ሰቈቃወ 3:1-66
ሰቈቃወ 3:1-66 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አሌፍ። በቍጣው በትር ችግር ያየ ሰው እኔ ነኝ። ብርሃን ወደሌለበት ወደ ጨለማ መርቶ ወሰደኝ። ዘወትር ቀኑን ሁሉ እጁን በላዬ መለሰ። ቤት። ሥጋዬንና ቁርበቴን አስረጀ፥ አጥንቴን ሰበረ። በዙሪያዬ ቅጥር ሠራብኝ፤ የመከራውንም ጎዳና በእኔ ላይ አቀና። እንደ ቀድሞ ሙታን በጨለማ አኖረኝ። ጋሜል። እንዳልወጣ በዙሪያዬ ቅጥር ሠራብኝ፤ ሰንሰለቴንም አከበደ። በጠራሁና በጮኽሁ ጊዜ ጸሎቴ ተከለከለ። መንገዴን በዓለት ላይ ሠራ፤ ጎዳናዬንም አጠረ። ዳሌጥ። እንደምትሸምቅ ድብ እንደ ተሸሸገም አንበሳ ሆነብኝ። ተከተለኝ፤ ጨረሰኝ፤ ባድማም አደረገኝ። ቀስቱን ገተረ፤ ለፍላጻውም እንደ ዒላማ አደረገኝ። ሄ። የሰገባውን ፍላጻዎች በኵላሊቴ ውስጥ ተከለ። ለወገኔ ሁሉ መሳቂያ ሆንሁ፤ ቀኑንም ሁሉ ዘፈኑብኝ። ምሬትን አጠገበኝ፤ በሐሞትም አሰከረኝ። ዋው። ጥርሴን በጭንጫ ሰበረ፤ አመድም አቃመኝ። ነፍሴን ከሰላም አራቀ፤ በጎ ነገርን ረሳሁ። እኔም፦ ኀይሌን፥ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ያለውን ተስፋዬን አጣሁ። ዛይ። ስደቴንና ችግሬን፥ እሬትንና ሐሞትን አስብ። ነፍሴ እያሰበችው በውስጤ ፈዘዘች። ይህችን በልቤ አኖራለሁ፤ ስለዚህ እታገሣለሁ። ሔት። ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና። ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህ ብዙ ነው። ነፍሴ፥ “እግዚአብሔር እድል ፋንታዬ ነው፤ ስለዚህ ጠበቅሁት” አለች። ጤት። እግዚአብሔር ለሚታገሡት ቸር ነው፤ ለምትሻውና ለምትታገሥ፥ ዝም ብላም የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ለምታደርግ ነፍስ መልካም ነው። ሰው በታናሽነቱ ቀንበር ቢሸከም መልካም ነው። ዮድ። እርሱ አሸክሞታልና ዝም ብሎ ለብቻው ይቀመጥ። ተስፋ ይሆነው እንደ ሆነ አፉን በአፈር ውስጥ ያኑር። ጕንጩን ለሚመታው ይሰጣል፤ ስድብንም ይጠግባል። ካፍ። ጌታ ለዘለዓለም አይጥልምና፤ ያሳዘነውን ሰው እንደ ይቅርታው ብዛት ይምረዋልና፤ ከልቡ አልተቈጣምና፥ የሰውንም ልጆች አላሳዘነምና፥ ላሜድ። በምድር የተጋዙትን ሁሉ ከእግሩ በታች ይረግጣቸው ዘንድ፥ የሰውን ፍርድ በልዑል ፊት ይመልስ ዘንድ፥ በሚፈርድበት ጊዜ የሰውን ፍርድ ያጣምም ዘንድ እግዚአብሔር አላዘዘም። ሜም። “እግዚአብሔር ያላዘዘው ይመጣል፥ ከልዑል አፍም ያልወጣ መልካም ወይም ክፉ ይሆናል” የሚል ማን ነው? ሰው ሕያው ሲሆን ስለ ኀጢአቱ ለምን ያጕረመርማል? ኖን። መንገዳችንን እንመርምርና እንፈትን፤ ወደ እግዚአብሔርም እንመለስ። ልባችንን ከእጃችን ጋር ወደ እግዚአብሔር ወደ ሰማይ እናንሣ። በድለናል፤ ዐምፀናልም፤ አንተም አልራራህልንም። ሳምኬት። በቍጣህ ከደንኸን፤ አሳደድኸንም፤ ገደልኸን፤ አልራራህልንም። ጸሎታችን እንዳያርግ ራስህን በደመና ከደንህ። እንድናዝንና እንዳናይም በአሕዛብ መካከል አስቀመጥኸን። ዔ። ጠላቶቻችን ሁሉ በእኛ ላይ አፋቸውን ከፈቱ። ፍርሀትና ቍጣ፥ ጥፋትና ቅጥቃጤ ያዘን። ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ ከዐይኔ የውኃ ጐርፍ ፈሰሰ። ፌ። ዐይኔ ተደፈነች፤ እንግዲህ ከማንጋጠጥ ዝም አልልም። እግዚአብሔር ከሰማይ ሆኖ እስኪመለከት ድረስ። ስለ ከተማዬ ቈነጃጅት ሁሉ ዐይኔ ነፍሴን አሳዘነች። ጻዴ። በከንቱ ነገር ጠላቶች ሁሉ እንደ ወፍ ማደንን አደኑኝ። ጠላቶች ሕይወቴን በጕድጓድ አጠፉ፤ በላዬም ድንጋይ ገጠሙ። በራሴ ላይ ውኃ ተከነበለ፤ እኔም፥ “ጠፋሁ” ብዬ ነበር። ቆፍ። አቤቱ፥ በጥልቅ ጕድጓድ ውስጥ ሆኜ ስምህን ጠራሁ። አንተ ድምፄን ሰማህ፤ ጆሮህንም ከልመናዬ አትመልስ። በጠራሁህ ቀን ወደ እኔ ቅረብ፤ “አትፍራም” በለኝ። ሬስ። አቤቱ፥ የነፍሴን ፍርድ ፈረድህ፤ ሕይወቴንም ተቤዥህ። አቤቱ፥ ጭንቀቴን አይተሃል፤ ፍርዴን ፍረድልኝ። በቀላቸውን ሁሉና በእኔ ላይ ያለውን ዐሳባቸውን ሁሉ አየህ። ሣን። አቤቱ፥ ስድባቸውንና በእኔ ላይ ያለውን ዐሳባቸውን ሁሉ ሰማህ። የተነሡብኝን ሰዎች ከንፈሮች ቀኑንም ሁሉ ያሰቡብኝን ዐሳባቸውን ሰማህ። መቀመጣቸውንና መነሣታቸውን ተመልከት፤ እኔ መዝፈኛቸው ነኝ። ታው። አቤቱ፥ እንደ እጃቸው ሥራ ፍዳቸውን ክፈላቸው። የልብ ሕማምንና ርግማንህን ስጣቸው። አቤቱ፥ እንደ ልባቸው ክፋት በቍጣህ ታሳድዳቸዋለህ፤ ከሰማይም በታች ታጠፋቸዋለህ።
ሰቈቃወ 3:1-66 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በቍጣው በትር፣ መከራ ያየ ሰው እኔ ነኝ። ከፊቱ አስወጣኝ፤ በብርሃን ሳይሆን በጨለማ እንድሄድ አደረገኝ። በርግጥ ቀኑን ሁሉ በመደጋገም፣ እጁን በላዬ ላይ መለሰ። እርሱ ሥጋዬንና ቈዳዬን አስረጀ፤ ዐጥንቶቼንም ሰባበረ። በምሬትና በድካም፣ ቅጥር ሠራብኝ፤ ዙሪያዬንም ከበበኝ። ከሞቱ ብዙ ጊዜ እንደ ሆናቸው፣ በጨለማ እንድኖር አደረገኝ። በቅጥር ውስጥ ዘጋብኝ፤ ስለዚህ ማምለጥ አልቻልሁም፤ የእስር ሰንሰለቴንም አከበደብኝ። ርዳታ ፈልጌ ብጣራና ብጮኽ እንኳ፣ ጸሎቴን መስማት አልፈለገም። መንገዴን በተጠረቡ ድንጋዮች ዘጋ፤ ጐዳናዬንም አጣመመ። አሸምቆ እንደ ተኛ ድብ፣ እንደ አደባም አንበሳ፣ ከመንገድ ጐትቶ አስወጣኝ፤ ቈራረጠኝም፤ ያለ ረዳትም ተወኝ። ቀስቱን ገተረ፤ ለፍላጻዎቹም ዒላማ አደረገኝ። ፍላጻዎችን ከሰገባው አውጥቶ፣ ልቤን ወጋው። ለሕዝቤ ሁሉ ማላገጫ ሆንሁኝ፤ ቀኑን ሙሉ በመሣለቅ ያዜሙብኛል። መራራ ሥር አበላኝ፤ ሐሞትም አጠገበኝ። ጥርሴን በድንጋይ ሰበረ፤ በትቢያ ውስጥ ረጋገጠኝ። ነፍሴ ሰላምን ዐጣች፤ ደስታ ምን እንደ ሆነ ረሳሁ። ስለዚህ፣ “ክብሬ፣ ከእግዚአብሔርም ተስፋ ያደረግሁት ሁሉ ሄዷል” አልሁ። የጭንቀቴንና የመንከራተቴን፣ ምሬትንና ሐሞትን ዐስባለሁ። ዘወትር አስበዋለሁ፤ ነፍሴም በውስጤ ተዋርዳለች። ሆኖም ይህን ዐስባለሁ፤ እንግዲያስ ተስፋ አለኝ፤ ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ታላቅ ፍቅር የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና። ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህም ብዙ ነው። ራሴን እንዲህ አልሁት፤ “እግዚአብሔር ዕድል ፈንታዬ ነው፤ ስለዚህ ተስፋ አደርገዋለሁ።” እርሱን ተስፋ ለሚያደርጉት፣ ለሚፈልገውም ሰው እግዚአብሔር መልካም ነው። ሰው የእግዚአብሔርን ማዳን፣ ዝም ብሎ ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው። ሰው በወጣትነቱ፣ ቀንበር ቢሸከም መልካም ነው። ብቻውን ዝም ብሎ ይቀመጥ፤ እግዚአብሔር አሸክሞታልና። ፊቱን በዐቧራ ውስጥ ይቅበር፤ ተስፋ ሊኖር ይችላልና። ጕንጩን ለሚመታው ሰው ይስጥ፤ ውርደትንም ይጥገብ። ጌታ ሰውን፣ ለዘላለም አይጥልምና፤ መከራን ቢያመጣ እንኳ ይራራል፤ ታላቅ ፍቅሩ አይለወጥምና። ሆን ብሎ ችግርን፣ ወይም መከራን በሰው ልጆች ላይ አያመጣምና። የምድሪቱ እስረኞች ሁሉ፣ በእግር ሲረገጡ፣ በልዑል ፊት፣ ሰው መብቱ ሲነፈገው፣ ሰው ፍትሕ ሲጓደልበት፣ ጌታ እንዲህ ዐይነቱን ነገር አያይምን? ጌታ ካላዘዘ በቀር፣ ተናግሮ መፈጸም የሚችል ማን ነው? ክፉም ሆነ መልካም ነገር፣ ከልዑል አፍ የሚወጣ አይደለምን? ታዲያ ሕያው ሰው በኀጢአቱ ሲቀጣ፣ ስለ ምን ያጕረመርማል? መንገዳችንን እንመርምር፤ እንፈትን፤ ወደ እግዚአብሔርም እንመለስ። ልባችንን ከእጃችን ጋር በሰማይ ወዳለው ወደ አምላካችን እናንሣ፤ እንዲህም እንበል፤ “ዐምፀናል፤ ኀጢአትም ሠርተናል፤ አንተም ይቅር አላልኸንም። “ራስህን በቍጣ ከደንህ፤ አሳደድኸንም፤ ያለ ርኅራኄም ገደልኸን። ጸሎት እንዳያልፍ፣ ራስህን በደመና ሸፈንህ። በአሕዛብ መካከል፣ አተላና ጥራጊ አደረግኸን። “ጠላቶቻችን ሁሉ፣ አፋቸውን በእኛ ላይ ከፈቱ። በጥፋትና በመፈራረስ፣ በችግርና በሽብር ተሠቃየን።” የእንባ ጐርፍ ከዐይኔ ፈሰሰ፤ ሕዝቤ ዐልቋልና። ያለ ዕረፍት፣ ያለ ማቋረጥ ዐይኖቼ እንባ ያፈስሳሉ፤ እግዚአብሔር ከላይ፣ ከሰማይ እስኪያይ ድረስ። በከተማዬ ባሉት ሴቶች ሁሉ ላይ የደረሰውን ማየቴ፣ ነፍሴን አስጨነቃት። ያለ ምክንያት ጠላቶቼ የሆኑ፣ እንደ ወፍ ዐደኑኝ። ሕይወቴን በጕድጓድ ውስጥ ሊያጠፉ ሞከሩ፣ ድንጋይም በላዬ አደረጉ። ውሃ ሞልቶ በዐናቴ ላይ ፈሰሰ፤ ጠፍቻለሁ ብዬ አሰብሁ። በጥልቁ ጕድጓድ ውስጥ ሳለሁ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ የአንተን ስም ጠራሁ። ልመናዬን ሰምተሃል፤ “ርዳታም ፈልጌ ስጮኽ፣ ከመስማት ጆሮህን አትከልክል።” በጠራሁህ ጊዜ ቀረብኸኝ፣ እንዲሁም፣ “አትፍራ” አልኸኝ። ጌታ ሆይ፤ ለእኔ ተሟገትኽልኝ፤ ሕይወቴንም ተቤዠህ። እግዚአብሔር ሆይ፤ በእኔ ላይ የተደረገውን ግፍ አየህ፤ ፍርዴን ፍረድልኝ! በቀላቸውን ሁሉ፣ በእኔም ላይ ያሰቡትን ዐድማ አየህ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ስድባቸውን ሁሉ፣ በእኔ ላይ ያሰቡትን ዐድማ ሁሉ ሰማህ፤ ይህም ቀኑን ሙሉ በእኔ ላይ፣ ጠላቶቼ የሚያውጠነጥኑትና የሚያንሾካሹኩት ነው። ተመልከታቸው! ቆመውም ሆነ ተቀምጠው፣ በዘፈናቸው ይሣለቁብኛል። እግዚአብሔር ሆይ፤ እጆቻቸው ላደረጉት፣ የሚገባውን መልሰህ ክፈላቸው። በልባቸው ላይ መጋረጃን ዘርጋ፤ ርግማንህም በላያቸው ይሁን! ከእግዚአብሔር ሰማያት በታች፣ በቍጣህ አሳድዳቸው፤ አጥፋቸውም።
ሰቈቃወ 3:1-66 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አሌፍ። በቍጣው በትር መከራ ያየ ሰው እኔ ነኝ። ብርሃን ወደ ሌለበት ወደ ጨለማ መርቶ ወሰደኝ። ዘወትር ቀኑን ሁሉ እጁን በላዬ መለሰ። ቤት። ሥጋዬንና ቁርበቴን አስረጀ፥ አጥንቴን ሰበረ። ቅጥር ሠራብኝ በሐሞትና በድካምም ከበበኝ። ቀድሞ ሞተው እንደ ነበሩ በጨለማ አኖረኝ። ጋሜል። እንዳልወጣ በዙሪያዬ ቅጥር ሠራብኝ፥ ሰንሰለቴን አከበደ። በጠራሁና በጮኽሁ ጊዜ ጸሎቴ ከለከለ። መንገዴን በተጠረበ ድንጋይ ዘጋ፥ ጐዳናዬንም አጣመመ። ዳሌጥ። እንደሚሸምቅ ድብ እንደ ተሸሸገም አንበሳ ሆነብኝ። መንገዴን ለወጠ፥ ገነጣጠለኝም፥ ባድማ አደረገኝ። ቀስቱን ገተረ ለፍላጻውም እንደ ጊጤ አደረገኝ። ሄ። የሰገባውን ፍላጻዎች በኵላሊቴ ውስጥ ተከለ። ለወገኔ ሁሉ ማላገጫ ቀኑንም ሁሉ መሳለቂያ ሆንሁ። ምሬት ሞላብኝ በእሬትም አጠገበኝ። ዋው። ጥርሴን በጭንጫ ሰበረ፥ በአመድም ከደነኝ። ነፍሴን ከሰላም አራቅህ፥ በጎ ነገርን ረሳሁ። እኔም፦ ኃይሌ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ያለው ተስፋዬ ጠፋ አልሁ። ዛይ። መከራዬንና ችግሬን እሬትንና ሐሞትን አስብ። ነፍሴ እያሰበችው በውስጤ ፈዘዘች። ይህችን በልቤ አኖራለሁ፥ ስለዚህ እታገሣለሁ። ሔት። ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፥ ርኅራኄው አያልቅምና። ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፥ ታማኝነትህ ብዙ ነው። ነፍሴ፦ እግዚአብሔር እድል ፈንታዬ ነው፥ ስለዚህ ተስፋ አደርገዋለሁ አለች። ጤት። እግዚአብሔር በተስፋ ለሚጠብቁት ለምትሻውም ነፍስ መልካም ነው። ሰው ዝም ብሎ የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው። ሰው በታናሽነቱ ቀንበር ቢሸከም መልካም ነው። ዮድ። እርሱ አሸክሞታልና ዝም ብሎ ለብቻው ይቀመጥ። ተስፋ የሆነው እንደ ሆነ አፉን በአፈር ውስጥ ያኑር። ጕንጩን ለሚመታው ይስጥ፥ ስድብንም ይጥገብ። ካፍ። ጌታ ለዘላለም አይጥልምና፥ ቢያሳዝንም እንደ ምሕረቱ ብዛት ይራራልና፥ የሰውን ልጆች ከልቡ አያስጨንቅም፥ አያሳዝንምም። ላሜድ። በምድር