ኦሪት ዘኊልቊ 22
22
ባላቅ እስራኤልን እንዲረግምለት በለዓምን ማስጠራቱ
1እስራኤላውያን ጒዞአቸውን በመቀጠል ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምሥራቅና በኢያሪኮ ትይዩ በሚገኘው በሞአብ ሜዳ ላይ ሰፈሩ።
2የሞአብ ንጉሥ የጺጶር ልጅ ባላቅ እስራኤላውያን በአሞራውያን ላይ ያደረሱትን ጒዳት አየ፥ 3በእስራኤላውያን ብዛት ምክንያት የሞአብ ሕዝብ ታላቅ ፍርሀት ዐደረባቸው፤ እስራኤላውያንንም በጣም ፈሩ። 4ሞአባውያን ለምድያማውያን ሽማግሌዎች “ይህ የምታዩት የሕዝብ ብዛት በሬ በመስክ የሚገኘውን ሣር ሁሉ ጠራርጎ እንደሚበላ በዙሪያችን ያለውን ነገር ሁሉ ጠራርጎ የሚያጠፋ ነው” አሉአቸው። ስለዚህ በዚያን ጊዜ የሞአብ ንጉሥ የነበረው የጺጶር ልጅ ባላቅ፥ 5በዓማው ምድር በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ በፐቶር ከተማ ይኖር ወደነበረው ወደ ቢዖር ልጅ ወደ በለዓም ይጠሩት ዘንድ መልእክተኞች እንዲህ ብሎ ላከበት፤ “ከግብጽ የወጣ አንድ ሕዝብ ምድሪቱን ሁሉ ሸፍኖአታል፤ እነርሱም በአቅራቢያችን ሰፍረዋል፤ #ዘኍ. 31፥8፤ 2ጴጥ. 2፥15-16፤ ይሁዳ 11። 6የሕዝቡም ቊጥር ከእኛ እጅግ የበዛ ነው፤ ስለዚህ ወደዚህ መጥተህ እነርሱን ርገምልኝ፤ በዚህ ዐይነት ምናልባት ድል ልነሣቸውና ከምድሪቱ ላስወጣቸው እችል ይሆናል፤ አንተ የምትመርቀው የተመረቀ፥ አንተም የምትረግመው የተረገመ እንደሚሆን ዐውቃለሁ።”
7ስለዚህ የሞአባውያንና የምድያማውያን ሽማግሌዎች ስለ ርግማን የሚከፈለውን ገንዘብ ይዘው ወደ በለዓም በመሄድ የባላቅን መልእክት ሰጡት፤ 8በለዓምም “እዚሁ ዕደሩና ነገ ጧት እግዚአብሔር የሚነግረኝን ሁሉ እነግራችኋለሁ” አላቸው፤ በዚህ ዐይነት የሞአባውያን መሪዎች ከበለዓም ጋር ቈዩ።
9እግዚአብሔርም ወደ በለዓም መጥቶ “እነዚህ ከአንተ ጋር ያሉት ሰዎች እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቀው።
10እርሱም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “የሞአብ ንጉሥ የጲዖር ልጅ ባላቅ እንዲህ ብሎ ወደ እኔ የላካቸው ናቸው፦ 11‘ከግብጽ የወጣ ሕዝብ ምድሪቱን ሸፍኖአታል፤ መጥተህ ብትረግምልኝ ምናልባት እነርሱን በጦርነት ተዋግቼ ላስወጣቸው እችል ይሆናል።’ ”
12እግዚአብሔርም በለዓምን “ከነዚህ ሰዎች ጋር አትሂድ፤ የተባረኩ ስለ ሆነ የእስራኤልን ሕዝብ አትርገም” አለው።
13በለዓምም በማግስቱ ጠዋት ሲነጋ ተነሥቶ፥ ለባላቅ ሹማምንት “እንግዲህ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ፤ እኔ ከእናንተ ጋር እንዳልሄድ እግዚአብሔር ከልክሎኛል” አላቸው፤ 14ስለዚህ የሞአብ ሹማምንት ወደ ባላቅ ተመለሱና በለዓም አብሮአቸው ለመምጣት እምቢ እንዳለ ነገሩት።
15ከዚያን በኋላ ባላቅ ከፊተኞቹ መልእክተኞች ይበልጥ የተከበሩና ቊጥራቸውም የበዛ ሹማምንት ወደ በለዓም ላከ፤ 16እነርሱም ወደ በለዓም ሄደው የባላቅን መልእክት እንዲህ ሲሉ ነገሩት፤ “ወደ እኔ መምጣት እንዳትችል የሚያግድህ ነገር አይኑር! 17ከፍ ባለ ክብር አከብርሃለሁ፤ የጠየቅከኝንም ሁሉ አደርግልሃለሁ፤ ስለዚህ እባክህ መጥተህ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ።”
18በለዓም ግን ለመልእክተኞቹ እንዲህ ሲል መልስ ሰጠ፤ “ባላቅ በቤተ መንግሥቱ የሚገኘውን ብርና ወርቅ ሁሉ ቢሰጠኝም በትንሽ ወይም በትልቅ ነገር የአምላኬን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መተላለፍ አይቻለኝም፤ 19ነገር ግን እግዚአብሔር የሚነግረኝ ሌላ ነገር ካለ ከእርሱ እረዳ ዘንድ እስቲ እናንተም እንደ ፊተኞቹ መልእክተኞች ሌሊቱን እዚሁ አሳልፉ።”
20በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ወደ በለዓም መጣና “እነዚህ ሰዎች ወደ አንተ የመጡት ይዘውህ ሊሄዱ ከሆነ ተነሥተህ አብረሃቸው ሂድ፤ ነገር ግን እኔ የምነግርህን ብቻ አድርግ” አለው። 21ስለዚህ በማግስቱ ጠዋት በለዓም ተነሣና አህያውን ጭኖ ከሞአባውያን መሪዎች ጋር ሄደ።
በለዓምና አህያይቱ
22በለዓም በመሄዱ እግዚአብሔር ተቈጣ፤ በለዓም ሁለቱን አሽከሮቹን በማስከተል በአህያው ላይ ተቀምጦ በሚጓዝበት ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በፊቱ ቆሞ መንገዱን ዘጋበት፤ 23መልአኩ ሰይፉን መዞ በመንገዱ ላይ መቆሙን አህያይቱ በተመለከተች ጊዜ መንገዱን ለቃ ወደ እርሻ ገባች፤ በለዓምም አህያይቱን ወደ መንገዱ ለመመለስ ደበደባት፤ 24መንገዱ በሁለት የወይን ተክል ቦታዎች መካከል እየጠበበ ሲሄድና በሁለቱም በኩል የድንጋይ ግንብ ሲገጥመው መልአኩ መጥቶ በፊት ለፊት ቆመ። 25አህያይቱ መልአኩን ባየች ጊዜ ወደ ግንቡ ተጠግታ የበለዓምን እግር ከግንቡ ጋር አጣበቀችው፤ በለዓም አሁንም አህያይቱን መደብደብ ጀመረ፤ 26እንደገናም መልአኩ ወደ ፊት ቀድሞ ሄደና በግራም ሆነ በቀኝ መተላለፊያ በሌለበት ጠባብ ቦታ ላይ ቆመ። 27በዚህን ጊዜ አህያይቱ መልአኩን ስታይ በመሬት ላይ ተኛች፤ በለዓምም እጅግ ተቈጥቶ አህያይቱን በብትር መደብደብ ጀመረ። 28በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ለአህያይቱ የመናገር ችሎታ ስለ ሰጣት በለዓምን “እኔ ምን አደረግሁህ? ሦስት ጊዜ የደበደብከኝ ስለምንድን ነው?” አለችው።
29በለዓምም “እጅግ ስለ ተጫወትሽብኝ ነዋ! ሰይፍ ቢኖረኝማ አሁን በገደልኩሽ ነበር!” አላት። 30አህያይቱም “በሕይወትህ ሙሉ ስትጋልበኝ የኖርክ አህያህ አይደለሁምን? ታዲያ ከዚህ በፊት እንደ ዛሬ ሆኜብህ ዐውቃለሁን?” ስትል መለሰችለት። በለዓምም “ከቶ እንዲህ ሆነሽብኝ አታውቂም” አላት።
31በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር በለዓም ሰይፍ ይዞ የቆመውን መልአክ ለማየት እንዲችል አደረገው፤ በለዓምም በግንባሩ ወደ መሬት ተደፋ፤ 32መልአኩም እንዲህ አለው፤ “አህያህን እንዲህ አድርገህ ሦስት ጊዜ የመታሃት ለምንድን ነው? እኔ መጥቼ መንገድህን የዘጋሁት በጥፋት ጐዳና እንዳትሄድ ልከለክልህ ብዬ ነው፤ 33የአንተ አህያ ግን እኔን በማየትዋ ሦስት ጊዜ ከፊቴ ሸሸች፤ አህያይቱ እንዲህ ባታደርግ ኖሮ አንተን ገድዬ እርስዋ በሕይወት እንድትኖር በተውኳት ነበር።”
34በለዓምም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “በእርግጥ ኃጢአት ሠርቻለሁ፤ አንተ እኔን ለመቃወም በመንገድ ላይ መቆምህን አላወቅሁም ነበር፤ አሁንም ወደዚያ መሄዴ ስሕተት መስሎ ከታየህ ወደ ቤቴ እመለሳለሁ።”
35መልአኩ ግን “ከእነዚህ ሰዎች ጋር መሄዱን ሂድ፤ ነገር ግን እኔ የምነግርህን ብቻ ተናገር” አለው፤ በዚህ ዐይነት በለዓም ከባላቅ ባለሥልጣኖች ጋር ሄደ።
ባላቅ በለዓምን በደስታ እንደ ተቀበለው
36ባላቅ የበለዓምን መምጣት በሰማ ጊዜ እርሱን ለመቀበል በሞአብ ጠረፍ በአርኖን ወንዝ ዳር ወደምትገኘው ወደ ዔር ከተማ ሄደ። 37ባላቅ በለዓምን “በመጀመሪያ ሰዎች በላክሁብህ ጊዜ ስለምን አልመጣህም? አንተን ለማክበር የማልችል መስሎህ ነውን?” ሲል ጠየቀው።
38በለዓምም “ያም ሆነ ይህ አሁን መጥቼ የለምን? ታዲያ አሁንስ ቢሆን በራሴ ምን ኀይል አለኝ? እኔ ልናገር የምችለው እግዚአብሔር የሚነግረኝን ብቻ ነው” ሲል መለሰለት። 39ስለዚህ በለዓም ከባላቅ ጋር ወደ ቂርያት ሑጾት ከተማ ሄደ። 40በዚያም ባላቅ፥ ከብቶችና በጎች አሳርዶ ከሥጋው ጥቂቱን አብረውት ለነበሩት መሪዎችና ለበለዓም ሰጠ።
41በማግስቱ ጠዋት ባላቅ በለዓምን የእስራኤልን ሕዝብ በከፊል ለማየት ወደሚቻልበት ወደ ባሞትበዓል አወጣው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኊልቊ 22: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997