ምሳሌ 14:1-35

ምሳሌ 14:1-35 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ብልሆች ሴቶች ቤቶችን ይሠራሉ፤ ሰነፎች ሴቶች ግን በእጃቸው ያፈርሳሉ። በቅንነት የሚሄድ ሰው እግዚአብሔርን ይፈራል፤ መንገዱን የሚያጣምም ግን ይናቃል። ከሰነፎች አፍ የስድብ በትር ይወጣል፤ የጠቢባን ከንፈር ግን ትጠብቃቸዋለች። በሬዎች በሌሉበት ስፍራ በረቱ ንጹሕ ነው፤ ብዙ እህል ግን በበሬዎች ኀይል ይገኛል። የታመነ ምስክር አይዋሽም፤ የሐሰት ምስክር ግን ሐሰትን ያቀጣጥላል። በክፉዎች ዘንድ ጥበብን ትፈልጋለህ፥ አታገኛትምም፤ ዕውቀት ግን በብልሆች ዘንድ በቀላሉ ይገኛል። በሰነፍ ሰው ፊት ሁሉ ጠማማ ነው፥ የብልሆች ከንፈር ግን የዕውቀት ጋሻ ነው። የዐዋቂዎች ጥበብ መንገዳቸውን ታውቃለች፤ የሰነፎች ስንፍና ግን ወደ ስሕተት ይመራል። የኃጥኣን ቤቶች መንጻትን ይሻሉ፥ የጻድቃን ቤቶች ግን የተወደዱ ናቸው። የዐዋቂ ሰው ልብ ለሰውነቱ ኀዘን ነው፤ ደስ ባለውም ጊዜ ከጥል ጋር ግንኙነት የለውም። የክፉዎች ቤቶች ይፈርሳሉ፤ የቅኖች ማደሪያዎች ግን ይጸናሉ። በሰዎች ዘንድ ቅን የምትመስል መንገድ አለች፤ ፍጻሜዋ ግን ወደ ሲኦል ጕድጓድ ታደርሳለች። ከደስታ ጋር ኀዘን አይቀላቀልም፥ የደስታ ፍጻሜ ግን ወደ ኀዘን ይመለሳል። ልበ ትዕቢተኛ ከራሱ መንገድ ይጠግባል። ደግ ሰውም ከራሱ ዐሳብ ይጠግባል። የዋህ ነገርን ሁሉ ያምናል፤ ዐዋቂ ግን ወደ ንስሓ ይመለሳል። ብልህ ሰው ፈርቶ ከክፉ ይሸሻል፤ አላዋቂ ግን ራሱን ተማምኖ ከኃጥኣን ጋር አንድ ይሆናል። ቍጡ ሰው ያለምክር ይሠራል፤ ብልህ ግን ብዙ ይታገሣል። አላዋቂዎች ሰዎች ክፋትን ይካፈላሉ፤ ዐዋቂዎች ሰዎች ግን ማስተዋልን ፈጥነው ይይዟታል። ክፉዎች በደጎች ፊት ይሰነካከላሉ፥ ኃጥኣን ግን በጻድቃን በር ያገለግላሉ። ባለጠጎች ወዳጆች ድሆች ወዳጆችን ይጠላሉ፤ የባለጠጎች ወዳጆች ግን ብዙዎች ናቸው። ድሃውን የሚንቅ ኀጢአትን ይሠራል፤ ለድሃ የሚራራ ግን ብፁዕ ነው። ስሕተተኞች ክፉን ያስባሉ፤ ደጋጎች ግን ምሕረትንና እውነትን ያስባሉ። ክፋትንም የሚሠሩ ምሕረትንና ይቅርታን አያውቁም። ነገር ግን ታማኝነትና ቸርነት ደግ በሚሠሩ ዘንድ ናቸው። በሁሉ ነገር ጠንቃቃ ለሆነ ብዙ ትርፍ አለው። ደስታን ፈላጊና ሰነፍ ግን ችግረኛ ነው። ዐዋቂ ሰው የጠቢባን ዘውድ ነው፤ የአላዋቂዎች ተግባር ግን ክፉ ነው። እውነተኛ ምስክር ነፍስን ከክፉ ያድናል፥ ሐሰተኛ ግን ሐሰትን ያቀጣጥላል። እግዚአብሔርን ለሚፈራ ጽኑዕ ተስፋ አለው፥ ለልጆቹም መጠጊያን ይተዋል። የእግዚአብሔር ትእዛዝ የሕይወት ምንጭ ነው። ሰዎችንም ከሞት ወጥመድ እንዲያመልጡ ያደርጋል። የንጉሥ ክብር በሕዝብ ብዛት ነው፤ የገዥ ውድቀት ግን በሕዝብ ማነስ ነው። ትዕግሥተኛ ሰው ጥበብ የበዛለት ይሆናል፤ ትዕግሥት የጐደለው ሰው ግን ሰነፍ ነው፤ የሚያስታርቅ ሰው የልብ ፈዋሽ ነው፤ ቀናተኛ ልብ ግን ለአጥንት ነቀዝ ነው። ድሃን የሚያስጨንቅ ፈጣሪውን ያስቈጣዋል፤ ፈጣሪውን የሚያከብር ግን ለድሃ ምሕረትን ያደርጋል። ኃጥእ በክፋቱ ይወገዳል፤ በቸርነቱ የሚታመን ግን ጻድቅ ነው። በደግ ሰው ልብ ጥበብ ታድራለች፤ በአላዋቂ ሰው ልብ ግን አትታወቅም። ጽድቅ ሕዝብን ከፍ ከፍ ታደርጋለች፤ ኀጢአት ግን ሕዝብን ታሳንሳለች። አስተዋይ መልእክተኛ በንጉሥ ዘንድ የተወደደ ነው፤ በመልካም ጠባዩም ውርደትን ከራሱ ያርቃል።

ምሳሌ 14:1-35 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ጠቢብ ሴት ቤቷን ትሠራለች፤ ቂል ሴት ግን በገዛ እጇ ታፈርሰዋለች። አካሄዱ ቅን የሆነ ሰው እግዚአብሔርን ይፈራል፤ መንገዱ ጠማማ የሆነ ግን ይንቀዋል። የቂል ሰው ንግግር ለጀርባው በትር ታስከትልበታለች፤ የጥበበኛ ከንፈር ግን ትጠብቃቸዋለች። በሬዎች በሌሉበት በረቱ ባዶ ይሆናል፤ በበሬ ጕልበት ግን ብዙ ምርት ይገኛል። ታማኝ ምስክር አይዋሽም፤ ሐሰተኛ ምስክር ግን ውሸትን ይዘከዝካል። ፌዘኛ ጥበብን ይሻል፤ ሆኖም አያገኛትም፤ ዕውቀት ግን ለአስተዋዮች በቀላሉ ትገኛለች። ከሞኝ ሰው ራቅ፣ ከከንፈሮቹ ዕውቀት አታገኝምና። የአስተዋዮች ጥበብ መንገዳቸውን ልብ ማለት ነው፤ የሞኞች ቂልነት ግን መታለል ነው። ቂሎች በሚያቀርቡት የበደል ካሳ ያፌዛሉ፤ በቅኖች መካከል ግን በጎ ፈቃድ ትገኛለች። እያንዳንዱ ልብ የራሱን መራራ ሐዘን ያውቃል፤ ደስታውንም ማንም ሊጋራው አይችልም። የክፉዎች ቤት ይፈርሳል፤ የቅኖች ድንኳን ግን ይስፋፋል። ለሰው ቀና መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤ በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ያደርሳል። በሣቅ ጊዜ እንኳ ልብ ይተክዛል፤ ደስታም በሐዘን ሊፈጸም ይችላል። ልባቸውን ከጽድቅ የሚመልሱ የእጃቸውን ሙሉ ዋጋ ይቀበላሉ፤ ደግ ሰውም ወሮታውን ያገኛል። አላዋቂው ሰው ሁሉን ያምናል፤ አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል። ጠቢብ ሰው ጥንቁቅ ነው፤ ከክፉም ይርቃል፤ ሞኝ ግን ችኵልና ደንታ ቢስ ነው። ግልፍተኛ ሰው የቂል ተግባር ይፈጽማል፤ መሠሪም ሰው አይወደድም። አላዋቂዎች ቂልነትን ይወርሳሉ፤ አስተዋዮች ግን ዕውቀትን እንደ ዘውድ ይጭናሉ። ክፉዎች በደጎች ፊት፣ ኃጥኣንም በጻድቃን ደጅ ያጐነብሳሉ። ድኾችን ወዳጆቻቸው እንኳ ይጠሏቸዋል፤ ባለጠጎች ግን ብዙ ወዳጆች አሏቸው። ጎረቤቱን የሚንቅ ኀጢአት ይሠራል፤ ለተቸገሩት የሚራራ ግን ብፁዕ ነው። ክፉ ነገር የሚያቅዱ ከትክክለኛው መንገድ ይወጡ የለምን? በጎ ነገር የሚያቅዱ ግን ፍቅርንና ታማኝነትን ያተርፋሉ። ለፍተው የሠሩት ሁሉ ትርፍ ያስገኛል፤ ከንቱ ወሬ ግን ወደ ድኽነት ያመራል። ጠቢባን ብልጽግና ዘውዳቸው ነው፤ የሞኞች ቂልነት ግን ፍሬው ከንቱነት ነው። እውነተኛ ምስክር ሕይወት ያድናል፤ ሐሰተኛ ምስክር ግን አባይ ነው። እግዚአብሔርን የሚፈራ ጽኑ ዐምባ አለው፤ ልጆቹም መጠጊያ ይኖራቸዋል። እግዚአብሔርን መፍራት የሕይወት ምንጭ ነው፤ ሰውን ከሞት ወጥመድ ያድነዋል። የሕዝብ ብዛት የንጉሥ ክብር ሲሆን፣ የዜጎች ማነስ ግን ለገዥ መጥፊያው ነው። ታጋሽ ሰው ትልቅ ማስተዋል አለው፤ ግልፍተኛ ሰው ግን ቂልነትን ያሳያል። ሰላም ያለው ልብ ለሰውነት ሕይወት ይሰጣል፤ ቅናት ግን ዐጥንትን ያነቅዛል። ድኾችን የሚያስጨንቅ ፈጣሪያቸውን ይንቃል፤ ለተቸገሩ የሚራራ ሁሉ ግን አምላክን ያከብራል። ክፉዎች በክፋታቸው ይወድቃሉ፤ ጻድቃን ግን በሞት ጊዜ እንኳ መጠጊያ አላቸው። ጥበብ በአስተዋዮች ልብ ታድራለች፤ በሞኞች መካከል እንኳ ራሷን ትገልጣለች። ጽድቅ ሕዝብን ከፍ ከፍ ታደርጋለች፤ ኀጢአት ግን ለየትኛውም ሕዝብ ውርደት ነው። ጠቢብ አገልጋይ ንጉሥን ደስ ያሰኛል፤ አሳፋሪ አገልጋይ ግን ቍጣውን በራሱ ላይ ያመጣል።

ምሳሌ 14:1-35 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ጥበበኛ ሴት ቤትዋን በሥነ ሥርዓት ታስተዳድራለች፤ ሞኝ ሴት ግን በገዛ እጅዋ ታፈርሰዋለች። አካሄዱ ቀጥተኛ የሆነ ሰው እግዚአብሔርን ይፈራል፤ መንገዱ ጠማማ የሆነ ሰው ግን እግዚአብሔርን አይፈራም። ሞኝን የገዛ ንግግሩ ያስቀጣዋል፤ ጥበበኞችን ግን መልካም አነጋገራቸው ይጠብቃቸዋል። የምታርስባቸው በሬዎች ከሌሉህ ጐተራህ ባዶ ይሆናል። በሬዎች ካሉህ ግን ጐተራህ በእህል የተሞላ ይሆናል። ታማኝ ምስክር አይዋሽም፤ ሐሰተኛ ምስክር ግን የሚናገረው ሐሰት ነው። ፌዘኛ ሰው ጥበብን ይፈልጋል፤ አያገኛትም። አስተዋዮች ግን ዕውቀትን በቀላሉ ይገበያሉ። ከእነርሱ የምትማረው ምንም ዕውቀት ስለሌለ ከሞኞች ራቅ። የብልኅ ሰው ጥበብ መንገዱን እንዳይስት ያደርገዋል። ሞኝን ሰው ግን ሞኝነቱ መንገዱን እንዲስት ያደርገዋል። ሞኞች ኃጢአት ሲሠሩ በመጸጸት ፈንታ ያፌዛሉ፤ ደጋግ ሰዎች ግን ኃጢአታቸው ይቅር እንዲባልላቸው ይፈልጋሉ። ደስታህም ሆነ ሐዘንህ የራስህ ነው፤ ማንም የሚካፈልህ የለም። የክፉ ሰው ቤት ይፈርሳል፤ የደግ ሰው ቤት ግን ጸንቶ ይኖራል። አንተ “ትክክለኛ መንገድ ነው” ብለህ የምታስበው ወደ ሞት ይመራህ ይሆናል። በሳቅ ጊዜ እንኳ በልብ ውስጥ ሐዘን ሊኖር ይችላል፤ የደስታም ፍጻሜ ለቅሶ ነው። ከሐዲዎች ሰዎች የክፉ ሥራቸውን ዋጋ ይቀበላሉ፤ ደጋግ ሰዎች ግን የመልካም ሥራቸውን ዋጋ ያገኛሉ። ሞኝ ሰው የሚነግሩትን ሁሉ አምኖ ይቀበላል፤ ብልኆች ግን እርምጃቸውን በጥንቃቄ ይመረምራሉ። ብልኆች እግዚአብሔርን ስለሚፈሩ ከክፉ ነገር ለመራቅ ይጠነቀቃሉ፤ ሞኞች ግን ከአደጋ የማይጠነቀቁ ችኲሎች ናቸው። ቊጡ ሰው የሞኝነትን ሥራ ይሠራል፤ ጥበበኛ ግን ይታገሣል። አላዋቂዎች የስንፍናቸውን ዋጋ ይቀበላሉ፤ ብልኆች ግን ዕውቀትን እንደ አክሊል ይቀዳጃሉ። ክፉዎች በደጋግ ሰዎች ፊት ይንበረከካሉ፤ ኃጢአተኞች በጻድቃን ደጅ ያጐነብሳሉ። ድኻ ሰው በጐረቤቱ ዘንድ እንኳ የተጠላ ነው። ሀብታሞች ግን ብዙ ወዳጆች አሉአቸው። ሰዎችን የሚንቅ ኃጢአተኛ ነው፤ ለድኾች የሚራራ ግን የተባረከ ነው፤ ክፉ የሚያቅዱ ሰዎች ስሕተተኞች አይደሉምን? መልካምን ነገር የሚያቅዱ ግን ምሕረትንና ታማኝነትን ያገኛሉ። ተግቶ መሥራት ጥቅምን ያስገኛል፤ ወሬኛነት ግን ያደኸያል። የብልኆች ዘውድ ጥበባቸው ነው፤ የሞኞች ጌጥ ግን ሞኝነታቸው ነው። እውነትን የሚናገር ምስክር ሕይወትን ያድናል፤ ሐሰት የሚናገር ምስክር ግን አታላይ ነው። እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ለራሱና ለቤተሰቡ ጽኑ መታመኛና ዋስትና አለው። እግዚአብሔርን መፍራት የሕይወት ምንጭ ነው፤ ስለዚህ ከሞት ወጥመድ ለማምለጥ ከፈለግህ እግዚአብሔርን ፍራ። የንጉሥ ታላቅነት የሚለካው በሚያስተዳድራቸው ሕዝብ ብዛት ነው፤ የሚገዛው ሕዝብ ከሌለው ግን ለንጉሡ ጥፋት ነው። ትዕግሥተኛ ብትሆን አስተዋይ መሆንህን ትገልጣለህ፤ ቊጡ ብትሆን ግን ስንፍናህን ታሳያለህ። ሰላም ያለው አእምሮ ለሰውነት ጤንነትን ያስገኛል፤ ቅንአት ግን አጥንትን ያደቃል። ድኾችን ማስጨነቅ ፈጣሪን መናቅ ነው፤ ለድኾች ቸርነትን ማድረግ ግን እግዚአብሔርን እንደ ማክበር ይቈጠራል። ችግር ሲመጣ ክፉዎች ይወድቃሉ፤ ጻድቃን ግን በታማኝነታቸው ይጠበቃሉ። የአስተዋይ ሰው ልብ ጥበብን የተሞላ ነው፤ በሞኞች ልብ ግን ጥበብ አትታወቅም። እውነተኛነት አንድን ሕዝብ ታላቅ ያደርገዋል፤ ኃጢአት ግን ማንኛውንም ሕዝብ ያዋርዳል። ነገሥታት ችሎታ ባላቸው አገልጋዮች ይደሰታሉ፤ አሳፋሪ አገልጋዮች ግን ንጉሡን ያስቈጣሉ።

ምሳሌ 14:1-35 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ብልሃተኛ ሴት ቤትዋን ትሠራለች፥ ሰነፍ ሴት ግን በእጅዋ ታፈርሰዋለች። በቅን የሚሄድ ሰው ጌታን ይፈራል፥ መንገዱን የሚያጣምም ግን ይንቀዋል። በሰነፍ አፍ የትዕቢት በትር አለ፥ የጠቢባን ከንፈር ግን ትጠብቃቸዋለች። በሬ በሌለበት ስፍራ እህል አይገኝም፥ ብዙ ሲሳይ ግን በበሬዎች ኃይል ነው። የታመነ ምስክር አይዋሽም፥ የሐሰት ምስክር ግን በሐሰት ይናገራል። ፌዘኛ ሰው ጥበብን ይፈልጋል አያገኛትም፥ ለአስተዋይ ግን እውቀትን ማግኘት አያስቸግረውም። ከሰነፍ ሰው ፊት ራቅ፥ በእርሱ ዘንድ የእውቀትን ከንፈር አታገኝምና። የብልህ ሰው ጥበብ መንገዱን ያስተውል ዘንድ ነው፥ የሰነፎች ስንፍና ግን ሽንገላ ነው። ሰነፉ በኃጢአት ያፌዛል፥ በቅኖች መካከል ግን ቸርነት አለች። የራሱን ኀዘን ልብ ያውቃል፥ ከደስታውም ጋር ሌላ ሰው አይገናኝም። የኀጥኣን ቤት ይፈርሳል፥ የቅኖች ማደሪያ ግን ያብባል። ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፥ ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው። በሳቅ ደግሞ ልብ ያዝናል፥ የደስታም ፍጻሜ ልቅሶ ነው። ልቡን ከጽድቅ የሚመልስ ሰው ከመንገዱ ፍሬ ይጠግባል፥ ጻድቅም ሰው ደግሞ በራሱ። የዋህ ቃልን ሁሉ ያምናል፥ ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል። ጠቢብ ሰው ይፈራል ከክፉም ይሸሻል፥ ሰነፍ ግን ራሱን ታምኖ ይኰራል። ቁጡ ሰው በስንፍና ይሠራል፥ አስተዋይ ግን ይታገሣል። አላዋቂዎች ሰዎች ስንፍናን ይወርሳሉ፥ ብልሆች ግን እውቀትን እንደ ዘውድ ይጭናሉ። ኃጢአተኞች በደጎች ፊት ይጐነበሳሉ፥ ኀጥኣንም በጻድቃን በር። ድሀ በባልንጀራው ዘንድ የተጠላ ነው፥ የሀብታም ወዳጆች ግን ብዙዎች ናቸው። ባልንጀራውን የሚንቅ ይበድላል፥ ለድሀ ግን የሚራራ ምስጉን ነው። ክፉ የሚያደርጉ ይስታሉ፥ ምሕረትና እውነት ግን መልካምን ለሚያደርጉ ናቸው። በድካም ሁሉ ልምላሜ ይገኛል፥ ብዙ ነገር በሚናገር ከንፈር ግን ድህነት ብቻ አለ። የጠቢባን ዘውድ ባለጠግነታቸው ነው፥ የሰነፎች ስንፍና ግን ስንፍና ነው። እውነተኛ ምስክር ነፍሶችን ያድናል፥ በሐሰት የሚናገር ግን ሸንጋይ ነው። ጌታን ለሚፈራ ጠንካራ መታመን አለው፥ ለልጆቹም መጠጊያ ይኖራል። ሰው ከሞት ወጥመድ ያመልጥ ዘንድ ጌታን መፍራት የሕይወት ምንጭ ነው። የንጉሥ ክብር በሕዝብ ብዛት ነው፥ በሰው ጥቂትነት ግን የገዥ ጥፋት አለ። ለትግሥተኛ ሰው ብዙ ማስተዋል አለው፥ ቁጡ ግን ስንፍናውን ከፍ ከፍ ያደርጋል። ትሑት ልብ የሥጋ ሕይወት ነው፥ ቅንዓት ግን አጥንትን ያነቅዛል። ድሀን የሚያስጨንቅ ፈጣሪውን ይሰድባል፥ ለድሀ ምሕረትን የሚያደርግ ግን ያከብረዋል። ኀጥእ በክፋቱ ይደፋል፥ ጻድቅ ግን በእውነቱ ይታመናል። በአዋቂ ልብ ጥበብ ትቀመጣለች፥ በሰነፎች ውስጥ ግን አትታወቅም። ጽድቅ፥ ሕዝብን ከፍ ከፍ ታደርጋለች፥ ኃጢአት ግን ሕዝብን ታስነውራለች። አስተዋይ አገልጋይ በንጉሥ ዘንድ ይወደዳል፥ በሚያሳፍር ላይ ግን ቁጣው ይሆናል።