ዘሌዋውያን 13:1-59
ዘሌዋውያን 13:1-59 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ “ሰው በሥጋው ቆዳ ላይ እባጭ ብትወጣበት፥ ብትነጣም፥ በሥጋውም ቆዳ እንደ ለምጽ ደዌ ብትመስል፥ ወደ ካህኑ ወደ አሮን ወይም ከካህናቱ ልጆች ወደ አንዱ ያምጡት። ካህኑም በሥጋው ቆዳ ያለችውን ያችን ደዌ ይያት፤ ጠጕሯም ተለውጣ ብትነጣ በሥጋው ቆዳ ያለች የዚያች ደዌ መልክ ቢከፋ፥ ደዌውም ወደ ሥጋው ቆዳ ቢጠልቅ፥ እርስዋ የለምጽ ደዌ ናት፤ ካህኑም አይቶ፦ ‘ርኩስ ነው’ ይበለው። ቋቍቻውም በሥጋው ቆዳ ላይ ቢነጣ፥ ከቆዳውም የጠለቀ ባይመስል፥ ጠጕሩም ባይነጣ፥ ካህኑ የታመመውን ሰው ሰባት ቀን ይዘጋበታል። በሰባተኛውም ቀን ካህኑ ያችን ደዌ ይያት፤ እነሆም፥ ያች ደዌ በፊት እንደ ነበረች ብትሆን፥ በቆዳውም ላይ ባትሰፋ፥ ካህኑ ሰባት ቀን ደግሞ ይለየዋል። ደግሞ በሰባተኛው ቀን ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ያች ደዌ ብትከስም፥ በቆዳውም ላይ ባትሰፋ፥ ካህኑ፦ ‘ንጹሕ ነው’ ይለዋል፤ ምልክት ነውና፥ ልብሱንም አጥቦ ንጹሕ ይሆናል። ስለ መንጻቱ በካህኑ ዘንድ ከታየ በኋላ ምልክቱ በቆዳው ላይ ቢሰፋ፥ እንደገና ሊታይ ወደ ካህኑ ይቀርባል። ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ ምልክቱ በቆዳው ላይ ቢሰፋ ካህኑ፦ ‘ርኩስ ነው’ ይለዋል፤ ለምጽ ነውና። “የለምጽ ደዌ በሰው ላይ ቢወጣ እርሱ ወደ ካህኑ ይሄዳል። ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም፥ በቆዳው ላይ ነጭ እባጭ ቢሆን፥ ጠጕሩም ተለውጦ ቢነጣ፥ ሥጋውም በእባጩ ውስጥ ቢያዥ፥ እርሱ በሥጋው ቆዳ ላይ አሮጌ ለምጽ ነው፤ ካህኑም፦ ‘ርኩስ ነው’ ይለዋል፤ እርሱ ርኩስ ነውና ይለየዋል። ለምጹም በቆዳው ላይ ሰፍቶ ቢወጣ፥ ለምጹም የታመመውን ሰው ቆዳውን ሁሉ ከራሱ እስከ እግሮቹ ድረስ እንደ ከደነው ለካህኑ ቢመስለው፤ ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ለምጹ ቆዳውን ሁሉ ቢከድን የታመመውን ሰው፦ ካህኑ ‘ንጹሕ ነህ’ ይለዋል፤ ሁለመናው ተለውጦ ነጭ ሆኖአልና ንጹሕ ነው። ደዌው በታየበት ቀን ጤነኛው ቆዳ ርኩስ ይሆናል። ካህኑም ጤነኛውን ቆዳ አይቶ፦ ‘ርኩስ ነው’ ይለዋል፤ ስለዚህ ለምጽ ነውና ርኩስ ነው። ጤነኛው ቆዳ ተመልሶ ቢነጣ እንደገና ወደ ካህኑ ይመጣል። ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ቢነጣ ካህኑ የታመመውን፦ ‘ንጹሕ ነው’ ይለዋል፤ ንጹሕ ነውና። “በሥጋውም ቆዳ ላይ ቍስል ቢሆንና ቢሽር፥ በቍስሉም ስፍራ ነጭ እባጭ ወይም ቀላ ያለ ቋቍቻ ቢወጣ፥ በካህኑ ዘንድ ይታያል። ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ ወደ ቆዳው ውስጥ ጠልቆ ቢታይ፥ ጠጕሩም ተለውጦ ቢነጣ፥ ካህኑ፦ ‘ርኩስ ነው’ ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው፤ ከቍስሉ ውስጥ ወጥቶአል። ካህኑም ቢያየው፥ ነጭም ጠጕር ባይኖርበት፥ ወደ ቆዳውም ውስጥ ባይጠልቅ ነገር ግን ቢከስም፥ ካህኑ ሰባት ቀን ይለየዋል። በቆዳውም ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ፦ ‘ርኩስ ነው’ ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው፤ በእትራቱ ላይ ወጥቶአልና። ያች ደዌ ግን በስፍራዋ ብትቆም፥ ባትሰፋም፥ የቍስል እትራት ናት፤ ካህኑም፦ ‘ንጹሕ ነው’ ይለዋል። “በሥጋውም ቆዳ የእሳት ትኩሳት ቢኖርበት፥ በተቃጠለውም ስፍራ ነጭ፥ ወይም ቀላ ያለ ቋቍቻ ቢታይ፥ ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ በቋቁቻው ጠጕሩ ተለውጦ ቢነጣ፥ ወደ ቆዳውም ውስጥ ቢጠልቅ፥ ለምጽ ነው፤ ከተቃጠለውም ስፍራ ወጥቶአል፤ ካህኑም፦ ‘ርኩስ ነው’ ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነውና። ካህኑም ቢያየው፥ በቋቍቻውም ነጭ ጠጕር ባይኖር፥ ወደ ቆዳውም ባይጠልቅ፥ ነገር ግን ቢከስም፥ ካህኑ ሰባት ቀን ይለየዋል። ካህኑም በሰባተኛው ቀን ያየዋል፤ በቆዳውም ላይ ቢሰፋ ካህኑ፦ ‘ርኩስ ነው’ ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነውና በእትራቱ ላይ ወጥቶአል። ቋቍቻውም በስፍራው ላይ ቢቆም፥ በቆዳውም ላይ ባይሰፋ፥ ነገር ግን ቢከስም፥ የትኩሳት እባጭ ነው፤ የትኩሳትም ጠባሳ ነውና ካህኑ፦ ‘ንጹሕ ነው’ ይለዋል። “ማናቸውም ወንድ ወይም ሴት በራሱ ወይም በአገጩ የለምጽ ደዌ ቢኖርበት፥ ካህኑ የለምጹን ደዌ ያያል፤ እነሆም፥ ወደ ቆዳው ቢጠልቅ፥ በውስጡም ቀጭን ብጫ ጠጕር ቢኖርበት፥ ካህኑ፦ ‘ርኩስ ነው’ ይለዋል፤ ቈረቈር ነው፤ የራስ ወይም የአገጭ ለምጽ ነው። ካህኑም የቈረቈሩን ደዌ ቢያይ፥ ወደ ቆዳውም ባይጠልቅ፥ ጥቁርም ጠጕር ባይኖርበት፥ ካህኑ የቈረቈር ደዌ ያለበትን ሰው ሰባት ቀን ይለየዋል። ካህኑም በሰባተኛው ቀን ደዌውን ያያል፤ እነሆም፥ ቈረቈሩ ባይሰፋ፥ በውስጡም ብጫ ጠጕር ባይኖር፥ የቈረቈሩም መልክ ወደ ቆዳው ባይጠልቅ፤ ይላጫል፤ ቈረቈሩ ግን አይላጭም፤ ካህኑም ቈርቈር ያለበትን ሰው ሰባት ቀን ደግሞ ይለየዋል። ካህኑም በሰባተኛው ቀን ቈረቈሩን ያያል፤ እነሆም፥ ከተላጨ በኋላ ቈረቈሩ በቆዳው ላይ ባይሰፋ፥ መልኩም ወደ ቆዳው ባይጠልቅ፥ ካህኑ፦ ‘ንጹሕ ነው’ ይለዋል፤ ልብሱን አጥቦ ንጹሕ ይሆናል። ከነጻ በኋላ ግን ቈረቈሩ በቆዳው ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ቈረቈሩ በቆዳው ላይ ቢሰፋ ካህኑ ብጫውን ጠጕር አይፈልግም፤ ርኩስ ነውና። ቈረቈሩ ግን ፊት እንደ ነበረ በቦታው ቢኖር፥ ጥቁርም ጠጕር ቢበቅልበት፥ ቈረቈሩ ሽሮአል፤ እርሱም ንጹሕ ነው፤ ካህኑም፦ ‘ንጹሕ ነው’ ይለዋል። “ማናቸውም ወንድ ወይም ሴት በሥጋው ቆዳ ላይ ነጭ ቋቍቻ ቢኖርበት፥ ካህኑ ያያል፤ እነሆም፥ በሥጋቸው ቆዳ ላይ ያለው ቋቍቻ ፈገግ ቢል አጓጐት ነው፤ ከቆዳው ውስጥ ወጥቶአል፤ ንጹሕ ነው። “የሰውም ጠጕር ከራሱ ቢመለጥ እርሱ በራ ነው፤ ነገር ግን ንጹሕ ነው። ጠጕሩ ከግንባሩ ቢመለጥ እርሱ ራሰ በራ ነው፤ ነገር ግን ንጹሕ ነው። በቡሀነቱ ወይም በራሰ በራነቱ ነጭ፥ ወይም ቀላ ያለ ደዌ ቢኖርበት፥ እርሱ ከቡሀነቱ ወይም ከራሰ በራነቱ የወጣ ለምጽ ነው። ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም፥ የደዌው እብጠት በሥጋው ቆዳ ላይ የሆነ ለምጽ መስሎ፥ በቡሀነቱ ወይም በራሰ በራነቱ ነጭ ወይም ቀላ ያለ ቢሆን፥ ለምጻም ሰው ነው፤ ርኩስ ነው፤ ካህኑ፦ በርግጥ ‘ርኩስ ነው’ ይለዋል፤ ደዌው በራሱ ነው። “የለምጽ ደዌ ያለበት ሰው ልብሱ የተቀደደ ይሁን፤ ራሱም የተገለጠ ይሁን፤ ከንፈሩንም ይሸፍን፤ ርኩስ ይባላል። ደዌው ባለበት ዘመን ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ እርሱ ርኩስ ነው፤ ብቻውን ይቀመጣል፤ መኖሪያውም ከሰፈር በውጭ ይሆናል። “የለምጽም ደዌ በልብስ ላይ ቢሆን፥ ልብሱም የበግ ጠጕር ወይም የተልባ እግር ቢሆን፥ በድሩ ወይም በማጉ ላይ ቢሆን፥ የበግ ጠጕር ወይም የተልባ እግር ቢሆን፥ ቆዳ ወይም ከቆዳ የሚደረግ ነገር ቢሆን፥ ደዌው በልብሱ ወይም በቆዳው ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከቆዳ በሚደረገው ነገር አረንጓዴ ወይም ቀይ ቢሆን፥ የለምጽ ደዌ ነው፤ ለካህኑ ያሳያል። ካህኑም ደዌውን አይቶ ደዌው ያለበትን ነገር ሰባት ቀን ይለየዋል። በሰባተኛውም ቀን ደዌውን ያያል፤ ደዌውም በልብስ ላይ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም በቆዳው ወይም ከቆዳው በሚደረግ ነገር ቢሰፋ፥ ደዌው እየፋገ የሚሄድ ለምጽ ነው፤ ርኩስ ነው። ልብሱን ያቃጥላል፤ ድሩ ወይም ማጉ የበግ ጠጕር ወይም የተልባ እግር ቢሆን ወይም ከቆዳ የተደረገ ቢሆን፥ ደዌ ያለበት ሁሉ እየፋገ የሚሄድ ለምጽ ነውና በእሳት ይቃጠላል። “ካህኑ ቢያይ፥ እነሆም፥ ደዌው በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከቆዳ በተደረገ ነገር ቢሆን በልብሱ ላይ ባይሰፋ፥ ካህኑ ደዌ ያለበቱ ነገር እንዲታጠብ ያዝዛል፤ ሌላም ሰባት ቀን ይለየዋል። ደዌውም ከታጠበ በኋላ ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው መልኩን ባይለውጥ፥ ባይሰፋም፥ ርኩስ ነው፤ በእሳት ያቃጥሉታል፤ በልብሱም ውስጥ በማጉም፥ በድሩም ወጥቶአልና። “ካህኑም ቢያይ፥ እነሆ፥ ደዌው ከታጠበ በኋላ ቢከስም፥ ከልብሱ ወይም ከድሩ ወይም ከማጉ ወይም ከቆዳው ይቅደደው። በልብሱም ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከቆዳ በተደረገ ነገር ላይ ደግሞ ቢታይ፥ የወጣ ለምጽ ነው፤ ደዌው ያለበትን ነገር ያቃጥሉት። ልብሱ ወይም ድሩ ወይም ማጉ ወይም ከቆዳ የተደረገው ነገር ከታጠበ በኋላ ደዌው ቢለቅቀው ሁለተኛ ጊዜ ይታጠባል፤ ንጹሕም ይሆናል። “በበግ ጠጕር ልብስ፥ ወይም በተልባ እግር ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከቆዳ በተደረገ ነገር ላይ ቢሆን፥ ንጹሕ ወይም ርኩስ ያሰኝ ዘንድ የለምጽ ደዌ ሕግ ይህ ነው።”
ዘሌዋውያን 13:1-59 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ “ማንኛውም ሰው በሰውነቱ ቈዳ ላይ ዕብጠት ወይም ችፍታ ወይም ቋቍቻ ቢወጣበትና ይህም ወደ ተላላፊ የቈዳ በሽታ የሚለወጥበት ከሆነ፣ ወደ ካህኑ አሮን ወይም ካህናት ከሆኑት ልጆቹ ወደ አንዱ ያምጡት። ካህኑም በሰውየው ቈዳ ላይ ያለውን ቍስል ይመርምር፤ በቍስሉ በተበከለው አካባቢ ያለው ጠጕር ወደ ነጭነት ተለውጦ ቢያገኘውና ቦታው ጐድጕዶ ወደ ውስጥ ቢገባ፣ ይህ ተላላፊ የቈዳ በሽታ ነው። ካህኑም መርምሮ ይህን ባወቀ ጊዜ፣ ሰውየው በአምልኮው ሥርዐት መሠረት ርኩስ መሆኑ ይገለጽ። በቈዳው ላይ ያለው ቋቍቻ ነጭ ሆኖ ቢታይ፣ ነገር ግን ከቈዳው በታች ዘልቆ ባይገባና በቦታው ላይ የሚገኘው ጠጕር ወደ ነጭነት ባይለወጥ፣ ካህኑ በሽተኛውን ሰባት ቀን ያግልለው። በሰባተኛውም ቀን ካህኑ በሽተኛውን ይመርምረው፤ ቍስሉ ለውጥ ካላመጣና በቈዳውም ላይ ካልተስፋፋ እንደ ገና ሰባት ቀን ያግልለው። በሰባተኛው ቀን ካህኑ እንደ ገና ይመርምረው፤ ቍስሉ ከከሰመና በቈዳው ላይ ካልተስፋፋ፣ ካህኑ ሰውየው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ ቍስሉ ችፍታ እንጂ ሌላ አይደለም። ሰውየው ልብሱን ይጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል። ራሱን ለካህን አሳይቶ መንጻቱ ከታወቀ በኋላ፣ ችፍታው በቈዳው ላይ እየተስፋፋ ከሆነ፣ እንደ ገና ካህኑ ፊት ይቅረብ፤ ካህኑም ይመርምረው፤ ችፍታው በቈዳው ላይ ተስፋፍቶ ከተገኘ፣ ካህኑ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቅ፤ ተላላፊ የቈዳ በሽታ ነው። “ማንኛውም ሰው ተላላፊ የቈዳ በሽታ ከያዘው፣ ወደ ካህኑ ያምጡት፤ ካህኑም ይመርምረው፤ በሰውነቱ ላይ ጠጕሩን ወደ ነጭነት የለወጠ ነጭ ዕባጭ ካለና በዕብጠቱም ውስጥ ቀይ ሥጋ ቢታይ፣ ሥር የሰደደ የቈዳ በሽታ ነውና ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ ርኩስ መሆኑ ግልጽ ስለ ሆነም ሰውየውን አያግልለው። “ደዌው በአካላቱ ሁሉ ላይ በመውጣት በሽተኛውን ከራስ ጠጕር እስከ እግር ጥፍር ያለበሰው መሆኑን ካህኑ እስካየ ድረስ፣ ካህኑ ይመርምረው፤ ደዌው የሰውየውን ሰውነት ሙሉ በሙሉ ሸፍኖት ከተገኘ፣ ያ ሰው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ ሙሉ በሙሉ ነጭ ስለ ሆነ ንጹሕ ነው፤ ነገር ግን ቍስሉ አመርቅዞ ቀይ ሥጋ ቢታይበት ርኩስ ይሁን። ካህኑም የተገለጠውን ቀይ ሥጋ በሚያይበት ጊዜ ርኩስ መሆኑን ያስታውቅ፤ ቀይ ሥጋ ርኩስ ስለ ሆነ፣ ተላላፊ በሽታ ነው። ቀይ ሥጋ ተለውጦ ከነጣ ግን ወደ ካህኑ ይሂድ፤ ካህኑም