የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማ​ቴ​ዎስ ወን​ጌል 27:31-56

የማ​ቴ​ዎስ ወን​ጌል 27:31-56 አማ2000

ከዘበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፤ ልብሱንም አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ወሰዱት። ሲወጡም ስምዖን የተባለው የቀሬናን ሰው አገኙ፤ እርሱንም መስቀሉን ይሸከም ዘንድ አስገደዱት። ትርጓሜው የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሆን ጎልጎታ ወደሚባለው ስፍራ በደረሱ ጊዜም፥ በሐሞት የተደባለቀ የወይን ጠጅ ሊጠጣ አቀረቡለት፤ ቀምሶም ሊጠጣው አልወደደም። ከሰቀሉትም በኋላ ልብሱን ዕጣ ጥለው ተካፈሉ፤ በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር። “ይህ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ ነው፤” የሚል የክሱን ጽሕፈት ከራሱ በላይ አኖሩ። በዚያን ጊዜ ሁለት ወንበዴዎች አንዱ በቀኝ አንዱም በግራ ከእርሱ ጋር ተሰቀሉ። የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበር፤ “ቤተ መቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራው፥ ራስህን አድን፤ የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ ከመስቀል ውረድ፤” አሉት። እንዲሁም ደግሞ የካህናት አለቆች ከጻፎችና ከሽማግሎች ጋር እየዘበቱበት እንዲህ አሉ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ሊያድን አይችልም፤ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ፥ አሁን ከመስቀል ይውረድ፤ እኛም እናምንበታለን። በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ፤’ ብሎአልና ከወደደውስ አሁን ያድነው።” ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዴዎች ደግሞ ያንኑ እያሉ ይነቅፉት ነበር። ከስድስት ሰዓትም ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ “ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ?” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም “አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ?” ማለት ነው። በዚያም ከቆሙት ሰዎች ሰምተው “ይህስ ኤልያስን ይጠራል፤” አሉ። ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጠ፤ ሰፍነግም ይዞ ሆምጣጤ ሞላበት፤ በመቃም አድርጎ አጠጣው። ሌሎቹ ግን “ተው፤ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደ ሆነ እንይ፤” አሉ። ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ተወ። እነሆም፥ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፤ ምድርም ተናወጠች፤ ዐለቶችም ተሰነጠቁ፤ መቃብሮችም ተከፈቱ፤ ተኝተው ከነበሩትም ከቅዱሳን ብዙ ሥጋዎች ተነሡ፤ ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ። የመቶ አለቃም ከእርሱም ጋር ኢየሱስን የሚጠብቁ መናወጡንና የሆነውን ነገር አይተው “ይህ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ፤” ብለው እጅግ ፈሩ። ኢየሱስን እያገለገሉ ከገሊላ የተከተሉት ብዙ ሴቶች በሩቅ ሆነው ሲመለከቱ በዚያ ነበሩ፤ ከእነርሱም መግደላዊት ማርያምና የያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ነበሩ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች

Free Reading Plans and Devotionals related to የማ​ቴ​ዎስ ወን​ጌል 27:31-56