ዘኍል 22:1-21
ዘኍል 22:1-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የእስራኤልም ልጆች ተጓዙ፤ በኢያሪኮ በኩል በዮርዳኖስ አጠገብ በሞዓብ ምዕራብም ሰፈሩ። የሴፎር ልጅ ባላቅ እስራኤል በአሞሬዎናውያን ላይ ያደረገውን ሁሉ አየ። ብዙም ነበረና ሞዓብ ከሕዝቡ እጅግ ፈራ፤ ከእስራኤልም ልጆች የተነሣ ሞዓብ ደነገጠ። ሞዓብም የምድያምን ሽማግሌዎች፥ “በሬ የለመለመውን ሣር እንደሚጨርስ ይህ ሠራዊት በዙሪያችን ያለውን ሁሉ ይጨርሳል” አላቸው። በዚያን ጊዜ የሶፎር ልጅ ባላቅ የሞዓብ ንጉሥ ነበረ። በወንዙም አጠገብ ባለችው በሕዝቡ ልጆች ምድር በፋቱራ ወደ ተቀመጠው ወደ ቢዖር ልጅ ወደ በለዓም፥ “እነሆ፥ ከግብፅ የወጣ ሕዝብ አለ፤ እነሆም፥ የምድሩን ሁሉ ፊት ሸፈነ፤ በአቅራቢያችንም ተቀምጦአል፤ አሁንም ይህ ሕዝብ ከእኔ ይበልጣልና ልወጋቸውና ከምድሪቱ ላሳድዳቸው እችል እንደ ሆነ፥ ና ርገምልኝ፤ አንተ የመረቅኸው ምሩቅ፥ የረገምኸውም ርጉም እንደ ሆነ አውቃለሁና” ብሎ ይጠሩት ዘንድ መልእክተኞችን ላከ። የሞዓብ ሽማግሌዎችና የምድያም ሽማግሌዎችም የምዋርቱን ዋጋ በእጃቸው ይዘው ሄዱ፤ ወደ በለዓምም መጡ፤ የባላቅንም ቃል ነገሩት። እርሱም፥ “ዛሬ ሌሊት በዚህ እደሩ፤ እግዚእብሔርም የሚነግረኝን እነግራችኋለሁ” አላቸው፤ የሞዓብ አለቆችም በበለዓም ዘንድ አደሩ። እግዚአብሔርም ወደ በለዓም መጥቶ፥ “እነዚህ በአንተ ዘንድ ያሉ ሰዎች እነማን ናቸው?” አለው። በለዓምም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፥ “የሞዓብ ንጉሥ የሶፎር ልጅ ባላቅ፦ እንዲህ ሲል ወደ እኔ ልኮአቸዋል፤ እነሆ፥ ከግብፅ የወጣ ሕዝብ የምድርን ፊት ሸፈነ፤ በአቅራቢያዬም ተቀምጦአል፤ ምናልባት እወጋው፥ አሳድደውም ዘንድ እችል እንደ ሆነ አሁንም ና እርሱን ርገምልኝ።” እግዚአብሔርም በለዓምን፥ “ከእነርሱ ጋር አትሂድ፤ የተባረከ ነውና ሕዝቡን አትርገም” አለው። በለዓምም ሲነጋ ተነሥቶ የባላቅን አለቆች፥ “ከእናንተ ጋር እሄድ ዘንድ እግዚአብሔር አልፈቀደልኝምና ወደ ጌታችሁ ሂዱ” አላቸው። የሞዓብ አለቆችም ተነሡ፤ ወደ ባላቅም መጥተው፥ “በለዓም ከእኛ ጋር ይመጣ ዘንድ አልፈቀደም” አሉት። ባላቅም ደግሞ ከእነዚያ የበዙና የከበሩ ሌሎችን አለቆች ሰደደ። ወደ በለዓምም መጥተው፥ “የሶፎር ልጅ ባላቅ፦ እባክህ ወደ እኔ መምጣትን ቸል አትበል፤ ክብርህን እጅግ ታላቅ አደርገዋለሁና፥ የተናገርኸውንም ሁሉ አደርግልሃለሁና ና፥ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ ብሏል” አሉት። በለዓምም መልሶ የባላቅን አለቆች፥ “ባላቅ በቤቱ የሞላውን ወርቅና ብር ቢሰጠኝ፥ በትንሹ ወይም በትልቁ ቢሆን የአምላኬን የእግዚአብሔርን ቃል እተላለፍ ዘንድ አይቻለኝም፤ አሁንም እግዚአብሔር ደግሞ የሚነግረኝን አውቅ ዘንድ ዛሬ ሌሊት ደግሞ በዚህ እደሩ” አላቸው። እግዚአብሔርም ወደ በለዓም በሌሊት መጥቶ፥ “ሰዎቹ ይጠሩህ ዘንድ መጥተው እንደ ሆነ፥ ተነሣ ከእነርሱ ጋር ሂድ፤ ነገር ግን የምነግርህን ቃል ታደርጋለህ” አለው። በለዓምም ሲነጋ ተነሣ፤ አህያዪቱንም ጭኖ ከሞዓብ አለቆች ጋር ሄደ።
