የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማቴዎስ 26:37-59

ማቴዎስ 26:37-59 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ጴጥሮስንም ሁለቱንም የዘብዴዎስን ልጆች ወስዶ ሊያዝን ሊተክዝም ጀመር። “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቆዩ፤ ከእኔም ጋር ትጉ፤” አላቸው። ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በፊቱ ወደቀና ሲጸልይ “አባቴ! ቢቻልስ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን፤” አለ። ወደ ደቀ መዛሙርቱም መጣ፤ ተኝተውም አገኛቸውና ጴጥሮስን “እንዲሁም ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳ ልትተጉ አልቻላችሁምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው፤” አለው። ደግሞ ሁለተኛ ሄዶ ጸለየና “አባቴ! ይህች ጽዋ ሳልጠጣት ታልፍ ዘንድ የማይቻል እንደ ሆነ፥ ፈቃድህ ትሁን፤” አለ። ደግሞም መጥቶ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው። ደግሞም ትቶአቸው ሄደ፤ ሦስተኛም ያንኑ ቃል ደግሞ ጸለየ። ከዚያ ወዲያ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥቶ “እንግዲህስ ተኙ፤ ዕረፉም፤ እነሆ፥ ሰዓቲቱ ቀርባለች፤ የሰው ልጅም በኀጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል። ተነሡ፤ እንሂድ፤ እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል፤” አላቸው። ይህንም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፤ ከእርሱም ጋር ብዙ ሕዝብ ሰይፍና ጐመድ ይዘው ከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሎች ዘንድ መጡ። አሳልፎ የሚሰጠውም “የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት፤” ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። ወዲያውም ወደ ኢየሱስ ቀረበና “መምህር ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን፤” ብሎ ሳመው። ኢየሱስም “ወዳጄ ሆይ! ለምን ነገር መጣህ?” አለው። በዚያን ጊዜ ቀረቡ፤ እጃቸውንም በኢየሱስ ላይ ጭነው ያዙት። እነሆም፥ ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ጆሮውን ቈረጠው። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ። ወይስ አባቴን እንድለምን እርሱም አሁን ከዐሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት እንዲሰድልኝ የማይችል ይመስልሃልን? እንዲህ ከሆነስ ‘እንደዚህ ሊሆን ይገባል፤’ የሚሉ መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማሉ?” በዚያን ሰዓት ኢየሱስ ለሕዝቡ “ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ልትይዙኝ ወጣችሁን? በመቅደስ ዕለት ዕለት እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስቀመጥ ሳለሁ አልያዛችሁኝም። ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነ የነቢያት መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ነው፤” አለ። በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሹ። ኢየሱስን የያዙትም ጻፎችና ሽማግሎች ወደ ተከማቹበት ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት። ጴጥሮስ ግን እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ድረስ ሩቅ ሆኖ ተከተለው፤ የነገሩንም ፍጻሜ ያይ ዘንድ ወደ ውስጥ ገብቶ ከሎሌዎቹ ጋር ተቀመጠ። የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ሸንጎውም ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር፤ አላገኙም፤

ማቴዎስ 26:37-59 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከእርሱም ጋር ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስ ልጆች ይዞ ሄዶ ይተክዝና ይጨነቅ ጀመር፤ ከዚያም፣ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ ዐዝናለች፤ ከእኔ ጋር በመትጋት እዚሁ ቈዩ” አላቸው። ጥቂት ዕልፍ ብሎ በግንባሩ በመደፋት፣ “አባቴ ሆይ፤ ቢቻል ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ፤ ነገር ግን እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን አንተ እንደምትፈልገው ይሁን” ብሎ ጸለየ። ከዚያም ተመልሶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሲመጣ፣ ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ፤ ከእኔ ጋር ለአንድ ሰዓት እንኳ መትጋት አቃታችሁን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” እንደ ገና ለሁለተኛ ጊዜ ሄዶ፣ “አባት ሆይ፤ ይህ ሳልጠጣው የማያልፍ ጽዋ ከሆነ፣ ፈቃድህ ይፈጸም” ብሎ ጸለየ። እንደ ገናም በመጣ ጊዜ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ስለ ነበር ተኝተው አገኛቸው። ትቷቸውም እንደ ገና በመሄድ ለሦስተኛ ጊዜ ቀደም ብሎ የጸለየውን ጸሎት ደገመ። ከዚያም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁንም ዐርፋችሁ ተኝታችኋል? እነሆ፣ ሰዓቱ ቀርቧል፤ የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ ዐልፎ ይሰጣል፤ ተነሡ እንሂድ፤ አሳልፎ የሚሰጠኝም እየመጣ ነው።” በመናገር ላይ እያለ፣ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፤ ከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ዘንድ የተላኩ ሰይፍና ዱላ የያዙ ብዙ ሰዎችም አብረውት ነበሩ። ይሁዳም፣ “እኔ የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት” ብሎ ምልክት ሰጥቷቸው ስለ ነበር፣ በቀጥታ ወደ ኢየሱስ ሄዶ፣ “መምህር ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን” በማለት ሳመው። ኢየሱስም፣ “ወዳጄ ሆይ፤ የመጣህበትን ፈጽም” አለው። በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ቀርበው ኢየሱስን ያዙት፤ አሰሩትም። ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ጆሮውን ቈረጠው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “በል ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤ ሰይፍን የሚመዝዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ። ካስፈለገ አባቴን ብለምነው ከዐሥራ ሁለት ክፍለ ሰራዊት የሚበልጡ መላእክት የማይሰድድልኝ ይመስልሃል? ይህ ቢሆን ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍት ይሆናል ያሉት ነገር እንዴት ይፈጸማል?” በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፤ “ወንበዴ እንደሚይዝ ሰው ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ ልትይዙኝ መጣችሁ? በየዕለቱ በቤተ መቅደስ ተቀምጬ ሳስተምር አልያዛችሁኝም ነበር፤ ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነው ነቢያት በቅዱሳት መጻሕፍት የተናገሩት ይፈጸም ዘንድ ነው።” በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ጥለውት ሸሹ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስን የያዙት ሰዎች፣ የኦሪት የሕግ መምህራንና የሕዝብ ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወደ ነበሩበት፣ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት። ነገር ግን ጴጥሮስ ከርቀት ሆኖ እስከ ሊቀ ካህናቱ ቅጥር ግቢ ይከተለው ነበር፤ ወደ ውስጥ ገብቶም የሁኔታውን መጨረሻ ለማየት ከጠባቂዎች ጋር ተቀመጠ። በዚህ ጊዜ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሸንጎ በሙሉ ኢየሱስን ለማስገደል የሐሰት ማስረጃ ይፈልጉ ነበር፤

ማቴዎስ 26:37-59 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ጴጥሮስንም ሁለቱንም የዘብዴዎስን ልጆች ወስዶ ሊያዝን ሊተክዝም ጀመር። ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቆዩ ከእኔም ጋር ትጉ አላቸው። ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በፊቱ ወደቀና ሲጸልይ፦ አባቴ፥ ቢቻልስ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን አለ። ወደ ደቀ መዛሙርቱም መጣ፤ ተኝተውም አገኛቸውና ጴጥሮስን፦ እንዲሁም ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳ ልትተጉ አልቻላችሁምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው። ደግሞ ሁለተኛ ሄዶ ጸለየና፦ አባቴ፥ ይህች ጽዋ ሳልጠጣት ታልፍ ዘንድ የማይቻል እንደ ሆነ፥ ፈቃድህ ትሁን አለ። ደግሞም መጥቶ ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው። ደግሞም ትቶአቸው ሄደ፥ ሦስተኛም ያንኑ ቃል ደግሞ ጸለየ። ከዚያ ወዲያ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥቶ፦ እንግዲህስ ተኙ ዕረፉም፤ እነሆ፥ ሰዓቲቱ ቀርባለች የሰው ልጅም በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል። ተነሡ፥ እንሂድ፤ እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል አላቸው። ይህንም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፥ ከእርሱም ጋር ብዙ ሕዝብ ሰይፍና ጕኦመድ ይዘው ከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሎች ዘንድ መጡ። አሳልፎ የሚሰጠውም፦ የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። ወዲያውም ወደ ኢየሱስ ቀረበና፦ መምህር ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን ብሎ ሳመው። ኢየሱስም፦ ወዳጄ ሆይ፥ ለምን ነገር መጣህ? አለው። በዚያን ጊዜ ቀረቡ እጃቸውንም በኢየሱስ ላይ ጭነው ያዙት። እነሆም፥ ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ጆሮውን ቍኦረጠው። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው፦ ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ። ወይስ አባቴን እንድለምን እርሱም አሁን ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት እንዲሰድልኝ የማይቻል ይመስልሃልን? እንዲህ ከሆነስ፦ እንደዚህ ሊሆን ይገባል የሚሉ መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማሉ? በዚያን ሰዓት ኢየሱስ ለሕዝቡ፦ ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ጕኦመድ ይዛችሁ ልትይዙኝ ወጣችሁን? በመቅደስ ዕለት ዕለት እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስቀመጥ ሳለሁ አልያዛችሁኝም። ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነ የነቢያት መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ነው አለ። በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሹ። ኢየሱስን የያዙትም ጻፎችና ሽማግሎች ወደ ተከማቹበት ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት። ጴጥሮስ ግን እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ድረስ ሩቅ ሆኖ ተከተለው፥ የነገሩንም ፍጻሜ ያይ ዘንድ ወደ ውስጥ ገብቶ ከሎሌዎቹ ጋር ተቀመጠ። የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ሸንጕኦውም ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር፥ አላገኙም፤

ማቴዎስ 26:37-59 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከእርሱ ጋር ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስን ልጆች አስከትሎ ሄደ፤ ያዝንና ይጨነቅም ጀመረ። እንዲህም አላቸው፦ “ለመሞት እስክደርስ ድረስ አዝኛለሁ፤ እናንተ እዚህ ቈዩ፤ ከእኔም ጋር ንቁ።” ከእነርሱ ጥቂት ራቅ ብሎ ሄደና፥ በመሬት ላይ በግንባሩ ተደፍቶ፥ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “አባት ሆይ! የሚቻል ከሆነ ይህ የመከራ ጽዋ ከእኔ ወዲያ ይለፍ! ነገር ግን የአንተ ፈቃድ ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ አይሁን።” ከዚህ በኋላ ወደ ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ተመልሶ በመጣ ጊዜ ተኝተው አገኛቸው፤ ስለዚህ፥ ጴጥሮስን እንዲህ አለው፦ “ከእኔ ጋር ለአንዲት ሰዓት እንኳ መንቃት አልቻላችሁምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ፤ መንፈስ በእርግጥ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” እንደገናም ኢየሱስ ለሁለተኛ ጊዜ ርቆ ሄደና “አባቴ ሆይ! ይህ የመከራ ጽዋ ሳልጠጣው ሊያልፍ የማይቻል ከሆነ የአንተ ፈቃድ ይሁን” ሲል ጸለየ። ደግሞም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ በመጣ ጊዜ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው። እንደገናም ትቶአቸው ሄደና ያንኑ የፊተኛውን ቃል በመናገር ሦስተኛ ጊዜ ጸለየ። ከዚህ በኋላ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ መጣና እንዲህ አላቸው፤ “አሁንም ገና ተኝታችኋልን? ዕረፍትም እያደረጋችሁ ነውን? እነሆ፥ የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ ተላልፎ የሚሰጥበት ሰዓቱ ደርሶአል፤ ተነሡ እንሂድ! እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል!” ኢየሱስ ገና ሲናገር ሳለ እነሆ፥ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ የሆነው ይሁዳ መጣ፤ ከእርሱም ጋር ሰይፍና ዱላ የያዙ ብዙ ሰዎች መጡ፤ እነርሱ ከካህናት አለቆችና ከሕዝብ ሽማግሌዎች የተላኩ ነበሩ። ኢየሱስን አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳ ለሰዎቹ “የምትፈልጉት እኔ የምስመው ነውና እርሱን ያዙት” ሲል ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። ይሁዳ ወዲያውኑ መጥቶ ወደ ኢየሱስ ቀረበና “መምህር ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን!” ብሎ ሳመው። ኢየሱስም “ወዳጄ ሆይ! እንግዲህ የመጣህበትን ጉዳይ ፈጽም” አለው፤ ከዚህ በኋላ ሰዎቹ ወደ ኢየሱስ ቀረቡና ያዙት። በዚህ ጊዜ ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የካህናት አለቃውን አገልጋይ መትቶ ጆሮውን ቈረጠው። ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፤ “ሰይፍን የሚያነሡ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልሰህ ክተተው። ለመሆኑ እኔ አባቴን ብለምን እርሱ በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ የመላእክት ሠራዊት ሊልክልኝ የማይችል ይመስልሃልን? እንዲህማ ቢሆን ኖሮ ‘መከራ መቀበል አለበት’ የሚለው የቅዱሳት መጻሕፍት ቃል እንዴት ይፈጸማል?” በዚያን ሰዓት ኢየሱስ በዚያ ለተሰበሰቡት ሕዝብ እንዲህ አለ፤ “ወንበዴን እንደምትይዙ እኔን ለመያዝ ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ መጣችሁን? በየቀኑ በቤተ መቅደስ እያስተማርኩ ከእናንተ ጋር ሳለሁ አልያዛችሁኝም ነበር፤ ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነው በነቢያት የተጻፈው እንዲፈጸም ነው።” በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሹ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስን የያዙት ሰዎች ወደ ካህናት አለቃው ወደ ቀያፋ ወሰዱት፤ በዚያም የሕግ መምህራንና ሽማግሌዎች ተሰብስበው ነበር። ጴጥሮስ ግን እስከ ካህናት አለቃው ግቢ ድረስ ኢየሱስን በሩቅ ተከተለው፤ ወደ ውስጥ ገብቶም የነገሩን ፍጻሜ ለማየት ከዘበኞች ጋር ተቀመጠ። የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሸንጎ አባሎች ሁሉ በኢየሱስ ላይ የሞት ፍርድ ለማስፈረድ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር።

ማቴዎስ 26:37-59 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስን ልጆች ይዞ ሄደና ማዘንና መጨነቅ ጀመረ። “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝናለች፤ እዚህ ቆዩ፤ ከእኔም ጋር ትጉ” አላቸው። ወደ ፊት ጥቂት እልፍ ብሎ በፊቱ ተደፋና እንዲህ ሲል ጸለየ “አባቴ! የሚቻል ከሆነ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን እንደ አንተ ፈቃድ እንጂ እንደ እኔ አይሁን።” ወደ ደቀ መዛሙርቱም በመጣ ጊዜ ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው፦ “ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳ መትጋት አልቻላችሁምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ፥ ጸልዩም፤ መንፈስ በእርግጥ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ ሄዶ “አባቴ ሆይ! ይህንን ሳልጠጣው ሊያልፍ የማይቻል ከሆነ፥ ፈቃድህ ይሁን” ብሎ ጸለየ። ዳግመኛ ሲመጣ ተኝተው አገኛቸው፥ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና። እንደገና ትቶአቸው ሄደ፤ ያንኑ ቃል ለሦስተኛ ጊዜ ደግሞ ጸለየ። ከዚህ በኋላ ወደ ደቀመዛሙርቱ መጥቶ እንዲህ አላቸው “ከእንግዲህስ ተኙ፥ ዕረፉም፤ እነሆ ሰዓቱ ቀርቦአል፤ የሰው ልጅም በኀጢአተኞች እጅ ተላልፎ ይሰጣል። ተነሡ፥ እንሂድ፤ እነሆ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል።” ይህንም ገና ሲናገር ሳለ፥ እነሆ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፤ ከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ዘንድ ብዙ ሕዝብ ሰይፍና ዱላ ይዘው ከእርሱ ጋር መጡ። አሳልፎ የሚሰጠውም “የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት” ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። ወዲያውም ወደ ኢየሱስ ቀረበና “መምህር ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን” ብሎ ሳመው። ኢየሱስም “ወዳጄ ሆይ! ለምን መጣህ?” አለው። በዚያን ጊዜ ቀረቡና እጃቸውን በኢየሱስ ላይ ጫኑ፥ ያዙትም። እነሆ ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የሊቀ ካህኑን ባርያ መትቶ ጆሮውን ቆረጠው። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው “ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ፤ ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና። ወይስ አባቴን ብለምነው ከዐሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት አሁን ሊልክልኝ የማይችል ይመስልሃልን? እንዲህ ከሆነ ‘እንደዚህ መሆን አለበት’ የሚሉት መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማል?” በዚያን ሰዓት ኢየሱስ ለሕዝቡ እንዲህ አላቸው “ወንበዴን እንደምትይዙ እኔን ለመያዝ ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ ወጣችሁን? ዕለት በዕለት በመቅደስ ተቀምጬ ሳስተምር ሳለሁ አልያዛችሁኝም። ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነው የነቢያት መጻሕፍት እንዲፈጸሙ ነው።” በዚያን ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሹ። ኢየሱስን የያዙት ሰዎች፥ ጻፎችና ሽማግሌዎች ወደ ተሰበሰቡበት ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት። ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህኑ ግቢ ድረስ ሩቅ ሆኖ ተከተለው፤ የነገሩንም ፍጻሜ ለማየት ወደ ውስጥ ገብቶ ከሎሌዎቹ ጋር ተቀመጠ። ሊቃነ ካህናትና ሸንጎው ሁሉ ሊገድሉት ፈልገው በኢየሱስ ላይ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር፤