የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሚክያስ 7

7
የእስራኤል ሕዝብ የሞራል ውድቀት
1የመከር ፍሬ ተሰብስቦ የወይኑም ቃርሚያ ከተቃረመ በኋላ ሊበላ የሚፈልገውን የወይን ዘለላ እንደማያገኝ ሰው ስለ ሆንኩ ወዮልኝ! እኔ የምመኘውም አስቀድሞ የደረሰው የበለስ ፍሬ የለም። 2ከምድሪቱ ላይ ታማኝ ሰው ጠፍቶአል፤ አንድም ትክክለኛ ሰው የለም፤ ሁላቸውም ሰውን ለመግደል ያደባሉ፤ እርስ በርሳቸውም አንዱ ሌላውን ተከታትሎ ያጠምዳል። 3እጆቻቸው ክፉ ነገርን ለማድረግ የተለማመዱ ናቸው፤ ባለ ሥልጣኑና ዳኛው ጉቦ ይጠይቃሉ፤ ኀይለኛ ፍላጎቱን በግዴታ ተግባራዊ ያስደርጋል፤ በዚህም ዐይነት ሁሉም ፍርድን ያጣምማሉ። 4ከእነርሱ መካከል እጅግ የተሻለ ነው የተባለው ሰው እንደ አሜከላ ነው፤ እጅግ ትክክለኛ ነው የተባለው እንደ ኲርንችት ነው፤
በነቢያቱ አማካይነት ባስጠነቀቃቸው መሠረት እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚቀጣበት ጊዜ ይመጣል፤ እነሆ አሁንም ቢሆን በሽብር ላይ ይገኛሉ። 5በሰው ላይ እምነትህን አትጣል፤ በቅርብ ወዳጅህም አትተማመን፤ አቅፈሃት ለምትተኛው ሚስትህ የምትናገረው ቃል እንኳ ጥንቃቄ የተሞላበት ይሁን። 6በዚያን ዘመን ወንድ ልጅ አባቱን ይንቃል፤ ሴት ልጅ በእናትዋ ላይ ምራትም በዐማትዋ ላይ በጠላትነት ይነሣሉ፤ የሰው ጠላቶቹ የገዛ ቤተ ሰዎቹ ይሆናሉ። #ማቴ. 10፥35-36፤ ሉቃ. 12፥53።
7እኔ ግን እግዚአብሔርን ተስፋ አደርጋለሁ፤ የሚያድነኝን አምላክ እጠባበቃለሁ፤ እርሱም ይሰማኛል።
ደኅንነት ከእግዚአብሔር ነው
8ጠላቴ ሆይ! እኔ ብወድቅም እንኳ እንደገና እነሣለሁና በእኔ ደስ አይበልህ፤ አሁን በጨለማ ውስጥ ብሆንም እግዚአብሔር ያበራልኛል። 9እግዚአብሔርን በድዬዋለሁ፤ ስለዚህም እርሱ የቀረበብኝን ክስ ተመልክቶ እስኪፈርድልኝ ድረስ ቊጣውን እታገሣለሁ፤ በመጨረሻም እርሱ ወደ ብርሃን ያወጣኛል፤ ፍትሕንም ይሰጠኛል። 10ጠላቴም ይህን ሁሉ ያያል፤ “አምላክህ እግዚአብሔር የት አለ?” ይለኝ የነበረው ጠላቴ ኀፍረትን ይከናነባል፤ እኔ የጠላቴን ውድቀት አያለሁ፤ በመንገድ ዳር እንዳለ ጭቃ ሲረገጥም እመለከታለሁ።
11እናንተ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ! የከተማይቱ ቅጽሮች የሚሠሩበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ግዛታችሁ ይሰፋል። 12በዚያን ጊዜ ሕዝባችሁ ወደ እናንተ ይመለሳል፤ ይኸውም በስተ ምሥራቅ ከአሦር፥ በስተ ደቡብ ከግብጽ፥ ከኤፍራጥስ ወንዝ አካባቢ፥ እንዲሁም ከሩቅ ባሕሮችንና ተራራዎችን አቋርጠው ይመጣሉ። 13ምድሪቱ ግን ከሚኖሩባት ሰዎች ክፋት የተነሣ ባድማ ትሆናለች።
እግዚአብሔር ለእስራኤል ያሳየው ርኅራኄ
14እግዚአብሔር ሆይ! የአንተ መንጋ የሆነውን ሕዝብህን በሥልጣንህ ጠብቅ፤ እነርሱም በለመለመ አትክልት ቦታ መካከል በጫካ ውስጥ ብቻቸውን የሚኖሩ ናቸው፤ እንደ ቀድሞው ዘመን በባሳንና በገለዓድ እንዲመገቡ አድርጋቸው።
15ከግብጽ ምድር ባወጣኸን ጊዜ እንዳደረግኸው ተአምራትን አሳየን። 16ኀይል ያላቸው ቢሆኑም ይህን አይተው ያፍራሉ፤ እጆቻቸውን በአፋቸው ላይ ያኖራሉ፤ ጆሮዎቻቸውንም ይደፍናሉ። 17እንደ እባብና እንደ ሌሎችም ተንፏቃቂ ፍጥረቶች ትቢያ ይልሳሉ፤ ከምሽጎቻቸው ወጥተው እየተንቀጠቀጡ ይመጣሉ፤ በፍርሃትም ወደ አንተ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ይመለሳሉ፤ አንተንም እየፈሩ ይኖራሉ።
18ኃጢአትን ይቅር የሚል፥ በቀሪውም ሕዝቡ ላይ በደልን የማይቈጥር እንደ አንተ ያለ አምላክ ማን ነው? ምሕረት ማድረግ ስለሚያስደስትህ ቊጣህ ለዘለዓለም የሚቈይ አይደለም። 19እንደገና ትራራልናለህ፤ በደላችንን በእግርህ ሥር ጥለህ ትረግጣለህ፤ ኃጢአታችንንም ሁሉ ወደ ጥልቅ ባሕር ትጥላለህ። 20ለቀደሙ አባቶቻችን በማልክላቸው መሠረት ለአብርሃምና ለያዕቆብ ዘር ታማኝነትህንና ዘለዓለማዊ ፍቅርህን ታሳያለህ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