ሆነ ክፉ ድርጊትን ይመለከታል።
4ለስላሳ አነጋገር ሕይወትን ይሰጣል።
ተንኰል የተሞላበት አነጋገር ግን መንፈስን ይሰብራል።
5ሞኝ የአባቱን ምክር ይንቃል፤
ተግሣጽን የሚቀበል ግን አስተዋይ ነው።
6የደጋግ ሰዎች ቤት በብዙ ሀብት የተሞላ ይሆናል፤
የክፉ ሰዎች ገቢ ግን ችግርን ያመጣባቸዋል።
7ዕውቀት የሚስፋፋው በብልኆች እንጂ በሞኞች አይደለም።
8እግዚአብሔር ኃጢአተኞች የሚያቀርቡለትን መሥዋዕት ይጸየፋል፤
የልበ ቅኖች ጸሎት ግን ደስ ያሰኘዋል።
9እግዚአብሔር የክፉ ሰዎችን መንገድ ይጠላል፤
ቅን አድራጊዎችን ግን ይወዳል።
10ትክክለኛውን መንገድ ትቶ ስሕተት የሆነ ነገር የሚያደርግ ይቀጣል፤
ተግሣጽንም የሚጠላ ይጠፋል።
11እግዚአብሔር በሲኦልና በጥፋት ቦታ ያለውን የሚያይ ከሆነ
በልባችን ውስጥ ያለውንማ እንዴት አያይም?
12ፌዘኛ ተግሣጽን አይወድም፤
ከጠቢባንም ምክርን አይጠይቅም።
13የልብ ደስታ ፊትን ያበራል፤
የልብ ሐዘን ግን መንፈስን ያደቃል።
14አስተዋይ አእምሮ ያለው ሰው ዕውቀትን ይፈልጋል፤
ሞኞች ግን በድንቊርናቸው ይረካሉ።
15የጭቊን ኑሮ ዘወትር ጐስቋላ ነው፤
ደስተኞች ሰዎች ግን ዘወትር በኑሮአቸው ይረካሉ።
16ሀብታም ሆኖ በሁከት ከመኖር
ድኻ ሆኖ እግዚአብሔርን በማክበር መኖር ይሻላል።
17ጥላቻ ባለበት ስፍራ ጮማ ሥጋ ከመብላት
ፍቅር ባለበት ስፍራ ጎመን መብላት ይሻላል።
18ቊጣ ጭቅጭቅን ያነሣሣል፤
ትዕግሥት ግን ጠብን ያበርዳል።
19የሰነፍ መንገድ በችግር እሾኽ የታጠረ ነው፤
የቅን ሰው መንገድ ግን እንደ ተስተካከለ ጐዳና ነው።
20ብልኅ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤
ሞኝ ልጅ ግን እናቱን ይንቃል።
21ማስተዋል የጐደላቸው ሰዎች በሞኝነታቸው ይደሰታሉ፤
ብልኆች ግን ትክክል የሆነውን ነገር ያደርጋሉ።
22መልካም ምክርን ብትቀበል ሁሉ ነገር ይሳካልሃል፤
ምክርን ባትቀበል ግን ምንም ነገር አይሳካልህም።
23ተገቢውን ቃል በተገቢው ቦታ መናገር እጅግ ያስደስታል።
24ብልኾች ወደ ላይ በሚያመራው በሕይወት መንገድ ይሄዳሉ እንጂ፥
ወደ ታች በሚያወርደው በሞት መንገድ አይሄዱም።
25እግዚአብሔር የትዕቢተኞችን ቤት ይደመስሳል፤
ባልዋ የሞተባትን ሴት ድንበር እንዳይገፋ ይጠብቃል።
26እግዚአብሔር ክፉ ሐሳብን ይጠላል፤
ንጹሕ በሆነ ቃል ግን ደስ ይለዋል።
27በማጭበርበር ትርፍ ለማግኘት ብትሞክር
ቤተሰብህን በችግር ላይ ትጥላለህ፤
ጉቦ አትቀበል፤ ለረጅም ዘመንም ትኖራለህ።
28ደጋግ ሰዎች ከመናገራቸው በፊት ያስባሉ፤
ክፉዎች ግን በችኰላ ክፉ ቃል ይናገራሉ።
29እግዚአብሔር ከክፉዎች የራቀ ነው፤
ደጋግ ሰዎች ሲጸልዩ ግን ይሰማቸዋል።
30በፈገግታ የተሞላ ፊት ልብን ያስደስታል፤
የምሥራች ቃልም አጥንትን ያለመልማል።
31ሕይወት የሚሰጥ ምክር የሚቀበል
የጠቢባን ጓደኛ ይሆናል።
32ተግሣጽን የሚጠላ ራሱን ይጐዳል።
ተግሣጽን የሚቀበል ግን ጥበብን ይጨምራል።
33እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብን የሚሰጥ ትምህርት ነው፤
ክብርን ለማግኘት በቅድሚያ ትሑት መሆን ያስፈልጋል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