ነህምያ 9:32-37
ነህምያ 9:32-37 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“አሁንም አምላካችን ሆይ፤ ቃል ኪዳንህንና ዘላለማዊ ፍቅርህን የምትጠብቅ ታላቅ፣ ኀያልና የተፈራህ አምላክ ሆይ፤ ከአሦር ነገሥታት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእኛ፣ በነገሥታታችንና በመሪዎቻችን፣ በካህናታችንና በነቢያታችን፣ በአባቶቻችንና በመላው ሕዝብህ ላይ የደረሰው ይህ ሁሉ መከራ በፊትህ እንደ ቀላል ነገር አይታይ። በደረሰብን ሁሉ አንተ ጻድቅ ነህ፤ እኛ በደለኞች ነን፤ አንተ ግን ትክክለኛውን አደረግህ። ነገሥታታችን፣ መሪዎቻችን፣ ካህናታችንና አባቶቻችን ሕግህን አልጠበቁም፤ ትእዛዞችህን ወይም የሰጠሃቸውን ማስጠንቀቂያዎች አልሰሙም። በገዛ መንግሥታቸው፣ በሰጠሃቸው ታላቅ በጎነትህና በፊታቸውም ባዘጋጀህላቸው ሰፊና ለም ምድር እንኳ፣ አንተን አላገለገሉም፤ ከክፉ መንገዳቸውም አልተመለሱም። “እነሆ፤ ዛሬም ባሮች ነን፤ አባቶቻችን ፍሬዋንና በረከቷን እንዲበሉ በሰጠሃቸው ምድር ባሮች ነን። ከኀጢአታችን የተነሣ የተትረፈረፈው መከር ሲሳይ የሆነው በላያችን ላስቀመጥሃቸው ነገሥታት ነው፤ እነርሱም ደስ እንዳሰኛቸው በሰውነታችንና በቀንድ ከብቶቻችን ላይ ያዝዛሉ። እኛም በታላቅ ጭንቀት ውስጥ እንገኛለን።
ነህምያ 9:32-37 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አሁንም አምላካችን ሆይ፥ ቃል ኪዳንና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና ኃያል የተፈራኸውም አምላክ ሆይ፥ ከአሦር ነገሥታት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእኛና በነገሥታቶቻችን በአለቆቻችንም በካህናቶቻችንም በነቢያቶቻችንም በአባቶቻችንም በሕዝብህ ሁሉ ላይ የደረሰው መከራ ሁሉ በፊትህ ጥቂት መስሎ አይታይህ። በደረሰብንም ነገር ሁሉ አንተ ጻድቅ ነህ፥ አንተ እውነት አድርገሃልና፥ እኛም ኃጢአት አድርገናል። ነገሥታቶቻችንም አለቆቻችንም ካህናቶቻችንም አባቶቻችንም ሕግህን አልጠበቁም፥ የመሰከርህባቸውንም ትእዛዝህንና ምስክርህን አልሰሙህም። በመንግሥታቸውም በሰጠሃቸውም ታላቅ በጎነትህ፥ በፊታቸውም በሰጠኸው በሰባው ምድር አላመለኩህም፥ ከክፉም ሥራቸው አልተመለሱም። እነሆ፥ ዛሬ ባሪያዎች ነን፥ ፍሬዋንና በረከትዋን ይበሉ ዘንድ ለአባቶቻችን በሰጠሃት ምድር፥ እነሆ፥ በእርስዋ ባሪያዎች ነን፥ ስለ ኃጢአታችንም ለሾምህብን ነገሥታት በረከትዋን ታበዛለች፥ ሰውነታችንንም ይገዛሉ፥ በእንስሶቻችንም የሚወድዱትን ያደርጋሉ፥ እኛም በጽኑ መከራ ላይ ነን።
ነህምያ 9:32-37 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“አሁንም አምላካችን ሆይ፥ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና ኀያል ጽኑዕና የተፈራኸው አምላክ ሆይ፥ ከአሦር ነገሥታት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ በእኛና በነገሥታቶቻችን፥ በአለቆቻችንም፥ በካህናቶቻችንም፥ በነቢያቶቻችንም፥ በአባቶቻችንም፥ በሕዝብህ ሁሉ ላይ የደረሰው መከራ ሁሉ በፊትህ ጥቂት መስሎ አይታይህ። በደረሰብንም ነገር ሁሉ አንተ ጻድቅ ነህ፤ አንተ እውነት አድርገሃልና፥ እኛም