ዘኍል 22:1-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚህ በኋላ እስራኤላውያን ወደ ሞዓብ ሜዳ ተጕዘው ከዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ከኢያሪኮ ማዶ ሰፈሩ። በዚህ ጊዜ የሴፎር ልጅ ባላቅ፣ እስራኤል በአሞራውያን ላይ ያደረገውን ሁሉ አየ፤ ሞዓብም ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ተሸበረ፤ በርግጥም ሞዓብ በእስራኤላውያን ምክንያት በፍርሀት ተውጦ ነበር። ሞዓባውያንም የምድያምን ሽማግሌዎች፣ “በሬ የመስክ ሣር ጠራርጎ እንደሚበላ ሁሉ፣ ይህም ሰራዊት በዙሪያችን ያለውን ሁሉ ጠራርጎ የሚያጠፋ ነው” አሏቸው። ስለዚህ በዚያን ጊዜ የሞዓብ ንጉሥ የነበረው የሴፎር ልጅ ባላቅ፣ ከወንዙ ዳር ባለች በትውልድ አገሩ በምትገኝ በፋቱራ የነበረውን የቢዖርን ልጅ በለዓምን እንዲጠሩት መልእክተኞች ላከ፤ እንዲህም አለ፤ “እነሆ፤ ከብዛቱ የተነሣ ምድሩን የሸፈነ ሕዝብ ከግብፅ ወጥቶ በአቅራቢያዬ ሰፍሯል። ስለዚህ ይህን ሕዝብ መቋቋም ስለማልችል መጥተህ ርገምልኝ፤ ምናልባትም ድል አድርጌ ከአገሪቱ ላስወጣቸው የምችለው ከዚያ በኋላ ሊሆን ይችላል፤ አንተ የምትባርከው ቡሩክ፣ የምትረግመውም ርጉም እንደሚሆን ዐውቃለሁና።” የሞዓብና የምድያም ሽማግሌዎችም ለሟርት የሚከፈለውን ዋጋ ይዘው ሄዱ፤ በለዓም ዘንድ በደረሱ ጊዜም የባላቅን መልእክት ነገሩት። በለዓምም፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚሰጠኝን መልስ አመጣላችኋለሁና የዛሬን ሌሊት እዚሁ ዕደሩ” አላቸው። ስለዚህም የሞዓብ አለቆች ከእርሱ ዘንድ ቈዩ። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ወደ በለዓም መጥቶ፣ “ከአንተ ጋር ያሉት እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቀው። በለዓምም እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) እንዲህ አለው፤ “የሞዓብ ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ ይህን መልእክት ልኮብኛል፤ ‘ከግብፅ የወጣ ሕዝብ የምድሩን ገጽ አጥለቅልቆታል፤ ስለዚህ መጥተህ ርገምልኝ፤ ምናልባት ልዋጋቸውና ላባርራቸው የምችለው ከዚያ በኋላ ሊሆን ይችላል።’ ” እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ግን በለዓምን፣ “አብረሃቸው አትሂድ፤ የተባረከ ሕዝብ ስለ ሆነም አትርገመው” አለው። በማግስቱም ጧት በለዓም ተነሥቶ የባላቅን አለቆች፣ “አብሬአችሁ እንዳልሄድ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከልክሎኛልና እናንተ ወደ አገራችሁ ተመለሱ አላቸው።” ስለዚህ የሞዓብ አለቆች ወደ ባላቅ ተመልሰው፣ “በለዓም አብሮን ለመምጣት እንቢ አለን” አሉት። ከዚያም ባላቅ ከፊተኞቹ ይልቅ ቍጥራቸው የበዛና ይበልጥ የተከበሩ ሌሎች አለቆች ላከ። እነርሱም ወደ በለዓም መጥተው እንዲህ አሉት፤ “የሴፎር ልጅ ባላቅ ይህን እንድንነግርህ ልኮናል፤ ወደ እኔ ለመምጣት የሚያግድህ ምንም ነገር አይኑር፤ ወሮታህን በእጅጉ እከፍላለሁ፤ የምትለውንም ሁሉ አደርጋለሁ፤ ስለዚህ መጥተህ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ።” በለዓም ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “ሌላው ይቅርና ባላቅ በብርና በወርቅ የተሞላ ቤተ መንግሥቱን ቢሰጠኝ እንኳ፣ የአምላኬን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዝ በመጣስ ከዚያ ያለፈ ወይም ያነሰ ማንኛውንም ነገር ማድረግ አልችልም። አሁንም ሌሎቹ እንዳደረጉት ሁሉ፣ እናንተም ዛሬ እዚሁ ዕደሩና እግዚአብሔር (ያህዌ) ምን እንደሚለኝ ደግሞ ልወቅ።” በዚያች ሌሊት እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወደ በለዓም መጥቶ፣ “እነዚህ ሰዎች የመጡት እንድትሄድላቸው እስከ ሆነ ድረስ አብረሃቸው ሂድ፤ ነገር ግን እኔ የምነግርህን ብቻ አድርግ።” በለዓም በጧት ተነሣ፤ አህያውንም ጭኖ ከሞዓብ አለቆች ጋር ሄደ።
ዘኍል 22:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የእስራኤልም ልጆች ተጓዙ፥ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በዮርዳኖስ ማዶ ባለው በሞዓብ ሜዳ ሰፈሩ። የሴፎር ልጅ ባላቅ እስራኤል በአሞራውያን ላየ ያደረገውን ሁሉ አየ። ብዙም ነበረና ሞዓብ ከሕዝቡ እጅግ ፈራ፤ ከእስራኤልም ልጆች የተነሣ ሞዓብ ደነገጠ። ሞዓብም የምድያምን ሽማግሌዎች፦ በሬ የለመለመውን ሣር እንደሚጨርስ ይህ ጭፍራ በዙሪያችን ያለውን ሁሉ ይጨርሳል አላቸው። በዚያን ጊዜም የሴፎር ልጅ ባላቅ የሞዓብ ንጉሥ ነበረ። በወንዙ አጠገብ ባለችው በሕዝቡ ልጆች ምድር በፋቱራ ወደ ተቀመጠው ወደ ቢዖር ልጅ ወደ በለዓም፦ እነሆ፥ ከግብፅ የወጣ ሕዝብ አለ፤ እነሆም፥ የምድሩን ሁሉ ፊት ሸፈነ፥ በአቅራቢያችንም ተቀምጦአል፤ አሁንም ይህ ሕዝብ ከእኔ ይበልጣልና ልወጋቸውና ከምድሪቱ ላሳድዳቸው እችል እንደ ሆነ፥ እባክህ፥ ና ርገምልኝ፤ አንተ የመረቅኸው ምሩቅ የረገምኸውም ርጉም እንደ ሆነ አውቃለሁና ብሎ ይጠሩት ዘንድ መልእክተኞቹን ላከ። የሞዓብ ሽማግሌዎችና የምድያም ሽማግሌዎችም የምዋርቱን ዋጋ በእጃቸው ይዘው ሄዱ፤ ወደ በለዓምም መጡ፥ የባላቅንም ቃል ነገሩት። እርሱም፦ ዛሬ ሌሊት በዚህ እደሩ፥ እግዚአብሔርም እንደሚነግረኝ እመልስላችኋለሁ አላቸው፤ የሞዓብም አለቆች በበለዓም ዘንድ ተቀመጡ። እግዚአብሔርም ወደ በለዓም መጥቶ፦ እነዚህ በአንተ ዘንድ ያሉ ሰዎች እነማን ናቸው? አለው። በለዓምም እግዚአብሔርን፦ የሞዓብ ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ፦ እነሆ፥ ከግብፅ የወጣ ሕዝብ የምድርን ፊት ሸፈነ፥ አሁንም ና እርሱንም ርገምልኝ፤ ምናልባት