የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 26:37-59

የማቴዎስ ወንጌል 26:37-59 አማ05

ከእርሱ ጋር ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስን ልጆች አስከትሎ ሄደ፤ ያዝንና ይጨነቅም ጀመረ። እንዲህም አላቸው፦ “ለመሞት እስክደርስ ድረስ አዝኛለሁ፤ እናንተ እዚህ ቈዩ፤ ከእኔም ጋር ንቁ።” ከእነርሱ ጥቂት ራቅ ብሎ ሄደና፥ በመሬት ላይ በግንባሩ ተደፍቶ፥ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “አባት ሆይ! የሚቻል ከሆነ ይህ የመከራ ጽዋ ከእኔ ወዲያ ይለፍ! ነገር ግን የአንተ ፈቃድ ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ አይሁን።” ከዚህ በኋላ ወደ ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ተመልሶ በመጣ ጊዜ ተኝተው አገኛቸው፤ ስለዚህ፥ ጴጥሮስን እንዲህ አለው፦ “ከእኔ ጋር ለአንዲት ሰዓት እንኳ መንቃት አልቻላችሁምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ፤ መንፈስ በእርግጥ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” እንደገናም ኢየሱስ ለሁለተኛ ጊዜ ርቆ ሄደና “አባቴ ሆይ! ይህ የመከራ ጽዋ ሳልጠጣው ሊያልፍ የማይቻል ከሆነ የአንተ ፈቃድ ይሁን” ሲል ጸለየ። ደግሞም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ በመጣ ጊዜ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው። እንደገናም ትቶአቸው ሄደና ያንኑ የፊተኛውን ቃል በመናገር ሦስተኛ ጊዜ ጸለየ። ከዚህ በኋላ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ መጣና እንዲህ አላቸው፤ “አሁንም ገና ተኝታችኋልን? ዕረፍትም እያደረጋችሁ ነውን? እነሆ፥ የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ ተላልፎ የሚሰጥበት ሰዓቱ ደርሶአል፤ ተነሡ እንሂድ! እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል!” ኢየሱስ ገና ሲናገር ሳለ እነሆ፥ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ የሆነው ይሁዳ መጣ፤ ከእርሱም ጋር ሰይፍና ዱላ የያዙ ብዙ ሰዎች መጡ፤ እነርሱ ከካህናት አለቆችና ከሕዝብ ሽማግሌዎች የተላኩ ነበሩ። ኢየሱስን አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳ ለሰዎቹ “የምትፈልጉት እኔ የምስመው ነውና እርሱን ያዙት” ሲል ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። ይሁዳ ወዲያውኑ መጥቶ ወደ ኢየሱስ ቀረበና “መምህር ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን!” ብሎ ሳመው። ኢየሱስም “ወዳጄ ሆይ! እንግዲህ የመጣህበትን ጉዳይ ፈጽም” አለው፤ ከዚህ በኋላ ሰዎቹ ወደ ኢየሱስ ቀረቡና ያዙት። በዚህ ጊዜ ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የካህናት አለቃውን አገልጋይ መትቶ ጆሮውን ቈረጠው። ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፤ “ሰይፍን የሚያነሡ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልሰህ ክተተው። ለመሆኑ እኔ አባቴን ብለምን እርሱ በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ የመላእክት ሠራዊት ሊልክልኝ የማይችል ይመስልሃልን? እንዲህማ ቢሆን ኖሮ ‘መከራ መቀበል አለበት’ የሚለው የቅዱሳት መጻሕፍት ቃል እንዴት ይፈጸማል?” በዚያን ሰዓት ኢየሱስ በዚያ ለተሰበሰቡት ሕዝብ እንዲህ አለ፤ “ወንበዴን እንደምትይዙ እኔን ለመያዝ ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ መጣችሁን? በየቀኑ በቤተ መቅደስ እያስተማርኩ ከእናንተ ጋር ሳለሁ አልያዛችሁኝም ነበር፤ ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነው በነቢያት የተጻፈው እንዲፈጸም ነው።” በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሹ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስን የያዙት ሰዎች ወደ ካህናት አለቃው ወደ ቀያፋ ወሰዱት፤ በዚያም የሕግ መምህራንና ሽማግሌዎች ተሰብስበው ነበር። ጴጥሮስ ግን እስከ ካህናት አለቃው ግቢ ድረስ ኢየሱስን በሩቅ ተከተለው፤ ወደ ውስጥ ገብቶም የነገሩን ፍጻሜ ለማየት ከዘበኞች ጋር ተቀመጠ። የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሸንጎ አባሎች ሁሉ በኢየሱስ ላይ የሞት ፍርድ ለማስፈረድ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች

Free Reading Plans and Devotionals related to የማቴዎስ ወንጌል 26:37-59