ዘኍል 22:19-35
ዘኍል 22:19-35 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አሁንም እግዚአብሔር ደግሞ የሚነግረኝን አውቅ ዘንድ ዛሬ ሌሊት ደግሞ በዚህ እደሩ” አላቸው። እግዚአብሔርም ወደ በለዓም በሌሊት መጥቶ፥ “ሰዎቹ ይጠሩህ ዘንድ መጥተው እንደ ሆነ፥ ተነሣ ከእነርሱ ጋር ሂድ፤ ነገር ግን የምነግርህን ቃል ታደርጋለህ” አለው። በለዓምም ሲነጋ ተነሣ፤ አህያዪቱንም ጭኖ ከሞዓብ አለቆች ጋር ሄደ። እርሱም ስለ ሄደ እግዚአብሔር ተቈጣ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ሊያሰናክለው ተነሣ። እርሱም በአህያዪቱ ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ሁለቱም ብላቴናዎቹ ከእርሱ ጋር ነበሩ። አህያዪቱም የእግዚአብሔርን መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየች፤ ከመንገዱም ላይ ፈቀቅ ብላ ወደ ሜዳ ውስጥ ገባች፤ በለዓምም ወደ መንገድ ይመልሳት ዘንድ አህያዪቱን መታት። የእግዚአብሔርም መልአክ ከወይኑ ቦታዎች መካከል በወዲያና በወዲህ ወገን ግንብ በነበረበት ቆመ። አህያዪቱም የእግዚአብሔርን መልአክ አይታ ወደ ቅጥሩ ተጠጋች፤ የበለዓምንም እግሩን ላጠችው፤ እርሱም ደግሞ መታት። የእግዚአብሔርም መልአክ ወደ ፊት ሄደ፤ በቀኝና በግራ መተላለፊያ በሌለበት በጠባብ ስፍራ ቆመ። አህያዪቱም የእግዚአብሔርን መልአክ አየች፤ ከበለዓምም በታች ተኛች፤ በለዓምም ተቈጣ፤ አህያዪቱንም በበትሩ ደበደባት። እግዚአብሔርም የአህያዪቱን አፍ ከፈተ፤ በለዓምንም፥ “ሦስት ጊዜ የመታኸኝ ምን አድርጌብህ ነው?” አለችው። በለዓምም አህያዪቱን፥ “ስለዘበትሽብኝ ነው፤ በእጄስ ሰይፍ ቢኖር አሁን በገደልሁሽ ነበር” አላት። አህያዪቱም በለዓምን፥ “ከወጣትነትህ ጀምሮ እስከ ዛሬ የምትቀመጥብኝ አህያህ አይደለሁምን? በውኑ አንተን ቸል ያልሁበት፥ በአንተም እንዲህ ያደረግሁበት ጊዜ ነበርን?” አለችው። እርሱም፥ “እንዲህ አላደረግሽብኝም” አላት። እግዚአብሔርም የበለዓምን ዐይኖች ከፈተ፤ የእግዚአብሔርንም መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ፥ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየ፤ በግንባሩም ወድቆ ሰገደለት። የእግዚአብሔርም መልአክ፥ “አህያህን ሦስት ጊዜ ለምን መታህ? እነሆ፥ መንገድህ በፊቴ ቀና አልነበረምና ላሰናክልህ ወጥቼአለሁ፤ አህያዪቱም አይታኝ ከፊቴ ፈቀቅ አለች፤ ይህም ሦስተኛ ጊዜ ነው፤ ከፊቴስ ፈቀቅ ባላለች በእውነት አሁን አንተን በገደልሁህ፤ እርሷንም ባዳንኋት ነበር” አለው። በለዓምም የእግዚአብሔርን መልአክ፥ “በድያለሁ፤ አንተ በመንገድ ላይ በፊቴ እንደ ቆምህብኝ አላወቅሁም፤ እንግዲህ አሁን አትወድድ እንደሆነ እመለሳለሁ” አለው። የእግዚእብሔርም መልአክ በለዓምን፥ “ከሰዎቹ ጋር ሂድ፤ ነገር ግን የምናገርህን ቃል ብቻ ለመናገር ተጠንቀቅ” አለው። በለዓምም ከባላቅ አለቆች ጋር ሄደ።