ይመርምረው፤ ቍስሎች ወደ ነጭነት ተለውጠው ከተገኙ፣ የታመመው ሰው ንጹሕ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ ንጹሕም ይሆናል። “አንድ ሰው በገላው ላይ ዕባጭ ወጥቶ ቢድን፣ ዕባጩ በነበረበት ቦታ ላይም ነጭ ዕብጠት ወይም ነጣ ያለ ቀይ ቋቍቻ ቢታይ፣ ካህኑ ዘንድ ይቅረብ። ካህኑም ይመርምረው፤ ከቈዳው በታች ዘልቆ የገባ ቢሆን በቦታውም ያለው ጠጕር ቢነጣ፣ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ። ነገር ግን ካህኑ በሚመረምርበት ጊዜ ነጭ ጠጕር በውስጡ ከሌለ፣ ዘልቆ ካልገባና የከሰመ ቢሆን፣ ካህኑ ሰባት ቀን ያግልለው። በቈዳው ላይ ተስፋፍቶ ካገኘውም፣ ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ የሚተላለፍ ነው። ቋቍቻው ግን ባለበት ከቈየና ወደ ሌላ ስፍራ ካልተስፋፋ፣ የዕባጩ ጠባሳ እንጂ ሌላ አይደለም፤ ካህኑም ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ። “አንድ ሰው እሳት ቈዳውን ቢያቃጥለውና በተቃጠለው ስፍራ ነጣ ያለ ቀይ ወይም ነጭ ቋቍቻ ቢታይበት፣ ካህኑ ይመርምረው፤ ቋቍቻው ባለበትም ቦታ ያለው ጠጕር ቢነጣና ከቈዳው በታች ዘልቆ ቢገባ፣ በቃጠሎው ሰበብ ከውስጥ የወጣ ተላላፊ በሽታ ነው፤ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ ተላላፊ የቈዳ በሽታ ነው። ነገር ግን ካህኑ በሚመረምርበት ጊዜ ነጭ ጠጕር የሌለበት፣ ከቈዳውም በታች ዘልቆ ያልገባና የከሰመ ቢሆን፣ ካህኑ ሰውየውን ሰባት ቀን ያግልለው። በሰባተኛው ቀን ካህኑ ይመርምረው፤ በሽታውም በቈዳው ላይ ተስፋፍቶ ቢያገኘው፣ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ ተላላፊ የቈዳ በሽታ ነው። ቋቍቻ ባለበት ከቈየና በቈዳው ላይ ካልተስፋፋ፣ ይልቁንም እየከሰመ ከሄደ፣ በቃጠሎው ሰበብ የተከሠተ ዕብጠት ነውና ካህኑ ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ የቃጠሎው ጠባሳ እንጂ ሌላ አይደለም። “በወንድ ወይም በሴት ዐናት ወይም አገጭ ላይ ቍስል ቢወጣ፣ ካህኑ ቍስሉን ይመርምር፤ ከቈዳው በታች ዘልቆ ከገባ፣ በውስጡም ያለው ጠጕር ቢጫና ቀጭን ከሆነ ያ ሰው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ የሚያሳክክ የራስ ወይም የአገጭ ተላላፊ በሽታ ነው። ካህኑ እንዲህ ዐይነቱን ቍስል በሚመረምርበት ጊዜ፣ ከቈዳው በታች ዘልቆ ካልገባና በውስጡም ጥቍር ጠጕር ከሌለ፣ ካህኑ ሰውየውን ሰባት ቀን ያግልለው። ካህኑም በሰባተኛው ቀን ቍስሉን ይመርምር፤ የሚያሳክከው ቦታ ያልሰፋ፣ ቢጫ ጠጕር የሌለውና ከቈዳው በታች ዘልቆ ያልገባ ከሆነ፣ ከቈሰለው ቦታ በቀር ጠጕሩን ይላጭ፤ ካህኑ ሰባት ተጨማሪ ቀን ሰውየውን ያግልል። ካህኑ በሰባተኛው ቀን የሚያሳክከውን የሰውየውን ቍስል ይመርምር፤ በቈዳው ላይ ካልሰፋና ከቈዳው በታች ዘልቆ ካልገባ ካህኑ ያ ሰው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ ልብሱን ዐጥቦ ንጹሕ ይሁን። ንጹሕ መሆኑ ከተገለጠ በኋላ ግን የሚያሳክከው ቍስል ተስፋፍቶ ቢገኝ፣ ካህኑ ይመርምረው፤ ቍስሉ በቈዳው ላይ ከሰፋ፣ ካህኑ የጠጕሩን ቢጫ መሆን አለመሆን ማየት አያሻውም፤ ሰውየው ርኩስ ነው። ነገር ግን ቍስሉ በካህኑ አመለካከት ለውጥ ያላሳየ ከሆነና በውስጡ ጥቍር ጠጕር ካበቀለ ቍስሉ ድኗል፤ ሰውየው ነጽቷል፤ ካህኑም ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ። “በወንድ ወይም በሴት ቈዳ ላይ ቋቍቻ ቢወጣ፣ ካህኑ ይመርምራቸው፤ ቋቍቻው ዳለቻ ከሆነ፣ በቈዳ ላይ የወጣ ጕዳት የማያስከትል ችፍታ ነው፤ ሰውየውም ንጹሕ ነው። “አንድ ሰው የራሱ ጠጕር ከዐናቱ ዐልቆ መላጣ ቢሆን ንጹሕ ነው። ጠጕሩ ከፊት ለፊት ተመልጦ ራሰ በራ ቢሆንም ንጹሕ ነው። ነገር ግን በመላጣው ወይም በበራው ላይ ነጣ ያለ ቀይ ቍስል ቢወጣበት፣ ያ ከመላጣው ወይም ከበራው የወጣ ተላላፊ በሽታ ነው። ካህኑ ይመርምረው፤ በመላጣው ወይም በበራው ላይ ያበጠው ተላላፊ የቈዳ በሽታ የሚመስል ነጣ ያለ ቍስል ከሆነ፣ ሰውየው ደዌ አለበት፤ ርኩስም ነው፤ በራሱ ላይ ካለው ቍስል የተነሣም ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ። “እንዲህ ያለ ተላላፊ በሽታ ያለበት ሰው የተቀደደ ልብስ ይልበስ፤ ጠጕሩን ይግለጥ፤ እስከ አፍንጫውም ድረስ ተሸፋፍኖ ‘ርኩስ ነኝ! ርኩስ ነኝ!’ እያለ ይጩኽ። ተላላፊ በሽታው እስካለበት ጊዜ ድረስ ርኩስ ነው፤ ብቻውን ይቀመጥ፤ ከሰፈር ውጪም ይኑር። “ከበግ ጠጕር ወይም ከበፍታ የተሠራ ማንኛውም ዐይነት ልብስ በተላላፊ በሽታ ቢበከል፣ በሸማኔ ዕቃ ወይም በእጅ የተሠራ ማንኛውም ዐይነት የበግ ጠጕር ወይም የበፍታ ልብስ ወይም ማንኛውም ቈዳ ወይም ከቈዳ የተሠራ ነገር ቢሆን፣ በልብስ ወይም በዐጐዛ፣ በሸማኔ ዕቃ በተሠራ ወይም በእጅ በተጠለፈ ወይም ከቈዳ በተሠራ ዕቃ ላይ አረንጓዴ ወይም ቀይ መሳይ ደዌ ቢከሠት፣ እየሰፋ የሚሄድ ተላላፊ በሽታ ስለ ሆነ ካህኑ ይየው። ካህኑ ደዌውን ይመርምር፤ በደዌ የተበከለውንም ዕቃ ሰባት ቀን ያግልል። በሰባተኛውም ቀን ይመርምረው፤ ደዌው በልብሱ፣ በሸማኔ ዕቃ በተሠራው ወይም በእጅ በተጠለፈው ጨርቅ ወይም ለማንኛውም አገልግሎት በሚውል ዐጐዛ ላይ ተስፋፍቶ ቢገኝ፣ ክፉ ደዌ ነው፤ ዕቃውም ርኩስ ነው። ልብሱን ወይም በሸማኔ ዕቃ የተሠራውን ወይም በእጅ የተጠለፈውን የበግ ጠጕር ወይም በፍታ ወይም ደዌው ያለበትን ማንኛውንም ከቈዳ የተሠራ ዕቃ ያቃጥል፤ ደዌው ክፉ ነውና፤ ዕቃው ይቃጠል። “ነገር ግን ካህኑ በሚመረምርበት ጊዜ ደዌው በልብሱ ወይም በሸማኔ ዕቃ በተሠራው ወይም በእጅ በተጠለፈው ጨርቅ ላይ፣ ወይም ከቈዳ በተሠራው ዕቃ ላይ ተስፋፍቶ ካልተገኘ፣ ካህኑ ደዌው ያለበት ነገር እንዲታጠብ ይዘዝ፤ ዕቃውንም ሰባት ቀን ደግሞ ያግልል። ደዌው ያለበት ዕቃ ከታጠበ በኋላ ካህኑ ይመርምረው፤ ደዌው ባይስፋፋም እንኳ መልኩን