ማርቆስ 10:13-34
ማርቆስ 10:13-34 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንዲዳስሳቸውም ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ያመጡአቸውን ገሠጹአቸው። ኢየሱስ ግን አይቶ ተቈጣና “ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉ፤ አትከልክሉአቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ናትና። እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም፤” አላቸው። አቀፋቸውም እጁንም ጭኖ ባረካቸው። እርሱም በመንገድ ሲወጣ አንድ ሰው ወደ እርሱ ሮጦ ተንበረከከለትና “ቸር መምህር ሆይ! የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም “ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም። ትእዛዛትን ታውቃለህ፤ አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አታታልል፥ አባትህንና እናትህን አክብር፤” አለው። እርሱም መልሶ “መምህር ሆይ! ይህን ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ፤” አለው። ኢየሱስም ወደ እርሱ ተመልክቶ ወደደውና “አንድ ነገር ጐደለህ፤ ሂድ፤ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፤ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፤ መስቀሉንም ተሸክመህ ና፤ ተከተለኝ፤” አለው። ነገር ግን ስለዚህ ነገር ፊቱ ጠቈረ፤ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነም ሄደ። ኢየሱስም ዘወር ብሎ አይቶ ደቀ መዛሙርቱን “ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል፤” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም እነዚህን ቃሎች አደነቁ። ኢየሱስም ደግሞ መልሶ “ልጆች ሆይ! በገንዘብ ለሚታመኑ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው። ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል፤” አላቸው። እነርሱም ያለ መጠን ተገረሙና እርስ በርሳቸው “እንግዲያ ማን ሊድን ይችላል?” ተባባሉ። ኢየሱስም ተመለከታቸውና “ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ እንጂ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላልና፤” አለ። ጴጥሮስም “እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤” ይለው ጀመር። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ “እውነት እላችኋለሁ፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፥ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንና እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም። ግን ብዙ ፊተኞች ኋለኞች ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ።” ወደ ኢየሩሳሌምም ሊወጡ በመንገድ ነበሩ፤ ኢየሱስም ይቀድማቸው ነበርና ተደነቁ፤ የተከተሉትም ይፈሩ ነበር። ደግሞም ዐሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ አቅርቦ ይደርስበት ዘንድ ያለውን ይነግራቸው ጀመር “እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች አልፎ ይሰጣል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፤ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል፤ ይዘብቱበትማል፤ ይተፉበትማል፤ ይገርፉትማል፤ ይገድሉትማል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል፤” አላቸው።
ማርቆስ 10:13-34 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው፣ ሰዎች ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ገሠጿቸው። ኢየሱስም ይህን ሲያይ ተቈጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና። እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበል ሁሉ ከቶ አይገባባትም።” ሕፃናቱንም ዐቀፋቸው፤ እጁንም ጭኖ ባረካቸው። ከዚያ ተነሥቶ መንገዱን ሲጀመር፣ አንድ ሰው ወደ እርሱ እየሮጠ መጣ፤ በፊቱም በጕልበቱ ተንበርክኮ፣ “ቸር መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይገባኛል” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ለምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ቸር የለም፤ ትእዛዞችን ታውቃለህ፤ አትግደል፤ አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አታታልል፤ አባትህንና እናትህን አክብር።” ሰውየውም፣ “መምህር ሆይ፤ እነዚህን ሁሉ ከልጅነቴ ጀምሮ ጠብቄአለሁ” አለው። ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው፤ “እንግዲያው አንድ ነገር ይጐድልሃል፤ ሂድና ያለህን ሁሉ ሽጥ፤ ለድኾችም ስጥ፤ በሰማይ የተከማቸ ሀብት ታገኛለህ፤ ከዚያ በኋላ ና፤ ተከተለኝም” አለው። ሰውየው ይህን ሲሰማ ክፉኛ ዐዘነ፤ ብዙ ሀብት ስለ ነበረውም እየተከዘ ሄደ። ኢየሱስ ዙሪያውን በመመልከት ደቀ መዛሙርቱን፣ “ለሀብታሞች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ከባድ ነገር ነው!” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም በንግግሩ ተገረሙ፤ ኢየሱስ ግን እንደ ገና መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ልጆች ሆይ፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ከባድ ነገር ነው! ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀልለዋል።” ደቀ መዛሙርቱም ይበልጥ በመገረም፣ “ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?” ተባባሉ። ኢየሱስም አያቸውና፣ “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላል” አላቸው። ጴጥሮስም፣ “እነሆ፤ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ” አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ሲል ቤቱን ወይም ወንድሞቹን ወይም እኅቶቹን ወይም እናቱን ወይም አባቱን ወይም ልጆቹን ወይም ዕርሻውን የተወ ሁሉ፣ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እኅቶችን፣ እናቶችን፣ ልጆችንና ዕርሻን መቶ ዕጥፍ የማይቀበል፣ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይወርስ የለም። ነገር ግን ብዙ ፊተኞች የሆኑ ኋለኞች፣ ኋለኞች የሆኑም ፊተኞች ይሆናሉ።” ወደ ኢየሩሳሌም ለመውጣት በመንገድ ላይ ሳሉ፣ ኢየሱስ ፊት ፊታቸው ይሄድ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ተገረሙ፣ ሌሎች የተከተሉት ደግሞ ፈርተው ነበር። ደግሞም ዐሥራ ሁለቱን ከሕዝቡ ለይቶ ምን እንደሚደርስበት ነገራቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም የሞት ፍርድ ይፈርዱበታል፤ አሳልፈው ለአሕዛብ ይሰጡታል፤ ያፌዙበታል፤ ይተፉበታል፤ ይገርፉታል፤ ከዚያም ይገድሉታል፤ እርሱ ግን ከሦስት ቀን በኋላ ይነሣል።”
ማርቆስ 10:13-34 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንዲዳስሳቸውም ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ያመጡአቸውን ገሠጹአቸው። ኢየሱስ ግን አይቶ ተቈጣና፦ ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉ አትከልክሉአቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ናትና። እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም አላቸው። አቀፋቸውም እጁንም ጭኖ ባረካቸው። እርሱም በመንገድ ሲወጣ አንድ ሰው ወደ እርሱ ሮጦ ተንበረከከለትና፦ ቸር መምህር ሆይ፥ የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም፦ ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም። ትእዛዛትን ታውቃለህ፤ አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አታታልል፥ አባትህንና እናትህን አክብር አለው። እርሱም መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ ይህን ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ አለው። ኢየሱስም ወደ እርሱ ተመልክቶ ወደደውና፦ አንድ ነገር ጐደለህ፤ ሂድ፥ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፥ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፥ መስቀሉንም ተሸክመህ ና፥ ተከተለኝ አለው። ነገር ግን ስለዚህ ነገር ፊቱ ጠቈረ፥ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነም ሄደ። ኢየሱስም ዘወር ብሎ አይቶ ደቀ መዛሙርቱን፦ ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም እነዚህን ቃሎች አደነቁ። ኢየሱስም ደግሞ መልሶ፦ ልጆች ሆይ፥ በገንዘብ ለሚታመኑ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው። ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል አላቸው። እነርሱም ያለ መጠን ተገረሙና እርስ በርሳቸው፦ እንግዲያ ማን ሊድን ይችላል? ተባባሉ። ኢየሱስም ተመለከታቸውና፦ ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ እንጂ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላልና አለ። ጴጥሮስም፦ እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ ይለው ጀመር። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፥ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንና እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም። ግን ብዙ ፊተኞች ኋለኞች ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ። ወደ ኢየሩሳሌምም ሊወጡ በመንገድ ነበሩ፥ ኢየሱስም ይቀድማቸው ነበርና ተደነቁ፤ የተከተሉትም ይፈሩ ነበር። ደግሞም አሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ አቅርቦ ይደርስበት ዘንድ ያለውን ይነግራቸው ጀመር፦ እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች አልፎ ይሰጣል፥ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፥ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል፥ ይዘብቱበትማል ይተፉበትማል ይገርፉትማል ይገድሉትማል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል አላቸው።
ማርቆስ 10:13-34 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው ሕፃናቱን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ሕፃናቱን ያመጡአቸውን ሰዎች ገሠጹአቸው። ኢየሱስም ይህን በማየት ተቈጥቶ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “የእግዚአብሔር መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ስለ ሆነች ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ፤ ተዉ፤ አትከልክሉአቸው፤ በእውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን ሆኖ የማይቀበላት ከቶ አይገባባትም።” ከዚህ በኋላ ሕፃናቱን ዐቀፋቸውና እጁን ጭኖ ባረካቸው። ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ በመሄድ ላይ ሳለ አንድ ሰው ወደ እርሱ ሮጦ በፊቱ ተንበረከከና “ቸር መምህር ሆይ፥ የዘለዓለምን ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ ይገባኛል?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ስለምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ማንም ቸር የለም፤ ትእዛዞችን ታውቃለህ፤ እነርሱም ‘አትግደል፤ አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አታታል፤ አባትህንና እናትህን አክብር፤’ የተባሉት ናቸው።” ሰውየውም “መምህር ሆይ፥ እነዚህንማ ትእዛዞች ከልጅነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ፤” አለው። ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው፤ እንዲህም አለው፦ “አንድ ነገር ብቻ ቀርቶሃል፤ ሂድ፤ ያለህን ሁሉ ሸጠህ ገንዘብህን ለድኾች ስጥ፤ የተከማቸ ሀብት በሰማይ ታገኛለህ፤ ከዚህም በኋላ ና፤ ተከተለኝ።” ሰውየውም ይህን በሰማ ጊዜ ፊቱ በሐዘን ጠቈረ፤ ብዙ ንብረትም ስለ ነበረው እያዘነ ሄደ። ኢየሱስ ዘወር ብሎ ተመለከተና ደቀ መዛሙርቱን፦ “ለሀብታሞች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት አስቸጋሪ ነው!” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም በቃሉ ተደነቁ፤ ኢየሱስ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ልጆች ሆይ! ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት አስቸጋሪ ነው! ሀብታም ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል።” ደቀ መዛሙርቱም በጣም ተገረሙና፥ “ታዲያ በዚህ ሁኔታ ማን ሊድን ይችላል?” ተባባሉ። ኢየሱስም ወደ እነርሱ ተመልክቶ፦ “እርግጥ ይህ ነገር በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ይቻላል፤ ለእግዚአብሔር ሁሉ ነገር ይቻለዋል፤” አላቸው። ጴጥሮስም “እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል፤” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ብሎ ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም እናትን ወይም አባትን ወይም ልጆችን ወይም ርስትን የሚተው ሰው ይበልጥ ያገኛል፤ በዚህ ዘመን እንኳ ከስደት ጋር ቤቶችን፥ ወንድሞችን፥ እኅቶችን፥ እናቶችን፥ ልጆችን፥ ርስትን በመቶ እጥፍ ይቀበላል፤ በሚመጣውም ዓለም የዘለዓለምን ሕይወት ያገኛል። ይሁን እንጂ ፊተኞች የሆኑት ብዙዎች ኋለኞች ይሆናሉ፤ ኋለኞች የሆኑትም ፊተኞች ይሆናሉ።” ወደ ኢየሩሳሌም በሚወስደው መንገድ ሳሉ፥ ኢየሱስ እፊት እፊታቸው ይሄድ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም በዚህ ነገር ተገረሙ፤ በስተኋላ የሚከተሉትም ፈርተው ነበር። እንደገናም ዐሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ አቅርቦ፥ ስለሚደርስበት ነገር እንዲህ ሲል ገለጸላቸው፦ “እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዳችን ነው፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለሕግ መምህራን ተላልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም የሞት ፍርድ ይፈርዱበታል፤ ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ አሕዛብም ያፌዙበታል፤ ይተፉበታል፤ ይገርፉታል፤ ይገድሉታልም፤ ነገር ግን ከሦስት ቀን በኋላ ይነሣል።”
ማርቆስ 10:13-34 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው፥ ሰዎች ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀመዛሙርቱ ግን ገሠጿቸው። ኢየሱስም ይህን ሲያይ ተቆጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና። እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበል ሁሉ ከቶ አይገባባትም።” ሕፃናቱንም ዐቀፋቸው፤ እጁንም ጭኖ ባረካቸው። ከዚያ ተነሥቶ መንገዱን ሲጀመር፥ አንድ ሰው ወደ እርሱ እየሮጠ መጣ፤ በፊቱም በጉልበቱ ተንበርክኮ፥ “ቸር መምህር ሆይ፤ የዘለዓለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይገባኛል” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ለምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ቸር የለም፤ ትእዛዛትን ታውቃለህ፤ አትግደል፤ አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አታታልል፤ አባትህንና እናትህን አክብር።” ሰውየውም፥ “መምህር ሆይ፤ እነዚህን ሁሉ ከልጅነቴ ጀምሮ ጠብቄአለሁ” አለው። ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው፤ “እንግዲያው አንድ ነገር ይጐድልሃል፤ ሂድና ያለህን ሁሉ ሽጥ፤ ለድኾችም ስጥ፤ በሰማይ የተከማቸ ሀብት ታገኛለህ፤ ከዚያ በኋላና፤ ተከተለኝም” አለው። ሰውየው ይህን ሲሰማ ክፉኛ አዘነ፤ ብዙ ሀብት ስለ ነበረውም እየተከዘ ሄደ። ኢየሱስ ዙሪያውን በመመልከት ደቀ መዛሙርቱን፥ “ለሀብታሞች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ከባድ ነገር ነው” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም በንግግሩ ተገረሙ፤ ኢየሱስ ግን እንደገና መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ልጆች ሆይ፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ከባድ ነገር ነው፤ ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀለዋል።” ደቀ መዛሙርቱም ይበልጥ በመገረም፥ “ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?” ተባባሉ። ኢየሱስም አያቸውና፥ “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላል” አላቸው። ጴጥሮስም፥ “እነሆ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ” አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ሲል ቤቱን ወይም ወንድሞቹን ወይም እኅቶቹን ወይም እናቱን ወይም አባቱን ወይም ልጆቹን ወይም ዕርሻውን የተወ ሁሉ፥ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን፥ ወንድሞችን፥ እኅቶችን፥ እናቶችን፥ ልጆችንና ዕርሻን መቶ ዕጥፍ የማይቀበል፥ በሚመጣውም ዓለም የዘለዓለም ሕይወት የማይወርስ የለም። ነገር ግን ብዙዎች ፊተኞች የሆኑ ኋለኞች፥ ኋለኞች የሆኑም ፊተኞች ይሆናሉ።” ወደ ኢየሩሳሌም ለመውጣት በመንገድ ላይ ሳሉ፥ ኢየሱስ ፊት ፊታቸው ይሄድ ነበር፤ ደቀመዛሙርቱ ተገረሙ፥ ሌሎች የተከተሉት ደግሞ ፈርተው ነበር። ደግሞም ዐሥራ ሁለቱን ከሕዝቡ ለይቶ ምን እንደሚደርስበት ነገራቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም የሞት ፍርድ ይፈርዱበታል፤ አሳልፈው ለአሕዛብ ይሰጡታል፤ ያፌዙበታል፤ ይተፉበታል፥ ይገርፉታል፥ ከዚያም ይገድሉታል፤ እርሱ ግን ከሦስት ቀን በኋላ ይነሣል።”