ዘኍል 22:19-35 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አሁንም ሌሎቹ እንዳደረጉት ሁሉ፣ እናንተም ዛሬ እዚሁ ዕደሩና እግዚአብሔር (ያህዌ) ምን እንደሚለኝ ደግሞ ልወቅ።” በዚያች ሌሊት እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወደ በለዓም መጥቶ፣ “እነዚህ ሰዎች የመጡት እንድትሄድላቸው እስከ ሆነ ድረስ አብረሃቸው ሂድ፤ ነገር ግን እኔ የምነግርህን ብቻ አድርግ።” በለዓም በጧት ተነሣ፤ አህያውንም ጭኖ ከሞዓብ አለቆች ጋር ሄደ። ይሁን እንጂ በለዓም በሄደ ጊዜ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በጣም ተቈጥቶ ስለ ነበር የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ ሊቃወመው በመንገዱ ላይ ቆመ። በለዓምም በአህያው ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ሁለት አሽከሮቹም አብረው ነበሩ። አህያዪቱም የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ የተመዘዘ ሰይፍ ይዞ በመንገድ ላይ መቆሙን ባየች ጊዜ ከመንገድ ወጥታ ዕርሻ ውስጥ ገባች፤ በለዓምም ወደ መንገዱ እንድትመለስ መታት። ከዚያም የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ በሁለቱም በኩል ግንብ ባለበት በሁለት የወይን ተክል ቦታ መካከል በሚገኝ ጠባብ መተላለፊያ ላይ ቆመ። አህያዪቱም የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መልአክ ባየች ጊዜ ወደ ግንቡ ተጠግታ የበለዓምን እግር አጣበቀችው፤ ስለዚህም እንደ ገና መታት። የእግዚአብሔርም (ያህዌ) መልአክ ወደ ፊት ሄድ ብሎ ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ መተላለፊያ በሌለበት ጠባብ ቦታ ላይ ቆመ። አህያዪቱም የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መልአክ ባየች ጊዜ ከበለዓም በታች ተኛች፤ በለዓም ተቈጥቶ ነበርና በበትሩ ደበደባት። ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) የአህያዪቱን አፍ ከፈተ፤ በለዓምንም፣ “እንዲህ አድርገህ ሦስት ጊዜ የመታኸኝ ምን አድርጌህ ነው?” አለችው። በለዓምም መልሶ አህያዪቱን፣ “ስላላገጥሽብኝ ነዋ! በእጄ ሰይፍ ይዤ ቢሆን ኖሮ አሁኑኑ በገደልሁሽ ነበር” አላት። አህያዪቱም ደግሞ በለዓምን እንዲህ አለችው፣ “ከብዙ ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የተቀመጥህብኝ አህያህ አይደለሁምን? ታዲያ ይህን የመሰለ ነገር የማድረግ ልማድ ነበረኝ?” እርሱም፣ “በጭራሽ!” አላት። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) የበለዓምን ዐይን ከፈተ፤ እርሱም የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ የተመዘዘ ሰይፍ እንደ ያዘ መንገዱ ላይ ቆሞ አየ፤ ጐንበስ ብሎም በግንባሩ ተደፋ። የእግዚአብሔርም (ያህዌ) መልአክ እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ “አህያህን እንዲህ አድርገህ ሦስት ጊዜ የመታሃት ስለ ምንድን ነው? መንገድህ በፊቴ ጠማማ ስለሆነ ልቃወምህ መጥቻለሁ። አህያዪቱ አይታኝ ሦስቱንም ጊዜ ከፊቴ ዞር ባትልማ ኖሮ በእውነት እስካሁን አንተን በገደልሁህ፣ አህያዪቱን ግን በሕይወት በተውኋት ነበር።” በለዓምም የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መልአክ፣ “ኀጢአት ሠርቻለሁ፤ እኔን ለመቃወም መንገዱ ላይ መቆምህን አላወቅሁም፤ አሁንም ደስ የማትሰኝ ከሆነ እመለሳለሁ” አለው። የእግዚአብሔርም (ያህዌ) መልአክ በለዓምን፣ “መሄዱን ከሰዎቹ ጋር ሂድ፤ ነገር ግን እኔ የምነግርህን ብቻ ተናገር” አለው። ስለዚህ በለዓም ከባላቅ አለቆች ጋር ሄደ።
ዘኍል 22:19-35 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አሁንም እግዚአብሔር ደግሞ የሚነግረኝን አውቅ ዘንድ፥ እባካችሁ፥ ዛሬ ሌሊት ደግሞ በዚህ እደሩ አላቸው። እግዚአብሔርም ወደ በለዓም በሌሊት መጥቶ፦ ሰዎቹ ይጠሩህ ዘንድ መጥተው እንደ ሆነ፥ ተነሣ ከእነርሱም ጋር ሂድ፤ ነገር ግን የምነግርህን ቃል ብቻ ታደርጋለህ አለው። በለዓምም ሲነጋ ተነሣ፥ አህያይቱንም ጭኖ ከሞዓብ አለቆች ጋር ሄደ። እርሱም ስለ ሄደ እግዚአብሔር ተቈጣ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ሊቍቍመው በመንገድ ላይ ቆመ። እርሱም በአህያይቱ ላይ፥ ሁለቱም ሎሌዎቹ ከእርሱ ጋር ነበሩ። አህያይቱም የእግዚአብሔርን መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየች፤ ከመንገዱም ፈቀቅ ብላ ወደ እርሻው ውስጥ ገባች፤ በለዓምም ወደ መንገድ ይመልሳት ዘንድ አህያይቱን መታት። የእግዚአብሔርም መልአክ ከወይኑ ቦታዎች መካከል በወዲያና በወዲህ ወገን ግንብ በነበረበት በጠባብ መንገድ ላይ ቆመ። አህያይቱም የእግዚአብሔርን መልአክ አይታ ወደ ቅጥሩ ተጠጋች፥ የበለዓምንም እግር ከቅጥሩ ጋር አጣበቀች፤ እርሱም ደግሞ መታት። የእግዚአብሔርም መልአክ ወደ ፊት ሄደ፥ በቀኝና በግራ መተላለፊያ በሌለበት በጠባብ ስፍራ ቆመ። አህያይቱም የእግዚአብሔርን መልአክ አየች፥ ከበለዓምም በታች ተኛች፤ በለዓምም እጅግ ተቈጣ፥ አህያይቱንም በበትሩ ደበደባት። እግዚአብሔርም የአህያይቱን አፍ ከፈተ፥ በለዓምንም፦ ሦስት ጊዜ የመታኸኝ ምን አድርጌብህ ነው? አለችው። በለዓምም አህያይቱን፦ ስላላገጥሽብኝ ነው፤ በእጄስ ሰይፍ ቢኖር አሁን በገደልሁሽ ነበር አላት። አህያይቱም በለዓምን፦ ከብዙ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የምትቀመጥብኝ አህያህ አይደለሁምን? በውኑ እንዲህ አደርግ ዘንድ ልማዴ ነበረን? አለችው። እርሱም፦ እንዲህ አላደረግሽብኝም አላት። እግዚአብሔርም የበለዓምን ዓይኖች ከፈተ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተምዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየ፤ ሰገደም፥ በግምባሩም ወደቀ። የእግዚአብሔርም መልአክ፦ አህያህን ሦስት ጊዜ ለምን መታህ? እነሆ፥ መንገድህ በፊቴ ጠማማ ነውና እቍቍምህ ዘንድ ወጥቼአለሁ፤ አህያይቱም አይታኝ ከፊቴ ሦስት ጊዜ ፈቀቅ አለች፤ ከፊቴስ ፈቀቅ ባላለች በእውነት አሁን አንተን በገደልሁህ፥ እርስዋንም ባዳንኋት ነበር አለው። በለዓምም የእግዚአብሔርን መልአክ፦ በድያለሁ፤ አንተ በመንገድ ላይ በፊቴ እንደቆምህብኝ አላወቅሁም፤ እንግዲህም አሁን አትወድድ እንደ ሆነ እመለሳለሁ አለው። የእግዚአብሔርም መልአክ በለዓምን፦ ከሰዎቹ ጋር ሂድ፥ ነገር ግን የምናገርህን ቃል ብቻ ትናገራለህ አለው። በለዓምም ከባላቅ አለቆች ጋር ሄደ።
