የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ነህምያ 9

9
ሕዝባዊ ኑዛዜ
1 # ዳን. 9፥3። በዚሁ ወር በሀያ አራተኛው ቀን የእስራኤል ልጆች ጾመው፥ ማቅም ለብሰውና በላያቸው ላይ ትቢያ#9፥1 አፈር። ነስንሰው ተሰበሰቡ። 2#ዕዝ. 9፥1-2፤ 10፥11።የእስራኤል ዘር ከባዕድ ሕዝቦች ሁሉ ራሳቸውን ለዩ፥ ቆመውም ኃጢአታቸውንና የአባቶቻቸውን በደል ተናዘዙ። 3በየስፍራቸውም ቆመው የጌታ አምላካቸውን የሕግ መጽሐፍ የቀኑ ሩብ ያህል አነበቡ፥ የቀኑ ሩብ ደግሞ እየተናዘዙና፥ ለጌታ አምላካቸው እየሰገዱ አሳለፉ። 4በሌዋውያኑ መድረክ ላይ ኢያሱ፥ ባኒ፥ ቃድምኤል፥ ሽባንያ፥ ቡኒ፥ ሼሬብያ፥ ባኒ፥ ክናኒ ቆመው ወደ ጌታ አምላካቸው በታላቅ ድምፅ ጮኹ።
5 # መዝ. 41፥14፤ 106፥48፤ ዳን. 2፥20፤ 3፥52። ሌዋውያኑ ኢያሱ፥ ቃድምኤል፥ ባኒ፥ ሐሻብንያ፥ ሼሬብያ፥ ሆዲያ፥ ሽባንያ፥ ፕታሕያ እንዲህ አሉ፦ “ቁሙ፥ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ጌታ አምላካችሁን ባርኩ። ከበረከትና ከምስጋና ሁሉ በላይ ከፍ ያለው የክብርህን ስም ይባርኩ። 6አንተ ብቻህን ጌታ ነህ፥ ሰማይንና የሰማያት ሰማይን ሠራዊታቸውንም ሁሉ፥ ምድርንና በእርሷ ያሉትን ሁሉ፥ ባሕሮቹንና በእነርሱ ውስጥ ያለውን ሁሉ፥ ፈጠርህ፥ ለሁሉም ሕይወትን ሰጠሃቸው፤ የሰማይ ሠራዊት ለአንተ ይሰግዳሉ። 7#ዘፍ. 12፥1፤ 17፥5።አብራምን የመረጥህ፥ ከከለዳውያን ኡር የአወጣኸው፥ ስሙንም አብርሃም ያልኸው፥ አንተ ጌታ አምላክ ነህ። 8#ዘፍ. 15፥18-19።ልቡም በፊትህ ታማኝ ሆኖ አገኘኸው፥ የከነዓናዊውን፥ የኬጢያዊው፥ የአሞራዊውን፥ የፌርዛዊውን፥ የኢያቡሳዊውንና የጌርጌሳዊውን ምድር ለዘሩ ልትሰጥ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረግህ፥ አንተም ጻድቅ ነህና ቃልህን ፈጸምህ።”
9 # ዘፀ. 2፥23-24። “በግብጽ የአባቶቻችንን መከራ አየህ፥ በቀይ ባሕርም ጩኸታቸውን ሰማህ፤ 10#ዘፀ. 7—11፤ 14።በፈርዖን፥ በአገልጋዮቹ ሁሉና በምድሩ ሕዝብ ሁሉ ላይ ምልክትና ተአምራት አሳየህ፤ በእነርሱ ላይ መታበያቸውን አውቀህ ነበርና፥ እስከ ዛሬም እንዳለው ለራስህ ስምን ሠራህ። 11#ዘፀ. 15፥5፤10።በፊታቸውም ባሕሩን ከፈልህ፥ በባሕሩ መካከል በደረቅ ምድር ተሻገሩ፤ አሳዳጆቻቸውን ግን በኃይለኛ ውኃ እንደሚጣል ድንጋይ ወደ ጥልቁ ጣልካቸው። 12#ዘፀ. 13፥21-22።በሚሄዱበትን መንገድ ልታበራላቸው ቀን በደመና ዓምድ፥ ሌሊት ደግሞ በእሳት ዓምድ መራሃቸው። 13#ዘፀ. 19—24።በሲና ተራራ ላይ ወረድህ፥ ከሰማይም ተናገርሃቸው፤ ቅን ፍርዶችን፥ ታማኝ ሕጎችን፥ መልካም ሥርዓቶችና ትእዛዞችን ሰጠሃቸው። 14#ዘፀ. 20፥8።ቅዱስ ሰንበትህን አስታወቅሃቸው፥ ትእዛዞችን፥ ሥርዓቶችንና ሕግን በባርያህ በሙሴ በኩል አዘዝሃቸው። 15#ዘፀ. 16፥4፤ 17፥1-2።ለረኃባቸው ከሰማይ ምግብ ሰጠሃቸው፥ ለጥማታቸውም ከዓለቱ ውኃ አፈለቅህላቸው፤ ልትሰጣቸው ወደ ማልክላቸው#9፥15 ዕብራይስጡ “እጅህን ወዳነሣህበት” ይላል። ምድር ገብተው እንዲወርሱ ነገርካቸው።”
16“እነርሱና አባቶቻችን ግን ታበዩ፥ አንገታቸውን አደነደኑ፥ ትእዛዞችህንም አልሰሙም፤ 17#ዘፀ. 34፥6፤ ዘኍ. 14፥1-4፤ ዘዳ. 9፥9።ለመስማትም እንቢ አሉ፥ በመካከላቸው ያደረግኸውን ተአምራት አላስታወሱም፤ አንገታቸውንም አደነደኑ፥ በዓመፃቸውም ወደ ባርነታቸው ለመመለስ መሪ ሾሙ፤ አንተ ግን ይቅር ባይ አምላክ፥ ቸር፥ ርኅሩኅ፥ ለቁጣ የዘገየህና ምሕረትህ የበዛ ነህ፥ አልተውካቸውምም።” 18#ዘፀ. 32፥4፤ 8።ከቀለጠ ብረት የተቀረጸ ጥጃ ሠርተው “ከግብጽ ያወጣህ አምላክህ ይህ ነው” አሉ፥ ብዙ ተሳደቡ፥ 19አንተ ግን ከርኅራኄህ ብዛት በምድረ በዳ አልተውካቸውም፤ በመንገድ እንዲመራቸው የደመና ዓምድ በቀን፥ የሚሄዱበትንም መንገድ እንዲያበራላቸው የእሳት ዓምድ በሌሊት ከእነርሱ አልተለየም። 20#ዘዳ. 2፥7።እንዲያስተምራቸው መልካሟን መንፈስህን ሰጠሃቸው፥ መናህን ከአፋቸው አልከለከልክም፥ ለጥማታቸውም ውኃን ሰጠሃቸው። 21#ዘዳ. 8፥4።አርባ ዓመትም በምድረ በዳ መገብካቸው፤ ምንም አላጡም፤ ልብሳቸው አላረጀም፥ እግራቸውም አላበጠም።
22 # ዘኍ. 21፥21-35፤ ዘዳ. 1፥4፤ 2፥26—3፥11። “መንግሥታትንና አሕዛብን ሰጠሃቸው፤ የሐሴቦንን ንጉሥ የሴዎንን ምድር፥ የባሳንንም ንጉሥ የዐግን ምድር ወረሱ። 23#ዘዳ. 1፥10።ልጆቻቸውን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛህ፥ እንዲገቡና እንዲወርሷት ለአባቶቻቸው ወደ ነገርሃቸው ምድር አገባሃቸው። 24ልጆቹም ገብተው ምድሪቷን ወረሱ፤ የምድሪቱን ሰዎች ከነዓናውያንን በፊታቸው ደመሰስካቸው፥ የወደዱትን ነገር እንዲያደረጉባቸው ከነገሥታቶቻቸውና ከምድሪቱ ሕዝቦች ጋር በእጃቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው። 25#ዘዳ. 3፥5፤ 6፥10-11፤ 11፥11፤ 32፥15።ምሽጎቹንም ከተሞች የሰባውንም ምድር ወሰዱ፥ መልካሙን ነገር የሞሉትን ቤቶች፥ የተማሱትንም ጉድጓዶች፥ ወይኖቹንና ወይራዎቹን ብዙዎቹንም የፍሬ ዛፎች ወረሱ፥ በሉም፥ ጠገቡም፥ ወፈሩም፥ በታላቅ በጎነትህም ደስ አላቸው።”
26 # ጥበ. 2፥10-20። “ነገር ግን እንቢተኞች ነበሩ፥ ዐመፁብህም፥ ሕግህንም ወደ ኋላቸው ጣሉት፥ ወደ አንተም ይመለሱ ዘንድ የመሰከሩባቸውን ነቢያትህን ገደሉ፥ እጅግም አስቆጡህ። 27#ዳን. 9፥19።ስለዚህ ለጠላቶቻቸው እጅ አሳልፈህ ሰጠሃቸው፥ አስጨነቁአቸውም፥ በመከራቸውም ጊዜ ወደ አንተ ጮኹ፥ ከሰማይም ሰማሃቸው፥ እንደ ምሕረትህም ብዛት ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳኑአቸውን ታዳጊዎችን ሰጠሃቸው። 28ባረፉም ጊዜ ተመልሰው በፊትህ ክፉ አደረጉ፥ በጠላቶቻቸው እጅ ተውካቸው፥ ገዙአቸውም፥ ተመልሰውም ወደ አንተ በጮኹ ጊዜ ከሰማይ ሰማሃቸው፥ እንደ ምሕረትህም ብዛት ታደግሃቸው፥ 29#ዘሌ. 18፥5፤ ዘዳ. 30፥16፤ 32፥47።ወደ ሕግህም ትመልሳቸው ዘንድ አስመሰከርህባቸው፥ ነገር ግን ታበዩ፥ ትእዛዝህንም አልሰሙም፥ ሰውም ባደረገው ጊዜ በሕይወት የሚኖርበትን ፍርድህን ተላለፉ፥ ትከሻቸውንም ሰጡ፥ አንገታቸውን አደነደኑ፥ አልሰሙምም። 30ነገር ግን ብዙ ዓመታት ታገሥሃቸው፥ በነቢያትህም እጅ በመንፈስህ መሰከርክባቸው፥ አላደመጡም፥ ስለዚህም በምድር አሕዛብ እጅ አሳልፈህ ሰጠሃቸው። 31ነገር ግን አንተ ቸርና መሐሪ አምላክ ነህና በምሕረትህ ብዛት ፈጽመህ አላጠፋሃቸውም፥ አልተውካቸውምም።
32 # ሰቆ.ኤ. 5። “አሁንም አምላካችን ሆይ፥ ቃል ኪዳንና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና ኃያል የተፈራኸውም አምላክ ሆይ፥ ከአሦር ነገሥታት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእኛና በነገሥታቶቻችን በአለቆቻችንም በካህናቶቻችንም በነብዮቻችንም በአባቶቻችንም በሕዝብህ ሁሉ ላይ የደረሰው መከራ ሁሉ በፊትህ ጥቂት መስሎ አይታይህ። 33#ዳን. 3፥27፤ 9፥14።በደረሰብንም ነገር ሁሉ አንተ ጻድቅ ነህ፥ አንተ እውነት አድርገሃልና፥ እኛም ኃጢአት አድርገናል። 34ነገሥታቶቻችንም አለቆቻችንም ካህናቶቻችንም አባቶቻችንም ሕግህን አልጠበቁም፥ የመሰከርህባቸውንም ትእዛዝህንና ምስክርህን አልሰሙህም። 35በመንግሥታቸውም በሰጠሃቸውም ታላቅ በጎነትህ፥ በፊታቸውም በሰጠኸው በሰባው ምድር አላመለኩህም፥ ከክፉም ሥራቸው አልተመለሱም። 36እነሆ፥ ዛሬ ባርያዎች ነን፥ ፍሬዋንና በረከትዋን ይበሉ ዘንድ ለአባቶቻችን በሰጠሃት ምድር፥ እነሆ፥ በእርሷ ባርያዎች ነን፥ 37ስለ ኃጢአታችንም ለሾምህብን ነገሥታት በረከትዋን ታበዛለች፥ ሰውነታችንንም ይገዛሉ፥ በእንስሶቻችንም የሚወድዱትን ያደርጋሉ፥ እኛም በጽኑ መከራ ላይ ነን።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