የማርቆስ ወንጌል 8
8
ኢየሱስ አራት ሺህ ሰዎች እንደመገበ
(ማቴ. 15፥32-39)
1በዚያን ጊዜ፥ እንደገና ብዙ ሕዝብ ተሰበሰበ። የሚበሉት ምንም ምግብ ስላልነበራቸው ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፥ እንዲህ አላቸው፤ 2ከእኔ ጋር ሦስት ቀን ስለቆዩና የሚበሉትም ስለ ሌላቸው እነዚህ ሰዎች ያሳዝኑኛል፤ 3እንዲህ እንደ ተራቡ ወደ ቤታቸው ብሰዳቸው አንዳንዶቹ ከሩቅ የመጡ ስለ ሆኑ በመንገድ ላይ ዝለው ይወድቃሉ። 4ደቀ መዛሙርቱም መልሰው፥ “በዚህ ምድረ በዳ እነዚህን ለመመገብ የሚያስችል እንጀራ ከወዴት ይገኛል?” አሉት። 5እርሱም፥ “ስንት እንጀራ አላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፥ “ሰባት” አሉት። 6እርሱም፥ መሬት ላይ እንዲቀመጡ ሕዝቡን አዘዘ፤ ሰባቱን እንጀራ ይዞ ካመሰገነ በኋላ ቆርሶ ለሰዎቹ እንዲያድሉ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ እነርሱም ለሕዝቡ አደሉት። 7እንዲሁም ትንንሽ ዓሣዎች ነበሯቸው፤ እርሱም ዓሣዎቹን ባርኮ እንዲያድሏቸው አዘዘ። 8ሕዝቡም በልተው ጠገቡ፤ ከዚያም ደቀመዛሙርቱ የተረፈውን ቁርስራሽ ሰባት መሶብ ሙሉ አነሡ። 9በዚያም አራት ሺህ ያህል ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱንም አሰናበታቸው። 10ከዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ዳልማኑታ ወደ ተባለ ስፍራ ሄደ።
ከሰማይ ምልክትን ስለ ጠየቁ ሰዎች
(ማቴ. 16፥1-4)
11 #
ማቴ. 12፥38፤ ሉቃ. 11፥16። ፈሪሳውያንም ወጥተው ከኢየሱስ ጋር ይከራከሩ ጀመር። ሊፈትኑትም ፈልገው ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት። 12#ማቴ. 12፥39፤ ሉቃ. 11፥29።እርሱም በመንፈሱ እጅግ በመቃተት፥ “ይህ ትውልድ ምልክት የሚፈልገው ለምንድን ነው? እውነት እላችኋለሁ፤ ለዚህ ትውልድ ምንም ምልክት አይሰጠውም” አለ። 13ከዚያም ትቷቸው በጀልባ ወደ ማዶ ተሻገረ።
ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ መጠበቅ
(ማቴ. 16፥5-12)
14ደቀመዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ስለረሱ፥ ከአንድ እንጀራ በቀር በጀልባ ውስጥ ምንም አልነበራቸውም። 15#ሉቃ. 12፥1።ኢየሱስም፥ “ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ” ብሎ አዘዛቸው። 16እነርሱም እርስ በርሳቸው፥ “እንዲህ የሚለን እኮ እንጀራ ስለሌለን ነው” ተባባሉ። 17ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ፥ እንዲህ አላቸው፤ “እንጀራ ስለሌለን ነው በማለት ምን ያነጋግራችኋል? አሁንም አታስተውሉምን? ልብ አትሉምን? ወይስ ልባችሁ ደንድኗል? 18#ኤር. 5፥21፤ ሕዝ. 12፥2፤ ማር. 4፥12።ዐይን እያላችሁ አታዩምን? ጆሮ እያላችሁ አትሰሙምን? አታስታውሱምን? 19አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰው በቆረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” እነርሱም፥ “ዐሥራ ሁለት” አሉት። 20“ሰባቱንስ እንጀራ ለአራት ሺህ በቆረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” አላቸው። እነርሱም፥ “ሰባት” አሉት። 21እርሱም፥ “እስከ አሁን አላስተዋላችሁም ማለት ነውን” አላቸው።
በቤተ ሳይዳ የተፈወሰው ዐይነ ስውር
22ከዚያም ወደ ቤተሳይዳ መጡ፤ ጥቂት ሰዎችም አንድ ዐይነ ስውር ወደ ኢየሱስ አምጥተው እንዲዳስሰው ለመኑት። 23እርሱም የዐይነ ስውሩን እጅ ይዞ ከሰፈር ውጭ አወጣው፤ በዐይኖቹም ላይ እንትፍ ብሎበት፥ እጁንም በላዩ ጭኖ፥ “ምን የሚታይህ ነገር አለ?” ሲል ጠየቀው። 24እርሱም ቀና ብሎ አይቶ፥ “ሰዎች እንደ ዛፍ ሲንቀሳቀሱ አያለሁ” አለ። 25ኢየሱስም እንደገና እጆቹን በሰውየው ዐይኖች ላይ ጫነ፤ በዚህ ጊዜ ዐይኖቹ በሩ፤ ብርሃኑም ተመለሰለት፤ ሁሉንም ነገር አጥርቶ ማየት ቻለ። 26ከዚያም፥ “ወደ መንደሩ አትግባ በመንደሩም ለማንም አትናገር” ብሎ ወደ ቤቱ ላከው።
ኢየሱስ መሢሕ መሆኑን ጴጥሮስ መግለጡ
(ማቴ. 16፥13-20፤ ሉቃ. 9፥18-21)
27ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ፈልጶስ ቂሳርያ መንደሮች ሄደ፤ በመንገድ ላይ ሳሉም ደቀ መዛሙርቱን፥ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው። 28#ማር. 6፥14፤15፤ ሉቃ. 9፥7፤8።እነርሱም፥ “መጥምቁ ዮሐንስ የሚሉህ አሉ፤ ሌሎች ኤልያስ ነው ይሉሃል፤ ሌሎች ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” ብለው ነገሩት። 29#ዮሐ. 6፥68፤69።ቀጥሎም፥ “እናንተሳ ማን ትሉኛላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። ጴጥሮስም፤ “አንተ ክርስቶስ ነህ” አለው። 30ኢየሱስም ስለ እርሱ ለማንም እንዳይናገሩ አስጠነቀቃቸው።
ኢየሱስ ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው እንደ ተናገረ
(ማቴ. 16፥21-28፤ ሉቃ. 9፥22-27)
31ከዚያም የሰው ልጅ ብዙ መከራ እንደሚቀበል፥ በሽማግሌዎች፥ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት እንደሚናቅ፥ እንደሚገደል፥ ከሦስት ቀንም በኋላ እንደሚነሣ ያስተምራቸው ጀመር። 32እርሱም ይህን በግልጽ ነገራቸው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን ለብቻው ወስዶ ይገሥጸው ጀመር። 33ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ደቀ መዛሙርቱን እያየ ጴጥሮስን፥ “አንተ ሰይጣን፥ ወደ ኋላዬ ሂድ አንተ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብምና” በማለት ገሠጸው።
34 #
ማቴ. 10፥38፤ ሉቃ. 14፥27። ከዚህ በኋላ፥ ሕዝቡን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ፤ 35#ማቴ. 10፥39፤ ሉቃ. 17፥33፤ ዮሐ. 12፥25።ነፍሱን ለማዳን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋት ሁሉ ግን ያድናታል። 36ሰው ዓለሙ ሁሉ የእርሱ ቢሆንና ነፍሱን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? 37ለመሆኑ፥ ሰው ለነፍሱ ምን መተኪያ አለው? 38በዚህ ዘማዊና ኀጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅም በአባቱ ግርማ፥ ከቅዱሳን መላእክት ጋር ሲመጣ ያፍርበታል።”
Currently Selected:
የማርቆስ ወንጌል 8: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