ዮሐንስ 21:1-20
ዮሐንስ 21:1-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ በጥብርያዶስ ባሕር አጠገብ ለደቀ መዛሙርቱ እንደገና ተገለጠላቸው፤ እንዲህም ተገለጠላቸው። ስምዖን ጴጥሮስ፥ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ፥ ከገሊላ ቃና የሆነው ናትናኤል፥ የዘብዴዎስ ልጆችና ሌሎችም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት አብረው ነበሩ። ስምዖን ጴጥሮስ፥ “እኔ ዓሣ ላጠምድ እሄዳለሁ” አላቸው፤ እነርሱም፥ “እኛም አብረንህ እንመጣለን” አሉት፤ ሄደውም ወደ ታንኳ ገቡ፤ ግን በዚያች ሌሊት የያዙት ምንም የለም። በነጋ ጊዜም ጌታችን ኢየሱስ በባሕሩ ዳር ቆሞ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም አዩት፤ ግን ጌታችን ኢየሱስ እንደ ሆነ አላወቁም። ጌታችን ኢየሱስም፥ “ልጆች ሆይ አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?” አላቸው፤ እነርሱም፥ “የለም” አሉት። ጌታችን ኢየሱስም፥ “መረባችሁን በታንኳዪቱ በስተቀኝ በኩል ጣሉ፤ ታገኛላችሁም” አላቸው፤ መረባቸውንም በጣሉ ጊዜ ከተያዘው ዓሣ ብዛት የተነሣ ስቦ ማውጣት ተሳናቸው። ጌታችን ኢየሱስ ይወደው የነበረ ያ ደቀ መዝሙርም ለጴጥሮስ፥ “ጌታችን ነው እኮ” አለው፤ ስምዖን ጴጥሮስም ጌታችን እንደ ሆነ በሰማ ጊዜ የሚለብሰውን ልብስ አንሥቶ በወገቡ ታጠቀ፤ ራቁቱን ነበርና ወደ ባሕር ተወረወረ። ሌሎች ደቀ መዛሙርት ግን በታንኳ መጡ፤ ከሁለት መቶ ክንድ ያህል በቀር ከምድር አልራቁም ነበርና፤ ዓሣ የመላባቸውን መረቦቻቸውንም እየሳቡ ሄዱ። ወደ ምድርም በወረዱ ጊዜ ፍሙ መርቶ፥ ዓሣም በላዩ ሆኖ፥ እንጀራም ተሠርቶ አገኙ። ጌታችን ኢየሱስም፥ “አሁን ከያዛችኋቸው ዓሣዎች አምጡ” አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም ወደ ታንኳ ገብቶ መቶ አምሳ ሦስት ታላላቅ ዓሣዎችን መልቶ የነበረውን መረብ ወደ ምድር ሳበ፤ ብዛቱም ይህን ያህል ሲሆን መረቡ አልተቀደደም። ጌታችን ኢየሱስም፥ “ኑ፥ ምሳ ብሉ” አላቸው፤ ከደቀ መዛሙርቱም አንተ ማነህ? ብሎ ሊጠይቀው የደፈረ የለም፤ ጌታችን እንደ ሆነ ዐውቀዋልና። ጌታችን ኢየሱስም መጣና ኅብስቱን አንሥቶ ሰጣቸው፤ ከዓሣውም እንዲሁ። ጌታችን ኢየሱስም ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲገለጥላቸው ይህ ሦስተኛ ጊዜዉ ነበር። ምሳም ከበሉ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ፦ ስምዖን ጴጥሮስን፥ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን?” አለው፤ እርሱም፥ “አዎን፥ ጌታዬ ሆይ፥ እኔ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “በጎችን ጠብቅ” አለው። ዳግመኛም፥ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን?” አለው፤ እርሱም፥ “አዎን፥ ጌታዬ ሆይ፥ እኔ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው፤ “ጠቦቶችን አሰማራ” አለው። ሦስተኛ ጊዜም፥ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን?” አለው፤ ጴጥሮስም ሦስት ጊዜ ትወደኛለህን? ስላለው ተከዘ፤ “ጌታዬ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እኔም እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው፤ “እንኪያስ ግልገሎችን ጠብቅ” አለው። “እውነት እውነት እልሃለሁ፤ አንተ ጐልማሳ ሳለህ በገዛ እጅህ ወገብህን ታጥቀህ ወደ ወደድኸው ትሄድ ነበር፤ በሸመገልህ ጊዜ ግን እጆችህን ትዘረጋለህ፤ ወገብህንም ሌላ ያስታጥቅሃል፤ ወደማትወደውም ይወስድሃል።” በምን ሞት እግዚአብሔርን ያከብር ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት ይህን ተናገረ፤ ይህንም ብሎ ተከተለኝ አለው። ጴጥሮስም መለስ ብሎ ጌታችን ኢየሱስ ይወደው የነበረውን ያን ደቀ መዝሙር ሲከተለው አየ፤ እርሱም ራት ሲበሉ በጌታችን በኢየሱስ አጠገብ የነበረውና “ጌታ ሆይ፥ አሳልፎ የሚሰጥህ ማነው?” ያለው ነው።