ካልለወጠ፣ ርኩስ ነው፤ ደዌው የወጣው በውስጥም ሆነ በውጭ ዕቃው በእሳት ይቃጠል። ዕቃው ከታጠበ በኋላ ካህኑ በሚመረምርበት ጊዜ ደዌው ከስሞ ቢገኝ፣ በደዌ የተበከለውን ቦታ ከልብሱ ወይም ከቈዳው ወይም በሸማኔ ዕቃ ከተሠራው ወይም በእጅ ከተጠለፈው ጨርቅ ቀዶ ያውጣ። ነገር ግን ደዌው በልብሱ ወይም በሸማኔ ዕቃ በተሠራው ወይም በእጅ በተጠለፈው ጨርቅ ላይ ወይም ከቈዳ በተሠራው ዕቃ ላይ ቢታይ፣ መስፋፋቱ ስለ ሆነ ደዌው ያለበት ማንኛውም ነገር በእሳት ይቃጠል። ታጥቦ ከደዌ የጠራ ልብስ ወይም በሸማኔ ዕቃ የተሠራ ወይም በእጅ የተጠለፈ ጨርቅ ወይም ከቈዳ የተሠራ ማንኛውም ዕቃ እንደ ገና ይታጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል።” ከበግ ጠጕር ወይም ከበፍታ የተሠራ ልብስ ወይም በሸማኔ ዕቃ የተሠራ ወይም በእጅ የተጠለፈ ጨርቅ ወይም ከቈዳ የተሠራ ማንኛውም ዕቃ በደዌ ቢበከል፣ ንጹሕ ወይም ርኩስ መሆኑን ለማወቅ ሕጉ ይህ ነው።
ዘሌዋውያን 13:1-59 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ ማናቸውም ሰው በሥጋው ቁርበት ላይ እባጭ ወይም ብጉር ወይም ቍቁቻ ቢታይ፥ በሥጋው ቁርበት እንደ ለምጽ ደዌ ቢመስል፥ ወደ ካህኑ ወደ አሮን ወይም ከካህናቱ ልጆቹ ወደ አንዱ ያምጡት። ካህኑም በሥጋው ቁርበት ያለውን ደዌ ያያል፤ ጠጉሩም ተለውጦ ቢነጣ ደዌውም ወደ ሥጋው ቁርበት ቢጠልቅ፥ እርሱ የለምጽ ደዌ ነው፤ ካህኑም አይቶ፦ ርኩስ ነው ይበለው። ቍቁቻውም በሥጋው ቁርበት ላይ ቢነጣ፥ ከቁርበቱም የጠለቀ ባይመስል፥ ጠጉሩም ባይነጣ፥ ካህኑ የታመመውን ሰው ሰባት ቀን ይዘጋበታል። በሰባተኛውም ቀን ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው በዓይኑ ፊት እንደ ነበረ ቢሆን፥ በቁርበቱም ላይ ባይሰፋ፥ ካህኑ ሰባት ቀን ደግሞ ይዘጋበታል። ደግሞ በሰባተኛው ቀን ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ቢከስም፥ ደዌውም በቁርበቱ ላይ ባይሰፋ፥ ካህኑ፦ ንጹሕ ነው ይለዋል፤ እከክ ነው፤ ልብሱንም አጥቦ ንጹሕ ይሆናል። ስለ መንጻቱ በካህኑ ዘንድ ከታየ በኋላ እከኩ በቁርበቱ ላይ ቢሰፋ፥ እንደ ገና ሊታይ ወደ ካህኑ ይቀርባል። ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ እከኩ በቁርበቱ ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ ለምጽ ነው። የለምጽ ደዌ በሰው ውስጥ ቢሆን እርሱን ወደ ካህኑ ያመጡለታል። ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ በቁርበቱ ላይ ነጭ እባጭ ቢሆን፥ ጠጉሩም ተለውጦ ቢነጣ፥ ሥጋውም በእባጩ ውስጥ ቢያዥ፥ እርሱ በሥጋው ቁርበት ላይ አሮጌ ለምጽ ነው፥ ካህኑም፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ እርሱ ርኩስ ነውና አይዘጋበትም። ለምጹም በቁርበቱ ላይ ሰፍቶ ቢወጣ፥ ለምጹም የታመመውን ሰው ቁርበቱን ሁሉ ከራሱ እስከ እግሮቹ ድረስ እንደ ከደነው ላካህኑ ቢመስለው፥ ካህኑ ያያል፤ እነሆም፥ ለምጹ ሥጋውን ሁሉ ቢከድን የታመመውን ሰው፦ ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ሥጋው ሁሉ ፈጽሞ ተለውጦ ነጭ ሆኖአል፤ ንጹሕ ነው። የሚያዠው ሥጋ ግን ሲታይበት ርኩስ ይሆናል። ካህኑም የሚያዠውን ሥጋ አይቶ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ የሚያዠው ሥጋ ለምጽ ነውና ርኩስ ነው። የሚያዠውም ሥጋ ተለውጦ ቢነጣ እንደ ገና ወደ ካህኑ ይመጣል። ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ቢነጣ ካህኑ የታመመውን፦ ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ንጹሕ ነው። በሥጋውም ቁርበት ላይ ቍስል ቢሆንና ቢሽር፥ በቍስሉም ስፍራ ነጭ እባጭ ወይም ቀላ ያለ ቍቁቻ ቢወጣ፥ በካህኑ ዘንድ ይታያል። ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ ወደ ቁርበቱ ውስጥ ጠልቆ ቢታይ፥ ጠጉሩም ተለውጦ ቢነጣ፥ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው፤ ከቍስሉ ውስጥ ወጥቶአል። ካህኑም ቢያየው፥ ነጭም ጠጉር ባይኖርበት፥ ወደ ቁርበቱም ውስጥ ባይጠልቅ ነገር ግን ቢከስም፥ ካህኑ ሰባት ቀን ይዘጋበታል። በቁርበቱም ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ ደዌ ነው። ቍቁቻው ግን በስፍራው ቢቆም ባይሰፋም፥ የቍስል ጠባሳ ነው፤ ካህኑም፦ ንጹሕ ነው ይለዋል። በሥጋው ቁርበት የእሳት ትኵሳት ቢኖርበት፥ በተቃጠለውም ስፍራ ነጭ ወይም ቀላ ያለ ቍቁቻ ቢታይ፥ ካህኑ ያየዋል፥ እነሆም፥ በቍቁቻው ጠጕሩ ተለውጦ ቢነጣ፥ ወደ ቁርበቱም ውስጥ ቢጠልቅ፥ ለምጽ ነው፤ ከተቃጠለውም ስፍራ ወጥቶአል፤ ካህኑም፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው። ካህኑም ቢያየው፥ በቍቁቻውም ነጭ ጠጕር ባይኖር፥ ወደ ቁርበቱም ባይጠልቅ ነገር ግን ቢከስም፥ ካህኑ ሰባት ቀን ይዘጋበታል። ካህኑም በሰባተኛው ቀን ያየዋል፤ በቁርበቱም ላይ ቢሰፋ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው። ቍቁቻውም በስፍራው ላይ ቢቆም፥ በቁርበቱም ላይ ባይሰፋ ነገር ግን ቢከስም፥ የትኩሳት እባጭ ነው፤ የትኩሳትም ጠባሳ ነውና ካህኑ፦ ንጹሕ ነው ይለዋል፥ ማናቸውም ወንድ ወይም ሴት በራሱ ወይም በአገጩ ደዌ ቢኖርበት፥ ካህኑ ደዌውን ያያል፤ እነሆም፥ ወደ ቁርበቱ ቢጠልቅ፥ በውስጡም ቀጭን ብጫ ጠጕር ቢኖርበት፥ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ ቈረቈር ነው፤ የራስ ወይም የአገጭ ለምጽ ነው። ካህኑም የቈረቈሩን ደዌ ቢያይ፥ ወደ ቁርበቱም ባይጠልቅ፥ ጥቁርም ጠጕር ባይኖርበት፥ ካህኑ የቈረቈር ደዌ ያለበትን ሰው ሰባት ቀን ይዘጋበታል። ካህኑም በሰባተኛው ቀን ደዌውን ያያል፤ እነሆም፥ ቈረቈሩ ባይሰፋ፥ በውስጡም ብጫ ጠጕር ባይኖር፥ የቈረቈሩም መልክ ወደ ቁርበቱ ባይጠልቅ፥ ይላጫል፥ ቈረቈሩ ግን አይላጭም፤ ካህኑም ቈረቈር ያለበትን ሰው ሰባት ቀን ደግሞ ይዘጋበታል። ካህኑም በሰባተኛው ቀን ቈረቈሩን ያያል፤ እነሆም፥ ቈረቈሩ በቁርበቱ ላይ ባይሰፋ፥ መልኩም ወደ ቁርበቱ ባይጠልቅ፥ ካህኑ፦ ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ልብሱን አጥቦ ንጹሕ ይሆናል። ከነጻ በኋላ ግን ቈረቈሩ በቁርበቱ ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ቈረቈሩ በቁርበቱ ላይ ቢሰፋ ካህኑ ብጫውን ጠጕር አይፈልግም፤ ርኩስ ነው። ቈረቈሩ ግን በዓይኑ ፊት እንደ ነበረ ቢሆን፥ ጥቁርም ጠጕር ቢበቅልበት፥ ቈረቈሩ ሽሮአል እርሱም ንጹሕ ነው፤ ካህኑም፦ ንጹሕ ነው ይለዋል። ማናቸውም ወንድ ወይም ሴት በሥጋው ቁርበት ላይ ነጭ ቍቁቻ ቢኖርበት፥ ካህኑ ያያል፤ እነሆም፥ በሥጋቸው ቁርበት ላይ ያለው ቍቁቻ ፈገግ ቢል አጓጐት ነው፤ ከቁርበቱ ውስጥ ወጥቶአል፤ ንጹሕ ነው። የሰውም ጠጕር ከራሱ ቢመለጥ እርሱ ቡሀ ነው፤ ነገር ግን ንጹሕ ነው። ጠጕሩም ከግምባሩ ቢመለጥ እርሱ ራሰ በራ ነው፤ ነገር ግን ንጹሕ ነው። በቡሀነቱ ወይም በራሰ በራነቱ ነጭ ወይም ቀላ ያለ ደዌ ቢኖርበት፥ እርሱ ከቡሀነቱ ወይም ከራሰ በራነቱ የወጣ ለምጽ ነው። ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም፥ የደዌው እብጠት፥ በሥጋው ቁርበት ላይ የሆነ ለምጽ መስሎ፥ በቡሀነቱ ወይም በራሰ በራነቱ ነጭ ወይም ቀላ ያለ ቢሆን፥ ለምጻም ሰው ነው፤ ርኩስ ነው፤ ካህኑ፦ በእርግጥ ርኩስ ነው ይለዋል፤ ደዌው በራሱ ነው። የለምጽ ደዌ ያለበት ሰው ልብሱ የተቀደደ ይሁን፥ ራሱም የተገለጠ ይሁን፥ ከንፈሩንም ይሸፍን፤ ርኩስ ርኩስ ነኝ ይበል። ደዌው ባለበት ዘመን ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ እርሱ ርኩስ ነው፤ ብቻውን ይቀመጣል፤ መኖሪያውም ከሰፈር በውጭ ይሆናል። የለምጽም ደዌ በልብስ ላይ ቢሆን፥ ልብሱም የበግ ጠጕር ወይም በፍታ ቢሆን፥ በድሩ ወይም በማጉ ላይ ቢሆን፥ በፍታ ወይም የበግ ጠጕር ቢሆን፥ አጐዛ ወይም ከአጐዛ የሚደረግ ነገር ቢሆን፥ ደዌው በልብሱ ወይም በአጐዛው ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከአጐዛው በሚደረገው ነገር አረንጓዴ ወይም ቀይ ቢሆን፥ የለምጽ ደዌ ነው፤ ለካህኑ ይታያል። ካህኑም ደዌውን አይቶ ደዌው ያለበትን ነገር ሰባት ቀን ይዘጋበታል። በሰባተኛውም ቀን ደዌውን ያያል፤ ደዌውም በልብስ ላይ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም በአጐዛው ወይም ከአጐዛው በሚደረግ ነገር ቢሰፋ፥ ደዌው እየገፋ የሚሄድ ለምጽ ነው፤ ርኩስ ነው። ልብሱን ያቃጥል፤ ድሩ ወይም ማጉ የበግ ጠጕር ወይም በፍታ ቢሆን ወይም ከአጐዛው የተደረገ ቢሆን፥ ደዌ ያለበት ሁሉ፥ እየገፋ የሚሄድ ለምጽ ነውና በእሳት ይቃጠል። ካህኑ ቢያይ፥ እነሆም፥ ደዌው በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከአጐዛ በተደረገ ነገር ቢሆን በልብሱ ላይ ባይሰፋ፥ ካህኑ ደዌ ያለበቱ ነገር እንዲታጠብ ይዘዝ፤ ሌላም ሰባት ቀን ይዘጋበታል። ደዌውም ከታጠበ በኋላ ካህኑ ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው መልኩን ባይለውጥ ባይሰፋም፥ ርኩስ ነው፤ በእሳት አቃጥለው፤ ምልክቱ በውስጥ ወይም በውጭ ቢሆን እየፋገ የሚሄድ ደዌ ነው። ካህኑም ቢያይ፥ እነሆም፥ ደዌው ከታጠበ በኋላ ቢከስም፥ ከልብሱ ወይም ከአጐዛው ወይም ከድሩ ወይም ከማጉ ይቅደደው። በልብሱም ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከአጐዛው በተደረገ ነገር ላይ ደግሞ ቢታይ፥ የወጣ ለምጽ ነው፤ ደዌው ያለበትን ነገር አቃጥለው። አንተም ካጠብኸው ልብስ ወይም ከድሩ ወይም ከማጉ ወይም ከአጐዛው ከተደረገው ነገር ላይ ደዌው ቢጠፋ፥ ሁለተኛ ጊዜ ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል። በበግ ጠጕር ልብስ ወይም በበፍታ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከአጐዛ በተደረገ ነገር ላይ ቢሆን፥ ንጹሕ ወይም ርኩስ ያሰኝ ዘንድ የለምጽ ደዌ ሕግ ይህ ነው።
ዘሌዋውያን 13:1-59 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ “ማንም ሰው በሰውነቱ ላይ እባጭ ወይም ሽፍታ ወይም ቋቊቻ ቢታይና በገላው ላይ የሥጋ ደዌ ቢመስል፥ ወደ ካህኑ ወደ አሮን ወይም ካህናት ከሆኑት ከልጆቹ ወደ አንዱ ያምጡት። ካህኑም ቊስሉን ይመርምር፤ በዚያም ቊስል ላይ ያለው ጠጒር ወደ ነጭነት ቢለወጥ፥ ቊስሉም በዙሪያው ካለው ቆዳ ይልቅ ጐድጒዶ ቢገኝ፥ እርሱ የሥጋ ደዌ በሽታ ነው፤ ካህኑም ያ ሰው ርኩስ መሆኑን ያስታውቅ። ነገር ግን ቊስሉ ነጭ ሆኖ በዙሪያው ካለው ቆዳ ይልቅ ጐድጐድ ብሎ ባይገኝና ጠጒሩም ወደ ነጭነት ባይለወጥ፥ ካህኑ ያን ሰው ለሰባት ቀን በቤት ውስጥ ተዘግቶበት እንዲቈይ ያድርግ፤ ካህኑ በሰባተኛው ቀን እንደገና ይመርምረው፤ በሚመረምረውም ጊዜ ቊስሉ ምንም ለውጥ ሳያሳይ እንደ ነበረ ሳይስፋፋ ቢያገኘው፥ አሁንም ለሰባት ቀን በቤት ውስጥ ተዘግቶበት እንዲቈይ ያድርግ። ካህኑም እንደገና በሰባተኛው ቀን ይመርምረው፤ በሚመረምረውም ጊዜ ቊስሉ በመስፋፋት ፈንታ ከስሞ ከተገኘ፥ ቊስሉ እከክ ብቻ መሆኑን ገልጦ ያ ሰው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ ያም ሰው ስለ መንጻቱ ልብሱን ይጠብ፤ ነገር ግን ካህኑ መርምሮ ንጹሕ መሆኑን ካስታወቀለት በኋላ፥ ቊስሉ ተስፋፍቶ ቢገኝ ያ ሰው እንደገና በካህኑ ፊት ይቅረብ፤ ካህኑም እንደገና ይመርምረው፤ ቊስሉም ተስፋፍቶ ከተገኘ የሥጋ ደዌ በሽታ ስለ ሆነ የረከሰ የሥጋ ደዌ በሽተኛ መሆኑን ያስታውቅ። “ማንም ሰው የሥጋ ደዌ በሽታ ቢይዘው ወደ ካህኑ ያምጡት፤ ካህኑም ይመርምረው፤ በቈዳው ላይ ነጭ እባጭ ቢሆን፥ ጠጒሩም ተለውጦ ቢነጣ፥ ሥጋውም በእባጩ ውስጥ ቢያዥ፥ እርሱ በቈዳው ላይ የቈየ የሥጋ ደዌ ስለ ሆነ ካህኑ ሕመምተኛው የረከሰ መሆኑን ያስታውቅ፤ የረከሰ መሆኑ በግልጥ ስለ ታወቀ እንደዚህ ያለው ሰው በቤት ውስጥ ተዘግቶበት መቈየት አያስፈልገውም። እንደ ካህኑ አስተያየት የሥጋ ደዌው በሽታ ሰውየውን ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ጠጒሩ የሸፈነው ከሆነ፥ ካህኑ እንደገና ይመርምረው፤ መላ ሰውነቱን ሸፍኖት ቢያገኘው፥ ቆዳው በሙሉ ወደ ነጭነት ከተለወጠ የነጻ ስለሚሆን ካህኑ ያ ሰው የነጻ መሆኑን ያስታውቅ፤ ነገር ግን በሥጋው ላይ የሚያዥ ቊስል ቢታይበት የረከሰ ይሆናል። ካህኑም እንደገና መርምሮት የሚያዥ ቊስል ቢያገኝ፥ ያ ሰው የረከሰ መሆኑን ያስታውቅ፤ የሚያዥ፥ የሥጋ ደዌ በሽታ ስለ ሆነ ያ ሰው ርኩስ ነው። ቊስሉ ቢፈወስና እንደገና ወደ ነጭነት ቢለወጥ ግን እንደገና ወደ ካህኑ ይሄዳል፤ ካህኑም እንደገና መርምሮት ቊስሉ ወደነጭነት ተለውጦ ከተገኘ ያ ሰው የነጻ ይሆናል፤ ካህኑም ሰውየው ንጹሕ መሆኑን ያሳውቅለታል። “አንድ ሰው የዳነ እባጭ ቢኖርበትና፥ ዘግየት ብሎም ቊስሉ ባለበት ቦታ ነጭ እባጭ ወይም ቀላ ያለ ቋቁቻ ዐይነት ቊስል ቢወጣበት ወደ ካህኑ ይሂድ፤ ካህኑም መርምሮት ቊስሉ ያለበት ቦታ ከሌላው የሰውነቱ ቆዳ ይልቅ ጐድጒዶ ቢገኝና በቈዳው ላይ ያለውም ጠጒር ወደ ነጭነት ቢለወጥ እርሱም በእባጭ የተጀመረ የሥጋ ደዌ በሽታ ስለ ሆነ ርኩስ መሆኑን ያስታውቅ። ነገር ግን ካህኑ መርምሮት በቈዳው ላይ ያለው ጠጒር ወደ ነጭነት ባይለወጥና ከሌላው የሰውነቱ ቆዳ ይበልጥ ጐድጒዶ ባይገኝ፥ የቀለሙ ልዩነት ስለ ተቀነሰ ካህኑ ያን ሰው ለሰባት ቀን በቤት ውስጥ ተዘግቶበት እንዲቈይ ያድርግ፤ ቊስሉ ያለበትም ቦታ እየሰፋ መሄዱ ከታወቀ፥ ያ የሥጋ ደዌ ስለ ሆነ ርኩስ መሆኑን ያስታውቅ። ነገር ግን ቋቁቻው ምንም ለውጥ ሳያደርግና ሳይስፋፋ ቢገኝ የእባጭ ጠባሳ መሆኑ ታውቆ መንጻቱን ካህኑ ያስታውቅለት። “የእሳት ቃጠሎ የደረሰበት ሰው ቢኖርና የተቃጠለ ሥጋው ቢነጣ ወይም ቀላ ያለ ነጭ ሆኖ ቢገኝ፥ ካህኑ ይመርምረው፤ ቊስሉ ባለበት ስፍራ የበቀለው ጠጒር ነጭ ቢሆንና ያም ስፍራ በዙሪያው ካለው የሰውነቱ ቆዳ ይልቅ ጐድጒዶ ከተገኘ፥ ከእሳት ቃጠሎ የመጣ የሥጋ ደዌ በሽታ ነው፤ ስለዚህም ካህኑ ያ ሰው የረከሰ መሆኑን ያስታውቅ። ይህም የሥጋ ደዌ ነው። ነገር ግን በእርሱ ላይ የበቀለው ጠጒር ወደ ነጭነት ካልተለወጠ በዙሪያውም ካለው የሰውነቱ ቆዳ ይልቅ ጐድጒዶ ካልተገኘና የቀለም መለዋወጥ ብቻ ሆኖ ከተገኘ፥ ካህኑ ያ ሰው ለሰባት ቀን በቤት ውስጥ ተዘግቶበት እንዲቈይ ያድርግ። በሰባተኛውም ቀን ካህኑ እንደገና ይመርምረው፤ ቊስሉ ተስፋፍቶ ከተገኘ የሥጋ ደዌ በሽታ ነው፤ ስለዚህም ያ ሰው የረከሰ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ። ነገር ግን ቊስሉ ያለበት ስፍራ ምንም ለውጥ ሳያሳይና ሳይስፋፋ የቀለም መለዋወጥ ብቻ ሆኖ ከተገኘ በእሳት ቃጠሎ ምክንያት የመጣ ጠባሳ ስለ ሆነ ያ ሰው ንጹሕ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅለት። “አንድ ወንድ ወይም አንዲት ሴት በራስ ወይም በአገጭ ላይ ቊስል ቢወጣበት ወይም ቢወጣባት፥ ካህኑ ቊስሉን ይመርምር፤ በዙሪያው ካለው የሰውነት ቆዳ ይልቅ ወደ ውስጥ ጐድጒዶ በእርሱ ላይ የበቀለውም ጠጒር ወደ ቢጫነት በመለወጥ ስስ ሆኖ ከተገኘ የራስ ወይም የአገጭ ቈረቈር ወይም የሥጋ ደዌ ስለ ሆነ ያ ሰው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ። ነገር ግን ካህኑ ሲመረምረው የሚያሳክከው ቊስል በዙሪያው ካለው የሰውነቱ ቆዳ ይልቅ ጐድጒዶ የማይታይ ከሆነና በላዩ ላይ ያለው ጠጒር ጤናማ ካልሆነ፥ በሚያሳክከው ቊስል ምክንያት ያ ሰው በቤት ውስጥ ተዘግቶበት ለሰባት ቀን እንዲቈይ ያድርግ፤ በሰባተኛው ቀን እንደገና ካህኑ ይመርምረው፤ ቊስሉ እየተስፋፋ ካልሄደ፥ ወደ ቢጫነት የተለወጠ ጠጒርም ከሌለና በዙሪያው ካለው ከሌላው ሰውነቱ ቆዳ ይልቅ ጐድጒዶ ካልተገኘ፥ ያ ሰው ቊስሉን ሳይሆን በቊስሉ ዙሪያ ያለውን ጠጒር ይላጭ፤ ካህኑም እንደገና በሚያሳክከው በሽታ ምክንያት ለሰባት ቀን በቤት ውስጥ ተዘግቶበት እንዲቈይ ያድርግ። በሰባተኛውም ቀን እንደገና ካህኑ ቊስሉን ይመርምር፤ ቊስሉ በመስፋፋት ላይ ካልተገኘና በዙሪያውም ካለው የሰውነቱ ቆዳ ይልቅ የጐደጐደ ካልሆነ ያ ሰው የነጻ መሆኑን ያስታውቅለት፤ ሰውየው ልብሱን ይጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል። ሆኖም ንጹሕ መሆኑ ከተገለጠ በኋላ ቊስሉ እያመረቀዘ ተስፋፍቶ ቢገኝ፥ ካህኑ እንደገና ይመርምረው፤ ቊስሉ በእርግጥ ተስፋፍቶ ከሆነ ሰውየው የረከሰ በመሆኑ ወደ ቢጫነት የተለወጠ ጠጒር መኖርና አለመኖሩ አስፈላጊ አይደለም። ነገር ግን በካህኑ አመለካከት ቊስሉ ካልተስፋፋና ጤናማ ጠጒርም በቅሎበት ከተገኘ፥ ቊስሉ የተፈወሰ ስለ ሆነ፥ ንጹሕ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅለት። “አንድ ሰው ወይም አንዲት ሴት በቈዳ ላይ ነጭ ቋቁቻ ቢወጣባቸው፥ ካህኑ ያን ሰው ይመርምር፤ ቋቁቻ ያለበትም ስፍራ ደብዘዝ ያለ ነጭ ቢሆን ብዙ ጒዳት የማያመጣ በቈዳ ላይ የሚታይ ሽፍታ ስለ ሆነ ያ ሰው ንጹሕ ነው። አንድ ሰው ጠጒሩ ከራሱ ላይ ቢመለጥ ራሰ በራ ነው እንጂ ንጹሕ ነው። አንድ ሰው ከግምባሩና ከዐናቱ ጠጒር ቢመለጥ ራሰ በራ ነው እንጂ ንጹሕ ነው። ነገር ግን በራ በሆነው ራስ ወይም ግንባር ላይ ወደ ቀይነት ያደላ ነጭ ቊስል ቢታይበት እርሱ የሥጋ ደዌ በሽታ ነው። ካህኑም መርምሮ በበራ ራሱ ወይም በበራ ግንባሩ ላይ በሰውነት ላይ የሚወጣ የሥጋ ደዌ በሽታ ዐይነት ቀላ ያለ የእባጭ ቊስል ቢያገኝ፥ እርሱ የሥጋ ደዌ በሽተኛ ሰው በመሆኑ የረከሰ ነውና የረከሰ መሆኑን ካህኑ ያውጅ፤ በሽታውም በራሱ ላይ ነው። “በዚህ ዐይነት የሥጋ ደዌ በሽታ ያለበት ሰው የተቀዳደደ ልብስ ይልበስ፤ ጠጒሩን አያበጥር፥ ከንፈሩን ይሸፍን፤ ከዚያም በኋላ ‘እኔ የረከስኩ ነኝ! የረከስኩ ነኝ!’ እያለ ይጩኽ። ይህም በሽታ እስካለበት ድረስ ያ ሰው የረከሰ ይሆናል። ስለዚህም ከኅብረተሰብ ተለይቶ መኖሪያው ከሰፈር ውጪ ይሆናል። “ሻጋታ ነገር ከበግ ጠጒር ወይም ከበፍታ በተሠራ ልብስ ቢወጣ፥ በድሩም ሆነ በማጉ ላይ፥ እንዲሁም ከሱፍ ወይም ከቈዳ ወይም ከቈዳ በተሠራ ልብስ ላይ ቢታይና፥ መልኩም ወደ አረንጓዴነት ወይም ወደ ቀይነት ቢያደላ፥ የሚተላለፍ ሻጋታ ስለ ሆነ ለካህኑ ይታይ። ካህኑም ይመርምረውና እነዚህ ሁሉ የልብስ ዐይነቶች እስከ ሰባት ቀን ድረስ በአንድ ክፍል ተዘግቶባቸው ይቈዩ። በሰባተኛውም ቀን እንደገና በሚመረምረው ጊዜ ሻጋታው ነገር ተስፋፍቶ ከታየበት ያ የታየው አጥፊ ሻጋታ ስለ ሆነ፥ የዚያ ዐይነቱ ልብስ ሁሉ ርኩስ ነው፤ ይህም አጥፊ ሻጋታ እየሰፋ የሚሄድ ስለ ሆነ በእሳት ይቃጠል። “ነገር ግን ካህኑ በሚመረምርበት ጊዜ ሻጋታው ተስፋፍቶ ካልተገኘ፥ ልብሱ በውሃ ታጥቦ እስከ ሰባት ቀን ድረስ ለብቻ እንዲቀመጥ ያድርግ። ከዚህም በኋላ እንደገና ይመርምረው፤ ምንም እንኳ በማፋግ ባይስፋፋ የሻጋታው ቀለም ካልተለወጠ በቀር፥ አሁንም ርኩስ ነው፤ ከፊትም ሆነ ከኋላ ሻጋታ ወይም የመበስበስ መልክ የሚታይበት ያ ልብስ ይቃጠል። ነገር ግን ካህኑ እንደገና በሚመረምርበት ጊዜ ሻጋታው ተቀንሶ ካገኘው፥ የመሻገት ምልክት ያለበትን ስፍራ ብቻ ከጨርቅ ወይም ከቈዳ ልብስ ቀዶ ያውጣው። ሻጋታው እንደገና ቢታይ እርሱ እየተስፋፋ የሚሄድ ስለ ሆነ፥ ባለ ንብረቱ ያቃጥለው። ልብሱ በሚታጠብበት ጊዜ የሻጋታው ምልክት ቢጠፋ እንደገና ይጠበው፤ ከዚያም በኋላ የነጻ ይሆናል።” ይህ እንግዲህ ከበፍታም ሆነ ከበግ ጠጒር፥ ወይም ከቈዳ በተሠራ ልብስ ላይ በድሩም ሆነ በማጉ በሻጋታ አማካይነት የሚተላለፍ ምልክት ተመርምሮ የሚታወቅበት የሥርዓት መመሪያ ነው።
ዘሌዋውያን 13:1-59 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ ማናቸውም ሰው በሰውነቱ ቆዳ ላይ እባጭ ወይም ብጉር ወይም ቋቁቻ ቢታይ፥ በሰውነቱ ቆዳ እንደ ለምጽ ደዌ ቢሆን፥ ወደ ካህኑ ወደ አሮን ወይም ካህናት ከሆኑት ከልጆቹ ወደ አንዱ ያምጡት። ካህኑም በሰውነቱ ቆዳ ላይ ያለውን ደዌ ያያል፤ ጠጉሩም ተለውጦ ቢነጣ ደዌውም ከሰውነቱ ቆዳ በታች ዘልቆ ቢታይ፥ እርሱ የለምጽ ደዌ ነው፤ ካህኑም አይቶ፦ ርኩስ ነው ይበለው። ነገር ግን ቋቁቻው በሰውነቱ ቆዳ ላይ ቢነጣ፥ ከቆዳውም በታች ዘልቆ ባይታይ፥ በእርሱም ላይ ያለው ጠጉር ባይነጣ፥ ካህኑ የታመመውን ሰው ሰባት ቀን ይለየዋል። በሰባተኛውም ቀን ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው መገታቱን ቢያይ፥ በቆዳውም ላይ ባይሰፋ፥ አሁንም ካህኑ ሰባት ቀን ይለየዋል። በሰባተኛውም ቀን ካህኑ ዳግም ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ቢከስም፥ ደዌውም በቆዳው ላይ ባይሰፋ፥ ካህኑ፦ ንጹሕ ነው ይለዋል፤ እከክ ነው፤ ልብሱንም ያጥብና ንጹሕ ይሆናል። ስለ መንጻቱ በካህኑ ዘንድ ከታየ በኋላ እከኩ በቆዳው ላይ ቢስፋፋ፥ እንደገና ሊታይ ወደ ካህኑ ይቀርባል። ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ እከኩ በቆዳው ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ እርሱ የለምጽ ደዌ ነው። ማናቸውም ሰው በለምጽ ደዌ ቢጠቃ እርሱን ወደ ካህኑ ያመጡታል፤ ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ በቆዳው ላይ ነጭ እባጭ ቢኖር፥ በእርሱም ላይ ያለውን ጠጉር ለውጦት ቢያነጣው፥ ሥጋውም በእባጩ ውስጥ ቢያዥ፥ እርሱ በሰውነቱ ቆዳ ላይ የቈየ የለምጽ ደዌ ነው፥ ካህኑም፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ እርሱ ርኩስ ነውና አይለየውም። ለምጹም በቆዳው ላይ ሰፍቶ ቢወጣ፥ ካህኑ ማየት እስከሚችልበት አካል የለምጹ ደዌ የታመመውን ሰው ቆዳ ሁሉ ከራሱ እስከ እግሮቹ ድረስ ቢሸፍነው፥ ካህኑ ያያል፤ እነሆም፥ የለምጹ ደዌ ሰውነቱን ሁሉ ቢሸፍነው የታመመውን ሰው፦ ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ሰውነቱ ሁሉ ፈጽሞ ተለውጦ ነጭ ሆኖአል፤ ንጹሕ ነው። የሚያዠው ሥጋ ግን ሲታይበት ርኩስ ይሆናል። ካህኑም የሚያዠውን ሥጋ አይቶ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ የሚያዠው ሥጋ የለምጽ ደዌ ነውና ርኩስ ነው። የሚያዠው ሥጋ ግን ተለውጦ ቢነጣ እንደገና ወደ ካህኑ ይመጣል። ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ቢነጣ ካህኑ የታመመውን፦ ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ንጹሕ ነው። በሰውነቱም ቆዳ ላይ የዳነ የብጉንጅ ቁስል ቢኖር፥ በብጉንጁም የቁስል ስፍራ ላይ ነጭ እባጭ ወይም ነጣ ብሎ ቀላ ያለ ቋቁቻ ቢወጣ፥ በካህኑ ዘንድ ይታያል። ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ ከቆዳውም በታች ዘልቆ ቢታይ፥ ጠጉሩም ተለውጦ ቢነጣ፥ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው፤ ከብጉንጁ ቁስል ውስጥ ወጥቶአል። ካህኑም ቢያየው፥ እነሆም፥ በእርሱ ላይ ነጭ ጠጉር ባይኖርበት፥ ከቆዳውም በታች ባይዘልቅ ነገር ግን ቢከስም፥ ካህኑ ሰባት ቀን ይለየዋል። በቆዳውም ላይ ቢስፋፋ፥ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ ደዌ ነው። ቋቁቻው ግን በስፍራው ቢቆም ባይሰፋም፥ የብጉንጅ ቁስል ጠባሳ ነው፤ ካህኑም፦ ንጹሕ ነው ይለዋል። “በሰውነቱም ቆዳ ላይ የእሳት ቃጠሎ ቢኖርበት፥ በተቃጠለውም ስፍራ ነጭ ወይም ነጣ ብሎ ቀላ ያለ ቋቁቻ ቢወጣበት፥ ካህኑ ያየዋል፥ እነሆም፥ በቋቁቻው ላይ ያለው ጠጉር ተለውጦ ቢነጣ፥ ከቆዳውም በታች ዘልቆ ቢታይ፥ የለምጽ ደዌ ነው፤ ከተቃጠለውም ስፍራ ወጥቶአል፤ ካህኑም፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው። ነገር ግን ካህኑ ቢያየው፥ በቋቁቻውም ላይ ነጭ ጠጉር ባይኖር፥ ከቆዳውም በታች ባይዘልቅ ነገር ግን ቢከስም፥ ካህኑ ሰባት ቀን ይለየዋል። ካህኑም በሰባተኛው ቀን ያየዋል፤ በቆዳውም ላይ ቢስፋፋ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው። ቋቁቻውም በስፍራው ላይ ቢቆም፥ በቆዳውም ላይ ባይሰፋ ነገር ግን ቢከስም፥ የቃጠሎው እባጭ ነው፤ የቃጠሎውም ጠባሳ ነውና ካህኑ፦ ንጹሕ ነው ይለዋል። “ማናቸውም ወንድ ወይም ሴት በራስ ወይም በአገጭ ላይ ደዌ ቢኖርባቸው፥ ካህኑ ደዌውን ያያል፤ እነሆም፥ ከቆዳው በታች ዘልቆ ቢታይ፥ በውስጡም ቀጭን ብጫ ጠጉር ቢኖርበት፥ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ ቈረቈር ነው፤ የራስ ወይም የአገጭ የለምጽ ደዌ ነው። ካህኑም የቈረቈሩን ደዌ ቢያይ፥ ከቆዳውም በታች ዘልቆ ባይታይ፥ ጥቁርም ጠጉር ባይኖርበት፥ ካህኑ የቈረቈር ደዌ ያለበትን ሰው ሰባት ቀን ይለየዋል። ካህኑም በሰባተኛው ቀን ደዌውን ያያል፤ እነሆም፥ ቈረቈሩ ባይሰፋ፥ በውስጡም ብጫ ጠጉር ባይኖር፥ የቈረቈሩም መልክ ከቆዳው በታች ባይዘልቅ፥ ይላጫል፥ ቈረቈሩ ግን አይላጭም፤ አሁንም ካህኑ ቈረቈር ያለበትን ሰው ሰባት ቀን ይለየዋል። ካህኑም በሰባተኛው ቀን ቈረቈሩን ያያል፤ እነሆም፥ ቈረቈሩ በቆዳው ላይ ባይሰፋ፥ ከቆዳውም በታች ዘልቆ ባይታይ፥ ካህኑ፦ ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ልብሱንም ያጥብና ንጹሕ ይሆናል። ከነጻ በኋላ ግን ቈረቈሩ በቆዳው ላይ ቢስፋፋ፥ ካህኑ ያየዋል፤እነሆም፥ ቈረቈሩ በቆዳው ላይ ቢሰፋ ካህኑ ብጫውን ጠጉር አይፈልግም፤ እርሱ ርኩስ ነው። ቈረቈሩ ግን መገታቱን ቢያይ፥ ጥቁርም ጠጉር ቢበቅልበት፥ ቈረቈሩ ድኖአል፤ እርሱም ንጹሕ ነው፤ ካህኑም፦ ንጹሕ ነው ይለዋል።” “ማናቸውም ወንድ ወይም ሴት በሰውነታቸው ቆዳ ላይ ነጭ ቋቁቻ ቢኖርባቸው፥ ካህኑ ያያል፤ እነሆም፥ በሰውነታቸው ቆዳ ላይ ያለው ቋቁቻ ደብዘዝ ያለ ነጭ ቢሆን በቆዳ ላይ የሚወጣ ሽፍታ ነው፤ ከቆዳው ውስጥ ወጥቶአል፤ እርሱ ንጹሕ ነው። “የሰውም ጠጉር ከራሱ ቢመለጥ እርሱ ቡሀ ነው፤ ነገር ግን ንጹሕ ነው። ጠጉሩም ከግምባሩ ቢመለጥ እርሱ ራሰ በራ ነው፤ ነገር ግን ንጹሕ ነው። ዳሩ ግን በቡሀነቱ ወይም በራሰ በራነቱ ነጣ ብሎ ቀላ ያለ ደዌ ቢኖርበት፥ እርሱ ከቡሀነቱ ወይም ከራሰ በራነቱ የወጣ የለምጽ ደዌ ነው። ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም፥ የደዌው እብጠት፥ በሰውነቱ ቆዳ ላይ የሆነ የለምጽ ደዌ መስሎ፥ በቡሀነቱ ወይም በራሰ በራነቱ ላይ ነጣ ብሎ ቀላ ያለ ቢሆን፥ በለምጽ ደዌ የተያዘ ሰው ነው፤ እርሱ ርኩስ ነው፤ ካህኑ፦ በእርግጥ ርኩስ ነው ይለዋል፤ ደዌው በራሱ ላይ የሚገኝ ነው። “የለምጽ ደዌ ያለበት ሰው የሚለብሳቸው ልብሶች የተቀደዱ ይሁኑ፥ የራሱም ጠጉር የተጐሳቈለ ይሁን፥ ከንፈሩንም ይሸፍን፤ ርኩስ ርኩስ ነኝ እያለ ይጩኽ። በእርሱ ደዌው እስካለበት ጊዜያት ድረስ ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ እርሱ ርኩስ ነው፤ ብቻውን ይቀመጣል፤ መኖሪያውም ከሰፈር ውጪ ይሆናል። “የለምጽም ደዌ በልብስ ላይ ቢወጣ፥ ልብሱም የበግ ጠጉር ወይም በፍታ ቢሆን፥ በድሩ ወይም በማጉ ላይ ቢሆን፥ በፍታ ወይም የበግ ጠጉር ቢሆን፥ በተለፋው ቆዳ ወይም ከተለፋው ቆዳ በተሠራ በማናቸውም ነገር ላይ ቢሆን፥ ደዌው በልብሱ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም በተለፋው ቆዳ ወይም ከተለፋው ቆዳ በተሠራ በማናቸውም ነገር ላይ አረንጓዴ ወይም ቀይ ሆኖ ቢይታ፥ የለምጽ ደዌ ነው፤ ለካህኑ እዲያየው ይደረጋል። ካህኑም ደዌውን ያያል፤ ደዌውም ያለበትን ነገር ሰባት ቀን ለይቶ ያስቀምጠዋል። በሰባተኛውም ቀን ደዌውን ያያል፤ ደዌውም በልብሱ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም በተለፋው ቆዳ ወይም ለማናቸውም አገልግሎት በሚውል የተለፋ ቆዳ ላይ ቢሰፋ፥ ደዌው እየሰፋ የሚሄድ የለምጽ ደዌ ነው፤ እርሱም ርኩስ ነው። ልብሱን ያቃጥል፤ ድሩ ወይም ማጉ የበግ ጠጉር ወይም በፍታ ወይም ከተለፋው ቆዳ የሆነ ማናቸውም ደዌው ያለበት ነገር ላይ ቢሆን፥ እየሰፋ የሚሄድ የለምጽ ደዌ ነውና በእሳት ይቃጠል። “ካህኑ ቢያይ፥ እነሆም፥ ደዌው በልብሱ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከተለፋው ቆዳ በተሠራ በማናቸውም ነገር ላይ ባይሰፋ፥ ካህኑ ደዌ ያለበን ነገር እንዲያጥቡ ያዝዛል፤ ሌላም ሰባት ቀን ለይቶ ያስቀምጠዋል። ደዌው ያለበት ነገር ከታጠበ በኋላ ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ባይሰፋ ነገር ግን መልኩን ባይለውጥ፥ እርሱ ርኩስ ነው፤ በእሳት አቃጥለው፤ የለምጽ ደዌው ምልክቱ በውስጥ ወይም በውጭ ቢሆን እየሰፋ የሚሄድ ደዌ ነው። “ካህኑም ቢያይ፥ እነሆም፥ ከታጠበ በኋላ ደዌው ቢከስም፥ ምልክቱ የነበረበትን ቦታ ከልብሱ ወይም ከተለፋው ቆዳ ወይም ከድሩ ወይም ከማጉ ይቅደደው። በልብሱም ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከተለፋው ቆዳ በተሠራ በማናቸውም ነገር ላይ ዳግም ቢታይ፥ እየሰፋ የሚሄድ ደዌ ነው፤ ደዌው ያለበትን ነገር በእሳት ታቃጥለዋለህ። ነገር ግን አንተ ካጠብኸው ልብስ ወይም ከድሩ ወይም ከማጉ ወይም ከተለፋው ቆዳ ከተሠራ ከማናቸውም ነገር ላይ ደዌው ቢጠፋ፥ ሁለተኛ ጊዜ ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል። “ንጹሕ ወይም ርኩስ መሆኑን ለመወሰን እንዲቻል፥ በበግ ጠጉር ልብስ ወይም በበፍታ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከተለፋው ቆዳ በተሠራ በማናቸውም ነገር ላይ የሚወጣ የለምጽ ደዌ ሕግ ይህ ነው።”