ዘሌዋውያን 4:27-35
ዘሌዋውያን 4:27-35 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“ከሀገሩም ሕዝብ አንድ ሰው ኀጢአትን ሳያውቅ ቢሠራ፥ እግዚአብሔርም፦ አትሥራ ያለውን ትእዛዝ ቢተላለፍ፥ ቢበድልም፥ ለእርሱም የሠራው ኀጢአት ቢታወቀውና ንስሓ ቢገባ፥ ስለ ሠራው ኀጢአት ነውር የሌለባትን እንስት ፍየል ለቍርባኑ ያመጣል። እጁንም በኀጢአት መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት እንስሳትን በሚያርዱበት ስፍራ የኀጢአት መሥዋዕት ፍየልዋን ያርዳታል። ካህኑም ከደምዋ በጣቱ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፤ ደሙንም ሁሉ ከመሠዊያው በታች ያፈስሰዋል። ስቡም ሁሉ ከደኅንነት መሥዋዕት ላይ እንደሚወሰድ፥ ስብዋን ሁሉ ይወስዳል፤ ካህኑም ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ይጨምረዋል፤ ካህኑም ስለ እርሱ ያስተሰርያል፤ ኀጢአቱም ይሰረይለታል። “ስለ ኀጢአትም መሥዋዕት የበግ ጠቦት ቢያቀርብ፥ ነውር የሌለባትን እንስት ያመጣል። እጁንም በኀጢአት መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፤ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ ለኀጢአት መሥዋዕት ያርዳታል። ካህኑም ከኀጢአት መሥዋዕት ደም በጣቱ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፤ ደሙንም ሁሉ ከመሠዊያው በታች ያፈስሰዋል። ስቡ ሁሉ ለደኅንነት መሥዋዕት ከታረደው የበግ ጠቦት ላይ እንደሚወሰድ ስብዋን ሁሉ ይወስዳሉ፤ ካህኑም ለእግዚአብሔር በእሳት በተቃጠለው ቍርባን ላይ በመሠዊያው ላይ ይጨምረዋል። ካህኑም ስለ ሠራው ኀጢአት ያስተሰርይለታል፤ ኀጢአቱም ይሰረይለታል።
ዘሌዋውያን 4:27-35 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ ‘ከሕዝቡ መካከል አንዱ ሰው ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፣ እግዚአብሔር አታድርጉ ብሎ ከከለከላቸው ትእዛዞች አንዱን ተላልፎ ቢገኝ እርሱ በደለኛ ነው። ኀጢአት መሥራቱን በተረዳ ጊዜ፣ እንከን የሌለባትን እንስት ፍየል ስለ ፈጸመው ኀጢአት የግሉ መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ። እጁን ለኀጢአት መሥዋዕት በቀረበችው ፍየል ራስ ላይ ይጫን፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራም ይረዳት። ካህኑ በጣቱ ከደሟ ጥቂት ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቅባ፤ የተረፈውንም ደም ሁሉ በመሠዊያው ግርጌ ያፍስሰው። ሥቡን ከኅብረት መሥዋዕት በወጣበት አኳኋን ሥቡን ሁሉ ያውጣ፤ ካህኑም ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ በዚህም መሠረት ካህኑ የሰውየውን ኀጢአት ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል። “ ‘ስለ ኀጢአት መሥዋዕት የበግ ጠቦት የሚያቀርብ ከሆነ፣ እንከን የሌለባትን እንስት ያቅርብ። እጁን በጠቦቷ ራስ ላይ ይጫን፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራም የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ይረዳት። ካህኑም ከኀጢአት መሥዋዕቱ ደም በጣቱ ጥቂት ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቅባ፤ የተረፈውንም ደም ሁሉ በመሠዊያ ግርጌ ያፍስሰው። ሥቡ ከኅብረት መሥዋዕት ጠቦት በወጣበት አኳኋን ሥቡን ሁሉ ያውጣ፤ ካህኑም በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር በእሳት በሚቀርበው መሥዋዕት ላይ ያቃጥለው። በዚህ መሠረት ሰውየው የሠራውን ኀጢአት ካህኑ ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል።
ዘሌዋውያን 4:27-35 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከአገሩ ሕዝብም አንድ ሰው ኃጢአትን ሳያውቅ ቢሠራ፥ እግዚአብሔርም፦ አትሥራ ያለውን ትእዛዝ ቢተላለፍ፥ ቢበድልም፥ ለእርሱም የሠራው ኃጢአት ቢታወቀው፥ ስለ ሠራው ኃጢአት ነውር የሌለባትን እንስት ፍየል ለቍርባኑ ያመጣል። እጁንም በኃጢአት መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፤ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ የኃጢአትን መሥዋዕት ያርዳል። ካህኑም ከደምዋ በጣቱ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፥ ደሙንም ሁሉ ከመሠዊያው በታች ያፈስሰዋል። ስቡም ሁሉ ከደኅንነት መሥዋዕት ላይ እንደሚወሰድ፥ ስብዋን ሁሉ ይወስዳል፤ ካህኑም ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ ካህኑም ስለ እርሱ ያስተሰርያል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። ስለ ኃጢአትም መሥዋዕት የበግ ጠቦት ቢያቀርብ፥ ነውር የሌለባትን እንስት ያመጣል። እጁንም በኃጢአት መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፥ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ ለኃጢአት መሥዋዕት ያርዳታል። ካህኑም ከኃጢአት መሥዋዕት ደም በጣቱ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፥ ደሙንም ሁሉ ከመሠዊያው በታች ያፈስሰዋል። ስቡ ሁሉ ለደኅንነት መሥዋዕት ከታረደው ጠቦት ላይ እንደሚወሰድ ስብዋን ይወስዳል፤ ካህኑም ለእግዚአብሔር በእሳት በተቃጠለው ቍርባን ላይ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። ካህኑም ስለ ሠራው ኃጢአት ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል።