ዘኍል 22:19-35 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ነገር ግን እግዚአብሔር የሚነግረኝ ሌላ ነገር ካለ ከእርሱ እረዳ ዘንድ እስቲ እናንተም እንደ ፊተኞቹ መልእክተኞች ሌሊቱን እዚሁ አሳልፉ።” በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ወደ በለዓም መጣና “እነዚህ ሰዎች ወደ አንተ የመጡት ይዘውህ ሊሄዱ ከሆነ ተነሥተህ አብረሃቸው ሂድ፤ ነገር ግን እኔ የምነግርህን ብቻ አድርግ” አለው። ስለዚህ በማግስቱ ጠዋት በለዓም ተነሣና አህያውን ጭኖ ከሞአባውያን መሪዎች ጋር ሄደ። በለዓም በመሄዱ እግዚአብሔር ተቈጣ፤ በለዓም ሁለቱን አሽከሮቹን በማስከተል በአህያው ላይ ተቀምጦ በሚጓዝበት ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በፊቱ ቆሞ መንገዱን ዘጋበት፤ መልአኩ ሰይፉን መዞ በመንገዱ ላይ መቆሙን አህያይቱ በተመለከተች ጊዜ መንገዱን ለቃ ወደ እርሻ ገባች፤ በለዓምም አህያይቱን ወደ መንገዱ ለመመለስ ደበደባት፤ መንገዱ በሁለት የወይን ተክል ቦታዎች መካከል እየጠበበ ሲሄድና በሁለቱም በኩል የድንጋይ ግንብ ሲገጥመው መልአኩ መጥቶ በፊት ለፊት ቆመ። አህያይቱ መልአኩን ባየች ጊዜ ወደ ግንቡ ተጠግታ የበለዓምን እግር ከግንቡ ጋር አጣበቀችው፤ በለዓም አሁንም አህያይቱን መደብደብ ጀመረ፤ እንደገናም መልአኩ ወደ ፊት ቀድሞ ሄደና በግራም ሆነ በቀኝ መተላለፊያ በሌለበት ጠባብ ቦታ ላይ ቆመ። በዚህን ጊዜ አህያይቱ መልአኩን ስታይ በመሬት ላይ ተኛች፤ በለዓምም እጅግ ተቈጥቶ አህያይቱን በብትር መደብደብ ጀመረ። በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ለአህያይቱ የመናገር ችሎታ ስለ ሰጣት በለዓምን “እኔ ምን አደረግሁህ? ሦስት ጊዜ የደበደብከኝ ስለምንድን ነው?” አለችው። በለዓምም “እጅግ ስለ ተጫወትሽብኝ ነዋ! ሰይፍ ቢኖረኝማ አሁን በገደልኩሽ ነበር!” አላት። አህያይቱም “በሕይወትህ ሙሉ ስትጋልበኝ የኖርክ አህያህ አይደለሁምን? ታዲያ ከዚህ በፊት እንደ ዛሬ ሆኜብህ ዐውቃለሁን?” ስትል መለሰችለት። በለዓምም “ከቶ እንዲህ ሆነሽብኝ አታውቂም” አላት። በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር በለዓም ሰይፍ ይዞ የቆመውን መልአክ ለማየት እንዲችል አደረገው፤ በለዓምም በግንባሩ ወደ መሬት ተደፋ፤ መልአኩም እንዲህ አለው፤ “አህያህን እንዲህ አድርገህ ሦስት ጊዜ የመታሃት ለምንድን ነው? እኔ መጥቼ መንገድህን የዘጋሁት በጥፋት ጐዳና እንዳትሄድ ልከለክልህ ብዬ ነው፤ የአንተ አህያ ግን እኔን በማየትዋ ሦስት ጊዜ ከፊቴ ሸሸች፤ አህያይቱ እንዲህ ባታደርግ ኖሮ አንተን ገድዬ እርስዋ በሕይወት እንድትኖር በተውኳት ነበር።” በለዓምም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “በእርግጥ ኃጢአት ሠርቻለሁ፤ አንተ እኔን ለመቃወም በመንገድ ላይ መቆምህን አላወቅሁም ነበር፤ አሁንም ወደዚያ መሄዴ ስሕተት መስሎ ከታየህ ወደ ቤቴ እመለሳለሁ።” መልአኩ ግን “ከእነዚህ ሰዎች ጋር መሄዱን ሂድ፤ ነገር ግን እኔ የምነግርህን ብቻ ተናገር” አለው፤ በዚህ ዐይነት በለዓም ከባላቅ ባለሥልጣኖች ጋር ሄደ።
