የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ምሳሌ 12:11-23

ምሳሌ 12:11-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

መሬቱን የሚያርስ የተትረፈረፈ ምግብ ያገኛል፤ ከንቱ ተስፋን የሚያሳድድ ግን ልበ ቢስ ነው። ኃጥኣን የክፉዎችን ምርኮ ይመኛሉ፤ የጻድቅ ሥር ግን ይንሰራፋል። ክፉ ሰው በክፉ ንግግሩ ይጠመዳል፤ ጻድቅ ሰው ግን ከመከራ ያመልጣል። ሰው ከከንፈሩ ፍሬ የተነሣ በበጎ ነገር ይሞላል፤ እንደ እጁ ሥራም ተገቢውን ዋጋ ያገኛል። ቂል ሰው መንገዱ ትክክል መስሎ ይታየዋል፤ ጠቢብ ሰው ግን ምክር ይሰማል። ቂል ሰው ቍጣው ወዲያውኑ ይታወቅበታል፤ አስተዋይ ሰው ግን ስድብን ንቆ ይተዋል። ሐቀኛ ምስክር በእውነት ይመሰክራል፤ ሐሰተኛ ምስክር ግን ውሸት ይናገራል። ግድ የለሽ ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤ የጠቢብ አንደበት ግን ፈውስን ያመጣል። እውነት የሚናገሩ ከንፈሮች ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ፤ ሐሰተኛ አንደበት ግን ለቅጽበት ያህል ብቻ ነው። ክፋትን በሚያውጠነጥኑ ሰዎች ልብ አታላይነት አለ፤ ሰላምን የሚያራምዱ ግን ደስታ አላቸው። ጻድቃን ጕዳት አያገኛቸውም፤ ክፉዎች ግን በመከራ የተሞሉ ናቸው። እግዚአብሔር ሐሰተኛ ከንፈርን ይጸየፋል፤ በእውነተኞች ሰዎች ግን ደስ ይለዋል። አስተዋይ ሰው ዕውቀቱን ይሰውራል፤ የሞኞች ልብ ግን ቂልነትን ይነዛል።

ምሳሌ 12:11-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ትጉህ ገበሬ የተትረፈረፈ ምግብ ይኖረዋል፤ በከንቱ ምኞት መጠመድ ግን ሞኝነት ነው። የክፉ ሰዎች ምኞት ዘወትር ክፉ ነገርን ለማድረግ ነው፤ ደጋግ ሰዎች ግን እንደ መልካም ተክል መልካም ፍሬን ያፈራሉ። ክፉን ሰው የራሱ ክፉ ንግግር ወጥመድ ሆኖ ይይዘዋል። ደግ ሰው ግን ከመከራ ያመልጣል። የምታገኘው በረከት የመልካም ንግግርህና ሥራህ ውጤት ነው፤ በዚህ ዐይነት ተገቢ ዋጋህን ታገኛለህ። ማስተዋል የጐደላቸው ሰዎች ሁልጊዜ ትክክል የሆኑ ይመስላቸዋል፤ ጠቢባን ግን መልካም ምክርን ይቀበላሉ። የሞኝ ቊጣ ወዲያው ይታወቃል፤ ብልኅ ሰው ግን በእርሱ ላይ የተሰነዘረውን ስድብ ችላ ይላል። እውነትን የሚናገር ሁሉ የታመነ ምስክርነትን ይሰጣል፤ ሐሰተኛ ምስክር ግን ሰውን ያታልላል። ያለ ጥንቃቄ የተነገረ ቃል እንደ ሰይፍ ያቈስላል፤ በጥበብ የተነገረ ቃል ግን ይፈውሳል። እውነት ግን ጸንታ ትኖራለች። ሐሰት ዘላቂነት የለውም፤ ክፋትን በሚያቅዱ ሰዎች ልብ ተንኰል አለ፤ ሰላም የሚገኝበትን ነገር የሚመክሩ ግን ደስታን ያገኛሉ። ደጋግ ሰዎች ምንም ክፉ ነገር አይገጥማቸውም፤ ክፉዎች ግን መከራ ይበዛባቸዋል። የሚያተርፉት ነገር የለም። እግዚአብሔር ሐሰተኛ አንደበትን ይጸየፋል፤ በእውነተኞች ሰዎች ግን ይደሰታል። አስተዋይ ሰዎች “ዐዋቂዎች ነን” እያሉ አይመጻደቁም፤ ሞኞች ግን “ዐዋቂዎች ነን” በማለት ድንቊርናቸውን ይገልጣሉ።

