ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 1:3-11

ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 1:3-11 አማ05

እናንተን በማስታውስበት ጊዜ ሁሉ አምላኬን አመሰግናለሁ፤ ስለ ሁላችሁም በምጸልይበት ጊዜ ሁሉ ጸሎቴ በደስታ የተሞላ ነው። ከመጀመሪያው ቀን አንሥቶ እስከ አሁን ወንጌልን በመስበክ የሥራዬ ተባባሪዎች ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ ይህን መልካም ሥራ በእናንተ ሕይወት ውስጥ የጀመረ አምላክ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍርድ በሚመለስበት ቀን ወደ ፍጻሜ እንደሚያደርሰው እርግጠኛ ነኝ። አሁን በእስር ቤት ባለሁበት ጊዜና ከመታሰሬም በፊት ለወንጌል እውነት ለመከላከልና እርሱንም ለማጽናት እግዚአብሔር በጸጋው በሰጠኝ ዕድል ሁላችሁም ተካፋዮች ስለ ሆናችሁ እናንተ ሁልጊዜ በልቤ ናችሁ። ስለዚህም ስለ እናንተ የሚሰማኝ ስሜት ትክክል ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ሁላችሁንም ምን ያኽል እንደምናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነው። ፍቅራችሁ ዕውቀትና ማስተዋል የሞላበት ሆኖ እያደገ እንዲሄድ እጸልያለሁ። ይኸውም የተሻለውን ነገር መርምራችሁ እንድታውቁና ክርስቶስ ተመልሶ በሚመጣበት ቀን ንጹሖችና ነውር የሌለባችሁ ሆናችሁ እንድትገኙ ነው። በዚህም ዐይነት ሕይወታችሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኘው የጽድቅ ፍሬ የተሞላ ሆኖ ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና የምታስገኙ ትሆናላችሁ።