ዘኍል 22:19-35 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አሁንም ጌታ ይበልጥ የሚነግረኝን ነገር እንዳውቅ፥ እባካችሁ፥ ሌሎቹ እንዳደረጉት እንዲሁ ዛሬ ሌሊት ደግሞ በዚህ እደሩ።” እግዚአብሔርም ወደ በለዓም በሌሊት መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ሰዎቹ ሊጠሩህ መጥተው እንደሆነ፥ ተነሣ ከእነርሱም ጋር ሂድ፤ ነገር ግን የምነግርህን ቃል ብቻ ታደርጋለህ።” በለዓምም ሲነጋ ተነሣ፥ አህያይቱንም ጭኖ ከሞዓብ ሹማምንት ጋር ሄደ። እርሱም ስለ ሄደ እግዚአብሔር ተቈጣ፤ የጌታም መልአክ ሊቃወመው በመንገድ ላይ ቆመ። እርሱም በአህያይቱ ላይ ሆኖ ይጓዝ ነበር፥ ሁለቱም ሎሌዎቹ ከእርሱ ጋር ነበሩ። አህያይቱም የጌታን መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየች፤ እርሷም ከመንገዱ ፈቀቅ ብላ ወደ እርሻው ውስጥ ገባች፤ በለዓምም ወደ መንገድ እንድትመለስ አህያይቱን መታት። የጌታም መልአክ ከወይኑ ቦታዎች መካከል በወዲያና በወዲህ ወገን ግንብ በነበረበት በጠባብ መንገድ ላይ ቆመ። አህያይቱም የጌታን መልአክ አይታ ወደ ቅጥሩ ተጠጋች፥ የበለዓምንም እግር ከቅጥሩ ጋር አጣበቀች፤ እርሱም ዳግመኛ መታት። የጌታም መልአክ ወደ ፊት ሄደ፥ በቀኝና በግራ መተላለፊያ በሌለበት በጠባብ ስፍራ ቆመ። አህያይቱም የጌታን መልአክ አየች፥ ከበለዓምም በታች ተምበርክካ ለጥ አለች፤ በለዓምም እጅግ ተቈጣ፥ አህያይቱንም በበትሩ ደበደባት። ጌታም የአህያይቱን አፍ ከፈተ፥ በለዓምንም፦ “ሦስት ጊዜ የመታኸኝ ምን አድርጌህ ነው?” አለችው። በለዓምም አህያይቱን፦ “ስላላገጥሽብኝ ነው፤ በእጄስ ሰይፍ ቢኖር አሁን በገደልሁሽ ነበር” አላት። አህያይቱም በለዓምን እንዲህ አለችው፦ “ከብዙ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የምትቀመጥብኝ አህያህ አይደለሁምን? በውኑ እንዲህ ማድረግ ልማዴ ነበረን?” እርሱም፦ “እንዲህ አላደረግሽብኝም” አላት። ጌታም የበለዓምን ዐይኖች ከፈተ፤ የጌታም መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተምዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየ፤ ሰገደም፥ በግምባሩም ወደ መሬት ተደፋ። የጌታም መልአክ እንዲህ አለው፦ “አህያህን ሦስት ጊዜ ለምን መታህ? እነሆ፥ መንገድህ በፊቴ ጠማማ ነውና ልቃወምህ ወጥቼአለሁ፤ አህያይቱም አይታኝ ከፊቴ ሦስት ጊዜ ፈቀቅ አለች፤ ከፊቴስ ፈቀቅ ባትል ኖሮ በእውነት አሁን አንተን በገደልሁህ፥ እርሷንም ባዳንኋት ነበር።” በለዓምም የጌታን መልአክ እንዲህ አለው፦ “ኃጢአትን ሠርቻለሁ፤ አንተ በመንገድ ላይ ልትቃወመኝ መቆምክን አላወቅሁም፤ እንግዲህም ይህ አሁን በፊትህ ክፉ የሆነ ነገር ቢሆን እመለሳለሁ።” የጌታም መልአክ በለዓምን፦ “ከሰዎቹ ጋር ሂድ፥ ነገር ግን የምነግርህን ቃል ብቻ ትናገራለህ” አለው። በለዓምም ከባላቅ ሹማምንት ጋር ሄደ።