የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሚክያስ 6

6
1አሁን፦ ተነሣ፥ በተራሮችም ፊት ተፋረድ፥ ኮረብቶችም ቃልህን ይስሙ ብሎ እግዚአብሔር የሚለውን ስሙ። 2ተራሮች ሆይ፥ ጠንካሮች የምድር መሠረቶችም ሆይ፥ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ክርክር አለውና፥ ከእስራኤልም ጋር ይፋረዳልና የእግዚአብሔርን ክርክር ስሙ። 3ሕዝቤ ሆይ፥ ምን አድርጌለሁ? በምንስ አድክሜሃለሁ? መስክርብኝ። 4ከግብጽ ምድር አውጥቼሃለሁ፥ ከባርነት ቤትም ተቤዥቼሃለሁ፥ በፊትህም ሙሴንና አሮንን ማርያምንም ልኬልህ ነበር። 5ሕዝቤ ሆይ፥ የሞዓብ ንጉሥ ባላቅ የመከረውን፥ የቢዖርም ልጅ በለዓም የመለሰለትን አሁን አስብ፥ የእግዚአብሔርንም የጽድቅ ሥራ ታውቅ ዘንድ ከሰጢም ጀምሮ እስከ ጌልገላ ድረስ አስብ።
6ምን ይዤ ወደ እግዚአብሔር ፊት ልምጣና በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ? የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንዱን ዓመት ጥጃ ይዤ በፊቱ ልምጣን? 7እግዚአብሔርስ በሺህ አውራ በጎች ወይስ በእልፍ የዘይት ፈሳሾች ደስ ይለዋልን? ወይስ የበኵር ልጄን ስለ በደሌ፥ የሆዴንም ፍሬ ስለ ነፍሴ ኃጢአት እሰጣለሁን? 8ሰው ሆይ፥ መልካሙን ነግሮሃል፥ እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፥ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፥ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን?
9የእግዚአብሔር ድምፅ ከተማይቱን ይጠራታል፥ ስምህን መፍራት ጥበብ ነው፥ የመቅሠፍትን በትር፥ እርሱንም ያዘጋጀ ማን እንደ ሆነ ስሙ። 10በውኑ በኃጢአተኛ ቤት የኃጢአት መዝገብ፥ የተጸየፈውም ውሸተኛ መስፈሪያ ገና አለ ይሆን? 11በአባይ ሚዛንና በከረጢት ባለ በተንኰል መመዘኛ ንጹሕ እሆናለሁን? 12ባለ ጠጎችዋን ግፍ ሞልቶባቸዋል፥ በእርስዋም የሚኖሩ በሐሰት ተናግረዋል፥ ምላሳቸውም በአፋቸው ውስጥ ተንኰለኛ ነው። 13ስለዚህ እኔ ደግሞ በክፉ ቍስል መታሁህ፥ ስለ ኃጢአትህም አፈረስሁህ። 14ትበላለህ፥ ነገር ግን አትጠግብም፥ ችጋርህም በመካከልህ ይሆናል፥ ትወስዳለህ፥ ነገር ግን አታድንም፥ የምታድነውንም ለሰይፍ እሰጣለሁ። 15ትዘራለህ፥ ነገር ግን አታጭድም፥ ወይራውንም ትጨምቃለህ፥ ነገር ግን ዘይቱን አትቀባም፥ ወይኑንም ትጨምቃለህ፥ ነገር ግን የወይን ጠጁን አትጠጣም። 16አንተን ለጥፋት፥ በእርስዋም የሚኖሩትን ለማፍዋጫ እሰጥ ዘንድ የዘንበሪን ሥርዓትና የአክዓብን ቤት ሥራ ሁሉ ጠብቃችኋል፥ በምክራቸውም ሄዳችኋል፥ የሕዝቤንም ስድብ ትሸከማላችሁ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