የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ምሳሌ 12:11-23

መጽሐፈ ምሳሌ 12:11-23 መቅካእኤ

መሬቱን የሚቆፍር ሰው እንጀራ ይጠግባል፥ ለከንቱ ነገር የሚሮጥ ግን ማስተዋል የተሣነው ነው። ክፉ ሰዎች በክፉዎች ወጥመድ ይደሰታሉ፥ የጻድቃን ሥር ግን ፍሬን ያፈራል። ክፉ ሰው በከንፈሩ ኃጢአት ይጠመዳል፥ ጻድቅ ግን ከመከራ ያመልጣል። የሰው ነፍስ ከአፉ ፍሬ መልካም ነገርን ትጠግባለች፥ ሰውም እንደ እጁ ሥራ ዋጋውን ይቀበላል። የሰነፍ መንገድ በዓይኑ የቀናች ናት፥ ጠቢብ ግን ምክርን ይሰማል። የሰነፍ ቁጣ ቶሎ ይታወቃል፥ ብልህ ሰው ግን ነውርን ይሰውራል። እውነተኛን ነገር የሚናገር ቅን ነገርን ያወራል፥ የሐሰት ምስክር ግን ተንኰልን ያወራል። እንደሚዋጋ ሰይፍ የሚለፈልፍ ሰው አለ፥ የጠቢባን ምላስ ግን ጤና ነው። የእውነት ከንፈር ለዘለዓለም ትቆማለች፥ ውሸተኛ ምላስ ግን ለቅጽበት ነው። ክፉን በሚያስቡ ልብ ውስጥ ተንኰል አለ፥ በሰላም ለሚመክሩ ግን ደስታ አላቸው። ጻድቅን መከራ አያገኘውም፥ ኀጥኣን ግን ክፋትን የተሞሉ ናቸው። ውሸተኛ ከንፈር በጌታ ዘንድ አስጸያፊ ነው፥ እውነትን የሚያደርጉ ግን በእርሱ ዘንድ የተወደዱ ናቸው። ብልህ ሰው እውቀትን ይሸሽጋል፥ የሰነፎች ልብ ግን ስንፍናን ያወራል።