አሌፍ። በቍጣው በትር ችግር ያየ ሰው እኔ ነኝ። ብርሃን ወደሌለበት ወደ ጨለማ መርቶ ወሰደኝ። ዘወትር ቀኑን ሁሉ እጁን በላዬ መለሰ። ቤት። ሥጋዬንና ቁርበቴን አስረጀ፥ አጥንቴን ሰበረ። በዙሪያዬ ቅጥር ሠራብኝ፤ የመከራውንም ጎዳና በእኔ ላይ አቀና። እንደ ቀድሞ ሙታን በጨለማ አኖረኝ። ጋሜል። እንዳልወጣ በዙሪያዬ ቅጥር ሠራብኝ፤ ሰንሰለቴንም አከበደ። በጠራሁና በጮኽሁ ጊዜ ጸሎቴ ተከለከለ። መንገዴን በዓለት ላይ ሠራ፤ ጎዳናዬንም አጠረ። ዳሌጥ። እንደምትሸምቅ ድብ እንደ ተሸሸገም አንበሳ ሆነብኝ። ተከተለኝ፤ ጨረሰኝ፤ ባድማም አደረገኝ። ቀስቱን ገተረ፤ ለፍላጻውም እንደ ዒላማ አደረገኝ። ሄ። የሰገባውን ፍላጻዎች በኵላሊቴ ውስጥ ተከለ። ለወገኔ ሁሉ መሳቂያ ሆንሁ፤ ቀኑንም ሁሉ ዘፈኑብኝ። ምሬትን አጠገበኝ፤ በሐሞትም አሰከረኝ። ዋው። ጥርሴን በጭንጫ ሰበረ፤ አመድም አቃመኝ። ነፍሴን ከሰላም አራቀ፤ በጎ ነገርን ረሳሁ። እኔም፦ ኀይሌን፥ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ያለውን ተስፋዬን አጣሁ። ዛይ። ስደቴንና ችግሬን፥ እሬትንና ሐሞትን አስብ። ነፍሴ እያሰበችው በውስጤ ፈዘዘች። ይህችን በልቤ አኖራለሁ፤ ስለዚህ እታገሣለሁ። ሔት። ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና። ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህ ብዙ ነው። ነፍሴ፥ “እግዚአብሔር እድል ፋንታዬ ነው፤ ስለዚህ ጠበቅሁት” አለች። ጤት። እግዚአብሔር ለሚታገሡት ቸር ነው፤ ለምትሻውና ለምትታገሥ፥ ዝም ብላም የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ለምታደርግ ነፍስ መልካም ነው። ሰው በታናሽነቱ ቀንበር ቢሸከም መልካም ነው። ዮድ። እርሱ አሸክሞታልና ዝም ብሎ ለብቻው ይቀመጥ። ተስፋ ይሆነው እንደ ሆነ አፉን በአፈር ውስጥ ያኑር። ጕንጩን ለሚመታው ይሰጣል፤ ስድብንም ይጠግባል። ካፍ። ጌታ ለዘለዓለም አይጥልምና፤ ያሳዘነውን ሰው እንደ ይቅርታው ብዛት ይምረዋልና፤ ከልቡ አልተቈጣምና፥ የሰውንም ልጆች አላሳዘነምና፥ ላሜድ። በምድር የተጋዙትን ሁሉ ከእግሩ በታች ይረግጣቸው ዘንድ፥ የሰውን ፍርድ በልዑል ፊት ይመልስ ዘንድ፥ በሚፈርድበት ጊዜ የሰውን ፍርድ ያጣምም ዘንድ እግዚአብሔር አላዘዘም። ሜም። “እግዚአብሔር ያላዘዘው ይመጣል፥ ከልዑል አፍም ያልወጣ መልካም ወይም ክፉ ይሆናል” የሚል ማን ነው? ሰው ሕያው ሲሆን ስለ ኀጢአቱ ለምን ያጕረመርማል? ኖን። መንገዳችንን እንመርምርና እንፈትን፤ ወደ እግዚአብሔርም እንመለስ። ልባችንን ከእጃችን ጋር ወደ እግዚአብሔር ወደ ሰማይ እናንሣ። በድለናል፤ ዐምፀናልም፤ አንተም አልራራህልንም። ሳምኬት። በቍጣህ ከደንኸን፤ አሳደድኸንም፤ ገደልኸን፤ አልራራህልንም። ጸሎታችን እንዳያርግ ራስህን በደመና ከደንህ። እንድናዝንና እንዳናይም በአሕዛብ መካከል አስቀመጥኸን። ዔ። ጠላቶቻችን ሁሉ በእኛ ላይ አፋቸውን ከፈቱ። ፍርሀትና ቍጣ፥ ጥፋትና ቅጥቃጤ ያዘን። ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ ከዐይኔ የውኃ ጐርፍ ፈሰሰ። ፌ። ዐይኔ ተደፈነች፤ እንግዲህ ከማንጋጠጥ ዝም አልልም። እግዚአብሔር ከሰማይ ሆኖ እስኪመለከት ድረስ። ስለ ከተማዬ ቈነጃጅት ሁሉ ዐይኔ ነፍሴን አሳዘነች። ጻዴ። በከንቱ ነገር ጠላቶች ሁሉ እንደ ወፍ ማደንን አደኑኝ። ጠላቶች ሕይወቴን በጕድጓድ አጠፉ፤ በላዬም ድንጋይ ገጠሙ። በራሴ ላይ ውኃ ተከነበለ፤ እኔም፥ “ጠፋሁ” ብዬ ነበር። ቆፍ። አቤቱ፥ በጥልቅ ጕድጓድ ውስጥ ሆኜ ስምህን ጠራሁ። አንተ ድምፄን ሰማህ፤ ጆሮህንም ከልመናዬ አትመልስ። በጠራሁህ ቀን ወደ እኔ ቅረብ፤ “አትፍራም” በለኝ። ሬስ። አቤቱ፥ የነፍሴን ፍርድ ፈረድህ፤ ሕይወቴንም ተቤዥህ። አቤቱ፥ ጭንቀቴን አይተሃል፤ ፍርዴን ፍረድልኝ። በቀላቸውን ሁሉና በእኔ ላይ ያለውን ዐሳባቸውን ሁሉ አየህ። ሣን። አቤቱ፥ ስድባቸውንና በእኔ ላይ ያለውን ዐሳባቸውን ሁሉ ሰማህ። የተነሡብኝን ሰዎች ከንፈሮች ቀኑንም ሁሉ ያሰቡብኝን ዐሳባቸውን ሰማህ። መቀመጣቸውንና መነሣታቸውን ተመልከት፤ እኔ መዝፈኛቸው ነኝ። ታው። አቤቱ፥ እንደ እጃቸው ሥራ ፍዳቸውን ክፈላቸው። የልብ ሕማምንና ርግማንህን ስጣቸው። አቤቱ፥ እንደ ልባቸው ክፋት በቍጣህ ታሳድዳቸዋለህ፤ ከሰማይም በታች ታጠፋቸዋለህ።
ሰቆቃወ ኤርምያስ ነቢይ 3 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሰቆቃወ ኤርምያስ ነቢይ 3:1-66
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos