መጽሐፈ ነህምያ 8
8
ዕዝራ የእግዚአብሔርን ሕግ ለሕዝቡ እንዳነበበ
1የእስራኤል ሕዝብ በሰባተኛው ወር በየከተሞቻቸው መስፈራቸውን አበቁ፤ በዚያም ወር በመጀመሪያው ቀን በኢየሩሳሌም የውሃ በር ተብሎ በሚጠራው አደባባይ በውስጥ በኩል ሕዝቡ ሁሉ በአንድነት ተሰበሰቡ፤ እነርሱም የሕግ ምሁሩን ዕዝራን እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ለእስራኤል ሕዝብ የሰጠውን የኦሪትን ሕግ መጽሐፍ ያመጣላቸው ዘንድ ለመኑት። 2ስለዚህም ካህኑ ዕዝራ ሰባተኛው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን፥ ማስተዋል የሚችል ሕዝብ ሁሉ ሴት፥ ወንድ፥ ልጅ ዐዋቂው በሙሉ ወደተሰበሰቡበት ስፍራ፥ የሕጉን መጽሐፍ አመጣ፤ 3በዚያም አደባባይ ዕዝራ በቅጽሩ በር አጠገብ ቆሞ ከንጋት እስከ ቀትር የሕጉን መጽሐፍ ከፍ ባለ ድምፅ አነበበላቸው፤ ወንዶችም ሴቶችም ሁሉ በከፍተኛ ስሜት አዳመጡት።
4የሕግ ምሁሩ ዕዝራ ለዚሁ ተግባር አመች ይሆን ዘንድ ከዕንጨት በተሠራ መድረክ ላይ ቆሞ ነበር፤ ከእርሱም ጋር በስተቀኙ በኩል የቆሙት ሰዎች ማቲትያ፥ ሼማዕ፥ ዓናያ፥ ኡሪያ፥ ሒልቂያና መዕሤያ ሲሆኑ፥ በስተ ግራው በኩል ደግሞ ፐዳያ፥ ሚሻኤል፥ ማልኪያ፥ ሐሹም፥ ሐሽባዳናህ፥ ዘካርያስና መሹላም ቆመው ነበር።
5ዕዝራ ከሕዝቡ ከፍ ብሎ በተሠራው መድረክ ላይ በቆመ ጊዜ፥ ሁሉም ትኲር ብለው ይመለከቱት ነበር፤ እርሱም የሕጉን መጽሐፍ በከፈተ ጊዜ፥ ሁሉም ከተቀመጡበት ተነሡ፤ 6ዕዝራም ታላቁን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገነ። ሁሉም እጆቻቸውን ወደ ላይ በማንሣት “አሜን! አሜን!” ሲሉ መለሱ፤ ወደ ምድርም ለጥ ብለው ለእግዚአብሔር ሰገዱ።
7ከዚህ በኋላ ተነሥተው ባሉበት ስፍራ ቆሙ፤ ከዚህ ቀጥሎ ስማቸው የተዘረዘረ ሌዋውያንም የሕጉን መጽሐፍ ትርጒም ለሕዝቡ አብራሩላቸው፤ እነርሱም ኢያሱ፥ ባኒ፥ ሼሬብያ፥ ያሚን፥ ዓቁብ፥ ሻበታይ፥ ሆዲያ፥ መዕሤያ፥ ቀሊጣ፥ ዐዛርያስ፥ ዮዛባድ፥ ሐናንና ፐላያ ነበሩ። 8እነርሱም ለሕዝቡ የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ አነበቡለት፤ ሕዝቡም የሚነበበው ይገባው ዘንድ ያብራሩለት ነበር።
9የሕጉን ቃል በሰሙ ጊዜ ሰዎቹ ስላለቀሱ፥ አገረ ገዢው ነህምያ፥ ካህኑና የሕግ ምሁሩ ዕዝራ፥ ሕዝቡን ያስተምሩ የነበሩት ሌዋውያን “ይህ ቀን ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ቀን ስለ ሆነ፥ አትዘኑ፤ አታልቅሱም” አሉአቸው። 10ነህምያ፦ “ሂዱና ምርጡን ምግብ ብሉ፤ ጣፋጩን መጠጥ ጠጡ፤ ምንም ለሌላቸውም ላኩ፤ ይህ ቀን ለአምላካችን የተቀደሰ ቀን ነው፤ የእግዚአብሔር ደስታ ኀይላችሁ ስለ ሆነ አትዘኑ” አላቸው።
11ሌዋውያኑም በዚህ በተቀደሰ ዕለት ማዘን እንደማይገባቸው በማስረዳት የሕዝቡን ጩኸት ጸጥ አደረጉ፤ 12የተነበበላቸውን ቃል ትርጒም በሚገባ ተረድተው ስለ ነበር ሕዝቡ ሁሉ ወደየቤታቸው ሄደው በመብላትና በመጠጣት እጅግ ተደሰቱ፤ ያላቸውንም ምግብ ከሌሎቹ ጋር አብረው ተካፈሉ፤
የዳስ በዓል መከበር
13በማግስቱ የጐሣ አለቆች ከካህናቱና ከሌዋውያኑ ጋር በአንድነት ሆነው የሕጉን ቃላት ትምህርት ለማጥናት ወደ ዕዝራ ዘንድ ሄዱ። 14እስራኤላውያን ሕጉን በሚያነቡበት ጊዜ የሰባተኛውን ወር በዓል በዳስ ውስጥ ሆነው እንዲያከብሩ መታዘዙን እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ባዘዘው ሕግ ውስጥ ተጽፎ አገኙ። 15የዳስን በዓል በተመለከተ ሕጉ በሚያዝዘው መሠረት ወደ ተራራማው አገር ሄደው የወይራ ዘይት ዛፍና የዱር ወይራ ቅርንጫፎችን የባርሰነትና የዘንባባ ቅርንጫፎችን ለማምጣት በየከተማውና በኢየሩሳሌም አካባቢ እንዲሄዱ አዘዙአቸው። #ዘሌ. 23፥33-36፤ ዘዳ. 16፥13-15።
16ስለዚህም ሕዝቡ የዛፍ ቅጠል እየቈረጡ አምጥተው በሚኖሩበት ግቢ፥ በየቤታቸው ጣራ ድምድማት ላይ፥ በቤተ መቅደሱ አደባባይና የውሃ በር ተብሎ በሚጠራው አደባባይ፥ እንዲሁም በኤፍሬም አደባባይ ዳስ ጣሉ፤ 17ከምርኮ ተመልሰው የመጡት ሰዎች ሁሉ ዳሶችን ሠርተው በዳሱ ውስጥ ተቀመጡ፤ ይህም ከነዌ ልጅ ኢያሱ ዘመን ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ ነበር፤ እያንዳንዳቸውም ወሰን የሌለው ደስታ ተሰምቶአቸው ነበር። 18በዓሉ ከተጀመረበት ዕለት አንሥቶ እስከ መጨረሻይቱ ቀን ድረስ ዕዝራ በየዕለቱ ከእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ አንዳንድ ክፍል ያነብላቸው ነበር፤ በዓሉንም እስከ ሰባት ቀን አከበሩ፤ በስምንተኛውም ቀን ሕጉ በሚያዝዘው መሠረት የበዓሉ መዝጊያ ሥነ ሥርዓት ተደረገ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነህምያ 8: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997