የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ምሳሌ 14

14
1ብልሃተኛ ሴት ቤትዋን ትሠራለች፥
ሰነፍ ሴት ግን በእጅዋ ታፈርሰዋለች።
2በቅን የሚሄድ ሰው ጌታን ይፈራል፥
መንገዱን የሚያጣምም ግን ይንቀዋል።
3በሰነፍ አፍ የትዕቢት በትር አለ፥
የጠቢባን ከንፈር ግን ትጠብቃቸዋለች።
4በሬ በሌለበት ስፍራ እህል አይገኝም፥
ብዙ ሲሳይ ግን በበሬዎች ኃይል ነው።
5የታመነ ምስክር አይዋሽም፥
የሐሰት ምስክር ግን በሐሰት ይናገራል።
6ፌዘኛ ሰው ጥበብን ይፈልጋል አያገኛትም፥
ለአስተዋይ ግን እውቀትን ማግኘት አያስቸግረውም።
7ከሰነፍ ሰው ፊት ራቅ፥
በእርሱ ዘንድ የእውቀትን ከንፈር አታገኝምና።
8የብልህ ሰው ጥበብ መንገዱን ያስተውል ዘንድ ነው፥
የሰነፎች ስንፍና ግን ሽንገላ ነው።
9ሰነፉ በኃጢአት ያፌዛል፥
በቅኖች መካከል ግን ቸርነት አለች።
10የራሱን ኀዘን ልብ ያውቃል፥
ከደስታውም ጋር ሌላ ሰው አይገናኝም።
11የኀጥኣን ቤት ይፈርሳል፥
የቅኖች ማደሪያ ግን ያብባል።
12 # ምሳ. 16፥25። ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፥
ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው።
13በሳቅ ደግሞ ልብ ያዝናል፥
የደስታም ፍጻሜ ልቅሶ ነው።
14ልቡን ከጽድቅ የሚመልስ ሰው ከመንገዱ ፍሬ ይጠግባል፥
ጻድቅም ሰው ደግሞ በራሱ።
15የዋህ ቃልን ሁሉ ያምናል፥
ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል።
16ጠቢብ ሰው ይፈራል ከክፉም ይሸሻል፥
ሰነፍ ግን ራሱን ታምኖ ይኰራል።
17ቁጡ ሰው በስንፍና ይሠራል፥
አስተዋይ ግን ይታገሣል።
18አላዋቂዎች ሰዎች ስንፍናን ይወርሳሉ፥
ብልሆች ግን እውቀትን እንደ ዘውድ ይጭናሉ።
19ኃጢአተኞች በደጎች ፊት ይጐነበሳሉ፥
ኀጥኣንም በጻድቃን በር።
20ድሀ በባልንጀራው ዘንድ የተጠላ ነው፥
የሀብታም ወዳጆች ግን ብዙዎች ናቸው።
21ባልንጀራውን የሚንቅ ይበድላል፥
ለድሀ ግን የሚራራ ምስጉን ነው።
22ክፉ የሚያደርጉ ይስታሉ፥
ምሕረትና እውነት ግን መልካምን ለሚያደርጉ ናቸው።
23በድካም ሁሉ ልምላሜ ይገኛል፥
ብዙ ነገር በሚናገር ከንፈር ግን ድህነት ብቻ አለ።
24የጠቢባን ዘውድ ባለጠግነታቸው ነው፥
የሰነፎች ስንፍና ግን ስንፍና ነው።
25እውነተኛ ምስክር ነፍሶችን ያድናል፥
በሐሰት የሚናገር ግን ሸንጋይ ነው።
26ጌታን ለሚፈራ ጠንካራ መታመን አለው፥
ለልጆቹም መጠጊያ ይኖራል።
27ሰው ከሞት ወጥመድ ያመልጥ ዘንድ
ጌታን መፍራት የሕይወት ምንጭ ነው።
28የንጉሥ ክብር በሕዝብ ብዛት ነው፥
በሰው ጥቂትነት ግን የገዥ ጥፋት አለ።
29ለትግሥተኛ ሰው ብዙ ማስተዋል አለው፥
ቁጡ ግን ስንፍናውን ከፍ ከፍ ያደርጋል።
30ትሑት ልብ የሥጋ ሕይወት ነው፥
ቅንዓት ግን አጥንትን ያነቅዛል።
31ድሀን የሚያስጨንቅ ፈጣሪውን ይሰድባል፥
ለድሀ ምሕረትን የሚያደርግ ግን ያከብረዋል።
32ኀጥእ በክፋቱ ይደፋል፥
ጻድቅ ግን በእውነቱ ይታመናል።
33በአዋቂ ልብ ጥበብ ትቀመጣለች፥
በሰነፎች ውስጥ ግን አትታወቅም።
34ጽድቅ፥ ሕዝብን ከፍ ከፍ ታደርጋለች፥
ኃጢአት ግን ሕዝብን ታስነውራለች።
35አስተዋይ አገልጋይ በንጉሥ ዘንድ ይወደዳል፥
በሚያሳፍር ላይ ግን ቁጣው ይሆናል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}