የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማቴዎስ 27:31-56

ማቴዎስ 27:31-56 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከዘበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፤ ልብሱንም አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ወሰዱት። ሲወጡም ስምዖን የተባለው የቀሬናን ሰው አገኙ፤ እርሱንም መስቀሉን ይሸከም ዘንድ አስገደዱት። ትርጓሜው የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሆን ጎልጎታ ወደሚባለው ስፍራ በደረሱ ጊዜም፥ በሐሞት የተደባለቀ የወይን ጠጅ ሊጠጣ አቀረቡለት፤ ቀምሶም ሊጠጣው አልወደደም። ከሰቀሉትም በኋላ ልብሱን ዕጣ ጥለው ተካፈሉ፤ በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር። “ይህ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ ነው፤” የሚል የክሱን ጽሕፈት ከራሱ በላይ አኖሩ። በዚያን ጊዜ ሁለት ወንበዴዎች አንዱ በቀኝ አንዱም በግራ ከእርሱ ጋር ተሰቀሉ። የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበር፤ “ቤተ መቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራው፥ ራስህን አድን፤ የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ ከመስቀል ውረድ፤” አሉት። እንዲሁም ደግሞ የካህናት አለቆች ከጻፎችና ከሽማግሎች ጋር እየዘበቱበት እንዲህ አሉ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ሊያድን አይችልም፤ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ፥ አሁን ከመስቀል ይውረድ፤ እኛም እናምንበታለን። በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ፤’ ብሎአልና ከወደደውስ አሁን ያድነው።” ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዴዎች ደግሞ ያንኑ እያሉ ይነቅፉት ነበር። ከስድስት ሰዓትም ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ “ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ?” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም “አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ?” ማለት ነው። በዚያም ከቆሙት ሰዎች ሰምተው “ይህስ ኤልያስን ይጠራል፤” አሉ። ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጠ፤ ሰፍነግም ይዞ ሆምጣጤ ሞላበት፤ በመቃም አድርጎ አጠጣው። ሌሎቹ ግን “ተው፤ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደ ሆነ እንይ፤” አሉ። ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ተወ። እነሆም፥ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፤ ምድርም ተናወጠች፤ ዐለቶችም ተሰነጠቁ፤ መቃብሮችም ተከፈቱ፤ ተኝተው ከነበሩትም ከቅዱሳን ብዙ ሥጋዎች ተነሡ፤ ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ። የመቶ አለቃም ከእርሱም ጋር ኢየሱስን የሚጠብቁ መናወጡንና የሆነውን ነገር አይተው “ይህ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ፤” ብለው እጅግ ፈሩ። ኢየሱስን እያገለገሉ ከገሊላ የተከተሉት ብዙ ሴቶች በሩቅ ሆነው ሲመለከቱ በዚያ ነበሩ፤ ከእነርሱም መግደላዊት ማርያምና የያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ነበሩ።

ማቴዎስ 27:31-56 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ካሾፉበት በኋላም ቀዩን ልብስ ገፍፈው የራሱን መጐናጸፊያ አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ይዘውት ሄዱ። ይዘውትም ሲሄዱ ስምዖን ተብሎ የሚጠራ የቀሬና ሰው አገኙ፤ መስቀሉንም እንዲሸከም አስገደዱት። ትርጕሙ፣ “የራስ ቅል ስፍራ” ከሆነው ጎልጎታ ከተባለው ቦታ ሲደርሱ፣ ከሐሞት ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን ቀምሶ ሊጠጣው አልፈቀደም። ከሰቀሉትም በኋላ ዕጣ ጥለው ልብሱን ተካፈሉ፤ በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር። ከራስጌውም፣ “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ኢየሱስ ነው” የሚል የክስ ጽሑፍ አኖሩ። ሁለት ወንበዴዎች አንዱ በቀኙ፣ አንዱ በግራው አብረውት ተሰቅለው