የተጋዙትን ሁሉ ከእግሩ በታች ይረግጣቸው ዘንድ፥ የሰውን ፍርድ በልዑል ፊት ይመልስ ዘንድ፥ የሰውን ፍርድ ያጣምም ዘንድ ጌታ እሺ አይልም። ሜም። ጌታ ያላዘዘውን የሚልና የሚፈጽም ማን ነው? ከልዑል አፍ ክፉና መልካም ነገር አይወጣምን? ሕያው ሰው የሚያጉረመርም፥ ሰው ስለ ኃጢአቱ ቅጣት የሚያጕረመርም ስለ ምንድር ነው? ኖን። መንገዳችንን እንመርምርና እንፈትን፥ ወደ እግዚአብሔርም እንመለስ። ልባችንን ከእጃችን ጋር በሰማይ ወዳለው ወደ እግዚአብሔር እናንሣ። በድለናል ዐምፀናልም፥ አንተም ይቅር አላልህም። ሳምኬት። በቍጣ ከደንኸን አሳደድኸንም፥ ገደልኸን፥ አልራራህም። ጸሎት እንዳያልፍ ራስህን በደመና ከደንህ። በአሕዛብ መካከል ጕድፍና ውዳቂ አደረግኸን። ዔ። ጠላቶቻችን ሁሉ አፋቸውን ኣላቀቁብን። ድንጋጤና ቍጣ፥ ጥፋትና ቅጥቃጤ ሆነብን። ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ ዓይኔ የውኃ ፈሳሽ አፈሰሰች። ፌ። እግዚአብሔር ከሰማይ እስኪጐበኝና እስኪመለከት ድረስ ዓይኔ ሳታቋርጥ ዝም ሳትል እንባ ታፈስሳለች። ስለ ከተማዬ ቈነጃጅት ሁሉ ዓይኔ ነፍሴን አሳዘነች። ጻዴ። በከንቱ ነገር ጠላቶች የሆኑኝ እንደ ወፍ ማደንን አደኑኝ። ሕይወቴን በጕድጓድ አጠፉ፥ በላዬም ድንጋይ ጣሉ። በራሴ ላይ ውኆች ተከነበሉ፥ እኔም፦ ጠፋሁ ብዬ ነበር። ቆፍ። አቤቱ፥ በጠለቀ ጕድጓድ ውስጥ ሆኜ ስምህን ጠራሁ። ድምፄን ሰማህ፥ ጆሮህን ከልመናዬ አትመልስ። በጠራሁህ ቀን ቀርበህ፦ አትፍራ አልህ። ሬስ። ጌታ ሆይ፥ ስለ ነፍሴ ተምዋግተህ ሕይወቴን ተቤዠህ። አቤቱ፥ ጭንቀቴን አይተሃል፥ ፍርዴን ፍረድልኝ። በቀላቸውን ሁሉና በእኔ ላይ ያለውን አሳባቸውን ሁሉ አየህ። ሳን። አቤቱ፥ ስድባቸውንና በእኔ ላይ ያለውን አሳባቸውን ሁሉ፥ የተነሡብኝን ሰዎች ከንፈሮች ቀኑንም ሁሉ ያሰቡብኝን አሳባቸውን ሰማህ። መቀመጣቸውንና መነሣታቸውን ተመልከት፥ እኔ መሳለቂያቸው ነኝ። ታው። አቤቱ፥ እንደ እጃቸው ሥራ ፍዳቸውን ትከፍላቸዋለህ። የልብ ዕውርነትንና እርግማንህን ትሰጣቸዋለህ። አቤቱ፥ በቍጣ ታሳድዳቸዋለህ ከሰማይም በታች ታጠፋቸዋለህ።
ሰቈቃወ 3:1-66 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በአምላክ የቊጣ በትር መከራን ያየሁ እኔ ነኝ። ምንም ብርሃን ወደሌለበት ጨለማ መርቶ ወሰደኝ። ቀኑን ሙሉ እኔን ብቻ መላልሶ ቀጣኝ። ሥጋዬንና ቆዳዬን አስረጀ፤ አጥንቶቼንም ሰባበረ። ከበባ አድርጎ ምርር ባለ ሐዘንና ችግር ውስጥ ከተተኝ። ከብዙ ጊዜ በፊት እንደ ሞተ ሰው በጨለማ ውስጥ እንድቀመጥ አስገደደኝ። እንዳላመልጥ ዙሪያዬን አጠረ፤ በከባድ ሰንሰለትም አሰረኝ። ለእርዳታ ጩኸቴን ባሰማም እንኳ አላዳምጥ አለኝ። መንገዴን በተጠረበ ድንጋይ ዘጋ፤ መተላለፊያዬንም አጣመመ። እርሱ ለእኔ እንደሚሸምቅ ድብና እንደ ተደበቀ አንበሳ ነው። ከመንገዴ አውጥቶ ገነጣጠለኝ፤ ብቸኛም አደረገኝ። ቀስቱን ገትሮ ለፍላጾች ዒላማ አደረገኝ። ፍላጻዎቹንም አስፈንጥሮ ወደ ሰውነቴ ጠልቀው እንዲገቡ አደረገ። ለሕዝቤ ሁሉ መሳቂያ ሆንኩ፤ በዘፈናቸውም ቀኑን ሙሉ አፌዙብኝ። ከችግር የተነሣ ሕይወት እንዲመረኝ አደረገ፤ በእሬትም አጠገበኝ። ጥርሶቼ በጠጠር እንዲሰበሩና ፊቴም በዐመድ ላይ እንዲደፋ አደረገ። ሕይወቴ ሰላም እንዲያጣ ተደረገ፤ ደስታም ምን እንደ ሆነ ረሳሁ። ስለዚህ፦ “ክብሬ ተለይቶኛል፤ ከእግዚአብሔር የምጠብቀውም ተስፋ ሁሉ ተቋርጦአል” አልኩ። መከራዬንና ከርታታነቴን ማስታወስ እንደ እሬትና እንደ ሐሞት ሆነብኝ። ስለዚህም ሁኔታ ሁልጊዜ ሳስብ መንፈሴ ይጨነቃል፤ ሆኖም ይህን አንድ ነገር በማስብበት ጊዜ በተስፋ እሞላለሁ። ይኸውም ሳንጠፋ የቀረነው የእግዚአብሔር ምሕረት ከቶ የማያቋርጥና ፍቅሩም ዘለዓለማዊ ስለ ሆነ ነው። እነርሱ በየማለዳው ይታደሳሉ፤ ስለዚህ የአንተ ታማኝነት ታላቅ ነው። የእኔ አለኝታ እግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ እርሱን ብቻ ተስፋ አደርጋለሁ። እግዚአብሔር በተስፋ ለሚጠባበቁትና እርሱን ለሚፈልጉ መልካም ነው። ሰው የእግዚአብሔርን አዳኝነት ጸጥ ብሎ መጠበቁ መልካም ነው። ሰው በወጣትነቱ መከራን በትዕግሥት ቢቀበል መልካም ነው። እግዚአብሔር መከራውን በሚአመጣበት ጊዜ ጸጥ ብሎ ለብቻው ቢቀመጥ መልካም ነው። እንደገና ተስፋ ሊኖር ስለሚችል ራሱን ዝቅ አድርጎ ያስገዛ። ለሚመታው ጒንጩን ይስጥ፤ ስድብንም ይቀበል። ይህን ሁሉ ቢያደርግ እግዚአብሔር ለዘለዓለም አይተወውም። ምንም እንኳ ጭንቀት በሰው ላይ እንዲደርስ ቢፈቅድ ከተትረፈረፈ ዘለዓለማዊ ፍቅሩ የተነሣ ይራራል። ይህም የሚሆነው እርሱ በራሱ ፍላጎት በሰው ላይ ችግርንና ሐዘንን ስለማያመጣ ነው። የአገሪቱ እስረኞች ሁሉ በግፍ በሚረገጡበት ጊዜ፥ ልዑል እግዚአብሔር እያየ ሰብአዊ መብት በሚጣስበት ጊዜ፥ የአንድ ሰው ጉዳይ ፍትሕ በሚያጣበት ጊዜ በውኑ ጌታ እነዚህን ነገሮች አያይምን? እግዚአብሔር አስቀድሞ የወሰነው ካልሆነ በትእዛዙ አንድን ነገር ማስደረግ የሚችል ማነው? ደግም ሆነ ክፉ ነገር ተግባራዊ የሚሆነው ልዑል እግዚአብሔር በሚናገረው መሠረት አይደለምን? ሰው በሕይወቱ እያለ በኃጢአት ምክንያት ሲቀጣ የሚያጒረመርመው ለምንድን ነው? አካሄዳችንን መርምረን፤ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ። በሰማይ ወዳለው አምላካችን ልባችንንና እጃችንን እናንሣ። “አምላክ ሆይ! እኛ ኃጢአትና ዐመፅ ሠርተናል፤ አንተም ይቅር አላልከንም። “በቊጣ ተሞልተህ አሳደድከን ያለ ርኅራኄ ገደልከን። ጸሎት አልፎ ሊገባ በማይችልበት ራስህን ጥቅጥቅ ባለ ደመና ሸፈንክ። መኖሪያህን በደመና ሸፈንክ። በሕዝቦች መካከል እንደ ጒድፍና ጥራጊ አደረግኸን። “ጠላቶቻችን ሁሉ አፋቸውን ከፈቱብን ፍርሀትና ውድቀት እንዲሁም ጥፋትና ውድመት በእኛ ላይ ደረሱ። በሕዝቤ ላይ በደረሰው ጥፋት ምክንያት