የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማርቆስ ወንጌል 10

10
ኢየሱስ ስለ ጋብቻ ማስተማሩ
(ማቴ. 19፥1-12ሉቃ. 16፥18)
1ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ፥ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ በኩል አድርጎ ወደ ይሁዳ ምድር ሄደ። እጅግ ብዙ ሰዎችም እንደገና ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ እርሱም እንደ ልማዱ ያስተምራቸው ነበር።
2ከፈሪሳውያንም ጥቂቶቹ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ ሊፈትኑትም ፈልገው፦ “ሰው ሚስቱን እንዲፈታ በሕግ ተፈቅዶለታልን?” ሲሉ ጠየቁት።
3ኢየሱስም “ሙሴ ስለዚህ ነገር ምን አዘዛችሁ?” አላቸው።
4እነርሱም “ሙሴማ የፍችዋን የምስክር ወረቀት ሰጥቶ እንዲፈታት ፈቅዶአል፤” አሉት። #ዘዳ. 24፥1-4፤ ማቴ. 5፥31።
5ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሙሴስ ይህን ትእዛዝ የጻፈላችሁ ልባችሁ ደንድኖ ስለማትሰሙ ነው፤ 6ነገር ግን ከፍጥረት መጀመሪያ አንሥቶ ‘እግዚአብሔር ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፤ #ዘፍ. 1፥27፤ 5፥2። 7ስለዚህ ሰው አባትና እናቱን ትቶ ከሚስቱ ጋር ይተባበራል፤ 8ሁለቱም አንድ አካል ይሆናሉ፤’ ከዚያም ወዲያ ሁለት መሆናቸው ቀርቶ አንድ ይሆናሉ። #ዘፍ. 2፥24። 9እንግዲህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።”
10ወደ ቤት በተመለሱ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ጉዳይ እንደገና ኢየሱስን ጠየቁት፤ 11እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሚስቱን ፈቶ ሌላ ሴት የሚያገባ በሚስቱ ላይ አመንዝሮአል፤ #ማቴ. 5፥32፤ 1ቆሮ. 7፥10-11። 12እንዲሁም ባልዋን ፈታ ሌላ ወንድ የምታገባ ሴት አመንዝራ ሆናለች ማለት ነው።”
ኢየሱስ ሕፃናትን መባረኩ
(ማቴ. 19፥13-15ሉቃ. 18፥15-17)
13ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው ሕፃናቱን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ሕፃናቱን ያመጡአቸውን ሰዎች ገሠጹአቸው። 14ኢየሱስም ይህን በማየት ተቈጥቶ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “የእግዚአብሔር መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ስለ ሆነች ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ፤ ተዉ፤ አትከልክሉአቸው፤ 15በእውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን ሆኖ የማይቀበላት ከቶ አይገባባትም።” #ማቴ. 18፥3። 16ከዚህ በኋላ ሕፃናቱን ዐቀፋቸውና እጁን ጭኖ ባረካቸው።
የምድር ሀብትና የእግዚአብሔር መንግሥት
(ማቴ. 19፥16-30ሉቃ. 18፥18-30)
17ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ በመሄድ ላይ ሳለ አንድ ሰው ወደ እርሱ ሮጦ በፊቱ ተንበረከከና “ቸር መምህር ሆይ፥ የዘለዓለምን ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ ይገባኛል?” ሲል ጠየቀው። 18ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ስለምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ማንም ቸር የለም፤ 19ትእዛዞችን ታውቃለህ፤ እነርሱም ‘አትግደል፤ አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አታታል፤ አባትህንና እናትህን አክብር፤’ የተባሉት ናቸው።” #ዘፀ. 20፥12-16፤ ዘዳ. 5፥16-20።
20ሰውየውም “መምህር ሆይ፥ እነዚህንማ ትእዛዞች ከልጅነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ፤” አለው።
21ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው፤ እንዲህም አለው፦ “አንድ ነገር ብቻ ቀርቶሃል፤ ሂድ፤ ያለህን ሁሉ ሸጠህ ገንዘብህን ለድኾች ስጥ፤ የተከማቸ ሀብት በሰማይ ታገኛለህ፤ ከዚህም በኋላ ና፤ ተከተለኝ።” 22ሰውየውም ይህን በሰማ ጊዜ ፊቱ በሐዘን ጠቈረ፤ ብዙ ንብረትም ስለ ነበረው እያዘነ ሄደ።
23ኢየሱስ ዘወር ብሎ ተመለከተና ደቀ መዛሙርቱን፦ “ለሀብታሞች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት አስቸጋሪ ነው!” አላቸው።
24ደቀ መዛሙርቱም በቃሉ ተደነቁ፤ ኢየሱስ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ልጆች ሆይ! ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት አስቸጋሪ ነው! 25ሀብታም ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል።”
26ደቀ መዛሙርቱም በጣም ተገረሙና፥ “ታዲያ በዚህ ሁኔታ ማን ሊድን ይችላል?” ተባባሉ።
27ኢየሱስም ወደ እነርሱ ተመልክቶ፦ “እርግጥ ይህ ነገር በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ይቻላል፤ ለእግዚአብሔር ሁሉ ነገር ይቻለዋል፤” አላቸው።
28ጴጥሮስም “እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል፤” አለው።
29ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ብሎ ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም እናትን ወይም አባትን ወይም ልጆችን ወይም ርስትን የሚተው ሰው ይበልጥ ያገኛል፤ 30በዚህ ዘመን እንኳ ከስደት ጋር ቤቶችን፥ ወንድሞችን፥ እኅቶችን፥ እናቶችን፥ ልጆችን፥ ርስትን በመቶ እጥፍ ይቀበላል፤ በሚመጣውም ዓለም የዘለዓለምን ሕይወት ያገኛል። 31ይሁን እንጂ ፊተኞች የሆኑት ብዙዎች ኋለኞች ይሆናሉ፤ ኋለኞች የሆኑትም ፊተኞች ይሆናሉ።” #ማቴ. 20፥16።
ኢየሱስ ስለ መሞቱና ከሞት ስለ መነሣት ለሦስተኛ ጊዜ አስቀድሞ እንደ ተናገረ
(ማቴ. 20፥17-19ሉቃ. 18፥31-34)
32ወደ ኢየሩሳሌም በሚወስደው መንገድ ሳሉ፥ ኢየሱስ እፊት እፊታቸው ይሄድ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም በዚህ ነገር ተገረሙ፤ በስተኋላ የሚከተሉትም ፈርተው ነበር። እንደገናም ዐሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ አቅርቦ፥ ስለሚደርስበት ነገር እንዲህ ሲል ገለጸላቸው፦ 33“እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዳችን ነው፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለሕግ መምህራን ተላልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም የሞት ፍርድ ይፈርዱበታል፤ ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ 34አሕዛብም ያፌዙበታል፤ ይተፉበታል፤ ይገርፉታል፤ ይገድሉታልም፤ ነገር ግን ከሦስት ቀን በኋላ ይነሣል።”
የያዕቆብና የዮሐንስ ልመና
(ማቴ. 20፥20-28)
35የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ “መምህር ሆይ፥ የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንፈልጋለን፤” አሉት።
36እርሱም “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው።
37እነርሱም “በመንግሥትህ ክብር አንዳችን በቀኝህ፥ አንዳችን በግራህ እንድንቀመጥ ፍቀድልን፤” አሉት።
38ኢየሱስ ግን “የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ የምጠጣውን (የመከራ) ጽዋ መጠጣት ትችላላችሁን? እኔስ የምጠመቀውን ጥምቀት መጠመቅ ትችላላችሁን?” አላቸው። #ሉቃ. 12፥50።
39እነርሱም “አዎ፥ እንችላለን፤” አሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “በእርግጥ እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ፤ እኔም የምጠመቀውን ጥምቀት ትጠመቃላችሁ፤ 40ነገር ግን በቀኜና በግራዬ መቀመጥን የምሰጥ እኔ አይደለሁም፤ ይህ የሚሰጠው እግዚአብሔር ላዘጋጀላቸው ሰዎች ብቻ ነው።”
41የቀሩት ዐሥሩ ይህን ሰምተው በያዕቆብና በዮሐንስ ላይ ተቈጡ። 42ኢየሱስ ሁሉንም ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “የአሕዛብ አለቆች የሕዝብ ገዢዎች ተብለው እንደሚጠሩና መሪዎቻቸውም በእነርሱ ላይ ሥልጣን እንዳላቸው ታውቃላችሁ፤ #ሉቃ. 22፥25-26። 43በእናንተ ዘንድ ግን እንዲህ መሆን አይገባም፤ ከመካከላችሁ ትልቅ ሊሆን የሚፈልግ፥ አገልጋያችሁ መሆን አለበት፤ #ማቴ. 23፥11፤ ማር. 9፥35፤ ሉቃ. 22፥60። 44እንዲሁም ከመካከላችሁ የበላይ ሊሆን የሚፈልግ የሁሉም ባሪያ ይሁን። 45የሰው ልጅ እንኳ ለማገልገልና ሕይወቱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት መጣ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።”
ኢየሱስ የዐይነ ስውሩን የበርጤሜዎስን ዐይን ማዳኑ
(ማቴ. 20፥29-34ሉቃ. 18፥35-43)
46ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ኢያሪኮ ከተማ መጣ። አልፎም ከከተማው ወጥቶ በሚሄድበት ጊዜ እጅግ ብዙ ሕዝብ ይከተለው ነበር፤ በመንገድ ዳር ደግሞ የጤሜዎስ ልጅ የሆነ በርጤሜዎስ የሚባል አንድ ዕውር ተቀምጦ ይለምን ነበር። 47በዚያም የሚያልፈው የናዝሬቱ ኢየሱስ መሆኑን ባወቀ ጊዜ “የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ እባክህ ራራልኝ!” እያለ ይጮኽ ጀመር።
48ብዙዎቹ “ዝም በል!” ብለው ገሠጹት፤ እርሱ ግን “የዳዊት ልጅ ሆይ! እባክህ ማረኝ!” እያለ ይበልጥ ጮኸ።
49ኢየሱስም ቆመና “ጥሩት!” አለ፤ እነርሱም ዕውሩንም “በል በርታ! ተነሥ! ኢየሱስ ይጠራሃል!” አሉት።
50እርሱም ሸማውን ጣለና ዘሎ ተነሥቶ ወደ ኢየሱስ ሄደ።
51ኢየሱስም “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” ሲል ጠየቀው።
ዕውሩም ሰው፥ “መምህር ሆይ፥ እባክህ ዐይኔ እንዲያይ አድርግልኝ፤” አለው።
52ኢየሱስም “በል ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል፤” አለው።
ሰውየውም ወዲያውኑ ማየት ቻለ፤ በመንገድም ኢየሱስን ተከትሎ ሄደ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮዎች ለየማርቆስ ወንጌል 10