ነበር። መንገድ ዐላፊዎችም በኀይል እየተሳደቡና ራሳቸውን እየነቀነቁ፣ “ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን ውስጥ የምትሠራው፤ እስቲ ራስህን አድን! የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ በል ከመስቀል ውረድ!” ይሉት ነበር። የካህናት አለቆችም ከኦሪት ሕግ መምህራንና ከሽማግሌዎች ጋር ሆነው እያሾፉበት እንዲህ ይሉ ነበር፤ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አይችልም! የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ አሁን ከመስቀል ይውረድ፤ እኛም እናምንበታለን። በእግዚአብሔር ታምኗል፤ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ይል ስለ ነበር እስቲ ከወደደው አሁን ያድነው!” ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዴዎችም እንደዚሁ የስድብ ናዳ ያወርዱበት ነበር። ከቀኑ ስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። በዘጠኝ ሰዓት ገደማ፣ ኢየሱስ ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ኤሎሄ! ኤሎሄ! ላማ ሰበቅታኒ?” እያለ ጮኸ፤ ትርጕሙም “አምላኬ፤ አምላኬ፤ ለምን ተውኸኝ?” ማለት ነው። በዚያ ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ጩኸቱን ሲሰሙ፣ “ኤልያስን እየተጣራ ነው!” አሉ። ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጦ ሰፍነግ በመውሰድ የኮመጠጠ ወይን ጠጅ ውስጥ ነከረው፤ ሰፍነጉንም በሸንበቆ ዘንግ ጫፍ ላይ በማድረግ እንዲጠጣው ለኢየሱስ አቀረበለት። የቀሩት ግን፣ “ተዉት፤ እስቲ ኤልያስ መጥቶ ሲያድነው እናያለን!” አሉ። ኢየሱስ እንደ ገና ከፍ ባለ ድምፅ ጮኸ፤ መንፈሱንም አሳልፎ ሰጠ። በዚያን ጊዜ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ፤ ምድር ተናወጠች፤ ዐለቶችም ተሰነጣጠቁ፤ መቃብሮች ተከፈቱ፤ አንቀላፍተው የነበሩትም ብዙዎች ቅዱሳን ተነሡ፤ ከመቃብርም በመውጣት ከኢየሱስ ትንሣኤ በኋላ ወደ ቅድስት ከተማ ገብተው ለብዙዎች ታዩ። የመቶ አለቃውና አብረውት ኢየሱስን ይጠብቁት የነበሩት የመሬት መናወጡንና የሆነውን ነገር ሁሉ ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው፤ ይህስ፣ “በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር!” አሉ። ከገሊላ የመጡና ኢየሱስን በሚያስፈልገው ነገር ለማገልገል የተከተሉት ብዙ ሴቶች ሁኔታውን ከርቀት እየተመለከቱ በአካባቢው ነበሩ። ከእነርሱም መካከል ማርያም መግደላዊት፣ ማርያም የያዕቆብና የዮሴፍ እናት እንዲሁም የዘብዴዎስ ልጆች እናት ነበሩ።

ማቴዎስ 27:31-56 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከዘበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፥ ልብሱንም አለበሱት ሊሰቅሉትም ወሰዱት። ሲወጡም ስምዖን የተባለው የቀሬናን ሰው አገኙ፤ እርሱንም መስቀሉን ይሸከም ዘንድ አስገደዱት። ትርጓሜው የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሆን ጎልጎታ ወደሚባለው ስፍራ በደረሱ ጊዜም፥ በሐሞት የተደባለቀ የወይን ጠጅ ሊጠጣ አቀረቡለት፤ ቀምሶም ሊጠጣው አልወደደም። ከሰቀሉትም በኋላ ልብሱን ዕጣ ጥለው ተካፈሉ፥ በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር። ይህ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ ነው የሚል የክሱን ጽሕፈት ከራሱ በላይ አኖሩ። በዚያን ጊዜ ሁለት ወንበዶች አንዱ በቀኝ አንዱም በግራ ከእርሱ ጋር ተሰቀሉ። የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበርና፦ ቤተ መቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራው፥ ራስህን አድን፤ የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ ከመስቀል ውረድ አሉት። እንዲሁም ደግሞ የካህናት አለቆች ከጻፎችና ከሽማግሎች ጋር እየዘበቱበት እንዲህ አሉ፦ ሌሎችን አዳነ፥ ራሱን ሊያድን አይችልም፤ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ፥ አሁን ከመስቀል ይውረድ እኛም እናምንበታለን። በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሎአልና ከወደደውስ አሁን ያድነው። ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዶች ደግሞ ያንኑ እያሉ ይነቅፉት ነበር። ከስድስት ሰዓትም ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ፦ ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም፦ አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ? ማለት ነው። በዚያም ከቆሙት ሰዎች ሰምተው፦ ይህስ ኤልያስን ይጠራል አሉ። ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጠ፤ ሰፍነግም ይዞ ሆምጣጤ ሞላበት፥ በመቃም አድርጎ አጠጣው። ሌሎቹ ግን፦ ተው፥ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደ ሆነ እንይ አሉ። ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ተወ። እነሆም፥ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፥ ምድርም ተናወጠች፥ ዓለቶችም ተሰነጠቁ፤ መቃብሮችም ተከፈቱ፥ ተኝተው ከነበሩትም ከቅዱሳን ብዙ ሥጋዎች ተነሡ፤ ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ። የመቶ አለቃም ከእርሱም ጋር ኢየሱስን የሚጠብቁ መናወጡንና የሆነውን ነገር አይተው፦ ይህ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ ብለው እጅግ ፈሩ። ኢየሱስን እያገለገሉ ከገሊላ የተከተሉት ብዙ ሴቶች በሩቅ ሆነው ሲመለከቱ በዚያ ነበሩ፤ ከእነርሱም መግደላዊት ማርያምና የያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ነበሩ።

ማቴዎስ 27:31-56 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ካፌዙበት በኋላ ቀዩን ልብስ አውልቀው የራሱን ልብስ አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ይዘውት ሄዱ። ከገዢው ግቢ ሲወጡ ሳሉ ስምዖን የተባለውን የቀሬና አገር ሰው አገኙና የኢየሱስን መስቀል እንዲሸከም አስገደዱት። ከዚህ በኋላ ትርጒሙ “የራስ ቅል” ወደ ሆነው ወደ ጎልጎታ ደረሱ። በዚያም ከሐሞት ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ለኢየሱስ አቀረቡለት፤ እርሱ ግን ቀመስ አድርጎ ሊጠጣው አልፈለገም። ኢየሱስን ከሰቀሉት በኋላ ልብሱን ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉ። በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር። የተከሰሰበትንም ወንጀል የሚያመለክት፥ “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ኢየሱስ ነው?” የሚል ጽሑፍ በመስቀሉ ራስጌ ላይ አኖሩ። በዚያን ጊዜ ከኢየሱስ ጋር ሁለት ወንበዴዎችን አንዱን በቀኝ አንዱን በግራ ሰቀሉ። በአጠገቡ ያልፉ የነበሩትም ሰዎች በንቀት ራሳቸውን እየነቀነቁ፥ “አንተ ቤተ መቅደስን የምታፈርስና በሦስት ቀን የምትሠራው! እስቲ ራስህን አድን! የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ እስቲ ከመስቀል ውረድ!” በማለት ያላግጡበት ነበር። በዚሁም ዓይነት የካህናት አለቆች ከሕግ መምህራንና ከሽማግሌዎች ጋር እንዲህ እያሉ ያፌዙበት ነበር፤ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አይችልም! እርሱ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ እስቲ አሁን ከመስቀል ይውረድ፤ እኛም እንመንበት! እርሱ በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ብሎአል፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የሚወደው ከሆነ እስቲ አሁን ያድነው!” እንዲሁም ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዴዎች ይሰድቡት ነበር። ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ጨለማ ሆነ። ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ኢየሱስ፦ “ኤሎሄ! ኤሎሄ! ላማ ሰበቅታኒ?” ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም “አምላኬ! አምላኬ! ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው። በዚያም ቆመው ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ ይህን ሰምተው “ይህስ ኤልያስን ይጠራል!” አሉ። በዚያን ጊዜ ከእነርሱ አንዱ ሰፍነግ አምጥቶ ሆምጣጤ ሞላበት፤ በመቃ ላይ አድርጎም ኢየሱስ እንዲጠጣ አቀረበለት። ሌሎች ግን “ቈይ እስቲ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደ ሆነ እንይ!” አሉ። ኢየሱስ እንደገና በታላቅ ድምፅ ጮኸና ነፍሱን ሰጠ። በዚያን ጊዜ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ተቀዶ ከሁለት ተከፈለ፤ ምድርም ተናወጠች፤ አለቶችም ተሰነጠቁ፤ መቃብሮችም ተከፍተው ሞተው ከነበሩት ቅዱሳን ሰዎች ብዙዎች ከሞት ተነሡ። ከመቃብርም ወጡና ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ወደ ቅድስት ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም ገቡ፤ በዚያም ለብዙ ሰዎች ታዩ። የመቶ አለቃውና ከእርሱም ጋር ኢየሱስን ይጠብቁ የነበሩት የምድርን መናወጥና የሆነውንም ነገር ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው “በእውነት ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ!” አሉ። በሩቅ ሆነው የሚመለከቱት ብዙ ሴቶችም በዚያ ነበሩ፤ እነርሱ ከገሊላ ጀምረው ኢየሱስን እያገለገሉ ይከተሉት የነበሩ ናቸው። ከእነርሱም መካከል መግደላዊት ማርያም፥ የያዕቆብና የዮሴፍ እናት ማርያም የዘብዴዎስ ልጆች እናት ይገኙባቸው ነበር።

ማቴዎስ 27:31-56 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከአፌዙበትም በኋላ ካባውን ገፈው የራሱን ልብስ አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ወሰዱት። ሲወጡም ስምዖን የሚባል የቀሬና ሰው አገኙ፤ መስቀሉንም እንዲሸከም አስገደዱት። ትርጉሙ የራስ ቅል ስፍራ ወደሚባል ጎልጎታ ወደ ተባለው ስፍራ በደረሱ ጊዜ፥ ከሐሞት ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅ እንዲጠጣ አቀረቡለት፤ ቀምሶም ሊጠጣው አልፈለገም። ከሰቀሉትም በኋላ ልብሶቹን ዕጣ ጥለው ተካፈሉት፤ በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር። የተከሰሰበትንም ምክንያት “ይህ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ ነው” የሚል ጽሑፍ ከራሱ በላይ አኖሩ። በዚያን ጊዜ ከእርሱ ጋር ሁለት ወንበዴዎች አንዱ በቀኙ አንዱ ደግሞ በግራው ተሰቀሉ። በዚያ የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበር፤ “ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምትሠራው፥ ራስህን አድን፤ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህሰ እስቲ ከመስቀል ውረድ፤” ይሉት ነበር። እንዲሁም ደግሞ ሊቃነ ካህናት፥ ከጻፎችና ከሽማግሌዎች ጋር እያፌዙ እንዲህ አሉት፦ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ሊያድን አይችልም፤ የእስራኤል ንጉሥ ነው፤ አሁን ከመስቀል ይውረድና እኛም በእርሱ እናምናለን። በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ብሏልና የሚወደው ከሆነ እስቲ አሁን ያድነው።” ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዴዎችም ደግሞ እንዲህ እያሉ ይሰድቡት ነበር። ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። በዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ኢየሱስ “ኤሊ ኤሊ ላማ ሰበቅታኒ?” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም “አምላኬ አምላኬ፥ ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው። በዚያ ቆሙት ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ ሰምተው “ኤልያስን ይጠራል” አሉ። ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጠና ሰፍነግ ወስዶ የወይን ሆምጣጤ ሞላበት፤ በመቃም አስሮ አጠጣው። የተቀሩት ግን “ተወው፤ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደሆነ እንይ” አሉ። ኢየሱስ እንደገና በታላቅ ድምፅ ጮኾ መንፈሱን ሰጠ። እነሆ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፤ ምድርም ተናወጠች፤ ዐለቶችም ተሰነጠቁ፤ መቃብሮችም ተከፈቱ፤ አንቀላፍተው ከነበሩት የብዙ ቅዱሳን በድን ተነሣ፤ ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስቷ ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ። የመቶ አለቃውና ከእርሱም ጋር ኢየሱስን ይጠብቁ የነበሩት የምድርን መናወጥና የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው “በእውነት ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ነበር” አሉ። ኢየሱስን እያገለገሉት ከገሊላ የተከተሉት፥ በሩቅ ሆነው የሚመለከቱ ብዙ ሴቶች እዚያ ነበሩ፤ ከእነርሱም መግደላዊት ማርያም፥ የያዕቆብና የዮሴፍ እናት ማርያምና የዘብዴዎስ ልጆች እናት ነበሩ።