ነህምያ 8:13-18
ነህምያ 8:13-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በሁለተኛውም ቀን ከሕዝቡ ሁሉ የአባቶች ቤቶች አለቆች፥ ካህናቱም፥ ሌዋውያኑም የሕጉን ቃል ይተረጕምላቸው ዘንድ ወደ ጸሓፊው ወደ ዕዝራ ተሰበሰቡ። በሰባተኛውም ወር ባለው በዓል የእስራኤል ልጆች በዳስ ይቀመጡ ዘንድ በከተሞቻቸውና በኢየሩሳሌምም ይናገሩና ያውጁ ዘንድ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ በሕጉ ውስጥ ተጽፎ አገኙ። ዕዝራም አላቸው፥ “ወደ ተራራ ሂዱ፤ የዘይትና የበረሃ ወይራ፥ የባርሰነትም፥ የዘንባባም፥ የለመለመውንም ዛፍ ቅርንጫፍ አምጡ፤ እንደ ተጻፈውም ዳሶችን ሥሩ።” ሕዝቡም ወጥተው አመጡ፤ እያንዳንዱም በቤቱ ሰገነት ላይ፥ በአደባባዩም ላይ፥ በእግዚአብሔርም ቤት አደባባይ ላይ፥ በውኃውም በር አደባባይና በኤፍሬም በር አደባባይ ላይ ዳስ ሠሩ። ከምርኮም የተመለሱት ማኅበር ሁሉ ዳስ ሠሩ፤ በዳሱም ውስጥ ተቀመጡ። ከነዌም ልጅ ከኢያሱ ዘመን ጀምሮ እስከዚያ ቀን ድረስ የእስራኤል ልጆች እንዲህ ያለ አላደረጉም ነበር። እጅግም ታላቅ ደስታ ሆነ። ከመጀመሪያውም ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ ዕለት ዕለት የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ ያነብብ ነበር። በዓሉንም ሰባት ቀን ያህል አደረጉ፤ በስምንተኛውም ቀን እንደ ሕጋቸው ወጡ።
ነህምያ 8:13-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከወሩም በሁለተኛው ቀን የየቤተ ሰቡ ሁሉ ኀላፊዎች፣ የሕጉን ቃል ለመማር ከካህናቱና ከሌዋውያኑ ጋር በጸሓፊው በዕዝራ ዙሪያ ተሰበሰቡ። እስራኤላውያን በሰባተኛው ወር በሚውለው በዓል በዳስ ውስጥ እንዲቀመጡ እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት የሰጠውን ትእዛዝ በሕጉ ውስጥ ተጽፎ አገኙ፤ ስለዚህ በየከተሞቻቸውና በኢየሩሳሌም ይህን ቃል እንዲያውጁና እንዲያሠራጩ እንዲህ በማለት አዘዟቸው፤ “ወደ ኰረብቶች ውጡ፤ ከዘይትና ከበረሓ ወይራ፣ ከባርስነት፣ ከዘንባባና ከለምለም ዛፎች ቅርንጫፎችን አምጡ፤ በተጻፈው መሠረት ዳሶችን ሥሩ።” ስለዚህ ሕዝቡ ወጥተው ቅርንጫፎች አመጡ፤ እያንዳንዳቸውም በየቤታቸው ጣራ ሰገነት፣ በየግቢያቸው፣ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ፣ “በውሃ በር” አደባባይና “በኤፍሬም በር” አደባባይ ላይ ዳስ ሠሩ። ከምርኮ የተመለሰውም ማኅበር ሁሉ ዳሱን ሠርቶ ተቀመጠ። ከነዌ ልጅ ከኢያሱ ዘመን ጀምሮ እስከዚያን ጊዜ ድረስ እስራኤላውያን እንደዚያ አድርገው በዓሉን አክብረው አያውቁም፤ ደስታቸውም ታላቅ ነበር። ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ፣ ዕዝራ በየዕለቱ ከእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ያነብብ ነበር። እነርሱም በዓሉን ሰባት ቀን አከበሩ፤ በስምንተኛውም ቀን በሕጉ መሠረት የተቀደሰ ጉባኤ ተደረገ።
ነህምያ 8:13-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በሁለተኛውም ቀን ከሕዝቡ ሁሉ የአባቶች ቤቶች አለቆች ካህናቱም ሌዋውያኑም የሕጉን ቃል ይተረጉምላቸው ዘንድ ወደ ጸሐፊው ወደ ዕዝራ ተሰበሰቡ። በሰባተኛውም ወር ባለው በዓል የእስራኤል ልጆች በዳስ ይቀመጡ ዘንድ በከተሞቻቸውና በኢየሩሳሌምም፦ ወደ ተራራ ሂዱ፥ የዘይትና የበረሀ ወይራ የባርሰነትም የዘንባባም የለመለመውን ዛፍ ቅርንጫፍ አምጡ፥ እንደ ተጻፈውም ዳሶችን ሥሩ ብለው ይናገሩ ያውጁም ዘንድ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ በሕጉ ውስጥ ተጽፎ አገኙ። ሕዝቡም ወጥተው አመጡ፥ እያንዳንዱም በቤቱ ሰገነት ላይ፥ በአደባባዩም ላይ፥ በእግዚአብሔርም ቤት አደባባዩ ላይ፥ በውኃውም በር አደባባይና በኤፍሬም በር አደባባይ ላይ ዳስ ሠራ። ከምርኮም የተመለሱት ማኅበር ሁሉ ዳስ ሠሩ፥ በዳሱም ውስጥ ተቀመጡ። ከነዌም ልጅ ከኢያሱ ዘመን ጀምሮ እስከዚያ ቀን ድረስ የእስራኤል ልጆች እንዲህ ያለ አላደረጉም ነበር። እጅግም ታላቅ ደስታ ሆነ። ከመጀመሪያውም ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ ዕለት ዕለት የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ ያነብብ ነበር። በዓሉን ሰባት ቀን ያህል አደረጉ፥ በስምንተኛውም ቀን እንደ ሕጉ የተቀደሰ ጉባኤ ነበረ።
ነህምያ 8:13-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በማግስቱ የጐሣ አለቆች ከካህናቱና ከሌዋውያኑ ጋር በአንድነት ሆነው የሕጉን ቃላት ትምህርት ለማጥናት ወደ ዕዝራ ዘንድ ሄዱ። እስራኤላውያን ሕጉን በሚያነቡበት ጊዜ የሰባተኛውን ወር በዓል በዳስ ውስጥ ሆነው እንዲያከብሩ መታዘዙን እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ባዘዘው ሕግ ውስጥ ተጽፎ አገኙ። የዳስን በዓል በተመለከተ ሕጉ በሚያዝዘው መሠረት ወደ ተራራማው አገር ሄደው የወይራ ዘይት ዛፍና የዱር ወይራ ቅርንጫፎችን የባርሰነትና የዘንባባ ቅርንጫፎችን ለማምጣት በየከተማውና በኢየሩሳሌም አካባቢ እንዲሄዱ አዘዙአቸው። ስለዚህም ሕዝቡ የዛፍ ቅጠል እየቈረጡ አምጥተው በሚኖሩበት ግቢ፥ በየቤታቸው ጣራ ድምድማት ላይ፥ በቤተ መቅደሱ አደባባይና የውሃ በር ተብሎ በሚጠራው አደባባይ፥ እንዲሁም በኤፍሬም አደባባይ ዳስ ጣሉ፤ ከምርኮ ተመልሰው የመጡት ሰዎች ሁሉ ዳሶችን ሠርተው በዳሱ ውስጥ ተቀመጡ፤ ይህም ከነዌ ልጅ ኢያሱ ዘመን ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ ነበር፤ እያንዳንዳቸውም ወሰን የሌለው ደስታ ተሰምቶአቸው ነበር። በዓሉ ከተጀመረበት ዕለት አንሥቶ እስከ መጨረሻይቱ ቀን ድረስ ዕዝራ በየዕለቱ ከእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ አንዳንድ ክፍል ያነብላቸው ነበር፤ በዓሉንም እስከ ሰባት ቀን አከበሩ፤ በስምንተኛውም ቀን ሕጉ በሚያዝዘው መሠረት የበዓሉ መዝጊያ ሥነ ሥርዓት ተደረገ።
ነህምያ 8:13-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በሁለተኛው ቀን ከሕዝቡ ሁሉ አለቆች የሆኑ አባቶች፥ ካህናቱ፥ ሌዋውያኑም የሕጉን ቃል እንዲተረጉምላቸው ወደ ጸሐፊው ወደ ዕዝራ ተሰበሰቡ። በሰባተኛው ወር ባለው በዓል የእስራኤል ልጆች በዳስ እንዲቀመጡ ጌታ በሙሴ በኩል ያዘዘውን በሕጉ ውስጥ ተጽፎ አገኙ፤ በከተሞቻቸው ሁሉና በኢየሩሳሌምም፦ “እንደተጻፈው ዳሶችን ለመስራት ወደ ተራራ ውጡ፥ የዘይትና የበረሀ ወይራ፥ የባርሰነት፥ የዘንባባና የለመለመውን ዛፍ ቅርንጫፍ አምጡ” ብለው ይናገሩና ያውጁ። ሕዝቡም ወጥተው አመጡ፥ እያንዳንዱ በቤቱ ሰገነት ላይ፥ በየግቢያቸው፥ በእግዚአብሔር ቤት ግቢ፥ በ “ውኃ በር” አደባባይና በኤፍሬም በር አደባባይ ላይ ዳሶችን ሠሩ። ከምርኮ የተመለሱት ማኅበር ሁሉ ዳሶችን ሠሩ፥ በዳሶቹም ውስጥ ተቀመጡ። ከነዌ ልጅ ከኢያሱ ዘመን ጀምሮ እስከዚያ ቀን ድረስ የእስራኤል ልጆች እንዲህ ያለ ነገር አድርገው አያውቁም ነበርና። እጅግ ታላቅ ደስታም ሆነ። ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ ዕዝራ ዕለት ዕለት የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ ያነብብ ነበር። በዓሉን ሰባት ቀን አከበሩ፤ በስምንተኛው ቀን በሕጉ መሠረት የተቀደሰ ጉባኤ ነበረ።