ምሳሌ 12:11-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ምድሩን የሚያርሳት ሰው እንጀራን ይጠግባል፤ ቦዘኔነትን የሚከተል ግን የአእምሮ ድህነትን ይሰበስባል። በወይን ግብዣ ራሱን ደስ የሚያሰኝ ሰው በሰውነቱ ውርደትን ያመጣል። የኃጥኣን ምኞት ክፋት ናት። የጻድቃን ሥር ግን የጸና ነው። ኀጢአተኛ ሰው በከንፈሩ ኀጢአት ወደ ወጥመድ ይወድቃል፤ ጻድቅ ግን ከእርሱ ያመልጣል። አስፍቶ የሚመለከት ሰው ብዙ ምሕረትን ያገኛል። ድንገት በበር የሚገናኝ ግን ነፍሳትን ያስጨንቃል። የሰው ነፍስ ከአፉ ፍሬ መልካም ነገርን ትጠግባለች፥ ሰውም የከንፈሩን ዋጋ ይቀበላል። የሰነፎች መንገድ በፊታቸው የቀናች ናት፤ ጠቢብ ግን ምክርን ይሰማል። ሰነፍ ቍጣውን በየቀኑ ይናገራል፤ ብልህ ሰው ግን ነውርን ይሰውራል። ጻድቅ ሰው የተገለጠ እውነትን ያስተምራል፤ የክፉዎች ምስክርነት ግን ውሸት ነው። በሐሰት የሚመሰክሩ በሰይፍ ይገድላሉ፤ በአፋቸው ሰይፍ አለና። የጠቢባን ምላስ ግን የቈሰለውን ይፈውሳል። የጻድቃን ከንፈሮች ምስክርነትን ያቀናሉ፥ የሚቸኩል ምስክር ግን ክፉ አንደበት አለው። ክፉን በሚያስብ ልብ ውስጥ ማታለል አለ፤ ሰላምን የሚወዱ ግን ደስ ይላቸዋል፥ ጻድቅን ምንም ክፉ ነገር ደስ አያሰኘውም፤ ክፉዎች ግን ክፋትን የተሞሉ ናቸው። ሐሰተኛ ከንፈር በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ እውነትን የሚያደርጉ ግን በእርሱ ዘንድ የተወደዱ ናቸው። ብልህ ሰው የጥበብ መንበር ነው፤ የሰነፎች ልብ ግን መርገምን ያገኛል።

ምሳሌ 12:11-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

መሬቱን የሚቆፍር ሰው እንጀራ ይጠግባል፥ ለከንቱ ነገር የሚሮጥ ግን ማስተዋል የተሣነው ነው። ክፉ ሰዎች በክፉዎች ወጥመድ ይደሰታሉ፥ የጻድቃን ሥር ግን ፍሬን ያፈራል። ክፉ ሰው በከንፈሩ ኃጢአት ይጠመዳል፥ ጻድቅ ግን ከመከራ ያመልጣል። የሰው ነፍስ ከአፉ ፍሬ መልካም ነገርን ትጠግባለች፥ ሰውም እንደ እጁ ሥራ ዋጋውን ይቀበላል። የሰነፍ መንገድ በዓይኑ የቀናች ናት፥ ጠቢብ ግን ምክርን ይሰማል። የሰነፍ ቁጣ ቶሎ ይታወቃል፥ ብልህ ሰው ግን ነውርን ይሰውራል። እውነተኛን ነገር የሚናገር ቅን ነገርን ያወራል፥ የሐሰት ምስክር ግን ተንኰልን ያወራል። እንደሚዋጋ ሰይፍ የሚለፈልፍ ሰው አለ፥ የጠቢባን ምላስ ግን ጤና ነው። የእውነት ከንፈር ለዘለዓለም ትቆማለች፥ ውሸተኛ ምላስ ግን ለቅጽበት ነው። ክፉን በሚያስቡ ልብ ውስጥ ተንኰል አለ፥ በሰላም ለሚመክሩ ግን ደስታ አላቸው። ጻድቅን መከራ አያገኘውም፥ ኀጥኣን ግን ክፋትን የተሞሉ ናቸው። ውሸተኛ ከንፈር በጌታ ዘንድ አስጸያፊ ነው፥ እውነትን የሚያደርጉ ግን በእርሱ ዘንድ የተወደዱ ናቸው። ብልህ ሰው እውቀትን ይሸሽጋል፥ የሰነፎች ልብ ግን ስንፍናን ያወራል።