የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሚክያስ 7:1-6

ሚክያስ 7:1-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ለእኔ ወዮልኝ! የወይን ዕርሻ በሚቃረምበት ጊዜ፣ የበጋ ፍራፍሬ እንደሚለቅም ሰው ሆኛለሁ፤ የሚበላ የወይን ዘለላ የለም፤ የምንጓጓለት፣ ቶሎ የሚደርሰው በለስም አልተገኘም። ፈሪሀ እግዚአብሔር ያደረበት ሰው ከምድር ጠፍቷል፤ አንድም እንኳ ቅን ሰው የለም፤ ሰው ሁሉ ደም ለማፍሰስ ያደባል፤ እያንዳንዱም ወንድሙን በመረብ ያጠምዳል። እጆቹ ክፉ ለማድረግ ሠልጥነዋል፤ ገዥው እጅ መንሻ ይፈልጋል፤ ፈራጁ ጕቦ ይቀበላል፤ ኀይለኞች ያሻቸውን ያስፈጽማሉ፤ ሁሉም አንድ ላይ ያሤራሉ። ከእነርሱ ይሻላል የተባለው እንደ አሜከላ፣ እጅግ ቀና የተባለውም እንደ ኵርንችት ነው፤ የጠባቂዎቻችሁ ቀን ደርሷል፤ የእግዚአብሔር የፍርድ ቀን መጥቷል፤ የሚሸበሩበትም ጊዜ አሁን ደርሷል። ባልንጀራህን አትመን፤ በጓደኛህም አትታመን፤ በዕቅፍህ ለምትተኛዋ እንኳ፣ ስለምትነግራት ቃል ተጠንቀቅ። ወንድ ልጅ አባቱን ይንቃል፤ ሴት ልጅ በእናቷ ላይ፣ ምራት በዐማቷ ላይ ትነሣለች፤ የሰው ጠላቶች የገዛ ቤተ ሰዎቹ ናቸውና።

ሚክያስ 7:1-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

የመከር ፍሬ ተሰብስቦ የወይኑም ቃርሚያ ከተቃረመ በኋላ ሊበላ የሚፈልገውን የወይን ዘለላ እንደማያገኝ ሰው ስለ ሆንኩ ወዮልኝ! እኔ የምመኘውም አስቀድሞ የደረሰው የበለስ ፍሬ የለም። ከምድሪቱ ላይ ታማኝ ሰው ጠፍቶአል፤ አንድም ትክክለኛ ሰው የለም፤ ሁላቸውም ሰውን ለመግደል ያደባሉ፤ እርስ በርሳቸውም አንዱ ሌላውን ተከታትሎ ያጠምዳል። እጆቻቸው ክፉ ነገርን ለማድረግ የተለማመዱ ናቸው፤ ባለ ሥልጣኑና ዳኛው ጉቦ ይጠይቃሉ፤ ኀይለኛ ፍላጎቱን በግዴታ ተግባራዊ ያስደርጋል፤ በዚህም ዐይነት ሁሉም ፍርድን ያጣምማሉ። ከእነርሱ መካከል እጅግ የተሻለ ነው የተባለው ሰው እንደ አሜከላ ነው፤ እጅግ ትክክለኛ ነው የተባለው እንደ ኲርንችት ነው፤ በነቢያቱ አማካይነት ባስጠነቀቃቸው መሠረት እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚቀጣበት ጊዜ ይመጣል፤ እነሆ አሁንም ቢሆን በሽብር ላይ ይገኛሉ። በሰው ላይ እምነትህን አትጣል፤ በቅርብ ወዳጅህም አትተማመን፤ አቅፈሃት ለምትተኛው ሚስትህ የምትናገረው ቃል እንኳ ጥንቃቄ የተሞላበት ይሁን። በዚያን ዘመን ወንድ ልጅ አባቱን ይንቃል፤ ሴት ልጅ በእናትዋ ላይ ምራትም በዐማትዋ ላይ በጠላትነት ይነሣሉ፤ የሰው ጠላቶቹ የገዛ ቤተ ሰዎቹ ይሆናሉ።