የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማርቆስ 8:27-33

ማርቆስ 8:27-33 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ወደ ፊልጶስ ቂሳርያ መንደሮች ሄደ፤ በመንገድ ላይ ሳሉም ደቀ መዛሙርቱን፣ “ሰዎች እኔን ማን ነው ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “መጥምቁ ዮሐንስ የሚሉህ አሉ፤ ሌሎች ኤልያስ ነው ይሉሃል፤ ሌሎች ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” ብለው ነገሩት። ቀጥሎም፣ “እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። ጴጥሮስም፣ “አንተ ክርስቶስ ነህ” አለው። ኢየሱስም ስለ እርሱ ለማንም እንዳይናገሩ አስጠነቀቃቸው። ከዚያም የሰው ልጅ ብዙ መከራ እንደሚቀበል፣ በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት እንደሚናቅ፣ እንደሚገደል፣ ከሦስት ቀንም በኋላ እንደሚነሣ ያስተምራቸው ጀመር። እርሱም ይህን በግልጽ ነገራቸው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን ለብቻው ወስዶ ይገሥጸው ጀመር። ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ደቀ መዛሙርቱን እያየ ጴጥሮስን፣ “አንተ ሰይጣን፤ ወደ ኋላዬ ሂድ! የሰው እንጂ የእግዚአብሔር ነገር በሐሳብህ የለምና” በማለት ገሠጸው።

ማርቆስ 8:27-33 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የፊልጶስ ቂሳርያ በሚባለው ክፍለ ሀገር አካባቢ ወዳሉት መንደሮች አመሩ፤ በመንገድም ላይ ሳሉ ኢየሱስ፦ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” ሲል ደቀ መዛሙርቱን ጠየቃቸው። እነርሱም፦ “አንዳንዶች መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ ሌሎች ኤልያስ ነው፤ ሌሎችም ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይሉሃል፤” ሲሉ መለሱለት። “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስም፦ “አንተ መሲሕ ነህ፤” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም፦ “ስለ እኔ ለማንም እንዳትናገሩ፤” ብሎ አስጠነቀቃቸው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ሲል ማስተማር ጀመረ፤ “የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበል ይገባዋል፤ በሽማግሌዎች፥ በካህናት አለቆችና በሕግ መምህራን ዘንድ ይናቃል፤ ይገደላልም፤ ይሁን እንጂ ከሦስት ቀን በኋላ ይነሣል።” ይህን ነገር በግልጥ ነገራቸው፤ በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ለብቻው ገለል አድርጎት ይገሥጸው ጀመር። “እንዲህ አትበል” ሲል ተቈጣው። ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ተመለከተና ጴጥሮስን፦ “አንተ ሰይጣን ከእኔ ኋላ ሂድ! አንተ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብም!” ሲል ገሠጸው።

ማርቆስ 8:27-33 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ፈልጶስ ቂሳርያ መንደሮች ሄደ፤ በመንገድ ላይ ሳሉም ደቀ መዛሙርቱን፥ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፥ “መጥምቁ ዮሐንስ የሚሉህ አሉ፤ ሌሎች ኤልያስ ነው ይሉሃል፤ ሌሎች ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” ብለው ነገሩት። ቀጥሎም፥ “እናንተሳ ማን ትሉኛላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። ጴጥሮስም፤ “አንተ ክርስቶስ ነህ” አለው። ኢየሱስም ስለ እርሱ ለማንም እንዳይናገሩ አስጠነቀቃቸው። ከዚያም የሰው ልጅ ብዙ መከራ እንደሚቀበል፥ በሽማግሌዎች፥ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት እንደሚናቅ፥ እንደሚገደል፥ ከሦስት ቀንም በኋላ እንደሚነሣ ያስተምራቸው ጀመር። እርሱም ይህን በግልጽ ነገራቸው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን ለብቻው ወስዶ ይገሥጸው ጀመር። ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ደቀ መዛሙርቱን እያየ ጴጥሮስን፥ “አንተ ሰይጣን፥ ወደ ኋላዬ ሂድ አንተ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብምና” በማለት ገሠጸው።