ዘሌዋውያን 4:27-35 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ኃጢአት የሠራውና ባለማወቅም እግዚአብሔር አታድርጉ ብሎ ካዘዛቸው ትእዛዞች አንዱን የተላለፈውና በደለኛ የሆነው ሰው ከተራው ሕዝብ ወገን ከሆነ፥ ኃጢአት መሥራቱን እንዳወቀ ወዲያውኑ ምንም ነውር የሌለባት እንስት ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት ያቅርብ። እጁንም በእንስሳይቱ ራስ ላይ ይጫን፤ ከመሠዊያው በስተ ሰሜን ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሶች በሚታረዱበት ስፍራ ይረዳት። ካህኑም የእንስሳይቱን ደም በጣቱ እያጠቀሰ በሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያው አራት ማእዘን በሚገኙ ጒጦች ላይ ያኑር፤ ከዚህም የተረፈውን ደም በመሠዊያው ሥር ያፍስሰው። ለአንድነት መሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሶችን ስብ በመግፈፍ በሚፈጽመው ዐይነት የዚህችንም እንስሳ ስብ ሁሉ ገፎ ያስወግድ፤ መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎም በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ በዚህ ዐይነት ካህኑ ስለዚያ ሰው የኃጢአት ስርየት መሥዋዕት ያቀርባል፤ ያም ሰው ኃጢአቱ ይቅር ይባልለታል። “ሰውየው ስለ ኃጢአቱ ስርየት የበግ መሥዋዕት ቢያቀርብ፥ ምንም ነውር የሌለባት እንስት ትሁን። እርሱም በእንስሳይቱ ራስ ላይ እጁን ይጫን፤ ከመሠዊያው በስተሰሜን በኩል ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሶች በሚታረዱበት ስፍራ ይረዳት፤ ካህኑም የእንስሳይቱን ደም በጣቱ እያጠቀሰ በሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያው አራት ማእዘን በሚገኙ ጒጦች ላይ ያኑር፤ ከዚህም የተረፈውን ደም በመሠዊያው ሥር ያፍስሰው፤ ከዚህም በኋላ ለአንድነት መሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሶችን ስብ በመግፈፍ በሚፈጽመው ዐይነት የዚህችንም እንስሳ ስብ ሁሉ ገፎ ያስወግድ፤ እርሱንም ለእግዚአብሔር ከሚቀርበው የምግብ መባ ጋር በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ በዚህም ዐይነት ካህኑ ስለዚያ ሰው የኃጢአት መሥዋዕትን በማቅረብ ያስተስርይለት፤ ያም ሰው ኃጢአቱ ይቅር ይባልለታል።
ዘሌዋውያን 4:27-35 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“ከአገሩ ሕዝብም አንድ ሰው ባለማወቅ ጌታ አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዱን ተላልፎ ኃጢአት ቢሠራና ቢበድል፥ ለእርሱም የሠራው ኃጢአት የታወቀ ቢሆን፥ ስለ ሠራው ኃጢአት ነውር የሌለባትን እንስት ፍየል ለቁርባኑ ያመጣል። እጁንም የኃጢአት መሥዋዕት በሆነችው እንስሳ ራስ ላይ ይጭናል፤ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ የኃጢአትን መሥዋዕት ያርዳል። ካህኑም ከደምዋ በጣቱ ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፥ የተረፈውንም ደምዋን ሁሉ ከመሠዊያው በታች ያፈስሳል። ከአንድነት መሥዋዕት ላይ እንደተወሰደው ስብ እንዲሁ የእርሷን ስብ ሁሉ ይወስዳል፤ ካህኑም ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ ካህኑም ስለ እርሱ ያስተሰርያል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። “ስለ ኃጢአትም መሥዋዕት የበግ ጠቦት ቢያቀርብ፥ ነውር የሌለባትን እንስት ያመጣል። እጁንም የኃጢአት መሥዋዕት በሆነችው እንስሳ ራስ ላይ ይጭናል፥ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚያርድበት ስፍራ ለኃጢአት መሥዋዕት ያርዳታል። ካህኑም ከኃጢአት መሥዋዕት ደም በጣቱ ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፥ የተረፈውንም ደምዋን ሁሉ ከመሠዊያው በታች ያፈስሳል። ለአንድነት መሥዋዕት ከሚቀርበው ጠቦት ላይ ስቡ እንደሚወሰድ እንዲሁ የእርሷን ስብ ሁሉ ይወስዳል፤ ካህኑም ለጌታ በእሳት ከሚቀርበው ቁርባን ጋር በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። ካህኑም ስለ ሠራው ኃጢአት ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል።