የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ነህምያ 9

9
1በዚህም ወር በሀያ አራተኛው ቀን የእስራኤል ልጆች ጾመው፥ ማቅም ለብሰው፥ በላያቸውም ትቢያ ነስንሰው ተከማቹ። 2የእስራኤልም ዘር ከእንግዶች ሁሉ ራሳቸውን ለዩ፥ ቆመውም ኃጢአታቸውንና የአባቶቻቸውን ኃጢአት ተናዘዙ። 3በየስፍራቸውም ቆመው የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን የሕግ መጽሐፍ የቀን ሩብ ያህል አነበቡ ሦስት የቀን ሩብም ያህል ተናዘዙ፥ ለአምላካቸው ለእግዚአብሔርም ሰገዱ። 4ሌዋውያኑም ኢያሱና ባኒ፥ ቀድምኤል፥ ሰበንያ፥ ቡኒ፥ ሰራብያ፥ ባኒ፥ ክናኒ በደረጃዎች ላይ ቆመው ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር በታላቅ ድምፅ ጮኹ።
5ሌዋውያኑም ኢያሱ፥ ቀድምኤል፥ ባኒ፥ አሰበንያ፥ ሰራብያ፥ ሆዲያ፥ ሰበንያ፥ ፈታያ እንዲህ አሉ፦ ቆማችሁ ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላካችንን እግዚአብሔርን ባርኩ። እንዲህም በሉ፦ በበረከትና በምስጋና ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያለው ክቡር ስምህ ይባረክ። 6አንተ ብቻ እግዚአብሔር ነህ፥ ሰማዩንና የሰማያት ሰማይን ሠራዊታቸውንም ሁሉ፥ ምድሩንና በእርስዋ ላይ ያሉትን ሁሉ፥ ባሕሮቹንና በእነርሱ ውስጥ ያለውን ሁሉ፥ ፈጥረሃል፥ ሁሉንም ሕያው አድርገኸዋል፥ የሰማዩም ሠራዊት ለአንተ ይሰግዳሉ። 7አንተ እግዚአብሔር አምላክ ነህ፥ አብራምን መረጥህ፥ ከዑር ከላውዴዎንም አወጣኸው፥ ስሙንም አብርሃም አልኸው፥ 8ልቡም በፊትህ የታመነ ሆኖ አገኘኸው፥ የከነዓናዊውንና የኬጢያዊውን የአሞራዊውንም የፌርዛዊውንም የኢያቡሳዊውንም የጌርጌሳዊውንም ምድር ለእርሱና ለዘሩ ትሰጥ ዘንድ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረግህ፥ አንተም ጻድቅ ነህና ቃልህን ፈጸምህ።
9በግብጽም ሳሉ የአባታችንን መከራ አየህ፥ በኤርትራ ባሕርም ሳሉ ጩኸታቸውን ሰማህ፥ 10እንደ ታበዩባቸውም አውቀህ ነበርና በፈርዖንና በባሪያዎቹ ሁሉ በምድሩም ሕዝብ ሁሉ ላይ ምልክትና ተአምራት አሳየህ፥ ዛሬም እንደ ሆነው ስምህን አስጠራህ። 11ከፊታቸውም ባሕሩን ከፈልህ፥ በባሕሩም መካከል በደረቅ አለፉ፥ ጠላቶቻቸውን ግን ድንጋይ ለጥልቅ ውኃ እንዲጣል በቀላይ ውስጥ ጣልሃቸው። 12የሚሄዱበትንም መንገድ ታበራላቸው ዘንድ በቀን በደመና ዓምድ፥ በሌሊትም በእሳት ዓምድ መራሃቸው። 13ወደ ሲናም ተራራ ወረድህ፥ ከሰማይም ተናገርሃቸው፥ ቅኑን ፍርድና እውነቱን ሕግ መልካሙንም ሥርዓትና ትእዛዝ ሰጠሃቸው፥ 14የተቀደሰውንም ሰንበትህን አስታወቅሃቸው፥ ትእዛዝንና ሥርዓትን ሕግንም በባሪያህ በሙሴ እጅ አዘዝሃቸው። 15ለራባቸውም ከሰማይ እንጀራ ሰጠሃቸው፥ ለጥማታቸውም ከዓለቱ ውኃ አመጣህላቸው፥ ወደ ማልህላቸውም ምድር ገብተው ይወርሱ ዘንድ አዘዝሃቸው።
16ነገር ግን እነርሱና አባቶቻችን ታበዩ፥ አንገታቸውንም አደነደኑ፥ ትእዛዝህንም አልሰሙም፥ 17ለመስማትም እንቢ አሉ፥ ያደረግህላቸውንም ተአምራት አላሰቡም፥ አንገታቸውንም አደነደኑ፥ በዓመፃቸውም ወደ ባርነታቸው ይመለሱ ዘንድ አለቃ አደረጉ፥ አንተ ግን ይቅር ባይ፥ ቸርና መሐሪ አምላክ፥ ለቁጣም የምትዘገይ፥ ምሕረትንም የምታበዛ ነህ፥ አልተውሃቸውም። 18ቀልጦ የተሠራውንም እምቦሳ አድርገው፦ ከግብጽ ያወጣህ አምላክህ ይህ ነው ባሉ ጊዜ፥ እጅግም ባስቈጡህ ጊዜ፥ 19አንተ በምሕረትህ ብዛት በምድረ በዳ አልተውሃቸውም፥ በመንገድም ይመራቸው ዘንድ የደመና ዓምድ በቀን፥ የሚሄዱበትንም መንገድ ያበራላቸው ዝነድ የእሳት ዓምድ በሌሊት ከእነርሱ አልራቀም። 20ያስተምራቸውም ዘንድ መልካሙን መንፈስህን ሰጠሃቸው፥ መናህንም ከአፋቸው አልከለከልህም፥ ለጥማታቸውም ውኃ ሰጠሃቸው። 21አርባ ዓመትም በምድረ በዳ መገብሃቸው፥ ምንም አላጡም፥ ልብሳቸውም አላረጀም፥ እግራቸውም አላበጠም።
