የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘኍል 22:1-41

ዘኍል 22:1-41 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ልጆች ተጓዙ፤ በኢ​ያ​ሪኮ በኩል በዮ​ር​ዳ​ኖስ አጠ​ገብ በሞ​ዓብ ምዕ​ራ​ብም ሰፈሩ። የሴ​ፎር ልጅ ባላቅ እስ​ራ​ኤል በአ​ሞ​ሬ​ዎ​ና​ው​ያን ላይ ያደ​ረ​ገ​ውን ሁሉ አየ። ብዙም ነበ​ረና ሞዓብ ከሕ​ዝቡ እጅግ ፈራ፤ ከእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ልጆች የተ​ነሣ ሞዓብ ደነ​ገጠ። ሞዓ​ብም የም​ድ​ያ​ምን ሽማ​ግ​ሌ​ዎች፥ “በሬ የለ​መ​ለ​መ​ውን ሣር እን​ደ​ሚ​ጨ​ርስ ይህ ሠራ​ዊት በዙ​ሪ​ያ​ችን ያለ​ውን ሁሉ ይጨ​ር​ሳል” አላ​ቸው። በዚ​ያን ጊዜ የሶ​ፎር ልጅ ባላቅ የሞ​ዓብ ንጉሥ ነበረ። በወ​ን​ዙም አጠ​ገብ ባለ​ችው በሕ​ዝቡ ልጆች ምድር በፋ​ቱራ ወደ ተቀ​መ​ጠው ወደ ቢዖር ልጅ ወደ በለ​ዓም፥ “እነሆ፥ ከግ​ብፅ የወጣ ሕዝብ አለ፤ እነ​ሆም፥ የም​ድ​ሩን ሁሉ ፊት ሸፈነ፤ በአ​ቅ​ራ​ቢ​ያ​ች​ንም ተቀ​ም​ጦ​አል፤ አሁ​ንም ይህ ሕዝብ ከእኔ ይበ​ል​ጣ​ልና ልወ​ጋ​ቸ​ውና ከም​ድ​ሪቱ ላሳ​ድ​ዳ​ቸው እችል እንደ ሆነ፥ ና ርገ​ም​ልኝ፤ አንተ የመ​ረ​ቅ​ኸው ምሩቅ፥ የረ​ገ​ም​ኸ​ውም ርጉም እንደ ሆነ አው​ቃ​ለ​ሁና” ብሎ ይጠ​ሩት ዘንድ መል​እ​ክ​ተ​ኞ​ችን ላከ። የሞ​ዓብ ሽማ​ግ​ሌ​ዎ​ችና የም​ድ​ያም ሽማ​ግ​ሌ​ዎ​ችም የም​ዋ​ር​ቱን ዋጋ በእ​ጃ​ቸው ይዘው ሄዱ፤ ወደ በለ​ዓ​ምም መጡ፤ የባ​ላ​ቅ​ንም ቃል ነገ​ሩት። እር​ሱም፥ “ዛሬ ሌሊት በዚህ እደሩ፤ እግ​ዚ​እ​ብ​ሔ​ርም የሚ​ነ​ግ​ረ​ኝን እነ​ግ​ራ​ች​ኋ​ለሁ” አላ​ቸው፤ የሞ​ዓብ አለ​ቆ​ችም በበ​ለ​ዓም ዘንድ አደሩ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ወደ በለ​ዓም መጥቶ፥ “እነ​ዚህ በአ​ንተ ዘንድ ያሉ ሰዎች እነ​ማን ናቸው?” አለው። በለ​ዓ​ምም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን እን​ዲህ አለው፥ “የሞ​ዓብ ንጉሥ የሶ​ፎር ልጅ ባላቅ፦ እን​ዲህ ሲል ወደ እኔ ልኮ​አ​ቸ​ዋል፤ እነሆ፥ ከግ​ብፅ የወጣ ሕዝብ የም​ድ​ርን ፊት ሸፈነ፤ በአ​ቅ​ራ​ቢ​ያ​ዬም ተቀ​ም​ጦ​አል፤ ምና​ል​ባት እወ​ጋው፥ አሳ​ድ​ደ​ውም ዘንድ እችል እንደ ሆነ አሁ​ንም ና እር​ሱን ርገ​ም​ልኝ።” እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም በለ​ዓ​ምን፥ “ከእ​ነ​ርሱ ጋር አት​ሂድ፤ የተ​ባ​ረከ ነውና ሕዝ​ቡን አት​ር​ገም” አለው። በለ​ዓ​ምም ሲነጋ ተነ​ሥቶ የባ​ላ​ቅን አለ​ቆች፥ “ከእ​ና​ንተ ጋር እሄድ ዘንድ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አል​ፈ​ቀ​ደ​ል​ኝ​ምና ወደ ጌታ​ችሁ ሂዱ” አላ​ቸው። የሞ​ዓብ አለ​ቆ​ችም ተነሡ፤ ወደ ባላ​ቅም መጥ​ተው፥ “በለ​ዓም ከእኛ ጋር ይመጣ ዘንድ አል​ፈ​ቀ​ደም” አሉት። ባላ​ቅም ደግሞ ከእ​ነ​ዚያ የበ​ዙና የከ​በሩ ሌሎ​ችን አለ​ቆች ሰደደ። ወደ በለ​ዓ​ምም መጥ​ተው፥ “የሶ​ፎር ልጅ ባላቅ፦ እባ​ክህ ወደ እኔ መም​ጣ​ትን ቸል አት​በል፤ ክብ​ር​ህን እጅግ ታላቅ አደ​ር​ገ​ዋ​ለ​ሁና፥ የተ​ና​ገ​ር​ኸ​ው​ንም ሁሉ አደ​ር​ግ​ል​ሃ​ለ​ሁና ና፥ ይህን ሕዝብ ርገ​ም​ልኝ ብሏል” አሉት። በለ​ዓ​ምም መልሶ የባ​ላ​ቅን አለ​ቆች፥ “ባላቅ በቤቱ የሞ​ላ​ውን ወር​ቅና ብር ቢሰ​ጠኝ፥ በት​ንሹ ወይም በት​ልቁ ቢሆን የአ​ም​ላ​ኬን የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ቃል እተ​ላ​ለፍ ዘንድ አይ​ቻ​ለ​ኝም፤ አሁ​ንም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ደግሞ የሚ​ነ​ግ​ረ​ኝን አውቅ ዘንድ ዛሬ ሌሊት ደግሞ በዚህ እደሩ” አላ​ቸው። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ወደ በለ​ዓም በሌ​ሊት መጥቶ፥ “ሰዎቹ ይጠ​ሩህ ዘንድ መጥ​ተው እንደ ሆነ፥ ተነሣ ከእ​ነ​ርሱ ጋር ሂድ፤ ነገር ግን የም​ነ​ግ​ር​ህን ቃል ታደ​ር​ጋ​ለህ” አለው። በለ​ዓ​ምም ሲነጋ ተነሣ፤ አህ​ያ​ዪ​ቱ​ንም ጭኖ ከሞ​ዓብ አለ​ቆች ጋር ሄደ። እር​ሱም ስለ ሄደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ተቈጣ፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም መል​አክ ሊያ​ሰ​ና​ክ​ለው ተነሣ። እር​ሱም በአ​ህ​ያ​ዪቱ ላይ ተቀ​ምጦ ነበር፤ ሁለ​ቱም ብላ​ቴ​ና​ዎቹ ከእ​ርሱ ጋር ነበሩ። አህ​ያ​ዪ​ቱም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን መል​አክ በመ​ን​ገድ ላይ ቆሞ የተ​መ​ዘ​ዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየች፤ ከመ​ን​ገ​ዱም ላይ ፈቀቅ ብላ ወደ ሜዳ ውስጥ ገባች፤ በለ​ዓ​ምም ወደ መን​ገድ ይመ​ል​ሳት ዘንድ አህ​ያ​ዪ​ቱን መታት። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም መል​አክ ከወ​ይኑ ቦታ​ዎች መካ​ከል በወ​ዲ​ያና በወ​ዲህ ወገን ግንብ በነ​በ​ረ​በት ቆመ። አህ​ያ​ዪ​ቱም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን መል​አክ አይታ ወደ ቅጥሩ ተጠ​ጋች፤ የበ​ለ​ዓ​ም​ንም እግ​ሩን ላጠ​ችው፤ እር​ሱም ደግሞ መታት። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም መል​አክ ወደ ፊት ሄደ፤ በቀ​ኝና በግራ መተ​ላ​ለ​ፊያ በሌ​ለ​በት በጠ​ባብ ስፍራ ቆመ። አህ​ያ​ዪ​ቱም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን መል​አክ አየች፤ ከበ​ለ​ዓ​ምም በታች ተኛች፤ በለ​ዓ​ምም ተቈጣ፤ አህ​ያ​ዪ​ቱ​ንም በበ​ትሩ ደበ​ደ​ባት። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም የአ​ህ​ያ​ዪ​ቱን አፍ ከፈተ፤ በለ​ዓ​ም​ንም፥ “ሦስት ጊዜ የመ​ታ​ኸኝ ምን አድ​ር​ጌ​ብህ ነው?” አለ​ችው። በለ​ዓ​ምም አህ​ያ​ዪ​ቱን፥ “ስለ​ዘ​በ​ት​ሽ​ብኝ ነው፤ በእ​ጄስ ሰይፍ ቢኖር አሁን በገ​ደ​ል​ሁሽ ነበር” አላት። አህ​ያ​ዪ​ቱም በለ​ዓ​ምን፥ “ከወ​ጣ​ት​ነ​ትህ ጀምሮ እስከ ዛሬ የም​ት​ቀ​መ​ጥ​ብኝ አህ​ያህ አይ​ደ​ለ​ሁ​ምን? በውኑ አን​ተን ቸል ያል​ሁ​በት፥ በአ​ን​ተም እን​ዲህ ያደ​ረ​ግ​ሁ​በት ጊዜ ነበ​ርን?” አለ​ችው። እር​ሱም፥ “እን​ዲህ አላ​ደ​ረ​ግ​ሽ​ብ​ኝም” አላት። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም የበ​ለ​ዓ​ምን ዐይ​ኖች ከፈተ፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም መል​አክ በመ​ን​ገድ ላይ ቆሞ፥ የተ​መ​ዘ​ዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየ፤ በግ​ን​ባ​ሩም ወድቆ ሰገ​ደ​ለት። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም መል​አክ፥ “አህ​ያ​ህን ሦስት ጊዜ ለምን መታህ? እነሆ፥ መን​ገ​ድህ በፊቴ ቀና አል​ነ​በ​ረ​ምና ላሰ​ና​ክ​ልህ ወጥ​ቼ​አ​ለሁ፤ አህ​ያ​ዪ​ቱም አይ​ታኝ ከፊቴ ፈቀቅ አለች፤ ይህም ሦስ​ተኛ ጊዜ ነው፤ ከፊ​ቴስ ፈቀቅ ባላ​ለች በእ​ው​ነት አሁን አን​ተን በገ​ደ​ል​ሁህ፤ እር​ሷ​ንም ባዳ​ን​ኋት ነበር” አለው። በለ​ዓ​ምም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን መል​አክ፥ “በድ​ያ​ለሁ፤ አንተ በመ​ን​ገድ ላይ በፊቴ እንደ ቆም​ህ​ብኝ አላ​ወ​ቅ​ሁም፤ እን​ግ​ዲህ አሁን አት​ወ​ድድ እን​ደ​ሆነ እመ​ለ​ሳ​ለሁ” አለው። የእ​ግ​ዚ​እ​ብ​ሔ​ርም መል​አክ በለ​ዓ​ምን፥ “ከሰ​ዎቹ ጋር ሂድ፤ ነገር ግን የም​ና​ገ​ር​ህን ቃል ብቻ ለመ​ና​ገር ተጠ​ን​ቀቅ” አለው። በለ​ዓ​ምም ከባ​ላቅ አለ​ቆች ጋር ሄደ። “ባላ​ቅም በለ​ዓም እንደ መጣ በሰማ ጊዜ ከዳ​ር​ቻ​ዎች በአ​ን​ደኛ ክፍል በአ​ለ​ችው በአ​ር​ኖን ዳርቻ ወደ አለ​ችው ወደ ሞዓብ ከተማ ሊገ​ና​ኘው ወጣ። ባላ​ቅም በለ​ዓ​ምን፥ “አን​ተን ለመ​ጥ​ራት የላ​ክ​ሁ​ብህ አይ​ደ​ለ​ምን? ለም​ንስ ወደ እኔ አል​መ​ጣ​ህም? አን​ተን ለማ​ክ​በር እኔ አል​ች​ል​ምን?” አለው። በለ​ዓ​ምም ባላ​ቅን፥ “እነሆ፥ ወደ አንተ መጥ​ቼ​አ​ለሁ፤ አሁን አን​ዳ​ችን ነገር ለመ​ና​ገር እች​ላ​ለ​ሁን? እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በአፌ የሚ​ያ​ደ​ር​ገ​ውን ቃል እር​ሱን እና​ገ​ራ​ለሁ” አለው። በለ​ዓ​ምም ከባ​ላቅ ጋር ሄደ፤ ወደ ቅጽር ግቢ​ውም ገቡ። ባላ​ቅም በሬ​ዎ​ች​ንና በጎ​ችን አርዶ ወደ በለ​ዓም፥ ከእ​ር​ሱም ጋር ወዳ​ሉት አለ​ቆች ላከ። በነ​ጋ​ውም ባላቅ በለ​ዓ​ምን ይዞ ወደ በአል ኮረ​ብታ አወ​ጣው፤ በዚ​ያም ሆኖ የሕ​ዝ​ቡን አንድ ወገን አሳ​የው።