እጅግ በድለናልና። ነገሥታቶቻችን፥ አለቆቻችንም፥ ካህናቶቻችንም፥ አባቶቻችንም ሕግህን አልጠበቁም፤ ትእዛዝህንና የመሰከርህባቸውን ምስክርህንም አልሰሙም። በመንግሥትህም በሰጠሃቸው ታላቅ በጎነትህ፥ በፊታቸውም በሰጠሃቸው በሰፊውና በሰባው ምድር አልተገዙልህም፤ ከክፉም ሥራቸው አልተመለሱም። እነሆ፥ ዛሬ ባሪያዎች ነን፤ ፍሬዋንና በረከቷን ይበሉ ዘንድ ለአባቶቻችን በሰጠሃት ምድር እነሆ፥ በእርስዋ ባሪያዎች ነን፥ ስለ ኀጢአታችንም ለሾምህብን ነገሥታት በረከቷን ታበዛለች፤ ሰውነታችንንም ይገዛሉ፤ በእንስሶቻችንም የሚወድዱትን ያደርጋሉ፤ እኛም በጽኑ መከራ ላይ ነን።
ነህምያ 9:32-37 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ቃል ኪዳንህንና ዘለዓለማዊ ፍቅርህን የምትጠብቅ፥ ታላቁ፥ ኀያሉና አስፈሪው አምላካችን ሆይ! በእኛ፥ በንጉሦቻችን፥ በመሪዎቻችን፥ በካህኖቻችን፥ በነቢዮቻችን፥ በቅድመ አያቶቻችን፥ እንዲሁም በሕዝብህ ሁሉ ላይ፥ ከአሦር ነገሥታት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፥ የደረሰውን መከራ ሁሉ አስብ። እኛን ለመቅጣት ያደረግኸው ውሳኔ ትክክል ነው፤ እኛ በደል ብንሠራም፥ አንተ በታማኝነትህ እንደ ጸናህ ነህ። የቀድሞ አባቶቻችን፥ ንጉሦቻችን፥ መሪዎቻችንና ካህኖቻችን ሕግህን አልጠበቁም፤ የሰጠሃቸውን ትእዛዞች ማስጠንቀቂያዎች አላዳመጡም። መንግሥታቸው በሰጠሃቸው ቸርነት፥ በሰጠሃቸው ሰፊና ለም መሬት፥ ይደሰቱ በነበረ ጊዜ እንኳ፥ አንተን አላመለኩም፥ ከኃጢአታቸውም አልተመለሱም። ስለዚህም አንተ ለአባቶቻችን ፍሬዋን እንዲበሉና በመልካም ነገሮችም እንዲደሰቱ፥ በሰጠሃቸው ምድር ላይ እነሆ፥ ዛሬ እኛ ባሪያዎች ሆነናል። እኛም ኃጢአት በመሥራታችን ምክንያት ስላሳዘንክ፥ የምድሪቱንም በረከት በእኛ ላይ ገዢዎች አድርገህ ላስነሣሃቸው ነገሥታት ገቢ ይሆናል፤ እነርሱ በእኛና በእንስሶቻችን ላይ ደስ ያሰኛቸውን ነገር ሁሉ ይፈጽማሉ፤ ከዚህም የተነሣ፥ በታላቅ ጭንቀት ላይ እንገኛለን።”
ነህምያ 9:32-37 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“አሁንም አምላካችን ሆይ፥ ቃል ኪዳንና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና ኃያል የተፈራኸውም አምላክ ሆይ፥ ከአሦር ነገሥታት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእኛና በነገሥታቶቻችን በአለቆቻችንም በካህናቶቻችንም በነብዮቻችንም በአባቶቻችንም በሕዝብህ ሁሉ ላይ የደረሰው መከራ ሁሉ በፊትህ ጥቂት መስሎ አይታይህ። በደረሰብንም ነገር ሁሉ አንተ ጻድቅ ነህ፥ አንተ እውነት አድርገሃልና፥ እኛም ኃጢአት አድርገናል። ነገሥታቶቻችንም አለቆቻችንም ካህናቶቻችንም አባቶቻችንም ሕግህን አልጠበቁም፥ የመሰከርህባቸውንም ትእዛዝህንና ምስክርህን አልሰሙህም። በመንግሥታቸውም በሰጠሃቸውም ታላቅ በጎነትህ፥ በፊታቸውም በሰጠኸው በሰባው ምድር አላመለኩህም፥ ከክፉም ሥራቸው አልተመለሱም። እነሆ፥ ዛሬ ባርያዎች ነን፥ ፍሬዋንና በረከትዋን ይበሉ ዘንድ ለአባቶቻችን በሰጠሃት ምድር፥ እነሆ፥ በእርሷ ባርያዎች ነን፥ ስለ ኃጢአታችንም ለሾምህብን ነገሥታት በረከትዋን ታበዛለች፥ ሰውነታችንንም ይገዛሉ፥ በእንስሶቻችንም የሚወድዱትን ያደርጋሉ፥ እኛም በጽኑ መከራ ላይ ነን።”