እወጋው አሳድደውም ዘንድ እችል እንደ ሆነ ብሎ ወደ እኔ ልኮአል አለው። እግዚአብሔርም በለዓምን፦ ከእነርሱ ጋር አትሂድ፤ የተባረከ ነውና ሕዝቡን አትረግምም አለው። በለዓምም ሲነጋ ተነሥቶ የባላቅን አለቆች፦ ከእናንተ ጋር እሄድ ዘንድ እግዚአብሔር አልፈቀደምና ወደ ምድራችሁ ሂዱ አላቸው። የሞዓብ አለቆች ተነሡ፥ ወደ ባላቅም መጥተው፦ በለዓም ከእኛ ጋር ይመጣ ዘንድ አልፈቀደም አሉት። ባላቅም ደግሞ ከፊተኞች የበዙና የከበሩ ሌሎችን አለቆች ሰደደ። ወደ በለዓምም መጥተው፦ የሴፎር ልጅ ባላቅ፦ ክብርህን እጅግ ታላቅ አደርገዋለሁና፥ የተናገርኸውንም ሁሉ አደርግልሃለሁና፥ እባክህ፥ ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ ምንም አይከልክልህ፤ እባክህ፥ ና፥ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ አለ ብለው ነገሩት። በለዓምም መልሶ የባላቅን ባሪያዎች፦ ባላቅ በቤቱ የሞላውን ወርቅና ብር ቢሰጠኝ፥ በትንሹ ወይም በትልቁ ቢሆን የአምላኬን የእግዚአብሔርን ቃል እተላለፍ ዘንድ አይቻለኝም፤ አሁንም እግዚአብሔር ደግሞ የሚነግረኝን አውቅ ዘንድ፥ እባካችሁ፥ ዛሬ ሌሊት ደግሞ በዚህ እደሩ አላቸው። እግዚአብሔርም ወደ በለዓም በሌሊት መጥቶ፦ ሰዎቹ ይጠሩህ ዘንድ መጥተው እንደ ሆነ፥ ተነሣ ከእነርሱም ጋር ሂድ፤ ነገር ግን የምነግርህን ቃል ብቻ ታደርጋለህ አለው። በለዓምም ሲነጋ ተነሣ፥ አህያይቱንም ጭኖ ከሞዓብ አለቆች ጋር ሄደ።
ዘኍል 22:1-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እስራኤላውያን ጒዞአቸውን በመቀጠል ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምሥራቅና በኢያሪኮ ትይዩ በሚገኘው በሞአብ ሜዳ ላይ ሰፈሩ። የሞአብ ንጉሥ የጺጶር ልጅ ባላቅ እስራኤላውያን በአሞራውያን ላይ ያደረሱትን ጒዳት አየ፥ በእስራኤላውያን ብዛት ምክንያት የሞአብ ሕዝብ ታላቅ ፍርሀት ዐደረባቸው፤ እስራኤላውያንንም በጣም ፈሩ። ሞአባውያን ለምድያማውያን ሽማግሌዎች “ይህ የምታዩት የሕዝብ ብዛት በሬ በመስክ የሚገኘውን ሣር ሁሉ ጠራርጎ እንደሚበላ በዙሪያችን ያለውን ነገር ሁሉ ጠራርጎ የሚያጠፋ ነው” አሉአቸው። ስለዚህ በዚያን ጊዜ የሞአብ ንጉሥ የነበረው የጺጶር ልጅ ባላቅ፥ በዓማው ምድር በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ በፐቶር ከተማ ይኖር ወደነበረው ወደ ቢዖር ልጅ ወደ በለዓም ይጠሩት ዘንድ መልእክተኞች እንዲህ ብሎ ላከበት፤ “ከግብጽ የወጣ አንድ ሕዝብ ምድሪቱን ሁሉ ሸፍኖአታል፤ እነርሱም በአቅራቢያችን ሰፍረዋል፤ የሕዝቡም ቊጥር ከእኛ እጅግ የበዛ ነው፤ ስለዚህ ወደዚህ መጥተህ እነርሱን ርገምልኝ፤ በዚህ ዐይነት ምናልባት ድል ልነሣቸውና ከምድሪቱ ላስወጣቸው እችል ይሆናል፤ አንተ የምትመርቀው የተመረቀ፥ አንተም የምትረግመው የተረገመ እንደሚሆን ዐውቃለሁ።” ስለዚህ የሞአባውያንና የምድያማውያን ሽማግሌዎች ስለ ርግማን የሚከፈለውን ገንዘብ ይዘው ወደ በለዓም በመሄድ የባላቅን መልእክት ሰጡት፤ በለዓምም “እዚሁ ዕደሩና ነገ ጧት እግዚአብሔር የሚነግረኝን ሁሉ እነግራችኋለሁ” አላቸው፤ በዚህ ዐይነት የሞአባውያን መሪዎች ከበለዓም ጋር ቈዩ። እግዚአብሔርም ወደ በለዓም መጥቶ “እነዚህ ከአንተ ጋር ያሉት ሰዎች እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቀው። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “የሞአብ ንጉሥ የጲዖር ልጅ ባላቅ እንዲህ ብሎ ወደ እኔ የላካቸው ናቸው፦ ‘ከግብጽ የወጣ ሕዝብ ምድሪቱን ሸፍኖአታል፤ መጥተህ ብትረግምልኝ ምናልባት እነርሱን በጦርነት ተዋግቼ ላስወጣቸው እችል ይሆናል።’ ” እግዚአብሔርም በለዓምን “ከነዚህ ሰዎች ጋር አትሂድ፤ የተባረኩ ስለ ሆነ የእስራኤልን ሕዝብ አትርገም” አለው። በለዓምም በማግስቱ ጠዋት ሲነጋ ተነሥቶ፥ ለባላቅ ሹማምንት “እንግዲህ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ፤ እኔ ከእናንተ ጋር እንዳልሄድ እግዚአብሔር ከልክሎኛል” አላቸው፤ ስለዚህ የሞአብ ሹማምንት ወደ ባላቅ ተመለሱና በለዓም አብሮአቸው ለመምጣት እምቢ እንዳለ ነገሩት። ከዚያን በኋላ ባላቅ ከፊተኞቹ መልእክተኞች ይበልጥ የተከበሩና ቊጥራቸውም የበዛ ሹማምንት ወደ በለዓም ላከ፤ እነርሱም ወደ በለዓም ሄደው የባላቅን መልእክት እንዲህ ሲሉ ነገሩት፤ “ወደ እኔ መምጣት እንዳትችል የሚያግድህ ነገር አይኑር! ከፍ ባለ ክብር አከብርሃለሁ፤ የጠየቅከኝንም ሁሉ አደርግልሃለሁ፤ ስለዚህ እባክህ መጥተህ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ።” በለዓም ግን ለመልእክተኞቹ እንዲህ ሲል መልስ ሰጠ፤ “ባላቅ በቤተ መንግሥቱ የሚገኘውን ብርና ወርቅ ሁሉ ቢሰጠኝም በትንሽ ወይም በትልቅ ነገር የአምላኬን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መተላለፍ አይቻለኝም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የሚነግረኝ ሌላ ነገር ካለ ከእርሱ እረዳ ዘንድ እስቲ እናንተም እንደ ፊተኞቹ መልእክተኞች ሌሊቱን እዚሁ አሳልፉ።” በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ወደ በለዓም መጣና “እነዚህ ሰዎች ወደ አንተ የመጡት ይዘውህ ሊሄዱ ከሆነ ተነሥተህ አብረሃቸው ሂድ፤ ነገር ግን እኔ የምነግርህን ብቻ አድርግ” አለው። ስለዚህ በማግስቱ ጠዋት በለዓም ተነሣና አህያውን ጭኖ ከሞአባውያን መሪዎች ጋር ሄደ።
ዘኍል 22:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የእስራኤልም ልጆች ተጓዙ፥ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በዮርዳኖስ ማዶ ባለው በሞዓብ ሜዳ ሰፈሩ። የሴፎር ልጅ ባላቅ እስራኤል በአሞራውያን ላይ ያደረገውን ሁሉ አየ። ብዙም ስለ ነበሩ ሞዓብ ሕዝቡን እጅግ ፈራ፤ ከእስራኤልም ልጆች የተነሣ ሞዓብ ደነገጠ። ሞዓብም የምድያምን ሽማግሌዎች፦ “በሬ የለመለመውን የሣር መስክ ግጦ እንደሚጨርስ ይህ ጭፍራ በዙሪያችን ያለውን ሁሉ አሁን ይጨርሳል” አላቸው። በዚያን ጊዜም የሞዓብ ንጉሥ የነበረው የሴፎር ልጅ ባላቅ፥ በወንዙ አጠገብ ባለችው በሕዝቡ ልጆች ምድር በፋቱራ የተቀመጠውን የቢዖርን ልጅ በለዓምን እዲጠሩት እንዲህ ብሎ መልእክተኞቹን ላከ፦ “እነሆ፥ ከግብጽ የወጣ ሕዝብ አለ፤ እነሆም፥ የምድሩን ሁሉ ፊት ሸፍኖአል፥ በአቅራቢያችንም ተቀምጦአል። አሁንም ከእኔ ይልቅ እጅግ ኃያል ናቸውና ልወጋቸውና ከምድሪቱ ላሳድዳቸው እችል እንደሆነ፥ ይህን ሕዝብ እባክህ፥ ና ርገምልኝ፤ አንተ የባረከው ቡሩክ የረገምኸውም ርጉም እንደሆነ አውቃለሁና።” የሞዓብ ሽማግሌዎችና የምድያም ሽማግሌዎችም ለምዋርቱ የሚከፈለውን ገንዘብ በእጃቸው ይዘው ሄዱ፤ ወደ በለዓምም መጡ፥ የባላቅንም ቃላት ነገሩት። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ዛሬ ሌሊት በዚህ እደሩ፥ ጌታም እንደሚነግረኝ እመልስላችኋለሁ”፤ የሞዓብም አለቆች በበለዓም ዘንድ ተቀመጡ። እግዚአብሔርም ወደ በለዓም መጥቶ፦ “እነዚህ ከአንተ ጋር ያሉት ሰዎች እነማን ናቸው?” አለው። በለዓምም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፦ “የሞዓብ ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ እንዲህ ብሎ ወደ እኔ ላከ፦ ‘እነሆ፥ ከግብጽ የወጣ ሕዝብ የምድርን ፊት ሸፈነ፥ ምናልባት ልወጋው ላሳድደውም እችል እንደሆነ አሁን ና እርሱን ርገምልኝ።’ ” እግዚአብሔርም በለዓምን፦ “ከእነርሱ ጋር አትሂድ፤ የተባረከ ነውና ሕዝቡን አትረግምም” አለው። በለዓምም ሲነጋ ተነሥቶ የባላቅን ሹማምንት፦ “ከእናንተ ጋር እንድሄድ ጌታ አልፈቀደምና ወደ ምድራችሁ ሂዱ” አላቸው። የሞዓብ ሹማምንት ተነሡ፥ ወደ ባላቅም ሄደው፦ “በለዓም ከእኛ ጋር ለመምጣት ፍቃደኛ አልሆነም” አሉት። ባላቅም ዳግመኛ ከፊተኞቹ ይልቅ እጅግ የበዙና የከበሩ ሌሎችን ሹማምንት ላከ። ወደ በለዓምም መጥተው እንዲህ አሉት፦ “የሴፎር ልጅ ባላቅ እንዲህ ይላል፦ ‘እባክህ፥ ወደ እኔ ለመምጣት ምንም ዓይነት ነገር አያግድህ፤ ክብርህን እጅግ ታላቅ አደርገዋለሁና፥ የምትነግረኝንም ሁሉ አደርግልሃለሁና፥ እባክህ፥ ና፥ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ።’ ” በለዓምም መልሶ የባላቅን ባርያዎች እንዲህ አላቸው፦ “ባላቅ በቤቱ የሞላውን ወርቅና ብር ቢሰጠኝ፥ ትንሹን ወይም ትልቁን ነገር በመፈጸም የአምላኬን የጌታን ቃል ለመተላለፍ አልችልም፤ አሁንም ጌታ ይበልጥ የሚነግረኝን ነገር እንዳውቅ፥ እባካችሁ፥ ሌሎቹ እንዳደረጉት እንዲሁ ዛሬ ሌሊት ደግሞ በዚህ እደሩ።” እግዚአብሔርም ወደ በለዓም በሌሊት መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ሰዎቹ ሊጠሩህ መጥተው እንደሆነ፥ ተነሣ ከእነርሱም ጋር ሂድ፤ ነገር ግን የምነግርህን ቃል ብቻ ታደርጋለህ።” በለዓምም ሲነጋ ተነሣ፥ አህያይቱንም ጭኖ ከሞዓብ ሹማምንት ጋር ሄደ።