22መንግሥታትንና አሕዛብን ከፍለህ ሰጠሃቸው፥ የሐሴቦንን ንጉሥ የሴዎንን ምድር፥ የባሳንንም ንጉሥ የዐግን ምድር ወረሱ። 23ልጆቻቸውንም እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛህ፥ ይገቡና ይወርሱ ዘንድ ለአባቶቻቸው ወደ ተናገርህላቸውም ምድር አገባሃቸው። 24ልጆቹም ገብተው ምድሩን ወረሱ፥ የምድሩን ሰዎች ከነዓናውያንን በፊታቸው አዋረድህ፥ የሚወድዱትንም ነገር ያደረጉባቸው ዘንድ እነርሱንና ነገሥታቶቻቸውን የምድሩንም አሕዛብ በእጃቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው። 25ምሽጎቹንም ከተሞች የሰባውንም ምድር ወሰዱ፥ መልካሙን ነገር የሞሉትን ቤቶች፥ የተማሱትንም ጕድጓዶች፥ ወይኖቹንና ወይራዎቹን ብዙዎቹንም የፍሬ ዛፎች ወረሱ፥ በሉም፥ ጠገቡም፥ ወፈሩም፥ በታላቅ በጎነትህም ደስ አላቸው።
26ነገር ግን እንቢተኞች ነበሩ፥ ዐመፁብህም፥ ሕግህንም ወደ ኋላቸው ጣሉት፥ ወደ አንተም ይመለሱ ዘንድ የመሰከሩባቸውን ነቢያትህን ገደሉ፥ እጅግም አስቈጡህ። 27ስለዚህ ለጠላቶቻቸው እጅ አሳልፈህ ሰጠሃቸው፥ አስጨነቁአቸውም፥ በመከራቸውም ጊዜ ወደ አንተ ጮኹ፥ ከሰማይም ሰማሃቸው፥ እንደ ምሕረትህም ብዛት ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳኑአቸውን ታዳጊዎችን ሰጠሃቸው። 28ባረፉም ጊዜ ተመልሰው በፊትህ ክፉ አደረጉ፥ በጠላቶቻቸው እጅ ተውሃቸው፥ ገዙአቸውም፥ ተመልሰውም ወደ አንተ በጮኹ ጊዜ ከሰማይ ሰማሃቸው፥ እንደ ምሕረትህም ብዛት ታደግሃቸው፥ 29ወደ ሕግህም ትመልሳቸው ዘንድ አስመሰከርህባቸው፥ ነገር ግን ታበዩ፥ ትእዛዝህንም አልሰሙም፥ ሰውም ባደረገው ጊዜ በሕይወት የሚኖርበትን ፍርድህን ተላለፉ፥ ትከሻቸውንም ሰጡ፥ አንገታቸውን አደነደኑ፥ አልሰሙምም። 30ነገር ግን ብዙ ዓመታት ታገሥሃቸው፥ በነቢያትህም እጅ በመንፈስህ መሰከርህባቸው፥ አላደመጡም፥ ስለዚህም በምድር አሕዛብ እጅ አሳልፈህ ሰጠሃቸው። 31ነገር ግን አንተ ቸርና መሐሪ አምላክ ነህና በምሕረትህ ብዛት ፈጽመህ አላጠፋሃቸውም፥ አልተውሃቸውምም።
32አሁንም አምላካችን ሆይ፥ ቃል ኪዳንና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና ኃያል የተፈራኸውም አምላክ ሆይ፥ ከአሦር ነገሥታት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእኛና በነገሥታቶቻችን በአለቆቻችንም በካህናቶቻችንም በነቢያቶቻችንም በአባቶቻችንም በሕዝብህ ሁሉ ላይ የደረሰው መከራ ሁሉ በፊትህ ጥቂት መስሎ አይታይህ። 33በደረሰብንም ነገር ሁሉ አንተ ጻድቅ ነህ፥ አንተ እውነት አድርገሃልና፥ እኛም ኃጢአት አድርገናል። 34ነገሥታቶቻችንም አለቆቻችንም ካህናቶቻችንም አባቶቻችንም ሕግህን አልጠበቁም፥ የመሰከርህባቸውንም ትእዛዝህንና ምስክርህን አልሰሙህም። 35በመንግሥታቸውም በሰጠሃቸውም ታላቅ በጎነትህ፥ በፊታቸውም በሰጠኸው በሰባው ምድር አላመለኩህም፥ ከክፉም ሥራቸው አልተመለሱም። 36እነሆ፥ ዛሬ ባሪያዎች ነን፥ ፍሬዋንና በረከትዋን ይበሉ ዘንድ ለአባቶቻችን በሰጠሃት ምድር፥ እነሆ፥ በእርስዋ ባሪያዎች ነን፥ 37ስለ ኃጢአታችንም ለሾምህብን ነገሥታት በረከትዋን ታበዛለች፥ ሰውነታችንንም ይገዛሉ፥ በእንስሶቻችንም የሚወድዱትን ያደርጋሉ፥ እኛም በጽኑ መከራ ላይ ነን። 38ስለዚህም ሁሉ የታመነውን ቃል ኪዳን አድርገን እንጽፋለን፥ አለቆቻችንም ሌዋውያኖቻችንም ካህናቶቻችንም ያትሙበታል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