ኢዩኤል 3:1-21
ኢዩኤል 3:1-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“እነሆም በዚያ ወራትና በዚያ ዘመን፥ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ምርኮ እመልሳለሁ። አሕዛብን ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደ ኢዮሳፍጥም ሸለቆ አወርዳቸዋለሁ፤ በአሕዛብም መካከል በተበተኑበትና ምድሬን በተካፈሉበት በዚያ ስለ ወገኖች ስለ ርስቴ ስለ እስራኤል እወቅሳቸዋለሁ። በሕዝቤም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ፤ ወንድ ልጅን ለአመንዝሮች ዋጋ ሰጡ፤ ሴት ልጅንም ለወይን ጠጅ ሸጡ፤ ጠጡም። “ጢሮስና ሲዶና የፍልስጥኤም አውራጃ ገሊላም ሁሉ ሆይ! ከእናንተ ጋራ ምን አለኝ? እናንተ በቀልን ትበቀሉኛላችሁን? ቂምንስ ትቀየሙኛላችሁን? ፈጥኜ በችኰላ ፍዳን በራሳችሁ ላይ እመልሳለሁ። ብሬንና ወርቄን ወስዳችኋልና፥ የተወደደውንም መልካሙን ዕቃዬን ወደ ቤተ መቅደሳችሁ አግብታችኋልና፥ ከዳርቻቸውም ታርቁአቸው ዘንድ የይሁዳን ልጆችና የኢየሩሳሌምን ልጆች ለግሪክ ልጆች ሸጣችኋልና፥ እነሆ እነርሱን ከሸጣችሁበት ስፍራ አስነሣቸዋለሁ፤ ብድራታችሁንም በራሳችሁ ላይ እመልሳለሁ። ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁን በይሁዳ ልጆች እጅ እሸጣለሁ፤ እነርሱም ለሩቆቹ ሕዝብ በምርኮ ይሸጡአችኋል። እግዚአብሔር ተናግሮአልና። “ይህን በአሕዛብ መካከል ዐውጁ፤ ለሰልፍ ተዘጋጁ፤ ኀያላንን አስነሡ፤ ሰልፈኞች ሁሉ ይቅረቡ፤ ይውጡም። ማረሻችሁን ሰይፍ፥ ማጭዳችሁንም ጦር ለማድረግ ቀጥቅጡ፤ ደካማውም፦ እኔ ብርቱ ነኝ ይበል። እናንተ በዙሪያ ያላችሁ አሕዛብ ሁሉ፥ ፈጥናችሁ ኑ፥ ተሰብሰቡ፤ የዋሃንም ሰልፈኞች ይሁኑ። “አሕዛብ ሁሉ ይነሡ፤ ወደ ኢዮሣፍጥ ሸለቆም ይውጡ፤ በዙሪያ ባሉ አሕዛብ ሁሉ ላይ እፈርድ ዘንድ በዚያ እቀመጣለሁና። መከሩ ደርሶአልና ማጭድ ስደዱ፤ መጭመቂያውም ሞልቶአልና ኑ ርገጡ፤ ክፋታቸውም በዝቶአልና መጭመቂያ ሁሉ ፈስሶአል።” የእግዚአብሔር ቀን በፍርድ ሸለቆ ቀርቦአልና ውካታዎች በፍርድ ሸለቆ ተሰሙ። ፀሐይና ጨረቃ ይጨልማሉ፤ ከዋክብትም ብርሃናቸውን ይሰውራሉ። እግዚአብሔርም በጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ቃሉን ይሰጣል፤ ሰማይና ምድርም ይናወጣሉ፤ እግዚአብሔር ግን ለሕዝቡ ይራራል፤ የእስራኤልንም ልጆች ያጸናል። “እኔም በተቀደሰ ተራራዬ በጽዮን የምቀመጥ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፤ ያን ጊዜም ኢየሩሳሌም የተቀደሰች ከተማ ትሆናለች፥ እንግዶችም ከእንግዲህ ወዲህ አያልፉባትም። “በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ተራሮች ማርን ያንጠባጥባሉ፤ ኮረብቶችም ወተትን ያፈስሳሉ፤ በይሁዳም ያሉት ፈፋዎች ሁሉ ውኃን ያጐርፋሉ፤ ከእግዚአብሔርም ቤት ምንጭ ትፈልቃለች፤ የሰኪኖንንም ሸለቆ ታጠጣለች። በሀገራቸው ንጹሑን ደም አፍስሰዋልና በይሁዳ ልጆች ላይ ስለ አደረጉት ግፍ ግብፅ ምድረ በዳ፥ ኤዶምያስም በረሃ ይሆናል። ነገር ግን ይሁዳ ለዘለዓለም፥ ኢየሩሳሌምም ለልጅ ልጅ መኖሪያ ትሆናለች። እኔም ደማቸውን እበቀላለሁ፤ አላነጻቸውምም፤ እግዚአብሔርም በጽዮን ያድራል።”