ዘኍል 22:1-41 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚህ በኋላ እስራኤላውያን ወደ ሞዓብ ሜዳ ተጕዘው ከዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ከኢያሪኮ ማዶ ሰፈሩ። በዚህ ጊዜ የሴፎር ልጅ ባላቅ፣ እስራኤል በአሞራውያን ላይ ያደረገውን ሁሉ አየ፤ ሞዓብም ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ተሸበረ፤ በርግጥም ሞዓብ በእስራኤላውያን ምክንያት በፍርሀት ተውጦ ነበር። ሞዓባውያንም የምድያምን ሽማግሌዎች፣ “በሬ የመስክ ሣር ጠራርጎ እንደሚበላ ሁሉ፣ ይህም ሰራዊት በዙሪያችን ያለውን ሁሉ ጠራርጎ የሚያጠፋ ነው” አሏቸው። ስለዚህ በዚያን ጊዜ የሞዓብ ንጉሥ የነበረው የሴፎር ልጅ ባላቅ፣ ከወንዙ ዳር ባለች በትውልድ አገሩ በምትገኝ በፋቱራ የነበረውን የቢዖርን ልጅ በለዓምን እንዲጠሩት መልእክተኞች ላከ፤ እንዲህም አለ፤ “እነሆ፤ ከብዛቱ የተነሣ ምድሩን የሸፈነ ሕዝብ ከግብፅ ወጥቶ በአቅራቢያዬ ሰፍሯል። ስለዚህ ይህን ሕዝብ መቋቋም ስለማልችል መጥተህ ርገምልኝ፤ ምናልባትም ድል አድርጌ ከአገሪቱ ላስወጣቸው የምችለው ከዚያ በኋላ ሊሆን ይችላል፤ አንተ የምትባርከው ቡሩክ፣ የምትረግመውም ርጉም እንደሚሆን ዐውቃለሁና።” የሞዓብና የምድያም ሽማግሌዎችም ለሟርት የሚከፈለውን ዋጋ ይዘው ሄዱ፤ በለዓም ዘንድ በደረሱ ጊዜም የባላቅን መልእክት ነገሩት። በለዓምም፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚሰጠኝን መልስ አመጣላችኋለሁና የዛሬን ሌሊት እዚሁ ዕደሩ” አላቸው። ስለዚህም የሞዓብ አለቆች ከእርሱ ዘንድ ቈዩ። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ወደ በለዓም መጥቶ፣ “ከአንተ ጋር ያሉት እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቀው። በለዓምም እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) እንዲህ አለው፤ “የሞዓብ ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ ይህን መልእክት ልኮብኛል፤ ‘ከግብፅ የወጣ ሕዝብ የምድሩን ገጽ አጥለቅልቆታል፤ ስለዚህ መጥተህ ርገምልኝ፤ ምናልባት ልዋጋቸውና ላባርራቸው የምችለው ከዚያ በኋላ ሊሆን ይችላል።’ ” እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ግን በለዓምን፣ “አብረሃቸው አትሂድ፤ የተባረከ ሕዝብ ስለ ሆነም አትርገመው” አለው። በማግስቱም ጧት በለዓም ተነሥቶ የባላቅን አለቆች፣ “አብሬአችሁ እንዳልሄድ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከልክሎኛልና እናንተ ወደ አገራችሁ ተመለሱ አላቸው።” ስለዚህ የሞዓብ አለቆች ወደ ባላቅ ተመልሰው፣ “በለዓም አብሮን ለመምጣት እንቢ አለን” አሉት። ከዚያም ባላቅ ከፊተኞቹ ይልቅ ቍጥራቸው የበዛና ይበልጥ የተከበሩ ሌሎች አለቆች ላከ። እነርሱም ወደ በለዓም መጥተው እንዲህ አሉት፤ “የሴፎር ልጅ ባላቅ ይህን እንድንነግርህ ልኮናል፤ ወደ እኔ ለመምጣት የሚያግድህ ምንም ነገር አይኑር፤ ወሮታህን በእጅጉ እከፍላለሁ፤ የምትለውንም ሁሉ አደርጋለሁ፤ ስለዚህ መጥተህ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ።” በለዓም ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “ሌላው ይቅርና ባላቅ በብርና በወርቅ የተሞላ ቤተ መንግሥቱን ቢሰጠኝ እንኳ፣ የአምላኬን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዝ በመጣስ ከዚያ ያለፈ ወይም ያነሰ ማንኛውንም ነገር ማድረግ አልችልም። አሁንም ሌሎቹ እንዳደረጉት ሁሉ፣ እናንተም ዛሬ እዚሁ ዕደሩና እግዚአብሔር (ያህዌ) ምን እንደሚለኝ ደግሞ ልወቅ።” በዚያች ሌሊት እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወደ በለዓም መጥቶ፣ “እነዚህ ሰዎች የመጡት እንድትሄድላቸው እስከ ሆነ ድረስ አብረሃቸው ሂድ፤ ነገር ግን እኔ የምነግርህን ብቻ አድርግ።” በለዓም በጧት ተነሣ፤ አህያውንም ጭኖ ከሞዓብ አለቆች ጋር ሄደ። ይሁን እንጂ በለዓም በሄደ ጊዜ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በጣም ተቈጥቶ ስለ ነበር የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ ሊቃወመው በመንገዱ ላይ ቆመ። በለዓምም በአህያው ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ሁለት አሽከሮቹም አብረው ነበሩ። አህያዪቱም የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ የተመዘዘ ሰይፍ ይዞ በመንገድ ላይ መቆሙን ባየች ጊዜ ከመንገድ ወጥታ ዕርሻ ውስጥ ገባች፤ በለዓምም ወደ መንገዱ እንድትመለስ መታት። ከዚያም የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ በሁለቱም በኩል ግንብ ባለበት በሁለት የወይን ተክል ቦታ መካከል በሚገኝ ጠባብ መተላለፊያ ላይ ቆመ። አህያዪቱም የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መልአክ ባየች ጊዜ ወደ ግንቡ ተጠግታ የበለዓምን እግር አጣበቀችው፤ ስለዚህም እንደ ገና መታት። የእግዚአብሔርም (ያህዌ) መልአክ ወደ ፊት ሄድ ብሎ ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ መተላለፊያ በሌለበት ጠባብ ቦታ ላይ ቆመ። አህያዪቱም የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መልአክ ባየች ጊዜ ከበለዓም በታች ተኛች፤ በለዓም ተቈጥቶ ነበርና በበትሩ ደበደባት። ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) የአህያዪቱን አፍ ከፈተ፤ በለዓምንም፣ “እንዲህ አድርገህ ሦስት ጊዜ የመታኸኝ ምን አድርጌህ ነው?” አለችው። በለዓምም መልሶ አህያዪቱን፣ “ስላላገጥሽብኝ ነዋ! በእጄ ሰይፍ ይዤ ቢሆን ኖሮ አሁኑኑ በገደልሁሽ ነበር” አላት። አህያዪቱም ደግሞ በለዓምን እንዲህ አለችው፣ “ከብዙ ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የተቀመጥህብኝ አህያህ አይደለሁምን? ታዲያ ይህን የመሰለ ነገር የማድረግ ልማድ ነበረኝ?” እርሱም፣ “በጭራሽ!” አላት። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) የበለዓምን ዐይን ከፈተ፤ እርሱም የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ የተመዘዘ ሰይፍ እንደ ያዘ መንገዱ ላይ ቆሞ አየ፤ ጐንበስ ብሎም በግንባሩ ተደፋ። የእግዚአብሔርም (ያህዌ) መልአክ እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ “አህያህን እንዲህ አድርገህ ሦስት ጊዜ የመታሃት ስለ ምንድን ነው? መንገድህ በፊቴ ጠማማ ስለሆነ ልቃወምህ መጥቻለሁ። አህያዪቱ አይታኝ ሦስቱንም ጊዜ ከፊቴ ዞር ባትልማ ኖሮ በእውነት እስካሁን አንተን በገደልሁህ፣ አህያዪቱን ግን በሕይወት በተውኋት ነበር።” በለዓምም የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መልአክ፣ “ኀጢአት ሠርቻለሁ፤ እኔን ለመቃወም መንገዱ ላይ መቆምህን አላወቅሁም፤ አሁንም ደስ የማትሰኝ ከሆነ እመለሳለሁ” አለው። የእግዚአብሔርም (ያህዌ) መልአክ በለዓምን፣ “መሄዱን ከሰዎቹ ጋር ሂድ፤ ነገር ግን እኔ የምነግርህን ብቻ ተናገር” አለው። ስለዚህ በለዓም ከባላቅ አለቆች ጋር ሄደ። በለዓም በመምጣት ላይ መሆኑን ባላቅ በሰማ ጊዜ በግዛቱ ዳርቻ በአርኖን ወሰን ላይ ወደምትገኘው ወደ ሞዓብ ከተማ ሊቀበለው ወጣ። ባላቅ በለዓምን፣ “በቶሎ እንድትመጣ ልኬብህ አልነበረምን? ለምን አልመጣህም? በርግጥ ወሮታህን ልከፍል የማልችል ሆኜ ነውን?” አለው። በለዓምም፣ “ይኸው አሁን መጥቻለሁ፤ ግን እንዲያው ማንኛውንም ነገር መናገር እችላለሁን? እኔ መናገር የሚገባኝ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በአፌ ያስቀመጠውን ብቻ ነው” ብሎ መለሰለት። ከዚያም በለዓም ከባላቅ ጋር ወደ ቂርያት ሐጾት ሄደ። ባላቅም ከብቶችና በጎች ሠዋ፤ ከፊሉንም ለበለዓምና ከእርሱ ጋር ለነበሩት አለቆች ሰጣቸው። በማግስቱም ጧት ባላቅ በለዓምን ወደ ባሞት በኣል አወጣው፤ እዚያም ሆኖ ሕዝቡን በከፊል አየ።

ዘኍል 22:1-41 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

የእስራኤልም ልጆች ተጓዙ፥ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በዮርዳኖስ ማዶ ባለው በሞዓብ ሜዳ ሰፈሩ። የሴፎር ልጅ ባላቅ እስራኤል በአሞራውያን ላየ ያደረገውን ሁሉ አየ። ብዙም ነበረና ሞዓብ ከሕዝቡ እጅግ ፈራ፤ ከእስራኤልም ልጆች የተነሣ ሞዓብ ደነገጠ። ሞዓብም የምድያምን ሽማግሌዎች፦ በሬ የለመለመውን ሣር እንደሚጨርስ ይህ ጭፍራ በዙሪያችን ያለውን ሁሉ ይጨርሳል አላቸው። በዚያን ጊዜም የሴፎር ልጅ ባላቅ የሞዓብ ንጉሥ ነበረ። በወንዙ አጠገብ ባለችው በሕዝቡ ልጆች ምድር በፋቱራ ወደ ተቀመጠው ወደ ቢዖር ልጅ ወደ በለዓም፦ እነሆ፥ ከግብፅ የወጣ ሕዝብ አለ፤ እነሆም፥ የምድሩን ሁሉ ፊት ሸፈነ፥ በአቅራቢያችንም ተቀምጦአል፤ አሁንም ይህ ሕዝብ ከእኔ ይበልጣልና ልወጋቸውና ከምድሪቱ ላሳድዳቸው እችል እንደ ሆነ፥ እባክህ፥ ና ርገምልኝ፤ አንተ የመረቅኸው ምሩቅ የረገምኸውም ርጉም እንደ ሆነ አውቃለሁና ብሎ ይጠሩት ዘንድ መልእክተኞቹን ላከ። የሞዓብ ሽማግሌዎችና የምድያም ሽማግሌዎችም የምዋርቱን ዋጋ በእጃቸው ይዘው ሄዱ፤ ወደ በለዓምም መጡ፥ የባላቅንም ቃል ነገሩት። እርሱም፦ ዛሬ ሌሊት በዚህ እደሩ፥ እግዚአብሔርም እንደሚነግረኝ እመልስላችኋለሁ አላቸው፤ የሞዓብም አለቆች በበለዓም ዘንድ ተቀመጡ። እግዚአብሔርም ወደ በለዓም መጥቶ፦ እነዚህ በአንተ ዘንድ ያሉ ሰዎች እነማን ናቸው? አለው። በለዓምም እግዚአብሔርን፦ የሞዓብ ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ፦ እነሆ፥ ከግብፅ የወጣ ሕዝብ የምድርን ፊት ሸፈነ፥ አሁንም ና እርሱንም ርገምልኝ፤ ምናልባት እወጋው አሳድደውም ዘንድ እችል እንደ ሆነ ብሎ ወደ እኔ ልኮአል አለው። እግዚአብሔርም በለዓምን፦ ከእነርሱ ጋር አትሂድ፤ የተባረከ ነውና ሕዝቡን አትረግምም አለው። በለዓምም ሲነጋ ተነሥቶ የባላቅን አለቆች፦ ከእናንተ ጋር እሄድ ዘንድ እግዚአብሔር አልፈቀደምና ወደ ምድራችሁ ሂዱ አላቸው። የሞዓብ አለቆች ተነሡ፥ ወደ ባላቅም መጥተው፦ በለዓም ከእኛ ጋር ይመጣ ዘንድ አልፈቀደም አሉት። ባላቅም ደግሞ ከፊተኞች የበዙና የከበሩ ሌሎችን አለቆች ሰደደ። ወደ በለዓምም መጥተው፦ የሴፎር ልጅ ባላቅ፦ ክብርህን እጅግ ታላቅ አደርገዋለሁና፥ የተናገርኸውንም ሁሉ አደርግልሃለሁና፥ እባክህ፥ ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ ምንም አይከልክልህ፤ እባክህ፥ ና፥ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ አለ ብለው ነገሩት። በለዓምም መልሶ የባላቅን ባሪያዎች፦ ባላቅ በቤቱ የሞላውን ወርቅና ብር ቢሰጠኝ፥ በትንሹ ወይም በትልቁ ቢሆን የአምላኬን የእግዚአብሔርን ቃል እተላለፍ ዘንድ አይቻለኝም፤ አሁንም እግዚአብሔር ደግሞ የሚነግረኝን አውቅ ዘንድ፥ እባካችሁ፥ ዛሬ ሌሊት ደግሞ በዚህ እደሩ አላቸው። እግዚአብሔርም ወደ በለዓም በሌሊት መጥቶ፦ ሰዎቹ ይጠሩህ ዘንድ መጥተው እንደ ሆነ፥ ተነሣ ከእነርሱም ጋር ሂድ፤ ነገር ግን የምነግርህን ቃል ብቻ ታደርጋለህ አለው። በለዓምም ሲነጋ ተነሣ፥ አህያይቱንም ጭኖ ከሞዓብ አለቆች ጋር ሄደ። እርሱም ስለ ሄደ እግዚአብሔር ተቈጣ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ሊቍቍመው በመንገድ ላይ ቆመ። እርሱም በአህያይቱ ላይ፥ ሁለቱም ሎሌዎቹ ከእርሱ ጋር ነበሩ። አህያይቱም የእግዚአብሔርን መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየች፤ ከመንገዱም ፈቀቅ ብላ ወደ እርሻው ውስጥ ገባች፤ በለዓምም ወደ መንገድ ይመልሳት ዘንድ አህያይቱን መታት። የእግዚአብሔርም መልአክ ከወይኑ ቦታዎች መካከል በወዲያና በወዲህ ወገን ግንብ በነበረበት በጠባብ መንገድ ላይ ቆመ። አህያይቱም የእግዚአብሔርን መልአክ አይታ ወደ ቅጥሩ ተጠጋች፥ የበለዓምንም እግር ከቅጥሩ ጋር አጣበቀች፤ እርሱም ደግሞ መታት። የእግዚአብሔርም መልአክ ወደ ፊት ሄደ፥ በቀኝና በግራ መተላለፊያ በሌለበት በጠባብ ስፍራ ቆመ። አህያይቱም የእግዚአብሔርን መልአክ አየች፥ ከበለዓምም በታች ተኛች፤ በለዓምም እጅግ ተቈጣ፥ አህያይቱንም በበትሩ ደበደባት። እግዚአብሔርም የአህያይቱን አፍ ከፈተ፥ በለዓምንም፦ ሦስት ጊዜ የመታኸኝ ምን አድርጌብህ ነው? አለችው። በለዓምም አህያይቱን፦ ስላላገጥሽብኝ ነው፤ በእጄስ ሰይፍ ቢኖር አሁን በገደልሁሽ ነበር አላት። አህያይቱም በለዓምን፦ ከብዙ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የምትቀመጥብኝ አህያህ አይደለሁምን? በውኑ እንዲህ አደርግ ዘንድ ልማዴ ነበረን? አለችው። እርሱም፦ እንዲህ አላደረግሽብኝም አላት። እግዚአብሔርም የበለዓምን ዓይኖች ከፈተ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተምዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየ፤ ሰገደም፥ በግምባሩም ወደቀ። የእግዚአብሔርም መልአክ፦ አህያህን ሦስት ጊዜ ለምን መታህ? እነሆ፥ መንገድህ በፊቴ ጠማማ ነውና እቍቍምህ ዘንድ ወጥቼአለሁ፤ አህያይቱም አይታኝ ከፊቴ ሦስት ጊዜ ፈቀቅ አለች፤ ከፊቴስ ፈቀቅ ባላለች በእውነት አሁን አንተን በገደልሁህ፥ እርስዋንም ባዳንኋት ነበር አለው። በለዓምም የእግዚአብሔርን መልአክ፦ በድያለሁ፤ አንተ በመንገድ ላይ በፊቴ እንደቆምህብኝ አላወቅሁም፤ እንግዲህም አሁን አትወድድ እንደ ሆነ እመለሳለሁ አለው። የእግዚአብሔርም መልአክ በለዓምን፦ ከሰዎቹ ጋር ሂድ፥ ነገር ግን የምናገርህን ቃል ብቻ ትናገራለህ አለው። በለዓምም ከባላቅ አለቆች ጋር ሄደ። ባላቅም በለዓም እንደ መጣ በሰማ ጊዜ በአርኖን ዳር ዳርቻ በመጨረሻ ወዳለችው ወደ ሞዓብ ከተማ ሊገናኘው ወጣ። ባላቅም በለዓምን፦ በውኑ አንተን ለመጥራት አልላክሁብህምን? ለምንስ ወደ እኔ አልመጣህም? በውኑ አንተን ለማክበር እኔ አልችልምን? አለው። በለዓምም ባላቅን፦ እነሆ፥ ወደ አንተ መጥቼአለሁ፤ በውኑ አሁን አንዳችን ነገር እናገር ዘንድ እችላለሁን? እግዚአብሔር በአፌ የሚያድርገውን ቃል እርሱን እናገራለሁ አለው። በለዓምም ከባላቅ ጋር ሄደ፥ ወደ ቂርያት ሐጾትም መጡ። ባላቅም በሬዎችንና በጎችን አርዶ ወደ በለዓም ከእርሱም ጋር ወዳሉት አለቆች ላከ። በነጋውም ባላቅ በለዓምን ይዞ ወደ በኣል ኮረብታ መስገጃ አወጣው፤ በዚያም ሆኖ የሕዝቡን ዳርቻ አየ።

