ዮሐንስ 21:4-8
ዮሐንስ 21:4-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በነጋ ጊዜም ጌታችን ኢየሱስ በባሕሩ ዳር ቆሞ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም አዩት፤ ግን ጌታችን ኢየሱስ እንደ ሆነ አላወቁም። ጌታችን ኢየሱስም፥ “ልጆች ሆይ አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?” አላቸው፤ እነርሱም፥ “የለም” አሉት። ጌታችን ኢየሱስም፥ “መረባችሁን በታንኳዪቱ በስተቀኝ በኩል ጣሉ፤ ታገኛላችሁም” አላቸው፤ መረባቸውንም በጣሉ ጊዜ ከተያዘው ዓሣ ብዛት የተነሣ ስቦ ማውጣት ተሳናቸው። ጌታችን ኢየሱስ ይወደው የነበረ ያ ደቀ መዝሙርም ለጴጥሮስ፥ “ጌታችን ነው እኮ” አለው፤ ስምዖን ጴጥሮስም ጌታችን እንደ ሆነ በሰማ ጊዜ የሚለብሰውን ልብስ አንሥቶ በወገቡ ታጠቀ፤ ራቁቱን ነበርና ወደ ባሕር ተወረወረ። ሌሎች ደቀ መዛሙርት ግን በታንኳ መጡ፤ ከሁለት መቶ ክንድ ያህል በቀር ከምድር አልራቁም ነበርና፤ ዓሣ የመላባቸውን መረቦቻቸውንም እየሳቡ ሄዱ።
ዮሐንስ 21:4-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሲነጋም፣ ኢየሱስ በባሕሩ ዳርቻ ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም ነበር። እርሱም፣ “ልጆች፣ ዓሣ አላችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “የለንም” አሉት። እርሱም፣ “መረባችሁን ከጀልባው በስተ ቀኝ ጣሉ፤ ዓሣ ታገኛላችሁ” አላቸው። እነርሱም በጣሉ ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ መረቡን መጐተት አቃታቸው። ኢየሱስ ይወድደው የነበረው ደቀ መዝሙርም፣ ጴጥሮስን፣ “ጌታ እኮ ነው!” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም፣ “ጌታ እኮ ነው!” የሚለውን ቃል በሰማ ጊዜ፣ አውልቆት የነበረውን መደረቢያ ልብስ ታጠቀና ዘልሎ ወደ ባሕሩ ገባ። ሌሎች ደቀ መዛሙርት ግን ከባሕሩ ዳርቻ የራቁት ሁለት መቶ ክንድ ያህል ብቻ ስለ ነበር፣ ዓሣ የሞላበትን መረብ እየሳቡ በጀልባዋ መጡ።
ዮሐንስ 21:4-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በነጋም ጊዜ ኢየሱስ በባሕር ዳር ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም። ኢየሱስም፦ “ልጆች ሆይ፥ አንዳች የሚበላ አላችሁን?” አላቸው። “የለንም” ብለው መለሱለት። እርሱም፦ “መረቡን በታንኳይቱ በስተ ቀኝ ጣሉት ታገኙማላችሁ” አላቸው። ስለዚህ ጣሉት፤ በዚህም ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ ሊጐትቱት አቃታቸው። ኢየሱስ ይወደው የነበረውም ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን፦ “ጌታ እኮ ነው” አለው። ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ጌታ መሆኑን በሰማ ጊዜ ዕራቁቱን ነበረና ልብሱን ታጥቆ ወደ ባሕር ራሱን ጣለ። ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ግን ከምድር ሁለት መቶ ክንድ ያህል እንጂ እጅግ አልራቁም ነበርና ዓሣ የሞላውን መረብ እየሳቡ በጀልባ መጡ።
ዮሐንስ 21:4-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሲነጋ ኢየሱስ በባሕሩ ዳር ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም። ኢየሱስም “ልጆች ሆይ! አንዳች ዓሣ አላችሁን?” አላቸው። እነርሱም “ምንም የለንም” አሉት። እርሱም “መረቡን ከጀልባው በስተቀኝ በኩል ጣሉና ታገኛላችሁ” አላቸው። ስለዚህ መረቡን በባሕሩ ውስጥ ጣሉት፤ ብዙ ዓሣም ከመያዛቸው የተነሣ መረቡን መጐተት አቃታቸው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ የሚወድደው ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን “ጌታ ነው እኮ!” አለው። ስምዖን ጴጥሮስ “ጌታ ነው” ማለትን በሰማ ጊዜ ለሥራ ብሎ ልብሱን አውልቆ ስለ ነበረ ወዲያው ልብሱን ለበሰና ወደ ባሕሩ ዘሎ ገባ። ሌሎች ደቀ መዛሙርት ግን ከምድር የራቁት መቶ ሜትር ያኽል ብቻ ስለ ነበረ ዓሣ የሞላበትን መረብ እየሳቡ በጀልባ መጡ።
ዮሐንስ 21:4-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በነጋም ጊዜ ኢየሱስ በባሕር ዳር ቆመ፤ ደቀመዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም። ኢየሱስም “ልጆች ሆይ! አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?” አላቸው። “የለንም” ብለው መለሱለት። እርሱም “መረቡን በታንኳዪቱ በስተ ቀኝ ጣሉትና ታገኛላችሁ” አላቸው። ስለዚህም ጣሉት፤ በዚህም ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ መረቡን መጎተት አቃታቸው። ኢየሱስ ይወደው የነበረውም ደቀመዝሙር ጴጥሮስን “ጌታ እኮ ነው” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም ጌታ መሆኑን በሰማ ጊዜ ዕራቁቱን ነበረና ልብሱን ታጥቆ ወደ ባሕር ዘለለ። ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ግን ከምድር የራቁት ሁለት መቶ ክንድ ያህል ብቻ ስለ ነበር ዓሣ የሞላውን መረብ እየሳቡ በጀልባ መጡ።