የማርቆስ ወንጌል 7
7
ፈሪሳውያንና ሥርዓታቸው
(ማቴ. 15፥1-20)
1ከዚህ በኋላ ፈሪሳውያንና ከኢየሩሳሌም የመጡ አንዳንድ ጸሐፍት በዙሪያው ተሰበሰቡ፤ 2ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንዶቹ ባልነጻ ማለትም ባልታጠበ እጅ እንጀራ ሲበሉ አዩ፤ 3ፈሪሳውያንና አይሁድ ሁሉ የአባቶችን ወግ ለመጠበቅ ሲሉ፥ በሥርዓቱ መሠረት እጃቸውን በጥንቃቄ ሳይታጠቡ አይበሉም ነበርና። 4ከገበያ ሲመለሱም ታጥበው ራሳቸውን ካላነጹ በስተቀር አይበሉም ነበር። እንዲሁም ዋንጫን፥ ማሰሮን፥ ሳሕንና ዐልጋን እንደማጠብ ያሉትን ሌሎችን ወጎች ይጠብቁ ነበር። 5ፈሪሳውያንና ጸሐፍትም፥ “ደቀ መዛሙርትህ እንደ አባቶች ወግ በመኖር ፈንታ ባልታጠበ እጃቸው ለምን እንጀራ ይበላሉ?” ብለው ጠየቁት። 6#ኢሳ. 29፥13።እርሱም እንዲህ ሲል መለሰ፤ ኢሳይያስ ስለ እናንተ፥ ስለ ግብዞች
ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤
ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤
7በከንቱ ያመልከኛል፤
ትምህርታቸውም ሰው ሠራሽ ሥርዓት ብቻ ነው።
ተብሎ እንደ ተጻፈ በእውነት ትንቢት ተናገረ። 8የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ የሰዎችን ወግና ሥርዓት ትጠብቃላችሁ።
9ደግሞም፥ እንዲህ አላቸው፤ “የራሳችሁን ወግ ለመጠበቅ ስትሉ፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የምትተውበት ዘዴ። 10#ዘፀ. 20፥12፤ ዘዳ. 5፥16፤ ዘፀ. 21፥17፤ ዘሌ. 20፥9።ሙሴ፥ አባትህንና እናትህን አክብር፤ አባቱን ወይም እናቱን የሚሳደብ ፈጽሞ ይሙት ብሎ ነበርና፤ 11እናንተ ግን አንድ ሰው አባቱን ወይም እናቱን፥ ከእኔ ማግኘት የሚገባችሁን ርዳታ ሁሉ ቁርባን ይኸውም መባ አድርጌለሁ ቢላቸው፥ 12እናንተም ይህ ሰው ለአባቱም ሆነ ለእናቱ ከዚህ በኋላ ምንም ነገር እንዲያደርግ አትፈቅዱለትም። 13ስለዚህ ለትውልድ በምታስተላልፉት ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ ይህን የመሰለም ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ።”
14ደግሞም ኢየሱስ ሕዝቡን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ስሙኝ፤ ሁላችሁም አስተውሉ፤ 15ከውጭ ወደ ውስጥ ገብቶ ሰውን የሚያረክሰው አንዳች ነገር የለም፤ ይልቁን ሰውን የሚያረክሰው ከራሱ ወደ ውጭ የሚወጣው ነገር ነው፤ 16ሰሚ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ።” 17ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ከገባ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ስለ ምሳሌው ጠየቁት። 18እርሱም፥ “እናንተም ነገሩ አይገባችሁምን? ከውጭ ወደ ሰው ገብቶ ሊያረክሰው የሚችል አንዳች ነገር የለም፤ 19ወደ ልቡ ሳይሆን ወደ ሆዱ ይገባል፤ ከዚያም ከሰውነቱ ይወጣልና። ኢየሱስ ይህን በማለቱ ምግብ ሁሉ ንጹሕ መሆኑን ገለጸ። 20ቀጥሎም፥ እንዲህ አለ፤ ከሰው የሚወጣ ያ ሰውን ያረክሰዋል፤ 21ከውስጥ፥ ከሰው ልብ የሚወጡት ክፉ ሐሳብ፥ ምንዝር፥ ስርቆት፤ ሰው መግደል፥ ዝሙት፥ 22መስገብገብ፥ ክፋት፥ ማታለል፥ መዳራት፥ ምቀኝነት፥ ስም ማጥፋት፥ ትዕቢት፥ ስንፍና ናቸው። 23እነዚህ ክፉ ነገሮች ሁሉ ከሰው ይወጣሉ ሰውንም ያረክሱታል።”
ስለ አንዲት ሲሮፊኒቃዊት እምነት
(ማቴ. 15፥21-28)
24ከዚያ ተነሥቶ ወደ ጢሮስ አገር ሄደ፤ ወደ አንድ ቤት ገብቶ እዚያ መኖሩን ማንም እንዳያውቅበት ፈለገ፤ ሆኖም እዚያ መኖሩ ሊሸሸግ አልቻለም። 25ወዲያው ግን ትንሺቱ ልጇ በርኩስ መንፈስ የተያዘችባት አንዲት ሴት ስለ እርሱ ሰምታ መጣችና በእግሩ ላይ ወደቀች። 26ሴትዮዋም ግሪካዊት፥ በትውልዷም ሲሮፊኒቃዊት ነበረች። እርሷም ኢየሱስ ርኩስ መንፈሱን ከልጇ እንዲያስወጣላት ለመነችው። 27እርሱ ግን፥ “የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መጣል ተገቢ ስላልሆነ፥ መጀመሪያ ልጆቹ ጠግበው ይብሉ” አላት። 28እርሷም መልሳ፥ “አዎን፥ ጌታ ሆይ፤ ውሾችም ከገበታ በታች ሆነው የልጆችን ትራፊ ይበላሉ” አለችው። 29እርሱም፥ “ስለዚህ ይህን ስላልሽ ሂጂ፤ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቷአል” አላት። 30እርሷም ወደ ቤቷ ስትመለስ ልጇ ዐልጋ ላይ ተኝታ፥ ጋኔኑም ለቋት አገኘቻት።
መስማትና መናገር የተሣነው ሰው መፈወስ
31ከዚያም ኢየሱስ ከጢሮስ አገር ተነሥቶ፥ በሲዶና በኩል አድርጎ ዐሥር ከተማ በተባለው አገር በማለፍ ወደ ገሊላ ባሕር መጣ። 32በዚያም ሰዎች ደንቆሮና ዲዳ የሆነ አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፤ እጁንም እንዲጭንበት ለመኑት። 33ኢየሱስም ሰውየውን ከሕዝቡ ለይቶ ከወሰደው በኋላ፥ ጣቶቹን በጆሮው አስገባ፤ ከዚያም እንትፍ ብሎ የሰውየውን ምላስ ዳሰሰ። 34ወደ ሰማይም ተመልክቶ ቃተተና፥ “ኤፋታህ” አለው፤ ይኸውም፥ “ተከፈት” ማለት ነው። 35ወዲያውም ጆሮዎቹ ተከፈቱ፤ ምላሱም ተፈቶ አጥርቶ መናገር ጀመረ። 36ኢየሱስ ይህን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው፤ ሆኖም እርሱ እንዳይናገሩ ባዘዛቸውም መጠን፥ ነገሩን አስፍተው አወሩት። 37ሕዝቡም ከመጠን በላይ በመደነቅ፥ “ያደረገው ሁሉ ጥሩ ነው፤ ደንቆሮዎች እንዲሰሙ፥ ድዳዎች እንዲናገሩ እንኳን አድርጓል” አሉ።
Currently Selected:
የማርቆስ ወንጌል 7: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