እንዲዳስሳቸውም ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ያመጡአቸውን ገሠጹአቸው። ኢየሱስ ግን አይቶ ተቈጣና “ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉ፤ አትከልክሉአቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ናትና። እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም፤” አላቸው። አቀፋቸውም እጁንም ጭኖ ባረካቸው። እርሱም በመንገድ ሲወጣ አንድ ሰው ወደ እርሱ ሮጦ ተንበረከከለትና “ቸር መምህር ሆይ! የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም “ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም። ትእዛዛትን ታውቃለህ፤ አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አታታልል፥ አባትህንና እናትህን አክብር፤” አለው። እርሱም መልሶ “መምህር ሆይ! ይህን ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ፤” አለው። ኢየሱስም ወደ እርሱ ተመልክቶ ወደደውና “አንድ ነገር ጐደለህ፤ ሂድ፤ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፤ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፤ መስቀሉንም ተሸክመህ ና፤ ተከተለኝ፤” አለው። ነገር ግን ስለዚህ ነገር ፊቱ ጠቈረ፤ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነም ሄደ። ኢየሱስም ዘወር ብሎ አይቶ ደቀ መዛሙርቱን “ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል፤” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም እነዚህን ቃሎች አደነቁ። ኢየሱስም ደግሞ መልሶ “ልጆች ሆይ! በገንዘብ ለሚታመኑ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው። ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል፤” አላቸው። እነርሱም ያለ መጠን ተገረሙና እርስ በርሳቸው “እንግዲያ ማን ሊድን ይችላል?” ተባባሉ። ኢየሱስም ተመለከታቸውና “ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ እንጂ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላልና፤” አለ። ጴጥሮስም “እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤” ይለው ጀመር። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ “እውነት እላችኋለሁ፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፥ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንና እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም። ግን ብዙ ፊተኞች ኋለኞች ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ።” ወደ ኢየሩሳሌምም ሊወጡ በመንገድ ነበሩ፤ ኢየሱስም ይቀድማቸው ነበርና ተደነቁ፤ የተከተሉትም ይፈሩ ነበር። ደግሞም ዐሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ አቅርቦ ይደርስበት ዘንድ ያለውን ይነግራቸው ጀመር “እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች አልፎ ይሰጣል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፤ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል፤ ይዘብቱበትማል፤ ይተፉበትማል፤ ይገርፉትማል፤ ይገድሉትማል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል፤” አላቸው።
የማርቆስ ወንጌል 10 ያንብቡ
ያዳምጡ የማርቆስ ወንጌል 10
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 10:13-34
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos