ፊልጵስዩስ 1:3-11
ፊልጵስዩስ 1:3-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እናንተን በማስብበት ጊዜ ሁሉ ዘወትር አምላኬን አመሰግነዋለሁ። ስለ እናንተም ሁልጊዜ እጸልያለሁ፤ የደስታ ጸሎትም አደርጋለሁ። ከመጀመሪያዪቱ ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ በወንጌል ትምህርት ከእኔ ጋር አንድ በመሆናችሁ፥ እርሱ የጀመረላችሁን በጎውን ሥራ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከሚመጣበት ቀን ድረስ እርሱ እንደሚፈጽምላችሁ አምናለሁ። ስለ እናንተ ይህን ላስብ ይገባኛል፤ በምታሰርበትና በምከራከርበት፥ ወንጌልንም በማስተምርበት ጊዜ ከእኔ ጋራ በጸጋ ስለ ተባበራችሁ በልቤ ውስጥ ናችሁና። በክርስቶስ ፍቅር ሁላችሁን እንደምወዳችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነው። ስለዚህም በአእምሮና በልብ ጥበብ ሁሉ ፍቅራችሁ እንዲበዛ፥ እንዲጨምርም እጸልያለሁ፤ የሚሻለውን ሥራ እንድትመረምሩና እንድትፈትኑ፥ ክርስቶስ በሚመጣበት ቀን ያለ ዕንቅፋት ቅዱሳን ትሆኑ ዘንድ፦ ለእግዚአብሔር ምስጋናና ክብርም በኢየሱስ ክርስቶስ የጽድቅን ፍሬ ትሞሉ ዘንድ እጸልያለሁ፤
ፊልጵስዩስ 1:3-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እናንተን ባስታወስሁ ቍጥር አምላኬን አመሰግናለሁ። ሁልጊዜ ስለ ሁላችሁ ስጸልይ፣ በደስታ እጸልያለሁ፤ ከመጀመሪያው ቀን አንሥቶ እስካሁን ድረስ በወንጌል አገልግሎት ተካፋይ ሆናችኋልና። በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እርሱ እስከ ክርስቶስ ኢየሱስ ቀን ድረስ ከፍጻሜው እንደሚያደርሰው ርግጠኛ ነኝ። በልቤ ስላላችሁ እና በእስራቴም ሆነ ለወንጌል ስመክትና ሳጸናው ሁላችሁም ከእኔ ጋራ የእግዚአብሔር ጸጋ ተካፋዮች ስለ ሆናችሁ፣ ስለ ሁላችሁ እንዲህ ማሰቤ ተገቢ ነው። በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ሁላችሁንም ምን ያህል እንደምናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነው። ጸሎቴ ይህ ነው፤ ፍቅራችሁ በጥልቅ ዕውቀትና በማስተዋል ሁሉ በዝቶ እንዲትረፈረፍ፣ ይኸውም ከሁሉ የሚሻለውን ለይታችሁ እንድታውቁ፣ እስከ ክርስቶስም ቀን ድረስ ንጹሓንና ነቀፋ የሌለባችሁ እንድትሆኑ፣ ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሚገኘው የጽድቅ ፍሬ እንድትሞሉ ነው።
ፊልጵስዩስ 1:3-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሁልጊዜ በጸሎቴ ሁሉ ስለ እናንተ ሁሉ በደስታ እየጸለይሁ፥ ከፊተኛው ቀን እስከ ዛሬ ድረስ ወንጌልን በመስበክ አብራችሁ ስለ ሠራችሁ፥ ባሰብኋችሁ ጊዜ ሁሉ አምላኬን አመሰግናለሁ። በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው ይህን ተረድቼአለሁና፤ በእስራቴም ወንጌልንም መመከቻና መጽኛ በማድረግ ሁላችሁ ከእኔ ጋር በጸጋ ተካፋዮች ስለ ሆናችሁ፥ በልቤ ትኖራላችሁና ስለ ሁላችሁ ይህን ላስብ ይገባኛል። በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ሁላችሁን እንዴት እንድናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነውና። ለእግዚአብሔርም ክብርና ምስጋና ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኝ የጽድቅ ፍሬ ሞልቶባችሁ፥ ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅታችሁ ቅኖችና አለ ነውር እንድትሆኑ የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ ትወዱ ዘንድ፥ ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ።
ፊልጵስዩስ 1:3-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እናንተን በማስታውስበት ጊዜ ሁሉ አምላኬን አመሰግናለሁ፤ ስለ ሁላችሁም በምጸልይበት ጊዜ ሁሉ ጸሎቴ በደስታ የተሞላ ነው። ከመጀመሪያው ቀን አንሥቶ እስከ አሁን ወንጌልን በመስበክ የሥራዬ ተባባሪዎች ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ ይህን መልካም ሥራ በእናንተ ሕይወት ውስጥ የጀመረ አምላክ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍርድ በሚመለስበት ቀን ወደ ፍጻሜ እንደሚያደርሰው እርግጠኛ ነኝ። አሁን በእስር ቤት ባለሁበት ጊዜና ከመታሰሬም በፊት ለወንጌል እውነት ለመከላከልና እርሱንም ለማጽናት እግዚአብሔር በጸጋው በሰጠኝ ዕድል ሁላችሁም ተካፋዮች ስለ ሆናችሁ እናንተ ሁልጊዜ በልቤ ናችሁ። ስለዚህም ስለ እናንተ የሚሰማኝ ስሜት ትክክል ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ሁላችሁንም ምን ያኽል እንደምናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነው። ፍቅራችሁ ዕውቀትና ማስተዋል የሞላበት ሆኖ እያደገ እንዲሄድ እጸልያለሁ። ይኸውም የተሻለውን ነገር መርምራችሁ እንድታውቁና ክርስቶስ ተመልሶ በሚመጣበት ቀን ንጹሖችና ነውር የሌለባችሁ ሆናችሁ እንድትገኙ ነው። በዚህም ዐይነት ሕይወታችሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኘው የጽድቅ ፍሬ የተሞላ ሆኖ ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና የምታስገኙ ትሆናላችሁ።
ፊልጵስዩስ 1:3-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እናንተን ባሰብኋችሁ ጊዜ ሁሉ አምላኬን አመሰግነዋለሁ፤ ሁልጊዜ በጸሎቴ ሁሉ ስለ ሁላችሁም በደስታ እጸልያለሁ፤ ምክንያቱም ከመጀመሪያዋ ቀን አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ወንጌልን በመስበክ አብራችሁ ስለ ሠራችሁ ነው። በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እርሱ እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንደሚፈጽመው በዚህ እርግጠኛ ሆኛለሁ፤ በእስራቴም ወንጌልንም መመከቻና መጽኛ በማድረግ ሁላችሁ ከእኔ ጋር በጸጋ ተካፋዮች ስለ ሆናችሁ፥ በልቤ ትኖራላችሁና ስለ ሁላችሁ ይህን ላስብ ይገባኛል። በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ሁላችሁንም ምን ያኽል እንደምናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነውና። ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ እጸልያለሁ፤ እንዲህም ያለው እውቀት የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ እንድትወድዱ ስለሚረዳችሁ ነው፤ በዚህም ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅታችሁ ንጹሖችና ያለ ነቀፋ በመሆን ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ከኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኝ የጽድቅ ፍሬ የተሞላችሁ እንድትሆኑ ነው።