እንባ ከዐይኖቼ እንደ ወንዝ ውሃ ይጐርፋል። “እንባዬ ያለማቋረጥ ይፈስሳል። ይህም የሚሆነው እግዚአብሔር ከሰማይ ወደ ታች ተመልክቶ እስኪያይ ድረስ ነው። በከተማዬ ውስጥ ባሉት ወጣት ሴቶች ላይ የደረሰውን ክፉ ዕድል በማየቴ የመረረ ሐዘን ደረሰብኝ። “ያለ ምክንያት የሚጠሉኝ ጠላቶቼ እንደ ወፍ አጠመዱኝ። ከነሕይወቴ ጒድጓድ ውስጥ ወርውረው የጒድጓዱን አፍ በድንጋይ ዘጉብኝ። ውሃ ከእራሴ በላይ ሞልቶ ሲፈስ የምሞትበት ጊዜ የተቃረበ መሰለኝ። “እግዚአብሔር ሆይ! በጥልቅ ጒድጓድ ውስጥ ሆኜ፥ ስምህን ጠራሁ። ጆሮህን ወደ እኔ መልስ፤ ለእርዳታም ድረስልኝ” የሚለውን ልመናዬን ሰምተሃል፤ ስለዚህ ዕረፍትን ስጠኝ። በጠራሁህ ጊዜ ወደ እኔ ቀርበህ “አትፍራ!” አልከኝ። “ጌታ ሆይ! የእኔን ጉዳይ ተከታትለህ ሕይወቴን አዳንክ። እግዚአብሔር ሆይ! በእኔ ላይ የደረሰውን በደል ሁሉ አይተሃልና ፍትሕን ስጠኝ። ጠላቶቼ በእኔ ላይ ያላቸውን የበቀል ስሜትና ያቀዱትን ሤራ አይተሃል። “እግዚአብሔር ሆይ! በእኔ ላይ የሰነዘሩትን ስድባቸውንና ያቀዱትንም ሤራ ሰምተሃል። ቀኑን ሙሉ ጠላቶቼ በእኔ ላይ ይንሾካሾካሉ፤ ያጒረመርማሉም። ተቀምጠውም ሆነ ቆመው በቅኔ በእኔ ላይ በአሽሙር የሚሳለቁ መሆናቸውን ተመልከት። “አምላክ ሆይ! ለፈጸሙት ተግባር የሚገባቸውን ዋጋ ስጣቸው። ርግማንህ በእነርሱ ላይ ይሁን! ተስፋ እንዲቈርጡም አድርጋቸው! እግዚአብሔር ሆይ! በቊጣህ አሳዳቸው፤ ከሰማያትም በታች ደምስሳቸው!”
ሰቈቃወ 3:1-66 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አሌፍ። በቁጣው በትር መከራ ያየ ሰው እኔ ነኝ። ብርሃን ወደሌለበት ወደ ጨለማ መርቶ ወሰደኝ። ዘወትር ቀኑን ሁሉ እጁን በላዬ መለሰ። ቤት። ሥጋዬንና ቁርበቴን አስረጀ፥ አጥንቴን ሰበረ። ቅጥር ሠራብኝ በሐሞትና በድካምም ከበበኝ። ቀድሞ ሞተው እንደ ነበሩ በጨለማ አኖረኝ። ጋሜል። እንዳልወጣ በዙሪያዬ ቅጥር ሠራብኝ፥ ሰንሰለቴን አከበደ። በጠራሁና በጮኽሁ ጊዜ ጸሎቴ ከለከለ። መንገዴን በተጠረበ ድንጋይ ዘጋ፥ ጐዳናዬንም አጣመመ። ዳሌጥ። እንደሚሸምቅ ድብ እንደ ተሸሸገም አንበሳ ሆነብኝ። መንገዴን ለወጠ፥ ገነጣጠለኝም፥ ባድማ አደረገኝ። ቀስቱን ገተረ ለፍላጻውም እንደ ጊጤ አደረገኝ። ሄ። የሰገባውን ፍላጻዎች በኩላሊቴ ውስጥ ተከለ። ለወገኔ ሁሉ ማላገጫ ቀኑንም ሁሉ መሳለቂያ ሆንሁ። ምሬት ሞላብኝ በእሬትም አጠገበኝ። ዋው። ጥርሴን በጭንጫ ሰበረ፥ በአመድም ከደነኝ። ነፍሴን ከሰላም አራቅህ፥ በጎ ነገርን ረሳሁ። እኔም፦ ኃይሌ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ያለው ተስፋዬ ጠፋ አልሁ። ዛይ። መከራዬንና ችግሬን እሬትንና ሐሞትን አስብ። ነፍሴ እያሰበችው በውስጤ ፈዘዘች። ይህችን በልቤ አኖራለሁ፥ ስለዚህ እታገሣለሁ። ሔት። ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፥ ርኅራኄው አያልቅምና። ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፥ ታማኝነትህ ብዙ ነው። ነፍሴ፦ እግዚአብሔር እድል ፈንታዬ ነው፥ ስለዚህ ተስፋ አደርገዋለሁ አለች። ጤት። ጌታ በተስፋ ለሚጠብቁት ለምትሻውም ነፍስ መልካም ነው። ሰው ዝም ብሎ የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው። ሰው በታናሽነቱ ቀንበር ቢሸከም መልካም ነው። ዮድ። እርሱ አሸክሞታልና ዝም ብሎ ለብቻው ይቀመጥ። ተስፋ የሆነው እንደሆነ አፉን በአፈር ውስጥ ያኑር። ጉንጩን ለሚመታው ይስጥ፥ ስድብንም ይጥገብ። ካፍ። ጌታ ለዘለዓለም አይጥልምና፥ ቢያሳዝንም እንደ ምሕረቱ ብዛት ይራራልና፥ የሰውን ልጆች ከልቡ አያስጨንቅም፥ አያሳዝንምም። ላሜድ። በምድር የተጋዙትን ሁሉ ከእግሩ በታች ይረግጣቸው ዘንድ፥ የሰውን ፍርድ በልዑል ፊት ይመልስ ዘንድ፥ የሰውን ፍርድ ያጣምም ዘንድ ጌታ እሺ አይልም። ሜም። ጌታ ያላዘዘውን የሚልና የሚፈጽም ማን ነው? ከልዑል አፍ ክፉና መልካም ነገር አይወጣምን? ሕያው ሰው የሚያጉረመርም፥ ሰው ስለ ኃጢአቱ ቅጣት የሚያጉረመርም ስለ ምንድነው? ኖን። መንገዳችንን እንመርምርና እንፈትን፥ ወደ እግዚአብሔርም እንመለስ። ልባችንን ከእጃችን ጋር በሰማይ ወዳለው ወደ እግዚአብሔር እናንሣ። በድለናል ዐምፀናልም፥ አንተም ይቅር አላልህም። ሳምኬት። በቁጣ ከደንኸን አሳደድኸንም፥ ገደልኸን፥ አልራራህም። ጸሎት እንዳያልፍ ራስህን በደመና ከደንህ። በአሕዛብ መካከል ጉድፍና ውዳቂ አደረግኸን። ዔ። ጠላቶቻችን ሁሉ አፋቸውን ኣላቀቁብን። ድንጋጤና ቁጣ፥ ጥፋትና ቅጥቃጤ ሆነብን። ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ ዓይኔ የውኃ ፈሳሽ አፈሰሰች። ፌ። እግዚአብሔር ከሰማይ እስኪጐበኝና እስኪመለከት ድረስ ዓይኔ ሳታቋርጥ ዝም ሳትል እንባ ታፈስሳለች። ስለ ከተማዬ ቈነጃጅት ሁሉ ዓይኔ ነፍሴን አሳዘነች። ጻዴ። በከንቱ ነገር ጠላቶች የሆኑኝ እንደ ወፍ ማደንን አደኑኝ። ሕይወቴን በጉድጓድ አጠፉ፥ በላዬም ድንጋይ ጣሉ። በራሴ ላይ ውኆች ተከነበሉ፥ እኔም፦ ጠፋሁ ብዬ ነበር። ቆፍ። አቤቱ፥ በጠለቀ ጉድጓድ ውስጥ ሆኜ ስምህን ጠራሁ። ድምፄን ሰማህ፥ ጆሮህን ከልመናዬ አትመልስ። በጠራሁህ ቀን ቀርበህ፦ አትፍራ አልህ። ሬስ። ጌታ ሆይ፥ ስለ ነፍሴ ተምዋግተህ ሕይወቴን ተቤዠህ። አቤቱ፥ ጭንቀቴን አይተሃል፥ ፍርዴን ፍረድልኝ። በቀላቸውን ሁሉና በእኔ ላይ ያለውን አሳባቸውን ሁሉ አየህ። ሳን። አቤቱ፥ ስድባቸውንና በእኔ ላይ ያለውን አሳባቸውን ሁሉ፥ የተነሡብኝን ሰዎች ከንፈሮች ቀኑንም ሁሉ ያሰቡብኝን አሳባቸውን ሰማህ። መቀመጣቸውንና መነሣታቸውን ተመልከት፥ እኔ መሳለቂያቸው ነኝ። ታው። አቤቱ፥ እንደ እጃቸው ሥራ ፍዳቸውን ትከፍላቸዋለህ። የልብ ዕውርነትንና እርግማንህን ትሰጣቸዋለህ። አቤቱ፥ በቁጣ ታሳድዳቸዋለህ ከሰማይም በታች ታጠፋቸዋለህ።