ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 1:3-11

ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 1:3-11 መቅካእኤ

እናንተን ባሰብኋችሁ ጊዜ ሁሉ አምላኬን አመሰግነዋለሁ፤ ሁልጊዜ በጸሎቴ ሁሉ ስለ ሁላችሁም በደስታ እጸልያለሁ፤ ምክንያቱም ከመጀመሪያዋ ቀን አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ወንጌልን በመስበክ አብራችሁ ስለ ሠራችሁ ነው። በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እርሱ እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንደሚፈጽመው በዚህ እርግጠኛ ሆኛለሁ፤ በእስራቴም ወንጌልንም መመከቻና መጽኛ በማድረግ ሁላችሁ ከእኔ ጋር በጸጋ ተካፋዮች ስለ ሆናችሁ፥ በልቤ ትኖራላችሁና ስለ ሁላችሁ ይህን ላስብ ይገባኛል። በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ሁላችሁንም ምን ያኽል እንደምናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነውና። ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ እጸልያለሁ፤ እንዲህም ያለው እውቀት የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ እንድትወድዱ ስለሚረዳችሁ ነው፤ በዚህም ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅታችሁ ንጹሖችና ያለ ነቀፋ በመሆን ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ከኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኝ የጽድቅ ፍሬ የተሞላችሁ እንድትሆኑ ነው።