የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሚክያስ 6

6
እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ እንደ ወቀሰ
1እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ ላይ የሚናገረውን ስሙ፤
ተነሡ! ያላችሁን ቅርታ በተራሮች ፊት አቅርቡ! ኰረብቶችም የምትሉትን ይስሙ።
2እናንተ ተራራዎች! እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ የሚያቀርበውን ወቀሳ ስሙ! እናንተም ጠንካራ የሆናችሁ የምድር መሠረቶች! አድምጡ! እግዚአብሔር ሕዝቡን እስራኤልን ይወቅሳል ይገሥጻልም።
3እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ሕዝቤ ሆይ! ምን አደረግሁህ? ያከበድኩብህስ ነገር ምንድን ነው? እስቲ መልስልኝ። 4ከግብጽ አወጣሁህ፤ ከባርነት ምድርም ታደግኹህ፤ ሙሴን፥ አሮንንና ማርያምን በፊትህ መሪዎች አድርጌ ሰጠሁህ። 5ሕዝቤ ሆይ! የሞአብ ንጉሥ ባላቅ ምን እንደ ዐቀደብህና የቢዖር ልጅ በለዓም ምን እንደ መለሰለት አስታውስ፤ ከሺጢም ተነሥተህ ወደ ጌልጌላ በምትሄድበት ጊዜ በመንገድ ላይ የሆነውን ሁሉ አስታውስ፤ ይህን ሁሉ ብታስታውስ አንተን ለማዳን ያደረግኹትን ሁሉ ታውቃለህ።” #ዘኍ. 22፥2—24፥25፤ ኢያሱ 3፥1—4፥19።
እግዚአብሔር ከሕዝቡ የሚፈልገው ነገር
6ለኀያሉ አምላክ ለእግዚአብሔር ለመስገድ በምመጣበት ጊዜ ምን ይዤ ልቅረብ? ለእርሱ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆኑ ዘንድ የአንድ ዓመት ጥጆችን ይዤ ልምጣን? 7በሺህ የሚቈጠሩ አውራ በጎችን ወይም የዐሥር ሺህ ወንዞችን ውሃ የሚያኽል የወይራ ዘይት ባቀርብለት ይደሰት ይሆን? ስለ በደሌና ስለ ኃጢአቴ የበኲር ልጄን ልሠዋለትን? 8እግዚአብሔር መልካም የሆነውንና ከአንተ የሚፈልገውን ነግሮሃል፤ ይኸውም ፍትሕን እንድትጠብቅ፥ ደግነትን እንድትወድ፥ ከአምላክህ ጋር በትሕትና እንድትመላለስ ነው።
9እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው፤ እርሱ ከተማይቱን እንዲህ ይላል፦ “እናንተ በከተማይቱ የተሰበሰባችሁ ሰዎች አድምጡ! 10ኃጢአተኛ በቤቱ በክፋት የሰበሰበውን ሀብትና የተረገመውን ሐሰተኛ ሚዛን ልረሳቸው እችላለሁን? 11ታዲያ በሐሰተኛ ሚዛንና መስፈሪያ የሚጠቀሙትን ሰዎች እታገሣለሁን? 12ሀብታሞቻችሁ በግፍ የተሞሉ ናቸው፤ የከተማይቱ ነዋሪዎችም ሐሰትን ይናገራሉ፤ በአንደበቶቻቸውም ይሸነግላሉ። 13ስለዚህ በኃጢአታችሁ ምክንያት እናንተን ለማጥፋትና ለመደምሰስ ተነሥቼአለሁ። 14ትበላላችሁ አትጠግቡም፤ ራቡም አይወገድላችሁም፤ ታግበሰብሳላችሁ እንጂ አይከማችላችሁም፤ ያጠራቀማችሁት ሀብት ቢኖርም በጦርነት አጠፋዋለሁ። 15እህል ትዘራላችሁ ሰብል ግን አትሰበስቡም፤ የወይራ ፍሬ ትጨምቃላችሁ፤ ነገር ግን በዘይቱ አትጠቀሙም፤ የወይን ፍሬ ትጨምቃላችሁ፤ የወይን ጠጅ ግን አትጠጡም። 16ይህ ሁሉ የሚደርስባችሁ የንጉሥ ዖምሪን ሥርዓት ስለ ጠበቃችሁና የንጉሥ አክዓብን አካሄድ ሁሉ ስለ ተከተላችሁ ነው፤ በእነርሱ ባህል ስለ ተመራችሁ አጠፋችኋለሁ፤ የከተማይቱን ነዋሪዎችም የሰው ሁሉ መሳቂያ አደርጋቸዋለሁ፤ በሕዝቤ ላይ የተሰነዘረውን ነቀፋ እንድትሸከሙ አደርጋችኋለሁ።” #1ነገ. 16፥23-34፤ 21፥25-26።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