የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኊልቊ 22

22
1የእስራኤልም ልጆች ተጓዙ፥ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በዮርዳኖስ ማዶ ባለው በሞዓብ ሜዳ ሰፈሩ። 2የሴፎር ልጅ ባላቅ እስራኤል በአሞራውያን ላየ ያደረገውን ሁሉ አየ። 3ብዙም ነበረና ሞዓብ ከሕዝቡ እጅግ ፈራ፤ ከእስራኤልም ልጆች የተነሣ ሞዓብ ደነገጠ። 4ሞዓብም የምድያምን ሽማግሌዎች፦ በሬ የለመለመውን ሣር እንደሚጨርስ ይህ ጭፍራ በዙሪያችን ያለውን ሁሉ ይጨርሳል አላቸው። በዚያን ጊዜም የሴፎር ልጅ ባላቅ የሞዓብ ንጉሥ ነበረ። 5-6በወንዙ አጠገብ ባለችው በሕዝቡ ልጆች ምድር በፋቱራ ወደ ተቀመጠው ወደ ቢዖር ልጅ ወደ በለዓም፦ እነሆ፥ ከግብፅ የወጣ ሕዝብ አለ፤ እነሆም፥ የምድሩን ሁሉ ፊት ሸፈነ፥ በአቅራቢያችንም ተቀምጦአል፤ አሁንም ይህ ሕዝብ ከእኔ ይበልጣልና ልወጋቸውና ከምድሪቱ ላሳድዳቸው እችል እንደ ሆነ፥ እባክህ፥ ና ርገምልኝ፤ አንተ የመረቅኸው ምሩቅ የረገምኸውም ርጉም እንደ ሆነ አውቃለሁና ብሎ ይጠሩት ዘንድ መልእክተኞቹን ላከ። 7የሞዓብ ሽማግሌዎችና የምድያም ሽማግሌዎችም የምዋርቱን ዋጋ በእጃቸው ይዘው ሄዱ፤ ወደ በለዓምም መጡ፥ የባላቅንም ቃል ነገሩት። 8እርሱም፦ ዛሬ ሌሊት በዚህ እደሩ፥ እግዚአብሔርም እንደሚነግረኝ እመልስላችኋለሁ አላቸው፤ የሞዓብም አለቆች በበለዓም ዘንድ ተቀመጡ። 9እግዚአብሔርም ወደ በለዓም መጥቶ፦ እነዚህ በአንተ ዘንድ ያሉ ሰዎች እነማን ናቸው? አለው። 10-11በለዓምም እግዚአብሔርን፦ የሞዓብ ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ፦ እነሆ፥ ከግብፅ የወጣ ሕዝብ የምድርን ፊት ሸፈነ፥ አሁንም ና እርሱንም ርገምልኝ፤ ምናልባት እወጋው አሳድደውም ዘንድ እችል እንደ ሆነ ብሎ ወደ እኔ ልኮአል አለው። 12እግዚአብሔርም በለዓምን፦ ከእነርሱ ጋር አትሂድ፤ የተባረከ ነውና ሕዝቡን አትረግምም አለው። 13በለዓምም ሲነጋ ተነሥቶ የባላቅን አለቆች፦ ከእናንተ ጋር እሄድ ዘንድ እግዚአብሔር አልፈቀደምና ወደ ምድራችሁ ሂዱ አላቸው። 14የሞዓብ አለቆች ተነሡ፥ ወደ ባላቅም መጥተው፦ በለዓም ከእኛ ጋር ይመጣ ዘንድ አልፈቀደም አሉት። 15ባላቅም ደግሞ ከፊተኞች የበዙና የከበሩ ሌሎችን አለቆች ሰደደ። 16-17ወደ በለዓምም መጥተው፦ የሴፎር ልጅ ባላቅ፦ ክብርህን እጅግ ታላቅ አደርገዋለሁና፥ የተናገርኸውንም ሁሉ አደርግልሃለሁና፥ እባክህ፥ ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ ምንም አይከልክልህ፤ እባክህ፥ ና፥ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ አለ ብለው ነገሩት። 18በለዓምም መልሶ የባላቅን ባሪያዎች፦ ባላቅ በቤቱ የሞላውን ወርቅና ብር ቢሰጠኝ፥ በትንሹ ወይም በትልቁ ቢሆን የአምላኬን የእግዚአብሔርን ቃል እተላለፍ ዘንድ አይቻለኝም፤ 19አሁንም እግዚአብሔር ደግሞ የሚነግረኝን አውቅ ዘንድ፥ እባካችሁ፥ ዛሬ ሌሊት ደግሞ በዚህ እደሩ አላቸው። 20እግዚአብሔርም ወደ በለዓም በሌሊት መጥቶ፦ ሰዎቹ ይጠሩህ ዘንድ መጥተው እንደ ሆነ፥ ተነሣ ከእነርሱም ጋር ሂድ፤ ነገር ግን የምነግርህን ቃል ብቻ ታደርጋለህ አለው። 21በለዓምም ሲነጋ ተነሣ፥ አህያይቱንም ጭኖ ከሞዓብ አለቆች ጋር ሄደ። 22እርሱም ስለ ሄደ እግዚአብሔር ተቈጣ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ሊቍቍመው በመንገድ ላይ ቆመ። እርሱም በአህያይቱ ላይ፥ ሁለቱም ሎሌዎቹ ከእርሱ ጋር ነበሩ። 23አህያይቱም የእግዚአብሔርን መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየች፤ ከመንገዱም ፈቀቅ ብላ ወደ እርሻው ውስጥ ገባች፤ በለዓምም ወደ መንገድ ይመልሳት ዘንድ አህያይቱን መታት። 24የእግዚአብሔርም መልአክ ከወይኑ ቦታዎች መካከል በወዲያና በወዲህ ወገን ግንብ በነበረበት በጠባብ መንገድ ላይ ቆመ። 25አህያይቱም የእግዚአብሔርን መልአክ አይታ ወደ ቅጥሩ ተጠጋች፥ የበለዓምንም እግር ከቅጥሩ ጋር አጣበቀች፤ እርሱም ደግሞ መታት። 26የእግዚአብሔርም መልአክ ወደ ፊት ሄደ፥ በቀኝና በግራ መተላለፊያ በሌለበት በጠባብ ስፍራ ቆመ። 27አህያይቱም የእግዚአብሔርን መልአክ አየች፥ ከበለዓምም በታች ተኛች፤ በለዓምም እጅግ ተቈጣ፥ አህያይቱንም በበትሩ ደበደባት። 28እግዚአብሔርም የአህያይቱን አፍ ከፈተ፥ በለዓምንም፦ ሦስት ጊዜ የመታኸኝ ምን አድርጌብህ ነው? አለችው። 29በለዓምም አህያይቱን፦ ስላላገጥሽብኝ ነው፤ በእጄስ ሰይፍ ቢኖር አሁን በገደልሁሽ ነበር አላት። 30አህያይቱም በለዓምን፦ ከብዙ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የምትቀመጥብኝ አህያህ አይደለሁምን? በውኑ እንዲህ አደርግ ዘንድ ልማዴ ነበረን? አለችው። እርሱም፦ እንዲህ አላደረግሽብኝም አላት። 31እግዚአብሔርም የበለዓምን ዓይኖች ከፈተ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተምዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየ፤ ሰገደም፥ በግምባሩም ወደቀ። 32የእግዚአብሔርም መልአክ፦ አህያህን ሦስት ጊዜ ለምን መታህ? እነሆ፥ መንገድህ በፊቴ ጠማማ ነውና እቍቍምህ ዘንድ ወጥቼአለሁ፤ 33አህያይቱም አይታኝ ከፊቴ ሦስት ጊዜ ፈቀቅ አለች፤ ከፊቴስ ፈቀቅ ባላለች በእውነት አሁን አንተን በገደልሁህ፥ እርስዋንም ባዳንኋት ነበር አለው። 34በለዓምም የእግዚአብሔርን መልአክ፦ በድያለሁ፤ አንተ በመንገድ ላይ በፊቴ እንደቆምህብኝ አላወቅሁም፤ እንግዲህም አሁን አትወድድ እንደ ሆነ እመለሳለሁ አለው። 35የእግዚአብሔርም መልአክ በለዓምን፦ ከሰዎቹ ጋር ሂድ፥ ነገር ግን የምናገርህን ቃል ብቻ ትናገራለህ አለው። በለዓምም ከባላቅ አለቆች ጋር ሄደ። 36ባላቅም በለዓም እንደ መጣ በሰማ ጊዜ በአርኖን ዳር ዳርቻ በመጨረሻ ወዳለችው ወደ ሞዓብ ከተማ ሊገናኘው ወጣ። 37ባላቅም በለዓምን፦ በውኑ አንተን ለመጥራት አልላክሁብህምን? ለምንስ ወደ እኔ አልመጣህም? በውኑ አንተን ለማክበር እኔ አልችልምን? አለው። 38በለዓምም ባላቅን፦ እነሆ፥ ወደ አንተ መጥቼአለሁ፤ በውኑ አሁን አንዳችን ነገር እናገር ዘንድ እችላለሁን? እግዚአብሔር በአፌ የሚያድርገውን ቃል እርሱን እናገራለሁ አለው። 39በለዓምም ከባላቅ ጋር ሄደ፥ ወደ ቂርያት ሐጾትም መጡ። 40ባላቅም በሬዎችንና በጎችን አርዶ ወደ በለዓም ከእርሱም ጋር ወዳሉት አለቆች ላከ። 41በነጋውም ባላቅ በለዓምን ይዞ ወደ በኣል ኮረብታ መስገጃ አወጣው፤ በዚያም ሆኖ የሕዝቡን ዳርቻ አየ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