ዘኍል 22:1-41 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እስራኤላውያን ጒዞአቸውን በመቀጠል ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምሥራቅና በኢያሪኮ ትይዩ በሚገኘው በሞአብ ሜዳ ላይ ሰፈሩ። የሞአብ ንጉሥ የጺጶር ልጅ ባላቅ እስራኤላውያን በአሞራውያን ላይ ያደረሱትን ጒዳት አየ፥ በእስራኤላውያን ብዛት ምክንያት የሞአብ ሕዝብ ታላቅ ፍርሀት ዐደረባቸው፤ እስራኤላውያንንም በጣም ፈሩ። ሞአባውያን ለምድያማውያን ሽማግሌዎች “ይህ የምታዩት የሕዝብ ብዛት በሬ በመስክ የሚገኘውን ሣር ሁሉ ጠራርጎ እንደሚበላ በዙሪያችን ያለውን ነገር ሁሉ ጠራርጎ የሚያጠፋ ነው” አሉአቸው። ስለዚህ በዚያን ጊዜ የሞአብ ንጉሥ የነበረው የጺጶር ልጅ ባላቅ፥ በዓማው ምድር በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ በፐቶር ከተማ ይኖር ወደነበረው ወደ ቢዖር ልጅ ወደ በለዓም ይጠሩት ዘንድ መልእክተኞች እንዲህ ብሎ ላከበት፤ “ከግብጽ የወጣ አንድ ሕዝብ ምድሪቱን ሁሉ ሸፍኖአታል፤ እነርሱም በአቅራቢያችን ሰፍረዋል፤ የሕዝቡም ቊጥር ከእኛ እጅግ የበዛ ነው፤ ስለዚህ ወደዚህ መጥተህ እነርሱን ርገምልኝ፤ በዚህ ዐይነት ምናልባት ድል ልነሣቸውና ከምድሪቱ ላስወጣቸው እችል ይሆናል፤ አንተ የምትመርቀው የተመረቀ፥ አንተም የምትረግመው የተረገመ እንደሚሆን ዐውቃለሁ።” ስለዚህ የሞአባውያንና የምድያማውያን ሽማግሌዎች ስለ ርግማን የሚከፈለውን ገንዘብ ይዘው ወደ በለዓም በመሄድ የባላቅን መልእክት ሰጡት፤ በለዓምም “እዚሁ ዕደሩና ነገ ጧት እግዚአብሔር የሚነግረኝን ሁሉ እነግራችኋለሁ” አላቸው፤ በዚህ ዐይነት የሞአባውያን መሪዎች ከበለዓም ጋር ቈዩ። እግዚአብሔርም ወደ በለዓም መጥቶ “እነዚህ ከአንተ ጋር ያሉት ሰዎች እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቀው። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “የሞአብ ንጉሥ የጲዖር ልጅ ባላቅ እንዲህ ብሎ ወደ እኔ የላካቸው ናቸው፦ ‘ከግብጽ የወጣ ሕዝብ ምድሪቱን ሸፍኖአታል፤ መጥተህ ብትረግምልኝ ምናልባት እነርሱን በጦርነት ተዋግቼ ላስወጣቸው እችል ይሆናል።’ ” እግዚአብሔርም በለዓምን “ከነዚህ ሰዎች ጋር አትሂድ፤ የተባረኩ ስለ ሆነ የእስራኤልን ሕዝብ አትርገም” አለው። በለዓምም በማግስቱ ጠዋት ሲነጋ ተነሥቶ፥ ለባላቅ ሹማምንት “እንግዲህ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ፤ እኔ ከእናንተ ጋር እንዳልሄድ እግዚአብሔር ከልክሎኛል” አላቸው፤ ስለዚህ የሞአብ ሹማምንት ወደ ባላቅ ተመለሱና በለዓም አብሮአቸው ለመምጣት እምቢ እንዳለ ነገሩት። ከዚያን በኋላ ባላቅ ከፊተኞቹ መልእክተኞች ይበልጥ የተከበሩና ቊጥራቸውም የበዛ ሹማምንት ወደ በለዓም ላከ፤ እነርሱም ወደ በለዓም ሄደው የባላቅን መልእክት እንዲህ ሲሉ ነገሩት፤ “ወደ እኔ መምጣት እንዳትችል የሚያግድህ ነገር አይኑር! ከፍ ባለ ክብር አከብርሃለሁ፤ የጠየቅከኝንም ሁሉ አደርግልሃለሁ፤ ስለዚህ እባክህ መጥተህ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ።” በለዓም ግን ለመልእክተኞቹ እንዲህ ሲል መልስ ሰጠ፤ “ባላቅ በቤተ መንግሥቱ የሚገኘውን ብርና ወርቅ ሁሉ ቢሰጠኝም በትንሽ ወይም በትልቅ ነገር የአምላኬን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መተላለፍ አይቻለኝም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የሚነግረኝ ሌላ ነገር ካለ ከእርሱ እረዳ ዘንድ እስቲ እናንተም እንደ ፊተኞቹ መልእክተኞች ሌሊቱን እዚሁ አሳልፉ።” በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ወደ በለዓም መጣና “እነዚህ ሰዎች ወደ አንተ የመጡት ይዘውህ ሊሄዱ ከሆነ ተነሥተህ አብረሃቸው ሂድ፤ ነገር ግን እኔ የምነግርህን ብቻ አድርግ” አለው። ስለዚህ በማግስቱ ጠዋት በለዓም ተነሣና አህያውን ጭኖ ከሞአባውያን መሪዎች ጋር ሄደ። በለዓም በመሄዱ እግዚአብሔር ተቈጣ፤ በለዓም ሁለቱን አሽከሮቹን በማስከተል በአህያው ላይ ተቀምጦ በሚጓዝበት ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በፊቱ ቆሞ መንገዱን ዘጋበት፤ መልአኩ ሰይፉን መዞ በመንገዱ ላይ መቆሙን አህያይቱ በተመለከተች ጊዜ መንገዱን ለቃ ወደ እርሻ ገባች፤ በለዓምም አህያይቱን ወደ መንገዱ ለመመለስ ደበደባት፤ መንገዱ በሁለት የወይን ተክል ቦታዎች መካከል እየጠበበ ሲሄድና በሁለቱም በኩል የድንጋይ ግንብ ሲገጥመው መልአኩ መጥቶ በፊት ለፊት ቆመ። አህያይቱ መልአኩን ባየች ጊዜ ወደ ግንቡ ተጠግታ የበለዓምን እግር ከግንቡ ጋር አጣበቀችው፤ በለዓም አሁንም አህያይቱን መደብደብ ጀመረ፤ እንደገናም መልአኩ ወደ ፊት ቀድሞ ሄደና በግራም ሆነ በቀኝ መተላለፊያ በሌለበት ጠባብ ቦታ ላይ ቆመ። በዚህን ጊዜ አህያይቱ መልአኩን ስታይ በመሬት ላይ ተኛች፤ በለዓምም እጅግ ተቈጥቶ አህያይቱን በብትር መደብደብ ጀመረ። በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ለአህያይቱ የመናገር ችሎታ ስለ ሰጣት በለዓምን “እኔ ምን አደረግሁህ? ሦስት ጊዜ የደበደብከኝ ስለምንድን ነው?” አለችው። በለዓምም “እጅግ ስለ ተጫወትሽብኝ ነዋ! ሰይፍ ቢኖረኝማ አሁን በገደልኩሽ ነበር!” አላት። አህያይቱም “በሕይወትህ ሙሉ ስትጋልበኝ የኖርክ አህያህ አይደለሁምን? ታዲያ ከዚህ በፊት እንደ ዛሬ ሆኜብህ ዐውቃለሁን?” ስትል መለሰችለት። በለዓምም “ከቶ እንዲህ ሆነሽብኝ አታውቂም” አላት። በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር በለዓም ሰይፍ ይዞ የቆመውን መልአክ ለማየት እንዲችል አደረገው፤ በለዓምም በግንባሩ ወደ መሬት ተደፋ፤ መልአኩም እንዲህ አለው፤ “አህያህን እንዲህ አድርገህ ሦስት ጊዜ የመታሃት ለምንድን ነው? እኔ መጥቼ መንገድህን የዘጋሁት በጥፋት ጐዳና እንዳትሄድ ልከለክልህ ብዬ ነው፤ የአንተ አህያ ግን እኔን በማየትዋ ሦስት ጊዜ ከፊቴ ሸሸች፤ አህያይቱ እንዲህ ባታደርግ ኖሮ አንተን ገድዬ እርስዋ በሕይወት እንድትኖር በተውኳት ነበር።” በለዓምም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “በእርግጥ ኃጢአት ሠርቻለሁ፤ አንተ እኔን ለመቃወም በመንገድ ላይ መቆምህን አላወቅሁም ነበር፤ አሁንም ወደዚያ መሄዴ ስሕተት መስሎ ከታየህ ወደ ቤቴ እመለሳለሁ።” መልአኩ ግን “ከእነዚህ ሰዎች ጋር መሄዱን ሂድ፤ ነገር ግን እኔ የምነግርህን ብቻ ተናገር” አለው፤ በዚህ ዐይነት በለዓም ከባላቅ ባለሥልጣኖች ጋር ሄደ። ባላቅ የበለዓምን መምጣት በሰማ ጊዜ እርሱን ለመቀበል በሞአብ ጠረፍ በአርኖን ወንዝ ዳር ወደምትገኘው ወደ ዔር ከተማ ሄደ። ባላቅ በለዓምን “በመጀመሪያ ሰዎች በላክሁብህ ጊዜ ስለምን አልመጣህም? አንተን ለማክበር የማልችል መስሎህ ነውን?” ሲል ጠየቀው። በለዓምም “ያም ሆነ ይህ አሁን መጥቼ የለምን? ታዲያ አሁንስ ቢሆን በራሴ ምን ኀይል አለኝ? እኔ ልናገር የምችለው እግዚአብሔር የሚነግረኝን ብቻ ነው” ሲል መለሰለት። ስለዚህ በለዓም ከባላቅ ጋር ወደ ቂርያት ሑጾት ከተማ ሄደ። በዚያም ባላቅ፥ ከብቶችና በጎች አሳርዶ ከሥጋው ጥቂቱን አብረውት ለነበሩት መሪዎችና ለበለዓም ሰጠ። በማግስቱ ጠዋት ባላቅ በለዓምን የእስራኤልን ሕዝብ በከፊል ለማየት ወደሚቻልበት ወደ ባሞትበዓል አወጣው።

ዘኍል 22:1-41 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

የእስራኤልም ልጆች ተጓዙ፥ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በዮርዳኖስ ማዶ ባለው በሞዓብ ሜዳ ሰፈሩ። የሴፎር ልጅ ባላቅ እስራኤል በአሞራውያን ላይ ያደረገውን ሁሉ አየ። ብዙም ስለ ነበሩ ሞዓብ ሕዝቡን እጅግ ፈራ፤ ከእስራኤልም ልጆች የተነሣ ሞዓብ ደነገጠ። ሞዓብም የምድያምን ሽማግሌዎች፦ “በሬ የለመለመውን የሣር መስክ ግጦ እንደሚጨርስ ይህ ጭፍራ በዙሪያችን ያለውን ሁሉ አሁን ይጨርሳል” አላቸው። በዚያን ጊዜም የሞዓብ ንጉሥ የነበረው የሴፎር ልጅ ባላቅ፥ በወንዙ አጠገብ ባለችው በሕዝቡ ልጆች ምድር በፋቱራ የተቀመጠውን የቢዖርን ልጅ በለዓምን እዲጠሩት እንዲህ ብሎ መልእክተኞቹን ላከ፦ “እነሆ፥ ከግብጽ የወጣ ሕዝብ አለ፤ እነሆም፥ የምድሩን ሁሉ ፊት ሸፍኖአል፥ በአቅራቢያችንም ተቀምጦአል። አሁንም ከእኔ ይልቅ እጅግ ኃያል ናቸውና ልወጋቸውና ከምድሪቱ ላሳድዳቸው እችል እንደሆነ፥ ይህን ሕዝብ እባክህ፥ ና ርገምልኝ፤ አንተ የባረከው ቡሩክ የረገምኸውም ርጉም እንደሆነ አውቃለሁና።” የሞዓብ ሽማግሌዎችና የምድያም ሽማግሌዎችም ለምዋርቱ የሚከፈለውን ገንዘብ በእጃቸው ይዘው ሄዱ፤ ወደ በለዓምም መጡ፥ የባላቅንም ቃላት ነገሩት። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ዛሬ ሌሊት በዚህ እደሩ፥ ጌታም እንደሚነግረኝ እመልስላችኋለሁ”፤ የሞዓብም አለቆች በበለዓም ዘንድ ተቀመጡ። እግዚአብሔርም ወደ በለዓም መጥቶ፦ “እነዚህ ከአንተ ጋር ያሉት ሰዎች እነማን ናቸው?” አለው። በለዓምም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፦ “የሞዓብ ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ እንዲህ ብሎ ወደ እኔ ላከ፦ ‘እነሆ፥ ከግብጽ የወጣ ሕዝብ የምድርን ፊት ሸፈነ፥ ምናልባት ልወጋው ላሳድደውም እችል እንደሆነ አሁን ና እርሱን ርገምልኝ።’ ” እግዚአብሔርም በለዓምን፦ “ከእነርሱ ጋር አትሂድ፤ የተባረከ ነውና ሕዝቡን አትረግምም” አለው። በለዓምም ሲነጋ ተነሥቶ የባላቅን ሹማምንት፦ “ከእናንተ ጋር እንድሄድ ጌታ አልፈቀደምና ወደ ምድራችሁ ሂዱ” አላቸው። የሞዓብ ሹማምንት ተነሡ፥ ወደ ባላቅም ሄደው፦ “በለዓም ከእኛ ጋር ለመምጣት ፍቃደኛ አልሆነም” አሉት። ባላቅም ዳግመኛ ከፊተኞቹ ይልቅ እጅግ የበዙና የከበሩ ሌሎችን ሹማምንት ላከ። ወደ በለዓምም መጥተው እንዲህ አሉት፦ “የሴፎር ልጅ ባላቅ እንዲህ ይላል፦ ‘እባክህ፥ ወደ እኔ ለመምጣት ምንም ዓይነት ነገር አያግድህ፤ ክብርህን እጅግ ታላቅ አደርገዋለሁና፥ የምትነግረኝንም ሁሉ አደርግልሃለሁና፥ እባክህ፥ ና፥ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ።’ ” በለዓምም መልሶ የባላቅን ባርያዎች እንዲህ አላቸው፦ “ባላቅ በቤቱ የሞላውን ወርቅና ብር ቢሰጠኝ፥ ትንሹን ወይም ትልቁን ነገር በመፈጸም የአምላኬን የጌታን ቃል ለመተላለፍ አልችልም፤ አሁንም ጌታ ይበልጥ የሚነግረኝን ነገር እንዳውቅ፥ እባካችሁ፥ ሌሎቹ እንዳደረጉት እንዲሁ ዛሬ ሌሊት ደግሞ በዚህ እደሩ።” እግዚአብሔርም ወደ በለዓም በሌሊት መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ሰዎቹ ሊጠሩህ መጥተው እንደሆነ፥ ተነሣ ከእነርሱም ጋር ሂድ፤ ነገር ግን የምነግርህን ቃል ብቻ ታደርጋለህ።” በለዓምም ሲነጋ ተነሣ፥ አህያይቱንም ጭኖ ከሞዓብ ሹማምንት ጋር ሄደ። እርሱም ስለ ሄደ እግዚአብሔር ተቈጣ፤ የጌታም መልአክ ሊቃወመው በመንገድ ላይ ቆመ። እርሱም በአህያይቱ ላይ ሆኖ ይጓዝ ነበር፥ ሁለቱም ሎሌዎቹ ከእርሱ ጋር ነበሩ። አህያይቱም የጌታን መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየች፤ እርሷም ከመንገዱ ፈቀቅ ብላ ወደ እርሻው ውስጥ ገባች፤ በለዓምም ወደ መንገድ እንድትመለስ አህያይቱን መታት። የጌታም መልአክ ከወይኑ ቦታዎች መካከል በወዲያና በወዲህ ወገን ግንብ በነበረበት በጠባብ መንገድ ላይ ቆመ። አህያይቱም የጌታን መልአክ አይታ ወደ ቅጥሩ ተጠጋች፥ የበለዓምንም እግር ከቅጥሩ ጋር አጣበቀች፤ እርሱም ዳግመኛ መታት። የጌታም መልአክ ወደ ፊት ሄደ፥ በቀኝና በግራ መተላለፊያ በሌለበት በጠባብ ስፍራ ቆመ። አህያይቱም የጌታን መልአክ አየች፥ ከበለዓምም በታች ተምበርክካ ለጥ አለች፤ በለዓምም እጅግ ተቈጣ፥ አህያይቱንም በበትሩ ደበደባት። ጌታም የአህያይቱን አፍ ከፈተ፥ በለዓምንም፦ “ሦስት ጊዜ የመታኸኝ ምን አድርጌህ ነው?” አለችው። በለዓምም አህያይቱን፦ “ስላላገጥሽብኝ ነው፤ በእጄስ ሰይፍ ቢኖር አሁን በገደልሁሽ ነበር” አላት። አህያይቱም በለዓምን እንዲህ አለችው፦ “ከብዙ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የምትቀመጥብኝ አህያህ አይደለሁምን? በውኑ እንዲህ ማድረግ ልማዴ ነበረን?” እርሱም፦ “እንዲህ አላደረግሽብኝም” አላት። ጌታም የበለዓምን ዐይኖች ከፈተ፤ የጌታም መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተምዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየ፤ ሰገደም፥ በግምባሩም ወደ መሬት ተደፋ። የጌታም መልአክ እንዲህ አለው፦ “አህያህን ሦስት ጊዜ ለምን መታህ? እነሆ፥ መንገድህ በፊቴ ጠማማ ነውና ልቃወምህ ወጥቼአለሁ፤ አህያይቱም አይታኝ ከፊቴ ሦስት ጊዜ ፈቀቅ አለች፤ ከፊቴስ ፈቀቅ ባትል ኖሮ በእውነት አሁን አንተን በገደልሁህ፥ እርሷንም ባዳንኋት ነበር።” በለዓምም የጌታን መልአክ እንዲህ አለው፦ “ኃጢአትን ሠርቻለሁ፤ አንተ በመንገድ ላይ ልትቃወመኝ መቆምክን አላወቅሁም፤ እንግዲህም ይህ አሁን በፊትህ ክፉ የሆነ ነገር ቢሆን እመለሳለሁ።” የጌታም መልአክ በለዓምን፦ “ከሰዎቹ ጋር ሂድ፥ ነገር ግን የምነግርህን ቃል ብቻ ትናገራለህ” አለው። በለዓምም ከባላቅ ሹማምንት ጋር ሄደ። ባላቅም በለዓም እንደመጣ በሰማ ጊዜ በአርኖን ድንበር በድንበሩም ጨረሻ ወዳለችው ወደ ሞዓብ ከተማ ሊገናኘው ወጣ። ባላቅም በለዓምን እንዲህ አለው፦ “በውኑ አንተን ለመጥራት አላክሁብህምን? ለምንስ ወደ እኔ አልመጣህም? በውኑ አንተን ለማክበር እኔ አልችልምን?” በለዓምም ባላቅን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፥ ወደ አንተ መጥቼአለሁ፤ በውኑ እኔ አሁን አንዳችን ነገር ለመናገር እችላለሁን? እግዚአብሔር በአፌ የሚያድርገውን ቃል እርሱን እናገራለሁ።” በለዓምም ከባላቅ ጋር ሄደ፥ ወደ ቂርያት ሐጾትም መጡ። ባላቅም በሬዎችንና በጎችን አርዶ ወደ በለዓም ከእርሱም ጋር ወዳሉት ሹማምንት ላከ። በማግስቱም ጠዋት ባላቅ በለዓምን ይዞ ወደ ባሞት-በኣል አወጣው፤ በዚያም ሆኖ ዳር ላይ የሰፈረውን ሕዝብ አየ።