ነህምያ 9:1-37
ነህምያ 9:1-37 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዚህም ወር በሃያ አራተኛው ቀን የእስራኤል ልጆች ጾመው፥ ማቅም ለብሰው፥ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነስንሰው ተሰበሰቡ። የእስራኤልም ልጆች ከባዕድ ሕዝብ ሁሉ ራሳቸውን ለዩ፤ ቆመውም ኀጢአታቸውንና የአባቶቻቸውን ኀጢአት ተናዘዙ። በየስፍራቸውም ቆመው የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን የሕግ መጽሐፍ አነበቡ፤ ለእግዚአብሔርም ተናዘዙ፤ ለአምላካቸውም ለእግዚአብሔር ሰገዱ። ሌዋውያኑም ኢያሱና የቀድምኤል ልጆች፥ የሰራብያ ልጅ ሴኬንያ፥ የከናኒ ልጆችም በደረጃዎች ላይ ቆመው ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር በታላቅ ድምፅ ጮኹ። ሌዋውያኑም ኢያሱና ቀድምኤል፥ እንዲህ አሉ፥ “ቆማችሁ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም አምላካችንን እግዚአብሔርን አመስግኑ። የከበረ ስሙንም አመስግኑ፤ በበረከትና በምስጋናም ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ አድርጉት።” ዕዝራም እንዲህ አለ፥ “አንተ ብቻ እግዚአብሔር ነህ፤ ሰማዩንና የሰማያት ሰማይን፥ ሠራዊታቸውንም ሁሉ፥ ምድርንና በእርስዋ ላይ ያሉትን ሁሉ፥ ባሕሮቹንና በእነርሱ ውስጥ ያለውን ሁሉ ፈጥረሃል፤ ሁሉንም ሕያው አድርገኸዋል፤ የሰማዩም ሠራዊት ለአንተ ይሰግዳሉ። አንተ እግዚአብሔር አምላክ ነህ፤ አብራምን መረጥህ፤ ከዑር ከላውዴዎንም አወጣኸው፤ ስሙንም አብርሃም አልኸው፤ ልቡም በፊትህ የታመነ ሆኖ አገኘኸው፤ የከነዓናዊውንና የኬጤዎናዊውን፥ የአሞሬዎናዊውንም፥ የፌርዜዎናዊውንም፥ የኢያቡሴዎናዊውንም፥ የጌርጌሴዎናዊውንም ምድር ለእርሱና ለዘሩ ትሰጥ ዘንድ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረግህ፤ አንተም ጻድቅ ነህና ቃልህን አጸናህ። “በግብጽም ሳሉ የአባቶቻችንን መከራ አየህ፤ በኤርትራ ባሕርም ሳሉ ጩኸታቸውን ሰማህ፤ እንደ ታበዩባቸውም ዐውቀህ ነበርና በፈርዖንና በባሪያዎቹ ሁሉ፥ በምድሩም ሕዝብ ሁሉ ላይ ምልክትንና ተአምራትን አሳየህ፤ ዛሬም እንደ ሆነው ስምህን አስጠራህ። ከፊታቸውም ባሕሩን ከፈልህ፤ በባሕሩም መካከል በደረቅ ዐለፉ፤ የተከተሉአቸውን ግን ድንጋይ በጥልቅ ውኃ እንዲጣል በቀላይ ውስጥ ጣልሃቸው። የሚሄዱበትንም መንገድ ታበራላቸው ዘንድ ቀን በደመና ዐምድ፥ ሌሊትም በእሳት ዐምድ መራሃቸው። ወደ ሲናም ተራራ ወረድህ፤ ከሰማይም ተናገርሃቸው፤ ቅኑን ፍርድና እውነቱን ሕግ፥ መልካሙንም ሥርዐትና ትእዛዝ ሰጠሃቸው፤ የተቀደሰውንም ሰንበትህን አስታወቅሃቸው፤ ትእዛዝንና ሥርዐትን፥ ሕግንም በባሪያህ በሙሴ እጅ አዘዝሃቸው። ለራባቸውም ከሰማይ እንጀራን ሰጠሃቸው፤ ለጥማታቸውም ከዓለቱ ውኃን አወጣህላቸው፤ ትሰጣቸውም ዘንድ እጅህን የዘረጋህባትን ምድር ገብተው ይወርሷት ዘንድ አዘዝሃቸው። “ነገር ግን እነርሱና አባቶቻችን ታበዩ፤ አንገታቸውንም አደነደኑ፤ ትእዛዝህንም አልሰሙም፥ ለመስማትም እንቢ አሉ፤ ያደረግህላቸውንም ተአምራት አላሰቡም፤ አንገታቸውንም አደነደኑ፤ ለባርነታቸውም ወደ ግብፅ ይመለሱ ዘንድ አለቃን ሾሙ፤ አንተ ግን መሓሪና ይቅር ባይ አምላክ፥ ለቍጣም የምትዘገይ፥ ምሕረትንም የምታበዛ ነህ፤ አልተውሃቸውም። ዳግመኛም ቀልጦ የተሠራውን እንቦሳ አድርገው፦ ‘ከግብፅ ያወጡን አምላኮቻችን እሊህ ናቸው’ አሉ፤ እጅግም አስቈጡህ፤ አንተ ግን ምሕረትህ ብዙ ነውና በምድረ በዳ አልተውሃቸውም፤ በመንገድም ይመራቸው ዘንድ የደመና ዓምድን በቀን፥ የሚሄዱበትንም መንገድ ያበራላቸው ዘንድ የእሳት ዓምድን በሌሊት ከእነርሱ አላራቅህም። ያስተምራቸውም ዘንድ መልካሙን መንፈስህን ሰጠሃቸው፤ መናህንም ከአፋቸው አልከለከልህም፤ ለጥማታቸውም ውኃን ሰጠሃቸው። አርባ ዓመትም በምድረ በዳ መገብሃቸው፤ ምንም አላሳጣሃቸውም፤ ልብሳቸውም አላረጀም፤ እግራቸውም አላበጠም። “መንግሥታትንና አሕዛብን ዕድል ፈንታ አድርገህ ሰጠሃቸው፤ የሐሴቦንን ንጉሥ የሴዎንን ምድር፥ የባሳንንም ንጉሥ የዐግን ምድር ወረሱ። ልጆቻቸውንም እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛህ፤ ለአባቶቻቸውም ወደ ተናገርህላቸው ምድር አገባሃቸው። እነርሱም ወረሱአት፤ በከነዓን ምድር የሚኖሩትንም ሰዎች በፊታቸው አጠፋሃቸው፤ የሚወድዱትንም ነገር ያደርጉባቸው ዘንድ እነርሱንና ነገሥታቶቻቸውን፥ የምድሩንም አሕዛብ በእጃቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው። ምሽጎቹንም ከተሞች፥ መልካምን ነገር የሞሉትን ቤቶች፥ የተማሱትንም ጕድጓዶች፥ የወይኖቹንና የወይራዎቹን ቦታዎች፥ ብዙዎቹንም የፍሬ ዛፎች ወረሱ፤ በሉም፤ ጠገቡም፤ ወፈሩም፤ በታላቅ በጎነትህም ደስ አላቸው። “ነገር ግን ተመልሰው ዐመፁብህ፤ ሕግህንም ወደ ኋላቸው ጣሉት፤ ወደ አንተም ይመለሱ ዘንድ የመሰከሩባቸውን ነቢያትህን ገደሉ፤ እጅግም አስቈጡህ። ስለዚህ በሚያሠቃዩአቸው ሰዎች እጅ አሳልፈህ ሰጠሃቸው፤ አስጨነቋቸውም፤ በመከራቸውም ጊዜ ወደ አንተ ጮኹ፤ ከሰማይም ሰማሃቸው፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት ታዳጊዎችን ሰጠሃቸው፤ ከሚያሠቃዩአቸውም እጅ አዳንሃቸው። ባረፉም ጊዜ ተመልሰው በፊትህ ክፉ አደረጉ፤ በጠላቶቻቸውም እጅ ተውሃቸው፤ ገዙአቸውም፤ ተመልሰውም ወደ አንተ በጮኹ ጊዜ ከሰማይ ሰማሃቸው፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት ታደግሃቸው፤ ወደ ሕግህም ትመልሳቸው ዘንድ አስመሰከርህባቸው፤ ነገር ግን አልሰሙህም፤ ሰውም ባደረገው ጊዜ በሕይወት የሚኖርበትን ትእዛዝህንና ፍርድህን ተላለፉ፤ ጀርባቸውን ሰጡ፤ አንገታቸውንም አደነደኑ፤ አልሰሙምም። ነገር ግን ብዙ ዓመታት ታገሥሃቸው፤ በነቢያትህም እጅ በመንፈስህ መሰከርህባቸው፤ አላደመጡም፤ ስለዚህም በምድር አሕዛብ እጅ አሳልፈህ ሰጠሃቸው። ነገር ግን አንተ ኀያል፥ ቸርና መሓሪ አምላክ ነህና በምሕረትህ ብዛት ፈጽመህ አላጠፋሃቸውም፤ አልተውሃቸውምም። “አሁንም አምላካችን ሆይ፥ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና ኀያል ጽኑዕና የተፈራኸው አምላክ ሆይ፥ ከአሦር ነገሥታት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ በእኛና በነገሥታቶቻችን፥ በአለቆቻችንም፥ በካህናቶቻችንም፥ በነቢያቶቻችንም፥ በአባቶቻችንም፥ በሕዝብህ ሁሉ ላይ የደረሰው መከራ ሁሉ በፊትህ ጥቂት መስሎ አይታይህ። በደረሰብንም ነገር ሁሉ አንተ ጻድቅ ነህ፤ አንተ እውነት አድርገሃልና፥ እኛም እጅግ በድለናልና። ነገሥታቶቻችን፥ አለቆቻችንም፥ ካህናቶቻችንም፥ አባቶቻችንም ሕግህን አልጠበቁም፤ ትእዛዝህንና የመሰከርህባቸውን ምስክርህንም አልሰሙም። በመንግሥትህም በሰጠሃቸው ታላቅ በጎነትህ፥ በፊታቸውም በሰጠሃቸው በሰፊውና በሰባው ምድር አልተገዙልህም፤ ከክፉም ሥራቸው አልተመለሱም። እነሆ፥ ዛሬ ባሪያዎች ነን፤ ፍሬዋንና በረከቷን ይበሉ ዘንድ ለአባቶቻችን በሰጠሃት ምድር እነሆ፥ በእርስዋ ባሪያዎች ነን፥ ስለ ኀጢአታችንም ለሾምህብን ነገሥታት በረከቷን ታበዛለች፤ ሰውነታችንንም ይገዛሉ፤ በእንስሶቻችንም የሚወድዱትን ያደርጋሉ፤ እኛም በጽኑ መከራ ላይ ነን።
ነህምያ 9:1-37 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚያ ወር ሃያ አራተኛ ቀን እስራኤላውያን ጾመው፣ ማቅ ለብሰው፣ በራሳቸው ላይ ትቢያ ነስንሰው በአንድነት ተሰበሰቡ። የእስራኤላውያን ዘር የሆኑትም ራሳቸውን ከባዕዳን ሁሉ ለዩ። ቆመውም ኀጢአታቸውንና የአባቶቻቸውን በደል ተናዘዙ። በያሉበትም ቦታ ቆመው ከአምላካቸው ከእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ሩብ ቀን አነበቡ፤ የቀረውን ሩብ ቀን ደግሞ ንስሓ በመግባትና ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር በመስገድ አሳለፉ። ሌዋውያኑ ኢያሱ፣ ባኒ፣ ቀድምኤል፣ ሰበንያ፣ ቡኒ፣ ሰራብያ፣ ባኒ፣ ክናኒ፣ በመውጫ ደረጃዎች ላይ ቆሙ፤ ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔርም በታላቅ ድምፅ ጮኹ። ሌዋውያኑ ኢያሱ፣ ቀድምኤል፣ ባኒ፣ አሰበንያ፣ ሰራብያ፣ ሆዲያ፣ ሰበንያና ፈታያ፣ “ተነሥታችሁ ቁሙ፤ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የሚኖረውን አምላካችሁን እግዚአብሔርን ወድሱ” አሉ። “ክቡር ስምህ የተመሰገነ ይሁን፤ ከምስጋና ሁሉና ከውዳሴም በላይ ከፍ ከፍ ይበል። አንተ ብቻ እግዚአብሔር ነህ። ሰማያትን፣ ከሰማያት በላይ ያሉትን ሰማያትና የከዋክብታቸውን ሰራዊት ሁሉ፣ ምድርንና በላይዋ ያለውን ሁሉ፣ ባሕሮችንና በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ ፈጥረሃል። ለሁሉም ሕይወትን ትሰጣለህ፤ የሰማይ ሰራዊትም ይሰግዱልሃል። “አብራምን የመረጥኸውና ከከለዳውያን ዑር አውጥተህ አብርሃም የሚል ስም የሰጠኸው አንተ እግዚአብሔር አምላክ ነህ። ልቡ ለአንተ የታመነ ሆኖ ስላገኘኸውም፣ የከነዓናውያንን የኬጢያውያንን፣ የአሞራውያንን፣ የፌርዛውያንን፣ የኢያቡሳውያንንና የጌርጌሳውያንን ምድር ለዘሮቹ ለመስጠት ከርሱ ጋራ ቃል ኪዳን ገባህ፤ ጻድቅ ስለ ሆንህም የሰጠኸውን ተስፋ ጠበቅህ። “አንተ በግብጽ የአባቶቻችንን ሥቃይ አየህ፤ በቀይ ባሕርም ጩኸታቸውን ሰማህ። ታምራታዊ ምልክቶችንና ድንቆችን በፈርዖንና፣ በሹማምቱ ሁሉ፣ በምድሩም ሕዝብ ሁሉ ላይ ላክህ፤ ይህንም ያደረግኸው ግብጻውያን እንዴት በእብሪት እንዳስጨነቋቸው ስላወቅህ ነው። እስከ ዛሬም የሚጠራ ስም ለራስህ እንዲኖርህ አደረግህ። በደረቅ ምድር እንዲሻገሩ ባሕሩን በፊታቸው ከፈልህ፤ ያሳደዷቸውን ግን በኀይለኛ ውሃ ውስጥ እንደሚጣል ድንጋይ ወደ ጥልቁ ውስጥ ወረወርሃቸው። ቀን በደመና ዐምድ፣ በሚሄዱበት መንገድ ታበራላቸውም ዘንድ ሌሊት በእሳት ዐምድ መራሃቸው። “በሲና ተራራ ላይ ወረድህ፤ ከሰማይም ተናገርሃቸው። ትክክለኛ ደንቦችንና እውነተኛ ሕጎችን፣ መልካም ሥርዐቶችንና ትእዛዞችን ሰጠሃቸው። የተቀደሰች ሰንበትህን አስታወቅሃቸው፤ ትእዛዞችን፣ ሥርዐቶችንና ሕጎችን በባሪያህ በሙሴ አማካይነት ሰጠሃቸው። በተራቡ ጊዜ ከሰማይ መና ሰጠሃቸው፤ በተጠሙም ጊዜ ከዐለት ውሃ አፈለቅህላቸው፤ ልትሰጣቸው በተዘረጋች እጅ ወደማልህላቸውም ምድር ገብተው እንዲወርሱ አዘዝሃቸው። “እነርሱና አባቶቻችን ግን ትምክሕተኞችና ዐንገተ ደንዳኖች ሆኑ፤ ትእዛዞችህንም አልፈጸሙም። ለመስማት አልፈለጉም፤ በመካከላቸውም ያደረግሃቸውን ታምራት ማስታወስ አልቻሉም። ዐንገታቸውን አደነደኑ፤ በዐመፃቸውም ወደ ባርነታቸው ለመመለስ መሪ ሾሙ። አንተ ግን ይቅር ባይ አምላክ፣ ቸርና ርኅሩኅ፣ ለቍጣም የዘገየህና ምሕረትህ የበዛ ነህ። ስለዚህ አልተውሃቸውም፤ የጥጃ ምስል ለራሳቸው አቅልጠው፣ ‘ከግብጽ ያወጣህ አምላክ ይህ ነው’ ባሉና አስጸያፊ የስድብ ቃል በተናገሩ ጊዜ እንኳ አልተለየሃቸውም። “ከርኅራኄህ ብዛት የተነሣ በምድረ በዳ አልተውሃቸውም፤ ቀን የደመናው ዐምድ በመንገዳቸው ላይ መምራቱን፣ ሌሊትም የእሳቱ ዐምድ በሚሄዱበት ላይ ማብራቱን አላቆመም። ያስተምራቸው ዘንድ ቸር መንፈስህን ሰጠሃቸው፤ መናውን ከአፋቸው አልከለከልህም፤ በተጠሙ ጊዜ ውሃ ሰጠሃቸው። በምድረ በዳ አርባ ዓመት መገብሃቸው፤ ምንም ያጡት አልነበረም፤ ልብሳቸው አላለቀም፤ እግራቸውም አላበጠም። “በሩቅ የሚገኙትን ድንበሮች እንኳ ሳይቀር፣ መንግሥታትንና አሕዛብን ሰጠሃቸው። የሐሴቦን ንጉሥ የሴዎንን ምድር፣ የባሳን ንጉሥ የዐግን ምድር ወረሱ። ወንዶች ልጆቻቸውን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛሃቸው፤ አባቶቻቸው ገብተው እንዲወርሱ ወዳዘዝሃቸውም ምድር አገባሃቸው። በምድሪቱ ወንዶች ልጆቻቸው ገቡባት፤ ወረሷትም። በምድሪቱ ላይ ይኖሩ የነበሩትን ከነዓናውያን በፊታቸው አንበረከክህ፤ ያሻቸውን ያደርጉባቸው ዘንድ ከነዓናውያንን ከንጉሦቻቸውና ከምድሪቱ ሕዝቦች ጋራ በእጃቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው። የተመሸጉ ከተሞቻቸውንና የሠባውን ምድር ያዙ፤ በመልካም ነገር ሁሉ የተሞሉ ቤቶቻቸውን፣ የተቈፈሩ የውሃ ጕድጓዶቻቸውን፣ የወይን ተክላቸውን፣ የወይራ ዛፎቻቸውንና ስፍር ቍጥር የሌላቸውን የፍሬ ዛፎች ያዙ። እስኪጠግቡ በሉ፤ ወፈሩም፤ በታላቅ በጎነትህም ደስ ተሠኙ። “ነገር ግን እንቢተኞች ሆኑ፤ ዐመፁብህም፤ ሕግህንም አሽቀንጥረው ጣሉ፤ ወደ አንተ እንዲመለሱ ሲያስጠነቅቋቸው የነበሩት ነቢያትህን ገደሉ፤ አስጸያፊ የስድብ ቃልም ተናገሩ። ስለዚህ ላስጨነቋቸው ጠላቶቻቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው። በተጨነቁ ጊዜ ግን ወደ አንተ ጮኹ፤ አንተም ከሰማይ ሰማሃቸው፤ ከርኅራኄህም ብዛት የተነሣ ከጠላቶቻቸው እጅ የሚያድኗቸውን ታዳጊዎች ሰጠሃቸው። “ነገር ግን ዕረፍት ባገኙ ጊዜ፣ በፊትህ ክፉውን ነገር እንደ ገና ፈጸሙ፤ ከዚያም ይገዟቸው ዘንድ በጠላቶቻቸው እጅ ጣልሃቸው፤ እንደ ገና ወደ አንተ በጮኹ ጊዜ፣ ከሰማይ ሰማህ፤ በርኅራኄህም በየጊዜው ታደግሃቸው። “ወደ ሕግህ እንዲመለሱ አስጠነቀቅሃቸው፤ እነርሱ ግን እብሪተኞች ሆኑ። ትእዛዞችህንም አልፈጸሙም፤ ‘አንድ ሰው ቢፈጽማቸው በሕይወት የሚኖርባቸውን’ ሥርዐቶችህን ተላለፉ። እንቢተኞች ሆነው ጀርባቸውን አዞሩብህ፤ ዐንገታቸውን አደነደኑ፤ መስማትም አልፈለጉም። ብዙ ዘመን ታገሥሃቸው፤ በነቢያትህ አማካይነት በመንፈስህ አስጠነቀቅሃቸው። ነገር ግን አላደመጡህም፤ ከዚህም የተነሣ ጎረቤቶቻቸው ለሆኑ አሕዛብ አሳልፈህ ሰጠሃቸው። አንተ ግን ቸርና መሓሪ አምላክ ነህና ከምሕረትህ ብዛት የተነሣ፣ ፈጽመህ አላጠፋሃቸውም፤ አልተውሃቸውምም። “አሁንም አምላካችን ሆይ፤ ቃል ኪዳንህንና ዘላለማዊ ፍቅርህን የምትጠብቅ ታላቅ፣ ኀያልና የተፈራህ አምላክ ሆይ፤ ከአሦር ነገሥታት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእኛ፣ በነገሥታታችንና በመሪዎቻችን፣ በካህናታችንና በነቢያታችን፣ በአባቶቻችንና በመላው ሕዝብህ ላይ የደረሰው ይህ ሁሉ መከራ በፊትህ እንደ ቀላል ነገር አይታይ። በደረሰብን ሁሉ አንተ ጻድቅ ነህ፤ እኛ በደለኞች ነን፤ አንተ ግን ትክክለኛውን አደረግህ። ነገሥታታችን፣ መሪዎቻችን፣ ካህናታችንና አባቶቻችን ሕግህን አልጠበቁም፤ ትእዛዞችህን ወይም የሰጠሃቸውን ማስጠንቀቂያዎች አልሰሙም። በገዛ መንግሥታቸው፣ በሰጠሃቸው ታላቅ በጎነትህና በፊታቸውም ባዘጋጀህላቸው ሰፊና ለም ምድር እንኳ፣ አንተን አላገለገሉም፤ ከክፉ መንገዳቸውም አልተመለሱም። “እነሆ፤ ዛሬም ባሮች ነን፤ አባቶቻችን ፍሬዋንና በረከቷን እንዲበሉ በሰጠሃቸው ምድር ባሮች ነን። ከኀጢአታችን የተነሣ የተትረፈረፈው መከር ሲሳይ የሆነው በላያችን ላስቀመጥሃቸው ነገሥታት ነው፤ እነርሱም ደስ እንዳሰኛቸው በሰውነታችንና በቀንድ ከብቶቻችን ላይ ያዝዛሉ። እኛም በታላቅ ጭንቀት ውስጥ እንገኛለን።
ነህምያ 9:1-37 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዚህም ወር በሀያ አራተኛው ቀን የእስራኤል ልጆች ጾመው፥ ማቅም ለብሰው፥ በላያቸውም ትቢያ ነስንሰው ተከማቹ። የእስራኤልም ዘር ከእንግዶች ሁሉ ራሳቸውን ለዩ፥ ቆመውም ኃጢአታቸውንና የአባቶቻቸውን ኃጢአት ተናዘዙ። በየስፍራቸውም ቆመው የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን የሕግ መጽሐፍ የቀን ሩብ ያህል አነበቡ ሦስት የቀን ሩብም ያህል ተናዘዙ፥ ለአምላካቸው ለእግዚአብሔርም ሰገዱ። ሌዋውያኑም ኢያሱና ባኒ፥ ቀድምኤል፥ ሰበንያ፥ ቡኒ፥ ሰራብያ፥ ባኒ፥ ክናኒ በደረጃዎች ላይ ቆመው ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር በታላቅ ድምፅ ጮኹ። ሌዋውያኑም ኢያሱ፥ ቀድምኤል፥ ባኒ፥ አሰበንያ፥ ሰራብያ፥ ሆዲያ፥ ሰበንያ፥ ፈታያ እንዲህ አሉ፦ ቆማችሁ ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላካችንን እግዚአብሔርን ባርኩ። እንዲህም በሉ፦ በበረከትና በምስጋና ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያለው ክቡር ስምህ ይባረክ። አንተ ብቻ እግዚአብሔር ነህ፥ ሰማዩንና የሰማያት ሰማይን ሠራዊታቸውንም ሁሉ፥ ምድሩንና በእርስዋ ላይ ያሉትን ሁሉ፥ ባሕሮቹንና በእነርሱ ውስጥ ያለውን ሁሉ፥ ፈጥረሃል፥ ሁሉንም ሕያው አድርገኸዋል፥ የሰማዩም ሠራዊት ለአንተ ይሰግዳሉ። አንተ እግዚአብሔር አምላክ ነህ፥ አብራምን መረጥህ፥ ከዑር ከላውዴዎንም አወጣኸው፥ ስሙንም አብርሃም አልኸው፥ ልቡም በፊትህ የታመነ ሆኖ አገኘኸው፥ የከነዓናዊውንና የኬጢያዊውን የአሞራዊውንም የፌርዛዊውንም የኢያቡሳዊውንም የጌርጌሳዊውንም ምድር ለእርሱና ለዘሩ ትሰጥ ዘንድ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረግህ፥ አንተም ጻድቅ ነህና ቃልህን ፈጸምህ። በግብጽም ሳሉ የአባታችንን መከራ አየህ፥ በኤርትራ ባሕርም ሳሉ ጩኸታቸውን ሰማህ፥ እንደ ታበዩባቸውም አውቀህ ነበርና በፈርዖንና በባሪያዎቹ ሁሉ በምድሩም ሕዝብ ሁሉ ላይ ምልክትና ተአምራት አሳየህ፥ ዛሬም እንደ ሆነው ስምህን አስጠራህ። ከፊታቸውም ባሕሩን ከፈልህ፥ በባሕሩም መካከል በደረቅ አለፉ፥ ጠላቶቻቸውን ግን ድንጋይ ለጥልቅ ውኃ እንዲጣል በቀላይ ውስጥ ጣልሃቸው። የሚሄዱበትንም መንገድ ታበራላቸው ዘንድ በቀን በደመና ዓምድ፥ በሌሊትም በእሳት ዓምድ መራሃቸው። ወደ ሲናም ተራራ ወረድህ፥ ከሰማይም ተናገርሃቸው፥ ቅኑን ፍርድና እውነቱን ሕግ መልካሙንም ሥርዓትና ትእዛዝ ሰጠሃቸው፥ የተቀደሰውንም ሰንበትህን አስታወቅሃቸው፥ ትእዛዝንና ሥርዓትን ሕግንም በባሪያህ በሙሴ እጅ አዘዝሃቸው። ለራባቸውም ከሰማይ እንጀራ ሰጠሃቸው፥ ለጥማታቸውም ከዓለቱ ውኃ አመጣህላቸው፥ ወደ ማልህላቸውም ምድር ገብተው ይወርሱ ዘንድ አዘዝሃቸው። ነገር ግን እነርሱና አባቶቻችን ታበዩ፥ አንገታቸውንም አደነደኑ፥ ትእዛዝህንም አልሰሙም፥ ለመስማትም እንቢ አሉ፥ ያደረግህላቸውንም ተአምራት አላሰቡም፥ አንገታቸውንም አደነደኑ፥ በዓመፃቸውም ወደ ባርነታቸው ይመለሱ ዘንድ አለቃ አደረጉ፥ አንተ ግን ይቅር ባይ፥ ቸርና መሐሪ አምላክ፥ ለቁጣም የምትዘገይ፥ ምሕረትንም የምታበዛ ነህ፥ አልተውሃቸውም። ቀልጦ የተሠራውንም እምቦሳ አድርገው፦ ከግብጽ ያወጣህ አምላክህ ይህ ነው ባሉ ጊዜ፥ እጅግም ባስቈጡህ ጊዜ፥ አንተ በምሕረትህ ብዛት በምድረ በዳ አልተውሃቸውም፥ በመንገድም ይመራቸው ዘንድ የደመና ዓምድ በቀን፥ የሚሄዱበትንም መንገድ ያበራላቸው ዝነድ የእሳት ዓምድ በሌሊት ከእነርሱ አልራቀም። ያስተምራቸውም ዘንድ መልካሙን መንፈስህን ሰጠሃቸው፥ መናህንም ከአፋቸው አልከለከልህም፥ ለጥማታቸውም ውኃ ሰጠሃቸው። አርባ ዓመትም በምድረ በዳ መገብሃቸው፥ ምንም አላጡም፥ ልብሳቸውም አላረጀም፥ እግራቸውም አላበጠም። መንግሥታትንና አሕዛብን ከፍለህ ሰጠሃቸው፥ የሐሴቦንን ንጉሥ የሴዎንን ምድር፥ የባሳንንም ንጉሥ የዐግን ምድር ወረሱ። ልጆቻቸውንም እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛህ፥ ይገቡና ይወርሱ ዘንድ ለአባቶቻቸው ወደ ተናገርህላቸውም ምድር አገባሃቸው። ልጆቹም ገብተው ምድሩን ወረሱ፥ የምድሩን ሰዎች ከነዓናውያንን በፊታቸው አዋረድህ፥ የሚወድዱትንም ነገር ያደረጉባቸው ዘንድ እነርሱንና ነገሥታቶቻቸውን የምድሩንም አሕዛብ በእጃቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው። ምሽጎቹንም ከተሞች የሰባውንም ምድር ወሰዱ፥ መልካሙን ነገር የሞሉትን ቤቶች፥ የተማሱትንም ጕድጓዶች፥ ወይኖቹንና ወይራዎቹን ብዙዎቹንም የፍሬ ዛፎች ወረሱ፥ በሉም፥ ጠገቡም፥ ወፈሩም፥ በታላቅ በጎነትህም ደስ አላቸው። ነገር ግን እንቢተኞች ነበሩ፥ ዐመፁብህም፥ ሕግህንም ወደ ኋላቸው ጣሉት፥ ወደ አንተም ይመለሱ ዘንድ የመሰከሩባቸውን ነቢያትህን ገደሉ፥ እጅግም አስቈጡህ። ስለዚህ ለጠላቶቻቸው እጅ አሳልፈህ ሰጠሃቸው፥ አስጨነቁአቸውም፥ በመከራቸውም ጊዜ ወደ አንተ ጮኹ፥ ከሰማይም ሰማሃቸው፥ እንደ ምሕረትህም ብዛት ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳኑአቸውን ታዳጊዎችን ሰጠሃቸው። ባረፉም ጊዜ ተመልሰው በፊትህ ክፉ አደረጉ፥ በጠላቶቻቸው እጅ ተውሃቸው፥ ገዙአቸውም፥ ተመልሰውም ወደ አንተ በጮኹ ጊዜ ከሰማይ ሰማሃቸው፥ እንደ ምሕረትህም ብዛት ታደግሃቸው፥ ወደ ሕግህም ትመልሳቸው ዘንድ አስመሰከርህባቸው፥ ነገር ግን ታበዩ፥ ትእዛዝህንም አልሰሙም፥ ሰውም ባደረገው ጊዜ በሕይወት የሚኖርበትን ፍርድህን ተላለፉ፥ ትከሻቸውንም ሰጡ፥ አንገታቸውን አደነደኑ፥ አልሰሙምም። ነገር ግን ብዙ ዓመታት ታገሥሃቸው፥ በነቢያትህም እጅ በመንፈስህ መሰከርህባቸው፥ አላደመጡም፥ ስለዚህም በምድር አሕዛብ እጅ አሳልፈህ ሰጠሃቸው። ነገር ግን አንተ ቸርና መሐሪ አምላክ ነህና በምሕረትህ ብዛት ፈጽመህ አላጠፋሃቸውም፥ አልተውሃቸውምም። አሁንም አምላካችን ሆይ፥ ቃል ኪዳንና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና ኃያል የተፈራኸውም አምላክ ሆይ፥ ከአሦር ነገሥታት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእኛና በነገሥታቶቻችን በአለቆቻችንም በካህናቶቻችንም በነቢያቶቻችንም በአባቶቻችንም በሕዝብህ ሁሉ ላይ የደረሰው መከራ ሁሉ በፊትህ ጥቂት መስሎ አይታይህ። በደረሰብንም ነገር ሁሉ አንተ ጻድቅ ነህ፥ አንተ እውነት አድርገሃልና፥ እኛም ኃጢአት አድርገናል። ነገሥታቶቻችንም አለቆቻችንም ካህናቶቻችንም አባቶቻችንም ሕግህን አልጠበቁም፥ የመሰከርህባቸውንም ትእዛዝህንና ምስክርህን አልሰሙህም። በመንግሥታቸውም በሰጠሃቸውም ታላቅ በጎነትህ፥ በፊታቸውም በሰጠኸው በሰባው ምድር አላመለኩህም፥ ከክፉም ሥራቸው አልተመለሱም። እነሆ፥ ዛሬ ባሪያዎች ነን፥ ፍሬዋንና በረከትዋን ይበሉ ዘንድ ለአባቶቻችን በሰጠሃት ምድር፥ እነሆ፥ በእርስዋ ባሪያዎች ነን፥ ስለ ኃጢአታችንም ለሾምህብን ነገሥታት በረከትዋን ታበዛለች፥ ሰውነታችንንም ይገዛሉ፥ በእንስሶቻችንም የሚወድዱትን ያደርጋሉ፥ እኛም በጽኑ መከራ ላይ ነን።
ነህምያ 9:1-37 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚሁ ወር በሃያ አራተኛው ቀን የእስራኤል ሕዝብ በአንድነት ተሰበሰቡ፤ ስለ ኃጢአታቸው መጸጸታቸውንና ማዘናቸውን ለመግለጥም ማቅ ለብሰው፥ በራሳቸው ላይ ትቢያ ነስንሰው ጾሙ፤ ራሳቸውንም ከባዕዳን ሕዝቦች ሁሉ ለዩ፤ ከዚህም በኋላ ሁሉም ተነሥተው በመቆም፥ እነርሱና የቀድሞ አባቶቻቸው የሠሩትን ኃጢአት ሁሉ ተናዘዙ። እዚያው እንደ ቆሙም፥ የአምላካቸው የእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ሦስት ሰዓት ሙሉ ተነበበላቸው፤ ሌላም ሦስት ሰዓት ኃጢአታቸውን በመናዘዝ፥ ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር ሰገዱ። ለሌዋውያኑ መቆሚያ መድረክ ነበር፤ በዚያም ላይ ኢያሱ፥ ባኒ፥ ቃድሚኤል፥ ሸባንያ፥ ቡኒ፥ ሼሬብያ፥ ባኒና ከናኒ በመቆም፥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር ጸለዩ። ኢያሱ፥ ቃድሚኤል፥ ባኒ፥ ሐሸባንያ፥ ሼሬብያ፥ ሆዲያ፥ ሸባንያና ፐታሕያ ተብለው የሚጠሩት ሌዋውያን፦ “ተነሥታችሁ በመቆም ዘለዓለማዊውን አምላካችሁን እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ከምስጋናና ከበረከት ሁሉ በላይ፥ ከፍ ከፍ ይበል! በሉ” አሉአቸው። ከዚህም ሁሉ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ሲሉ ጸለዩ፦ “እግዚአብሔር ሆይ፥ አምላክ አንተ ብቻ ነህ፤ ሰማያትን፥ የሰማያትንም ሰማያት ከነሠራዊታቸው፥ ምድርንና በእርስዋም ላይ የሚገኘውን ሁሉ፥ ባሕሮችንና በእነርሱም ውስጥ የሚገኙትን ሁሉ፥ ፈጠርክ፤ ለሁሉም ሕይወትን ሰጠሃቸው፤ የሰማይ ሠራዊት ይሰግዱልሃል። የባቢሎን ክፍል ከሆነችው ዑር፥ አብራምን መርጠህ ያመጣኸው፥ ስሙንም አብርሃም ያልከው፥ አንተ እግዚአብሔር አምላክ ነህ። እርሱም ለአንተ ታማኝ እንደ ሆነ ተመልክተህ፥ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳንን አደረግህ፤ ከነዓናውያን፥ ሒታውያን፥ አሞራውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ኢያቡሳውያንና ጌርጌሳውያን የሚኖሩባትንም የከነዓንን ምድር ለዘሮቹ መኖሪያ ርስት አድርገህ ልትሰጠው ቃል ገባህለት፤ አንተ ታማኝ ስለ ሆንክ ቃል ኪዳንህን አጽንተህ ጠብቀሃል። “አንተ የቀድሞ አባቶቻችን በግብጽ የደረሰባቸውን መከራ አየህ፤ ቀይ ባሕር አጠገብ ሆነው እንድትረዳቸው ያቀረቡትን ልመና ሰማህ። በግብጽ ንጉሥ ላይ በባለሥልጣኖቹና በምድሩ በሚኖሩትም ሕዝብ ሁሉ ላይ ድንቅ ተአምራትን ገልጠህ አሳየህ። ይህንንም ያደረግኸው የቀድሞ አባቶቻችን እንዴት እንደሚጨቈኑ በማየትህ ነው፤ ይህንንም በማድረግህ እስከ ዛሬ ድረስ ዝናህ የገነነ ሆኖአል። ባሕሩን በፊታቸው ለሁለት ከፈልክ፤ በደረቅ ምድርም ተሻገሩ፤ ድንጋይ ወደ ጥልቅ ባሕር እንደሚጣል፥ እነርሱን ያሳድዱ የነበሩትንም ወደ ጥልቁ ጣልካቸው። በቀን በደመና ዐምድ መራሃቸው፤ በሌሊትም መንገዳቸውን በእሳት ዐምድ አበራህላቸው። ወደ ሲና ተራራ ወርደህ ከሰማይ ሕዝብህን አነጋገርካቸው፤ ትክክለኛና ፍትሓዊ ሕግንና ሥርዓትን፥ መልካም የሆኑትን ደንቦችንና ትእዛዞችን ሰጠሃቸው። የተቀደሰውን ሰንበትህንም እንዲያውቁ አደረግሃቸው፤ በአገልጋይህም በሙሴ አማካይነት ትእዛዞችህን፥ ድንጋጌህንና ሕጎችህን ሰጠሃቸው። “በተራቡም ጊዜ ምግብን ከሰማይ ሰጠሃቸው፤ በተጠሙም ጊዜ ውሃን ከአለት አፈለቅህላቸው፤ ለእነርሱ ልትሰጣቸው ቃል የገባህላቸውንም ምድር በቊጥጥራቸው ሥር ያደርጉ ዘንድ አዘዝካቸው። ነገር ግን የቀድሞ አባቶቻችን ትዕቢተኞችና እልኸኞች ሆኑ፤ ትእዛዞችህንም አልጠበቁም፤ ታዛዦችም አልሆኑም። በመካከላቸው ያደረግኸውን ተአምራት ሁሉ ረሱ፤ እልኸኞችም ሆነው፤ ወደ ግብጹ ባርነታቸው እንዲመልሳቸው መሪ መረጡ። አንተ ግን በፍቅር የተሞላህ፥ ለቊጣ የዘገየህ፥ ይቅር ባይ፥ ቸርና መሐሪ አምላክ በመሆንህ አልተውካቸውም። በጥጃ አምሳል ለራሳቸው ጣዖትን ሠርተው፥ ‘ከግብጽ ምድር መርቶ ያወጣን አምላክ ይህ ነው!’ አሉ፤ በአንተ ላይም ከፍተኛ የስድብን ቃል እንኳ ተናገሩ፤ ምሕረትህም ታላቅ በመሆኑ በዚያ ምድረ በዳ ይጠፉ ዘንድ አልተውካቸውም፤ ነገር ግን የደመናው ዐምድ በቀን ይመራቸው ነበር፤ የእሳቱ ዐምድ በሌሊት ያበራላቸው ነበር። የሚያስተምራቸውን ቸር መንፈስህን ሰጠሃቸው፤ የሚመገቡትን መና፥ የሚጠጡትንም ውሃ ሰጠሃቸው። አርባ ዓመት ሙሉ በበረሓ ረዳሃቸው፤ ከሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ ምንም አላሳጣሃቸውም፤ ልብሳቸው አላለቀም፤ እግራቸው አላበጠም። “የአሕዛብን መንግሥታትና ነገሥታትን ድል ነሥተው፥ ከምድራቸው አዋሳኞች የሆኑትን ጠረፎች እንዲይዙ አደረግህ፤ ሲሖን የተባለ ንጉሥ ይገዛት የነበረችውን ሐሴቦን ተብላ የምትጠራውን ምድር፥ በድል አድራጊነት ያዙ፤ ዖግ የተባለው ንጉሥ ይገዛት የነበረችውንም የባሳንን ምድር ወረሱ። ብዛታቸው እንደ ሰማይ ከዋክብት የሆኑ ልጆችን ሰጠሃቸው፥ ለቀድሞ አባቶቻቸው ትሰጣቸው ዘንድ ቃል የገባህላቸውን ምድር፥ በድል አድራጊነት እንዲይዙ ፈቀድክላቸው። ልጆቻቸው የከነዓንን ምድር ድል አድርገው ያዙ፤ በዚያ ይኖሩ የነበሩትንም ሕዝብ በፊታቸው ሆነህ አንተ ድል ነሣህላቸው፤ በነገሥታትና በዚያች የከነዓን አገር ሕዝብ ላይ የፈለጉትን ሁሉ ያደርጉባቸው ዘንድ ኀይልን ሰጠሃቸው። የተመሸጉ ከተሞችንና፥ ለም የሆነችውን ምድር፤ በመልካም ነገር ሁሉ የተሟሉ ቤቶችን፥ የውሃ ጒድጐዶችንና የወይን ተክል ቦታዎችን የወይራና ብዙ የፍሬ ዛፎችን ወረሱ፤ በልተው በመጥገብም ሰውነታቸውን አወፈሩ፤ በቸርነትህ በሰጠሃቸው መልካም ነገር ሁሉ ተደሰቱ። “ነገር ግን እነርሱ በአንተ ላይ ዐምፀው ለቃልህ አንታዘዝም አሉ፤ ሕግህንም ላለመስማት ፊታቸውን መለሱ፤ በማስጠንቀቅ ወደ አንተ እንዲመለሱ ያስተማሩአቸውን ነቢያትህን ገደሉ፤ በየጊዜውም በአንተ ላይ ክፉ የስድብ ቃል ተናገሩ፤ ስለዚህም ጠላቶቻቸው እነርሱን ድል አድርገው ይገዙአቸው ዘንድ አሳልፈህ ሰጠሃቸው፤ እነርሱም አስጨነቁአቸው። በችግራቸውም ጊዜ ወደ አንተ ጮኹ፤ አንተም በሰማይ ሆነህ ሰማሃቸው፤ ከምሕረትህ ታላቅነት የተነሣ፥ ከጠላቶቻቸው የሚታደጉ መሪዎችን ላክህላቸው። ነገር ግን ሰላም ባገኙ ጊዜ እንደገና ኃጢአት ሠሩ፤ አንተም እንደገና ድል ለሚነሡ ጠላቶቻቸው ተውካቸው እነርሱም ገዙአቸው፤ ነገር ግን አንተ እንድትረዳቸው እንደገና በጠየቁ ጊዜ በሰማይ ሆነህ ሰማሃቸው፤ ከርኅራኄህም የተነሣ በየጊዜው ታደግኻቸው። እነርሱም ወደ ሕግህ እንዲመለሱ አስጠነቀቅኻቸው፤ በትዕቢታቸው ግን ትእዛዞችህን ናቁ፤ ቢፈጽሙአቸው ሕይወት በሚሰጡት ሕጎችህ ላይ ኃጢአት ሠሩ። በልበ ደንዳናነት ፊታቸውን አዞሩ፤ በእልኸኛነታቸውም እምቢተኞች ሆኑ። አንተም ለብዙ ዓመቶች ታገሥካቸው፤ ያስተምሩአቸውም ዘንድ ነቢያትን በመንፈስህ አስነሣህላቸው፤ ነገር ግን እነርሱ አላዳመጡም፤ ስለዚህም ለጐረቤት ሕዝቦች ድል እንዲነሡአቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው። እንደገናም ከምሕረትህ ታላቅነት የተነሣ አልተውካቸውም፤ አንተ ቸርና ይቅር ባይ አምላክም ስለ ሆንክ አልደመሰስካቸውም። “ቃል ኪዳንህንና ዘለዓለማዊ ፍቅርህን የምትጠብቅ፥ ታላቁ፥ ኀያሉና አስፈሪው አምላካችን ሆይ! በእኛ፥ በንጉሦቻችን፥ በመሪዎቻችን፥ በካህኖቻችን፥ በነቢዮቻችን፥ በቅድመ አያቶቻችን፥ እንዲሁም በሕዝብህ ሁሉ ላይ፥ ከአሦር ነገሥታት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፥ የደረሰውን መከራ ሁሉ አስብ። እኛን ለመቅጣት ያደረግኸው ውሳኔ ትክክል ነው፤ እኛ በደል ብንሠራም፥ አንተ በታማኝነትህ እንደ ጸናህ ነህ። የቀድሞ አባቶቻችን፥ ንጉሦቻችን፥ መሪዎቻችንና ካህኖቻችን ሕግህን አልጠበቁም፤ የሰጠሃቸውን ትእዛዞች ማስጠንቀቂያዎች አላዳመጡም። መንግሥታቸው በሰጠሃቸው ቸርነት፥ በሰጠሃቸው ሰፊና ለም መሬት፥ ይደሰቱ በነበረ ጊዜ እንኳ፥ አንተን አላመለኩም፥ ከኃጢአታቸውም አልተመለሱም። ስለዚህም አንተ ለአባቶቻችን ፍሬዋን እንዲበሉና በመልካም ነገሮችም እንዲደሰቱ፥ በሰጠሃቸው ምድር ላይ እነሆ፥ ዛሬ እኛ ባሪያዎች ሆነናል። እኛም ኃጢአት በመሥራታችን ምክንያት ስላሳዘንክ፥ የምድሪቱንም በረከት በእኛ ላይ ገዢዎች አድርገህ ላስነሣሃቸው ነገሥታት ገቢ ይሆናል፤ እነርሱ በእኛና በእንስሶቻችን ላይ ደስ ያሰኛቸውን ነገር ሁሉ ይፈጽማሉ፤ ከዚህም የተነሣ፥ በታላቅ ጭንቀት ላይ እንገኛለን።”
ነህምያ 9:1-37 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚሁ ወር በሀያ አራተኛው ቀን የእስራኤል ልጆች ጾመው፥ ማቅም ለብሰውና በላያቸው ላይ ትቢያ ነስንሰው ተሰበሰቡ። የእስራኤል ዘር ከባዕድ ሕዝቦች ሁሉ ራሳቸውን ለዩ፥ ቆመውም ኃጢአታቸውንና የአባቶቻቸውን በደል ተናዘዙ። በየስፍራቸውም ቆመው የጌታ አምላካቸውን የሕግ መጽሐፍ የቀኑ ሩብ ያህል አነበቡ፥ የቀኑ ሩብ ደግሞ እየተናዘዙና፥ ለጌታ አምላካቸው እየሰገዱ አሳለፉ። በሌዋውያኑ መድረክ ላይ ኢያሱ፥ ባኒ፥ ቃድምኤል፥ ሽባንያ፥ ቡኒ፥ ሼሬብያ፥ ባኒ፥ ክናኒ ቆመው ወደ ጌታ አምላካቸው በታላቅ ድምፅ ጮኹ። ሌዋውያኑ ኢያሱ፥ ቃድምኤል፥ ባኒ፥ ሐሻብንያ፥ ሼሬብያ፥ ሆዲያ፥ ሽባንያ፥ ፕታሕያ እንዲህ አሉ፦ “ቁሙ፥ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ጌታ አምላካችሁን ባርኩ። ከበረከትና ከምስጋና ሁሉ በላይ ከፍ ያለው የክብርህን ስም ይባርኩ። አንተ ብቻህን ጌታ ነህ፥ ሰማይንና የሰማያት ሰማይን ሠራዊታቸውንም ሁሉ፥ ምድርንና በእርሷ ያሉትን ሁሉ፥ ባሕሮቹንና በእነርሱ ውስጥ ያለውን ሁሉ፥ ፈጠርህ፥ ለሁሉም ሕይወትን ሰጠሃቸው፤ የሰማይ ሠራዊት ለአንተ ይሰግዳሉ። አብራምን የመረጥህ፥ ከከለዳውያን ኡር የአወጣኸው፥ ስሙንም አብርሃም ያልኸው፥ አንተ ጌታ አምላክ ነህ። ልቡም በፊትህ ታማኝ ሆኖ አገኘኸው፥ የከነዓናዊውን፥ የኬጢያዊው፥ የአሞራዊውን፥ የፌርዛዊውን፥ የኢያቡሳዊውንና የጌርጌሳዊውን ምድር ለዘሩ ልትሰጥ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረግህ፥ አንተም ጻድቅ ነህና ቃልህን ፈጸምህ።” “በግብጽ የአባቶቻችንን መከራ አየህ፥ በቀይ ባሕርም ጩኸታቸውን ሰማህ፤ በፈርዖን፥ በአገልጋዮቹ ሁሉና በምድሩ ሕዝብ ሁሉ ላይ ምልክትና ተአምራት አሳየህ፤ በእነርሱ ላይ መታበያቸውን አውቀህ ነበርና፥ እስከ ዛሬም እንዳለው ለራስህ ስምን ሠራህ። በፊታቸውም ባሕሩን ከፈልህ፥ በባሕሩ መካከል በደረቅ ምድር ተሻገሩ፤ አሳዳጆቻቸውን ግን በኃይለኛ ውኃ እንደሚጣል ድንጋይ ወደ ጥልቁ ጣልካቸው። በሚሄዱበትን መንገድ ልታበራላቸው ቀን በደመና ዓምድ፥ ሌሊት ደግሞ በእሳት ዓምድ መራሃቸው። በሲና ተራራ ላይ ወረድህ፥ ከሰማይም ተናገርሃቸው፤ ቅን ፍርዶችን፥ ታማኝ ሕጎችን፥ መልካም ሥርዓቶችና ትእዛዞችን ሰጠሃቸው። ቅዱስ ሰንበትህን አስታወቅሃቸው፥ ትእዛዞችን፥ ሥርዓቶችንና ሕግን በባርያህ በሙሴ በኩል አዘዝሃቸው። ለረኃባቸው ከሰማይ ምግብ ሰጠሃቸው፥ ለጥማታቸውም ከዓለቱ ውኃ አፈለቅህላቸው፤ ልትሰጣቸው ወደ ማልክላቸው ምድር ገብተው እንዲወርሱ ነገርካቸው።” “እነርሱና አባቶቻችን ግን ታበዩ፥ አንገታቸውን አደነደኑ፥ ትእዛዞችህንም አልሰሙም፤ ለመስማትም እንቢ አሉ፥ በመካከላቸው ያደረግኸውን ተአምራት አላስታወሱም፤ አንገታቸውንም አደነደኑ፥ በዓመፃቸውም ወደ ባርነታቸው ለመመለስ መሪ ሾሙ፤ አንተ ግን ይቅር ባይ አምላክ፥ ቸር፥ ርኅሩኅ፥ ለቁጣ የዘገየህና ምሕረትህ የበዛ ነህ፥ አልተውካቸውምም።” ከቀለጠ ብረት የተቀረጸ ጥጃ ሠርተው “ከግብጽ ያወጣህ አምላክህ ይህ ነው” አሉ፥ ብዙ ተሳደቡ፥ አንተ ግን ከርኅራኄህ ብዛት በምድረ በዳ አልተውካቸውም፤ በመንገድ እንዲመራቸው የደመና ዓምድ በቀን፥ የሚሄዱበትንም መንገድ እንዲያበራላቸው የእሳት ዓምድ በሌሊት ከእነርሱ አልተለየም። እንዲያስተምራቸው መልካሟን መንፈስህን ሰጠሃቸው፥ መናህን ከአፋቸው አልከለከልክም፥ ለጥማታቸውም ውኃን ሰጠሃቸው። አርባ ዓመትም በምድረ በዳ መገብካቸው፤ ምንም አላጡም፤ ልብሳቸው አላረጀም፥ እግራቸውም አላበጠም። “መንግሥታትንና አሕዛብን ሰጠሃቸው፤ የሐሴቦንን ንጉሥ የሴዎንን ምድር፥ የባሳንንም ንጉሥ የዐግን ምድር ወረሱ። ልጆቻቸውን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛህ፥ እንዲገቡና እንዲወርሷት ለአባቶቻቸው ወደ ነገርሃቸው ምድር አገባሃቸው። ልጆቹም ገብተው ምድሪቷን ወረሱ፤ የምድሪቱን ሰዎች ከነዓናውያንን በፊታቸው ደመሰስካቸው፥ የወደዱትን ነገር እንዲያደረጉባቸው ከነገሥታቶቻቸውና ከምድሪቱ ሕዝቦች ጋር በእጃቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው። ምሽጎቹንም ከተሞች የሰባውንም ምድር ወሰዱ፥ መልካሙን ነገር የሞሉትን ቤቶች፥ የተማሱትንም ጉድጓዶች፥ ወይኖቹንና ወይራዎቹን ብዙዎቹንም የፍሬ ዛፎች ወረሱ፥ በሉም፥ ጠገቡም፥ ወፈሩም፥ በታላቅ በጎነትህም ደስ አላቸው።” “ነገር ግን እንቢተኞች ነበሩ፥ ዐመፁብህም፥ ሕግህንም ወደ ኋላቸው ጣሉት፥ ወደ አንተም ይመለሱ ዘንድ የመሰከሩባቸውን ነቢያትህን ገደሉ፥ እጅግም አስቆጡህ። ስለዚህ ለጠላቶቻቸው እጅ አሳልፈህ ሰጠሃቸው፥ አስጨነቁአቸውም፥ በመከራቸውም ጊዜ ወደ አንተ ጮኹ፥ ከሰማይም ሰማሃቸው፥ እንደ ምሕረትህም ብዛት ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳኑአቸውን ታዳጊዎችን ሰጠሃቸው። ባረፉም ጊዜ ተመልሰው በፊትህ ክፉ አደረጉ፥ በጠላቶቻቸው እጅ ተውካቸው፥ ገዙአቸውም፥ ተመልሰውም ወደ አንተ በጮኹ ጊዜ ከሰማይ ሰማሃቸው፥ እንደ ምሕረትህም ብዛት ታደግሃቸው፥ ወደ ሕግህም ትመልሳቸው ዘንድ አስመሰከርህባቸው፥ ነገር ግን ታበዩ፥ ትእዛዝህንም አልሰሙም፥ ሰውም ባደረገው ጊዜ በሕይወት የሚኖርበትን ፍርድህን ተላለፉ፥ ትከሻቸውንም ሰጡ፥ አንገታቸውን አደነደኑ፥ አልሰሙምም። ነገር ግን ብዙ ዓመታት ታገሥሃቸው፥ በነቢያትህም እጅ በመንፈስህ መሰከርክባቸው፥ አላደመጡም፥ ስለዚህም በምድር አሕዛብ እጅ አሳልፈህ ሰጠሃቸው። ነገር ግን አንተ ቸርና መሐሪ አምላክ ነህና በምሕረትህ ብዛት ፈጽመህ አላጠፋሃቸውም፥ አልተውካቸውምም። “አሁንም አምላካችን ሆይ፥ ቃል ኪዳንና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና ኃያል የተፈራኸውም አምላክ ሆይ፥ ከአሦር ነገሥታት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእኛና በነገሥታቶቻችን በአለቆቻችንም በካህናቶቻችንም በነብዮቻችንም በአባቶቻችንም በሕዝብህ ሁሉ ላይ የደረሰው መከራ ሁሉ በፊትህ ጥቂት መስሎ አይታይህ። በደረሰብንም ነገር ሁሉ አንተ ጻድቅ ነህ፥ አንተ እውነት አድርገሃልና፥ እኛም ኃጢአት አድርገናል። ነገሥታቶቻችንም አለቆቻችንም ካህናቶቻችንም አባቶቻችንም ሕግህን አልጠበቁም፥ የመሰከርህባቸውንም ትእዛዝህንና ምስክርህን አልሰሙህም። በመንግሥታቸውም በሰጠሃቸውም ታላቅ በጎነትህ፥ በፊታቸውም በሰጠኸው በሰባው ምድር አላመለኩህም፥ ከክፉም ሥራቸው አልተመለሱም። እነሆ፥ ዛሬ ባርያዎች ነን፥ ፍሬዋንና በረከትዋን ይበሉ ዘንድ ለአባቶቻችን በሰጠሃት ምድር፥ እነሆ፥ በእርሷ ባርያዎች ነን፥ ስለ ኃጢአታችንም ለሾምህብን ነገሥታት በረከትዋን ታበዛለች፥ ሰውነታችንንም ይገዛሉ፥ በእንስሶቻችንም የሚወድዱትን ያደርጋሉ፥ እኛም በጽኑ መከራ ላይ ነን።”