ምሳሌ 14:1-18

ምሳሌ 14:1-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ብልሆች ሴቶች ቤቶችን ይሠራሉ፤ ሰነፎች ሴቶች ግን በእጃቸው ያፈርሳሉ። በቅንነት የሚሄድ ሰው እግዚአብሔርን ይፈራል፤ መንገዱን የሚያጣምም ግን ይናቃል። ከሰነፎች አፍ የስድብ በትር ይወጣል፤ የጠቢባን ከንፈር ግን ትጠብቃቸዋለች። በሬዎች በሌሉበት ስፍራ በረቱ ንጹሕ ነው፤ ብዙ እህል ግን በበሬዎች ኀይል ይገኛል። የታመነ ምስክር አይዋሽም፤ የሐሰት ምስክር ግን ሐሰትን ያቀጣጥላል። በክፉዎች ዘንድ ጥበብን ትፈልጋለህ፥ አታገኛትምም፤ ዕውቀት ግን በብልሆች ዘንድ በቀላሉ ይገኛል። በሰነፍ ሰው ፊት ሁሉ ጠማማ ነው፥ የብልሆች ከንፈር ግን የዕውቀት ጋሻ ነው። የዐዋቂዎች ጥበብ መንገዳቸውን ታውቃለች፤ የሰነፎች ስንፍና ግን ወደ ስሕተት ይመራል። የኃጥኣን ቤቶች መንጻትን ይሻሉ፥ የጻድቃን ቤቶች ግን የተወደዱ ናቸው። የዐዋቂ ሰው ልብ ለሰውነቱ ኀዘን ነው፤ ደስ ባለውም ጊዜ ከጥል ጋር ግንኙነት የለውም። የክፉዎች ቤቶች ይፈርሳሉ፤ የቅኖች ማደሪያዎች ግን ይጸናሉ። በሰዎች ዘንድ ቅን የምትመስል መንገድ አለች፤ ፍጻሜዋ ግን ወደ ሲኦል ጕድጓድ ታደርሳለች። ከደስታ ጋር ኀዘን አይቀላቀልም፥ የደስታ ፍጻሜ ግን ወደ ኀዘን ይመለሳል። ልበ ትዕቢተኛ ከራሱ መንገድ ይጠግባል። ደግ ሰውም ከራሱ ዐሳብ ይጠግባል። የዋህ ነገርን ሁሉ ያምናል፤ ዐዋቂ ግን ወደ ንስሓ ይመለሳል። ብልህ ሰው ፈርቶ ከክፉ ይሸሻል፤ አላዋቂ ግን ራሱን ተማምኖ ከኃጥኣን ጋር አንድ ይሆናል። ቍጡ ሰው ያለምክር ይሠራል፤ ብልህ ግን ብዙ ይታገሣል። አላዋቂዎች ሰዎች ክፋትን ይካፈላሉ፤ ዐዋቂዎች ሰዎች ግን ማስተዋልን ፈጥነው ይይዟታል።

ምሳሌ 14:1-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ጠቢብ ሴት ቤቷን ትሠራለች፤ ቂል ሴት ግን በገዛ እጇ ታፈርሰዋለች። አካሄዱ ቅን የሆነ ሰው እግዚአብሔርን ይፈራል፤ መንገዱ ጠማማ የሆነ ግን ይንቀዋል። የቂል ሰው ንግግር ለጀርባው በትር ታስከትልበታለች፤ የጥበበኛ ከንፈር ግን ትጠብቃቸዋለች። በሬዎች በሌሉበት በረቱ ባዶ ይሆናል፤ በበሬ ጕልበት ግን ብዙ ምርት ይገኛል። ታማኝ ምስክር አይዋሽም፤ ሐሰተኛ ምስክር ግን ውሸትን ይዘከዝካል። ፌዘኛ ጥበብን ይሻል፤ ሆኖም አያገኛትም፤ ዕውቀት ግን ለአስተዋዮች በቀላሉ ትገኛለች። ከሞኝ ሰው ራቅ፣ ከከንፈሮቹ ዕውቀት አታገኝምና። የአስተዋዮች ጥበብ መንገዳቸውን ልብ ማለት ነው፤ የሞኞች ቂልነት ግን መታለል ነው። ቂሎች በሚያቀርቡት የበደል ካሳ ያፌዛሉ፤ በቅኖች መካከል ግን በጎ ፈቃድ ትገኛለች። እያንዳንዱ ልብ የራሱን መራራ ሐዘን ያውቃል፤ ደስታውንም ማንም ሊጋራው አይችልም። የክፉዎች ቤት ይፈርሳል፤ የቅኖች ድንኳን ግን ይስፋፋል። ለሰው ቀና መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤ በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ያደርሳል። በሣቅ ጊዜ እንኳ ልብ ይተክዛል፤ ደስታም በሐዘን ሊፈጸም ይችላል። ልባቸውን ከጽድቅ የሚመልሱ የእጃቸውን ሙሉ ዋጋ ይቀበላሉ፤ ደግ ሰውም ወሮታውን ያገኛል። አላዋቂው ሰው ሁሉን ያምናል፤ አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል። ጠቢብ ሰው ጥንቁቅ ነው፤ ከክፉም ይርቃል፤ ሞኝ ግን ችኵልና ደንታ ቢስ ነው። ግልፍተኛ ሰው የቂል ተግባር ይፈጽማል፤ መሠሪም ሰው አይወደድም። አላዋቂዎች ቂልነትን ይወርሳሉ፤ አስተዋዮች ግን ዕውቀትን እንደ ዘውድ ይጭናሉ።

ምሳሌ 14:1-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ጥበበኛ ሴት ቤትዋን በሥነ ሥርዓት ታስተዳድራለች፤ ሞኝ ሴት ግን በገዛ እጅዋ ታፈርሰዋለች። አካሄዱ ቀጥተኛ የሆነ ሰው እግዚአብሔርን ይፈራል፤ መንገዱ ጠማማ የሆነ ሰው ግን እግዚአብሔርን አይፈራም። ሞኝን የገዛ ንግግሩ ያስቀጣዋል፤ ጥበበኞችን ግን መልካም አነጋገራቸው ይጠብቃቸዋል። የምታርስባቸው በሬዎች ከሌሉህ ጐተራህ ባዶ ይሆናል። በሬዎች ካሉህ ግን ጐተራህ በእህል የተሞላ ይሆናል። ታማኝ ምስክር አይዋሽም፤ ሐሰተኛ ምስክር ግን የሚናገረው ሐሰት ነው። ፌዘኛ ሰው ጥበብን ይፈልጋል፤ አያገኛትም። አስተዋዮች ግን ዕውቀትን በቀላሉ ይገበያሉ። ከእነርሱ የምትማረው ምንም ዕውቀት ስለሌለ ከሞኞች ራቅ። የብልኅ ሰው ጥበብ መንገዱን እንዳይስት ያደርገዋል። ሞኝን ሰው ግን ሞኝነቱ መንገዱን እንዲስት ያደርገዋል። ሞኞች ኃጢአት ሲሠሩ በመጸጸት ፈንታ ያፌዛሉ፤ ደጋግ ሰዎች ግን ኃጢአታቸው ይቅር እንዲባልላቸው ይፈልጋሉ። ደስታህም ሆነ ሐዘንህ የራስህ ነው፤ ማንም የሚካፈልህ የለም። የክፉ ሰው ቤት ይፈርሳል፤ የደግ ሰው ቤት ግን ጸንቶ ይኖራል። አንተ “ትክክለኛ መንገድ ነው” ብለህ የምታስበው ወደ ሞት ይመራህ ይሆናል። በሳቅ ጊዜ እንኳ በልብ ውስጥ ሐዘን ሊኖር ይችላል፤ የደስታም ፍጻሜ ለቅሶ ነው። ከሐዲዎች ሰዎች የክፉ ሥራቸውን ዋጋ ይቀበላሉ፤ ደጋግ ሰዎች ግን የመልካም ሥራቸውን ዋጋ ያገኛሉ። ሞኝ ሰው የሚነግሩትን ሁሉ አምኖ ይቀበላል፤ ብልኆች ግን እርምጃቸውን በጥንቃቄ ይመረምራሉ። ብልኆች እግዚአብሔርን ስለሚፈሩ ከክፉ ነገር ለመራቅ ይጠነቀቃሉ፤ ሞኞች ግን ከአደጋ የማይጠነቀቁ ችኲሎች ናቸው። ቊጡ ሰው የሞኝነትን ሥራ ይሠራል፤ ጥበበኛ ግን ይታገሣል። አላዋቂዎች የስንፍናቸውን ዋጋ ይቀበላሉ፤ ብልኆች ግን ዕውቀትን እንደ አክሊል ይቀዳጃሉ።

ምሳሌ 14:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ብልሃተኛ ሴት ቤትዋን ትሠራለች፥ ሰነፍ ሴት ግን በእጅዋ ታፈርሰዋለች። በቅን የሚሄድ ሰው ጌታን ይፈራል፥ መንገዱን የሚያጣምም ግን ይንቀዋል። በሰነፍ አፍ የትዕቢት በትር አለ፥ የጠቢባን ከንፈር ግን ትጠብቃቸዋለች። በሬ በሌለበት ስፍራ እህል አይገኝም፥ ብዙ ሲሳይ ግን በበሬዎች ኃይል ነው። የታመነ ምስክር አይዋሽም፥ የሐሰት ምስክር ግን በሐሰት ይናገራል። ፌዘኛ ሰው ጥበብን ይፈልጋል አያገኛትም፥ ለአስተዋይ ግን እውቀትን ማግኘት አያስቸግረውም። ከሰነፍ ሰው ፊት ራቅ፥ በእርሱ ዘንድ የእውቀትን ከንፈር አታገኝምና። የብልህ ሰው ጥበብ መንገዱን ያስተውል ዘንድ ነው፥ የሰነፎች ስንፍና ግን ሽንገላ ነው። ሰነፉ በኃጢአት ያፌዛል፥ በቅኖች መካከል ግን ቸርነት አለች። የራሱን ኀዘን ልብ ያውቃል፥ ከደስታውም ጋር ሌላ ሰው አይገናኝም። የኀጥኣን ቤት ይፈርሳል፥ የቅኖች ማደሪያ ግን ያብባል። ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፥ ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው። በሳቅ ደግሞ ልብ ያዝናል፥ የደስታም ፍጻሜ ልቅሶ ነው። ልቡን ከጽድቅ የሚመልስ ሰው ከመንገዱ ፍሬ ይጠግባል፥ ጻድቅም ሰው ደግሞ በራሱ። የዋህ ቃልን ሁሉ ያምናል፥ ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል። ጠቢብ ሰው ይፈራል ከክፉም ይሸሻል፥ ሰነፍ ግን ራሱን ታምኖ ይኰራል። ቁጡ ሰው በስንፍና ይሠራል፥ አስተዋይ ግን ይታገሣል። አላዋቂዎች ሰዎች ስንፍናን ይወርሳሉ፥ ብልሆች ግን እውቀትን እንደ ዘውድ ይጭናሉ።