ትንቢተ ሚክያስ 7
7
1የዛፍ ፍሬና የወይን ፍሬ ከተለቀሙ በኋላ እንደ ቀረው ቃርሚያ ሆኛለሁና ወዮልኝ! መብል የሚሆን ዘለላ፥ ነፍሴም የተመኘችው በመጀመሪያ የበሰለው በለስ የለም። 2ደግ ሰው ከምድር ጠፍቶአል፥ በሰውም መካከል ቅን የለም፥ ሁሉ ደምን ለማፍሰስ ያደባሉ፥ ሰውም ሁሉ ወንድሙን በመረብ ለመያዝ ይከታተለዋል። 3እጆቻቸውን ለክፋት ያነሣሉ፥ አለቃውና ፈራጁ ጉቦን ይፈልጋሉ፥ ትልቁም ሰው እንደ ነፍሱ ምኞት ይናገራል፥ እንዲሁም ክፋትን ይጐነጕናሉ። 4ከእነርሱም ሁሉ የተሻለው እርሱ እንደ አሜከላ ነው፥ ከሁሉም ቅን የሆነው እንደ ኵርንችት ነው፥ ጠባቆችህ የሚጐበኙበት ቀን መጥቶአል፥ አሁን ይሸበራሉ። 5ባልንጀራን አትመኑ፥ በወዳጅም አትታመኑ፥ የአፍህን ደጅ በብብትህ ከምትተኛው ጠብቅ። 6ወንድ ልጅ አባቱን ይንቃልና፥ ሴት ልጅ በእናትዋ ላይ፥ ምራቲቱም በአማትዋ ላይ ትነሣለችና፥ የሰው ጠላቶች የቤቱ ሰዎች ናቸውና።
7እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር እመለከታለሁ፥ የመድኃኒቴንም አምላክ ተስፋ አደርጋለሁ፥ አምላኬም ይሰማኛል። 8ጠላቴ ሆይ፥ ብወድቅ እነሣለሁና፥ በጨለማም ብቀመጥ እግዚአብሔር ብርሃን ይሆንልኛልና በእኔ ላይ ደስ አይበልሽ። 9በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠርቻለሁና እስኪምዋገትልኝ ድረስ፥ ፍርድን ለእኔ እስኪያደርግ ድረስ ቍጣውን እታገሣለሁ። ወደ ብርሃን ያወጣኛል፥ ጽድቅንም አያለሁ። 10ጠላቴም ታያለች፥ እኔንም፦ አምላክህ እግዚአብሔር ወዴት ነው? ያለች በእፍረት ትከደናለች። 11ዓይኖቼ ይመለከቱአታል፥ አሁን እንደ መንገድ ጭቃ ትረገጣለች። ቅጥርሽ በሚሠራበት በዚያ ቀን ድንበርሽ ትስፋፋለች። 12በዚያ ቀን ከአሦርና ከግብጽ ከተሞች፥ ከግብጽ እስከ ወንዙ፥ ከባሕርም እስከ ባሕር፥ ከተራራም እስከ ተራራ ድረስ ወደ አንቺ ይመጣሉ። 13ምድሪቱ ግን በሚኖሩባት በሥራቸው ፍሬ ምክንያት ባድማ ትሆናለች።
14በቀርሜሎስ መካከል ባለው ዱር ብቻቸውን የተቀመጡት ሰዎችህ፥ የርስትህን በጎች፥ በበትርህ አግድ፥ እንደ ቀደመውም ዘመን በበሳንና በገለዓድ ይሰማሩ። 15ከግብጽ ምድር እንደ ወጣህበት ዘመን ተአምራትን አሳያቸዋለሁ። 16አሕዛብ አይተው በጕልበታቸው ሁሉ ያፍራሉ፥ እጃቸውን በአፋቸው ላይ ያኖራሉ፥ ጆሮአቸውም ትደነቍራለች፥ እንደ እባብም መሬት ይልሳሉ፥ 17እንደ ምድርም ተንቀሳቃሾች እየተንቀጠቀጡ ከግንባቸው ይመጣሉ፥ ፈርተውም ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ይመጣሉ፥ ስለ አንተም ይፈራሉ።
18በደልን ይቅር የሚል፥ የርስቱንም ቅሬታ ዓመፅ የሚያሳልፍ እንደ አንተ ያለ አምላክ ማን ነው? ምሕረትን ይወድዳልና ቍጣውን ለዘላለም አይጠብቅም። 19ተመልሶ ይምረናል፥ ክፋታችንንም ይጠቀጥቃል፥ ኃጢአታችንንም በባሕሩ ጥልቅ ይጥለዋል። 20ከቀድሞ ዘመን ጀምረህ ለአባቶቻችን የማልህላቸውን እውነት ለያዕቆብ፥ ምሕረትንም ለአብርሃም ታደርጋለህ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሚክያስ 7: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