ኢዩኤል 3:1-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“በዚያ ዘመን፣ በዚያ ጊዜ፣ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ምርኮ ስመልስ፣ አሕዛብን ሁሉ እሰበስባለሁ፤ ወደ ኢዮሣፍጥም ሸለቆ አወርዳቸዋለሁ፤ ስለ ርስቴ፣ ስለ ሕዝቤ፣ ስለ እስራኤል፣ በዚያ ልፈርድባቸው እገባለሁ፤ ምድሬን ከፋፍለዋል፤ ሕዝቤንም በሕዝቦች መካከል በታትነዋልና። በሕዝቤ ላይ ዕጣ ተጣጣሉ፤ ወንዶች ልጆችን በዝሙት ዐዳሪዎች ለወጡ፤ ወይን ጠጅ ለመጠጣትም፣ ሴቶች ልጆችን ሸጡ። “ጢሮስና ሲዶና እንዲሁም እናንተ የፍልስጥኤም ግዛቶች ሁሉ ሆይ፤ እንግዲህ በእኔ ላይ ምን አላችሁ? ስላደረግሁት ነገር ብድር ልትመልሱልኝ ነውን? የምትመልሱልኝ ከሆነ፣ በፍጥነትና በችኰላ እናንተ ያደረጋችሁትን በራሳችሁ ላይ መልሼ አደርግባችኋለሁ። ብሬንና ወርቄን ወስዳችኋል፤ የተመረጠውንም ንብረቴን ተሸክማችሁ ወደ ቤተ መቅደሳችሁ አስገብታችኋልና። ከገዛ ምድራቸው ልታርቋቸው፣ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሰዎች ለግሪኮች ሸጣችኋቸው። “እነሆ፤ እነርሱን ከሸጣችሁባቸው ቦታዎች አነሣሣቸዋለሁ፤ እናንተም ያደረጋችሁትን በገዛ ራሳችሁ ላይ እመልስባችኋለሁ። ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻችሁን ለይሁዳ ሰዎች ሸጣለሁ፤ እነርሱም መልሰው በሩቅ ላሉት ለሳባ ሰዎች ይሸጧቸዋል፤” እግዚአብሔር ይህን ተናግሯልና። በሕዝቦች መካከል ይህን ዐውጁ፤ ለጦርነት ተዘጋጁ፤ ተዋጊዎችን አነሣሡ፤ ጦረኞችም ሁሉ ቀርበው ያጥቁ። ማረሻችሁ ሰይፍ፣ ማጭዳችሁም ጦር እንዲሆን ቀጥቅጡት፤ ደካማውም ሰው፣ “እኔ ብርቱ ነኝ” ይበል። እናንት በዙሪያ ያላችሁ ሕዝቦች ሁላችሁ፤ ፈጥናችሁ ኑ፤ በዚያም ተሰብሰቡ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ተዋጊዎችህን ወደዚያ አውርድ! “ሕዝቦች ይነሡ፤ ወደ ኢዮሣፍጥም ሸለቆ ፈጥነው ይውረዱ፤ ዙሪያውን ባሉት ሕዝቦች ሁሉ ላይ ልፈርድ፣ በዚያ እቀመጣለሁና። ማጭዱን ስደዱ፤ መከሩ ደርሷልና፤ ኑ ወይኑን ርገጡ፤ የወይን መጭመቂያው ሞልቶ፣ ከጕድጓዶቹም ተርፎ ፈስሷልና፤ ክፋታቸው እንደዚህ ታላቅ ነው።” ብዙ ሕዝብ፣ በጣም ብዙ ሕዝብ፣ ፍርድ በሚሰጥበት ሸለቆ ተሰብስቧል፤ ፍርድ በሚሰጥበት ሸለቆ፣ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቧልና። ፀሓይና ጨረቃ ይጨልማሉ፤ ከዋክብትም ከእንግዲህ አያበሩም። እግዚአብሔር ከጽዮን ጮኾ ይናገራል፤ ከኢየሩሳሌም ያንጐደጕዳል፤ ሰማይና ምድርም ይናወጣሉ፤ እግዚአብሔር ግን ለሕዝቡ መሸሸጊያ፣ ለእስራኤልም ልጆች መጠጊያ ይሆናል። “ከዚያም እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር፣ በቅዱሱ ተራራዬ በጽዮን እንደምኖር ታውቃላችሁ፤ ኢየሩሳሌም የተቀደሰች ትሆናለች፤ ከእንግዲህም ወዲያ ባዕዳን አይወርሯትም። “በዚያ ጊዜ ተራሮች፣ አዲስ የወይን ጠጅ ያንጠባጥባሉ፤ ኰረብቶችም ወተት ያፈስሳሉ፤ በይሁዳ ያሉ ሸለቆዎች ሁሉ ውሃ ያጐርፋሉ፤ ከእግዚአብሔር ቤት ምንጭ ይፈልቃል፤ የሰጢምን ሸለቆ ያጠጣል። ግብፅ ባድማ፣ ኤዶምም ምድረ በዳ ትሆናለች፤ በምድራቸው ንጹሕ ደም በማፍሰስ፣ በይሁዳ ሕዝብ ላይ ግፍ ፈጽመዋልና። ይሁዳ ለዘላለም፣ ኢየሩሳሌምም ለትውልድ ሁሉ መኖሪያ ትሆናለች፤ ደማቸውን እበቀላለሁ፤ በደለኛውንም ንጹሕ አላደርግም።”
ኢዩኤል 3:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እነሆም፥ በዚያ ወራትና በዚያ ዘመን፥ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ምርኮ በምመልስበት ጊዜ፥ አሕዛብን ሁሉ ሰብስቤ ወደ ኢዮሣፍጥ ሸለቆ አወርዳቸዋለሁ፥ በዚያም ስለ ሕዝቤና ስለ ርስቴ ስለ እስራኤል በአሕዛብ መካከል የበተኑአቸውን ምድሬንም የተካፈሉአትን እፋረድባቸዋለሁ። በሕዝቤም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ፥ ወንድ ልጅን ለጋለሞታ ዋጋ ሰጡ፥ ሴት ልጅን ለወይን ጠጅ ሸጡ፥ ጠጡም። ጢሮስና ሲዶና የፍልስጥኤምም ግዛት ሁሉ ሆይ፥ ከእናንተ ጋር ለእኔ ምን አለኝ? በውኑ ብድራትን ትመልሱልኛላችሁን? ብድራትን ብትመልሱልኝ ፈጥኜ በችኰላ ብድራታችሁን በራሳችሁ ላይ እመልሳለሁ። ብሬንና ወርቄን ወስዳችኋልና፥ የተወደደውንም መልካሙን ዕቃዬን ወደ መቅደሳችሁ አግብታችኋልና፥ ከዳርቻቸውም ታርቁአቸው ዘንድ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ልጆች ለግሪክ ሰዎች ሸጣችኋልና፥ እነሆ፥ እነርሱን ከሸጣችሁበት ስፍራ አስነሣቸዋለሁ፥ ብድራታችሁንም በራሳችሁ ላይ እመልሳለሁ። እግዚአብሔር ተናግሮአልና ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁን በይሁዳ ልጆች እጅ እሸጣለሁ፥ እነርሱም ለሩቆቹ ሕዝብ ለሳባ ሰዎች ይሸጡአችኋል። ይህን በአሕዛብ መካከል አውጁ፥ ለሰልፍ ተዘጋጁ፥ ኃያላንን አስነሡ፥ ሰልፈኞች ሁሉ ይቅረቡ ይውጡም። ማረሻችሁን ሰይፍ፥ ማጭዳችሁንም ጦር ለማድረግ ቀጥቅጡ፥ ደካማውም፦ እኔ ብርቱ ነኛ ይበል። እናንተ በዙሪያ ያላችሁ አሕዛብ ሁሉ፥ ቸኵላችሁ ኑ፥ ተሰብሰቡ፥ አቤቱ፥ ኃያላኖችህን ወደዚያ አውርድ። አሕዛብ ይነሡ፥ ወደ ኢዮሣፍጥ ሸለቆም ይውጡ፥ በዙሪያ ባሉ አሕዛብ ሁሉ ላይ እፈርድ ዘንድ በዚያ እቀመጣለሁና። መከሩ ደርሶአልና ማጭድ ስደዱ፥ መጥመቂያውም ሞልቶአልና ኑ እርገጡ፥ ክፉታቸውም በዝቶአልና መጥመቂያ ሁሉ ፈርሶአል። የእግዚአብሔር ቀን በፍርድ ሸለቆ ቀርቦአልና የብዙ ብዙ ሕዝብ ውካታ በፍርድ ሸለቆ አለ። ፀሐይና ጨረቃ ጨልመዋል፥ ከዋክብትም ብርሃናቸውን ሰውረዋል። እግዚአብሔርም በጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል፥ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ቃሉን ይሰጣል፥ ሰማይና ምድርም ይናወጣሉ፥ እግዚአብሔር ግን ለሕዝቡ መሸሸጊያ፥ ለእስራኤልም ልጆች መጠጊያ ይሆናል። እኔም በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን የምቀመጥ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፥ የዚያን ጊዜም ኢየሩሳሌም የተቀደሰች ትሆናለች፥ እንግዶችም ከእንግዲህ ወዲህ አያልፉባትም። በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ተራሮች በተሃ ጠጅ ያንጠባጥባሉ፥ ኮረብቶችም ወተትን ያፈስሳሉ፥ በይሁዳም ያሉት ፈፋዎች ሁሉ ውኃን ያጐርፋሉ፥ ከእግዚአብሔርም ቤት ምንጭ ትፈልቃለች፥ የሰጢምንም ሸለቆ ታጠጣለች። በአገራቸው ንጹሑን ደም አፍስሰዋልና በይሁዳ ልጆች ላይ ስላደረጉት ግፍ ግብጽ ምድረ በዳ፥ ኤዶምያስም በረሃ ይሆናል። ነገር ግን ይሁዳ ለዘላለም፥ ኢየሩሳሌምም ለልጅ ልጅ መኖሪያ ይሆናል። እኔም ንጹሕ ያላደረግሁትን ደማቸውን ንጹሕ አደርገዋለሁ፥ እግዚአብሔርም በጽዮን ያድራል።
ኢዩኤል 3:1-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በዚያን ጊዜ የኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ምርኮ እመልሳለሁ፤ አሕዛብን ሁሉ ሰብስቤ፥ ወደ ኢዮሣፍጥ ሸለቆ አወርዳቸዋለሁ፤ የእኔ የሆኑትን ሕዝቤን እስራኤልን በሕዝቦች መካከል ስለ በታተኑና ምድሪቱን ስለ ተካፈሉ በኢዮሣፍጥ ሸለቆ ወደ ፍርድ አቀርባቸዋለሁ። የማረኩአቸውን ሕዝቤንም ለመከፋፈል ዕጣ ተጣጥለዋል፤ አመንዝራ ሴቶችን ለማግኘት ወንዶች ልጆችን ሰጡ፤ ወይን ጠጅ ለመጠጣትም ሴቶች ልጆችን ባሪያ አድርገው ሸጡ። “እናንተ የጢሮስ፥ የሲዶናና የፍልስጥኤም አውራጃዎች ሕዝብ ሆይ፥ ምን እያደረጋችሁ ነው? እኔን ለመበቀል ይቃጣችኋልን? ይህ ከሆነ ሥራችሁ ወዲያው በፍጥነት በራሳችሁ ላይ እንዲመለስ አደርጋለሁ። ብሬንና ወርቄን እንዲሁም ውድ የሆነ ሀብቴን ሁሉ ወስዳችሁ ወደ ጣዖት ማምለኪያ ቤታችሁ አስገብታችኋል። የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ተወላጆች ከአገራቸው ድንበር አርቃችሁ በመውሰድ ለግሪክ ሰዎች ሸጣችኋል። እነሆ አሁን ከተሸጡባቸው ስፍራዎች አነሣሥቼ እንዲወጡ አደርጋለሁ፤ በእነርሱ ላይ የፈጸማችሁትን በደል ሁሉ በእናንተ ላይ መልሼ አመጣባችኋለሁ። የእናንተንም ወንዶችና ሴቶች ልጆች ለይሁዳ ሕዝብ ተላልፈው እንዲሸጡ አደርጋለሁ፤ እነርሱም ሩቅ ላሉት ለሳባውያን ይሸጡአቸዋል፤ ይህንንም የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። “ይህን ለአሕዛብ ሁሉ ዐውጁ፤ ለጦርነት ተዘጋጁ፤ ጀግኖችን ቀስቅሱ፤ ጦረኞቻችሁ ሁሉ ተሰብስበው ለጦርነት ይሰለፉ። ማረሻችሁ ሰይፍ፥ ማጭዳችሁም ጦር እንዲሆን ቀጥቅጡ፤ ደካማውም እንኳ ‘እኔ ብርቱ ነኝ’ ይበል፤ እናንተ በዙሪያ ያላችሁ አሕዛብ ሁሉ፤ በፍጥነት ውጡ! በሸለቆውም ተሰብሰቡ።” እግዚአብሔር ሆይ፥ ተዋጊ ሠራዊትህን ላክ። “አሕዛብ ሁሉ ተነሣሥተው ወደ ኢዮሣፍጥ ሸለቆ ይሂዱ፤ እኔ እግዚአብሔር በዙሪያ ባሉት አሕዛብ ላይ ለመፍረድ እዚያ እቀመጣለሁ። የእነርሱ ክፋት እጅግ በዝቶአል፤ የደረሰ መከር በማጭድ እንደሚታጨድ እጨዱአቸው፤ የወይን ዘለላ በመጥመቂያው ሞልቶ እንደሚረገጥ ርገጡአቸው፤” ጌታ በፍርድ ሸለቆ ፍርድ የሚሰጥበት ቀን ደርሶአል፤ ስለዚህ ቊጥሩ እጅግ የበዛ ሕዝብ በዚያ ተሰብስቦአል። በዚያን ቀን ፀሐይና ጨረቃ ይጨልማሉ፤ ከዋክብትም ብርሃናቸውን ያጣሉ። እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ በኢየሩሳሌም ሆኖ፥ የሚያስፈራ ድምፁን ያሰማል፤ ሰማይና ምድር ይናወጣሉ፤ እግዚአብሔር ግን ለሕዝቡ ለእስራኤል መጠጊያ ምሽግ ይሆናል፤ “እስራኤል ሆይ! በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንኩ ታውቃላችሁ፤ በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን ላይ እኖራለሁ፤ ኢየሩሳሌምም የተቀደሰች ከተማ ትሆናለች፤ ከእንግዲህ ወዲህ የባዕድ ወታደሮች አይወሩአትም። “በዚያን ጊዜ ተራራዎችም ሁሉ በወይን ተክል ይሸፈናሉ፤ በኰረብቶችም ላይ ብዙ ወተት የሚሰጡ ከብቶች ይሰማራሉ፤ በይሁዳ ምድር የሚገኙ ወንዞች ሁሉ በውሃ የተሞሉ ይሆናሉ፤ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ምንጭ ይፈልቃል፤ የሺጢምንም ሸለቆ ያጠጣል። “የግብጽና የኤዶም ሰዎች በይሁዳ ሕዝብ ላይ ግፍ ስለ ፈጸሙና ንጹሑንም ሕዝብ ስለ ገደሉ፥ ‘ግብጽ ወደ በረሓነት ትለወጣለች፤ ኤዶምም ሰው የማይኖርባት ምድረ በዳ ትሆናለች።’ ስለዚህ እስከ አሁን ድረስ ሳልበቀልላቸው የቀረሁትን የንጹሐንን ደም እበቀላለሁ፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ግን ለዘለዓለም ለሕዝቤ መኖሪያ ይሆናሉ፤ እኔም እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ ላይ እኖራለሁ።”
ኢዩኤል 3:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እነሆም፥ በዚያ ወራትና በዚያ ዘመን፥ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ምርኮ በምመልስበት ጊዜ፥ አሕዛብን ሁሉ ሰብስቤ ወደ ኢዮሣፍጥ ሸለቆ አወርዳቸዋለሁ፥ በዚያም ስለ ሕዝቤና ስለ ርስቴ ስለ እስራኤል በአሕዛብ መካከል የበተኑአቸውን፥ ምድሬንም የተካፈሉአትን እፈርድባቸዋለሁ። በሕዝቤም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ፥ ወንድ ልጅን ለጋለሞታ ዋጋ ሰጡ፥ ሴት ልጅን ለወይን ጠጅ ሲሉ ሸጡ፥ ጠጡም። ጢሮስና ሲዶና የፍልስጥኤምም ግዛት ሁሉ ሆይ፥ ከእናንተ ጋር ምን ጉዳይ አለኝ? በውኑ ልትበቀሉኝ ትፈልጋላችሁን? በቀልን በእኔ ላይ ማውረድ ብትሞክሩ፥ በቀሉን መልሼ በፍጥነት በእናንተ ላይ አወርደዋለሁ። ብሬንና ወርቄን ወስዳችኋልና፥ የተወደደውንም ብርቅዬ ዕቃዎቼንም ወደ መቅደሳችሁ አስግብታችኋልና፥ ከዳርቻቸውም ታርቁአቸው ዘንድ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ልጆች ለግሪክ ሰዎች ሸጣችኋልና፥ እነሆ፥ እነርሱን ከሸጣችሁበት ስፍራ አስነሣቸዋለሁ፥ በደሉን በራሳችሁ ላይ እመልሳለሁ። ጌታ ተናግሮአልና ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁን በይሁዳ ልጆች እጅ እሸጣለሁ፥ እነርሱም ለሩቆቹ ሕዝብ ለሳባ ሰዎች ይሸጡአችኋል። ይህን በአሕዛብ መካከል አውጁ፥ ለጦርነት ተዘጋጁ፥ ኃያላንን አስነሡ፥ ጦረኖች ሁሉ ይቅረቡ ይውጡም። ማረሻችሁን ሰይፍ፥ ማጭዳችሁንም ጦር ለማድረግ ቀጥቅጡ፥ ደካማውም፦ እኔ ብርቱ ነኛ ይበል። እናንተ በዙሪያ ያላችሁ አሕዛብ ሁሉ፥ ቸኩላችሁ ኑ፥ ተሰብሰቡ፥ አቤቱ፥ ኃያላኖችህን ወደዚያ አውርድ። አሕዛብ ይነሡ፥ ወደ ኢዮሣፍጥ ሸለቆም ይውጡ፥ በዙሪያ ባሉ አሕዛብ ሁሉ ላይ እፈርድ ዘንድ በዚያ እቀመጣለሁና። መከሩ ደርሶአልና ማጭድ ስደዱ፥ መጥመቂያውም ሞልቶአልና ኑ እርገጡ፥ ክፉታቸውም በዝቶአልና መጥመቂያ ሁሉ ፈርሶአል። የጌታ ቀን በፍርድ ሸለቆ ቀርቧልና የብዙ ብዙ ሕዝብ ውካታ በፍርድ ሸለቆ አለ። ፀሐይና ጨረቃ ጨልመዋል፥ ከዋክብትም ብርሃናቸውን ሰውረዋል። ጌታም በጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል፥ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ቃሉን ያሰማል፥ ሰማይና ምድርም ይናወጣሉ፥ ጌታ ግን ለሕዝቡ መሸሸጊያ፥ ለእስራኤልም ልጆች መጠጊያ ይሆናል። እኔም በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን የምቀመጥ ጌታ አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ፥ የዚያን ጊዜም ኢየሩሳሌም የተቀደሰች ትሆናለች፥ እንግዶችም ከእንግዲህ ወዲህ አያልፉባትም። በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ተራሮች አዲስ ወይን ጠጅ ያንጠባጥባሉ፥ ኮረብቶችም ወተትን ያፈስሳሉ፥ በይሁዳም ያሉት ፈፋዎች ሁሉ ውኃን ያጐርፋሉ፥ ከጌታም ቤት ምንጭ ትፈልቃለች፥ የሰጢምንም ሸለቆ ታጠጣለች። በአገራቸው ንጹሑን ደም አፍስሰዋልና በይሁዳ ልጆች ላይ ስላደረጉት ግፍ ግብጽ ምድረ በዳ፥ ኤዶምያስም በረሃ ይሆናል። ነገር ግን ይሁዳ ለዘለዓለም፥ ኢየሩሳሌምም ለልጅ ልጅ መኖሪያ ይሆናል። እኔም ሳልበቀላቸው እቀራለሁን? መበቀሌ አይቀርም፤ ጌታም በጽዮን ያድራል።