ዮሐንስ 21:20-23
ዮሐንስ 21:20-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጴጥሮስም መለስ ብሎ ጌታችን ኢየሱስ ይወደው የነበረውን ያን ደቀ መዝሙር ሲከተለው አየ፤ እርሱም ራት ሲበሉ በጌታችን በኢየሱስ አጠገብ የነበረውና “ጌታ ሆይ፥ አሳልፎ የሚሰጥህ ማነው?” ያለው ነው። ጴጥሮስም እርሱን አይቶ፥ “ጌታ ሆይ፥ ይህስ እንዴት ይሆናል?” አለው። ጌታችን ኢየሱስም፥ “እስክመጣ ይኖር ዘንድ ብወድድስ አንተን ምን አግዶህ፤ አንተ ግን ተከተለኝ” አለው። ያም ደቀ መዝሙር እንደማይሞት ይህ ነገር በወንድሞች ዘንድ ተነገረ፤ ጌታችን ኢየሱስ ግን፥ “እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድድስ አንተን ምን አግዶህ” አለ እንጂ አይሞትም አላለውም።
ዮሐንስ 21:20-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ጴጥሮስ ወደ ኋላው ዘወር ሲል፣ ኢየሱስ ይወድደው የነበረ ደቀ መዝሙር ሲከተላቸው አየ፤ ይህም ደቀ መዝሙር ያን ጊዜ እራት ሲበሉ ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ፣ “ጌታ ሆይ፤ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ያለው ነበር። ጴጥሮስም ባየው ጊዜ፣ “ጌታ ሆይ፤ እርሱስ?” ብሎ ጠየቀ። ኢየሱስም፣ “እስክመለስ ድረስ በሕይወት እንዲኖር ብፈልግ እንኳ አንተን ምን ቸገረህ? አንተ ራስህ ተከተለኝ” አለው። በዚህ ምክንያት ይህ ደቀ መዝሙር አይሞትም የሚል ወሬ በወንድሞች መካከል ተሠራጨ። ኢየሱስ ግን፣ “እስክመለስ ድረስ በሕይወት እንዲኖር ብፈልግ አንተን ምን ቸገረህ?” አለው እንጂ እንደማይሞት አልነገረውም።
ዮሐንስ 21:20-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ጴጥሮስም ዘወር ብሎ ኢየሱስ ይወደው የነበረውን ደቀ መዝሙር ሲከተለው አየ፤ እርሱም ደግሞ በእራት ጊዜ በደረቱ ተጠግቶ፦ “ጌታ ሆይ፥ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ያለው ነበረ። ጴጥሮስም ይህን አይቶ ኢየሱስን፦ “ጌታ ሆይ፥ ይህስ እንዴት ይሆናል?” አለው። ሲየሱስም፦ “እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ፥ ምን አግዶህ? አንተ ተከተለኝ” አለው። ስለዚህ፦ “ያ ደቀ መዝሙር አይሞትም” የሚለው ይህ ነገር ወደ ወንድሞች ወጣ፤ ነገር ግን ኢየሱስ፦ “እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ ምን አግዶህ?” አለው እንጂ አይሞትም አላለውም።
ዮሐንስ 21:20-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ጴጥሮስ ዘወር ብሎ ኢየሱስ የሚወድደው ደቀ መዝሙር ሲከተለው አየ፤ ይህ ደቀ መዝሙር በእራት ጊዜ ወደ ኢየሱስ ተጠግቶ፥ “ጌታ ሆይ፥ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ብሎ የጠየቀው ነው። ጴጥሮስ እርሱን አየና “ጌታ ሆይ! ይህስ ሰው ምን ይሆናል?” ሲል ኢየሱስን ጠየቀ። ኢየሱስም “እኔ እስክመጣ ድረስ እንዲኖር ብፈቅድ አንተን ምን አገባህ? አንተ ተከተለኝ!” አለው። በዚህ ምክንያት በወንድሞች መካከል፥ “ይህ ደቀ መዝሙር አይሞትም” የሚል ወሬ ተሰራጨ፤ ነገር ግን ኢየሱስ፥ “እኔ እስክመጣ ድረስ እንዲኖር ብፈቅድ አንተ ምን አገባህ” አለ እንጂ፥ “አይሞትም” አላለም።
ዮሐንስ 21:20-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጴጥሮስም ዘወር ሲል ኢየሱስ ይወደው የነበረውን ደቀመዝሙር ከበስተኋላው አየ፤ እርሱም በእራት ጊዜ ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ “ጌታ ሆይ! አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ያለው ነበረ። ጴጥሮስም እርሱን አይቶ ኢየሱስን “ጌታ ሆይ! እርሱስ እንዴት ይሆናል?” አለው። ኢየሱስም “እስክመጣ ድረስ እንዲኖር ብፈቅድስ፥ ምን ግድ አለህ? አንተ ተከተለኝ” አለው። ስለዚህ “ያ ደቀመዝሙር አይሞትም” የሚል ወሬ በወንድሞች መካከል ተሰማ፤ ነገር ግን ኢየሱስ “እስክመጣ ድረስ እንዲኖር ብፈቅድ ምን ግድ አለህ?” አለው እንጂ “አይሞትም፤” አላለውም ነበር።