ዮሐንስ 21:1-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም በኋላ ኢየሱስ በጥብርያዶስ ባሕር እንደ ገና ለደቀ መዛሙርቱ ታየ፤ በዚህም ሁኔታ ተገለጠ፤ ስምዖን ጴጥሮስ፣ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ፣ የቃና ዘገሊላው ናትናኤል፣ የዘብዴዎስ ልጆችና ከደቀ መዛሙርቱ ሌሎች ሁለት አንድ ላይ ነበሩ፤ ስምዖን ጴጥሮስም፣ “ዓሣ ላጠምድ መሄዴ ነው” አላቸው፤ እነርሱም፣ “እኛም ከአንተ ጋር እንሄዳለን” አሉት። ወጥተውም ወደ ጀልባዋ ገቡ፤ በዚያ ሌሊት ግን ምንም አላጠመዱም። ሲነጋም፣ ኢየሱስ በባሕሩ ዳርቻ ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም ነበር። እርሱም፣ “ልጆች፣ ዓሣ አላችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “የለንም” አሉት። እርሱም፣ “መረባችሁን ከጀልባው በስተ ቀኝ ጣሉ፤ ዓሣ ታገኛላችሁ” አላቸው። እነርሱም በጣሉ ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ መረቡን መጐተት አቃታቸው። ኢየሱስ ይወድደው የነበረው ደቀ መዝሙርም፣ ጴጥሮስን፣ “ጌታ እኮ ነው!” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም፣ “ጌታ እኮ ነው!” የሚለውን ቃል በሰማ ጊዜ፣ አውልቆት የነበረውን መደረቢያ ልብስ ታጠቀና ዘልሎ ወደ ባሕሩ ገባ። ሌሎች ደቀ መዛሙርት ግን ከባሕሩ ዳርቻ የራቁት ሁለት መቶ ክንድ ያህል ብቻ ስለ ነበር፣ ዓሣ የሞላበትን መረብ እየሳቡ በጀልባዋ መጡ። ወደ ምድርም በደረሱ ጊዜ፣ ዓሣ በላዩ የነበረበት የከሰል ፍምና እንጀራ አዩ። ኢየሱስም፣ “አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ እስቲ አምጡ” አላቸው። ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ወደ ጀልባዋ ወጥቶ መረቡን ወደ ምድር ጐተተው፤ መረቡንም መቶ አምሳ ሦስት ትልልቅ ዓሣ ሞልተውት ነበር፤ ይህን ያህል ቢይዝም መረቡ አልተቀደደም። ኢየሱስም “ኑ፤ ቍርስ ብሉ” አላቸው። ጌታ እንደ ሆነ ዐውቀው ስለ ነበር፣ ከደቀ መዛሙርቱ፣ “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ለመጠየቅ የደፈረ አልነበረም። ኢየሱስም መጥቶ እንጀራውን አንሥቶ ሰጣቸው፤ እንዲሁም ዓሣውን። እንግዲህ ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲታይ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነው። በልተው ካበቁ በኋላ፣ ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን፣ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፤ ከእነዚህ አብልጠህ ትወድደኛለህን?” አለው። እርሱም፣ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤ እንደምወድድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም፣ “ጠቦቶቼን መግብ” አለው። ኢየሱስም ለሁለተኛ ጊዜ፣ “የዮና ልጅ፣ ስምዖን ሆይ፤ በእውነት ትወድደኛለህን?” አለው። እርሱም፣ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤ እንደምወድድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም፣ “በጎቼን ጠብቅ” አለው። ሦስተኛም ጊዜ፣ “የዮና ልጅ፣ ስምዖን ሆይ፤ ትወድደኛለህን?” አለው። ጴጥሮስም ሦስተኛ ጊዜ ኢየሱስ፣ “ትወድደኛለህን?” ብሎ ስለ ጠየቀው ዐዝኖ፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንደምወድድህም ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “በጎቼን መግብ። እውነት እልሃለሁ፤ ወጣት ሳለህ ልብስህን ራስህ ለብሰህ ወደ ፈለግህበት ትሄድ ነበር፤ ስትሸመግል ግን እጅህን ትዘረጋለህ፤ ሌላም ሰው ልብስህን አስታጥቆህ ልትሄድ ወደማትፈልግበት ይወስድሃል።” ኢየሱስ ይህን ያለው ጴጥሮስ በምን ዐይነት ሞት እግዚአብሔርን እንደሚያከብረው ለማመልከት ነው። ከዚህ በኋላም፣ “ተከተለኝ” አለው። ጴጥሮስ ወደ ኋላው ዘወር ሲል፣ ኢየሱስ ይወድደው የነበረ ደቀ መዝሙር ሲከተላቸው አየ፤ ይህም ደቀ መዝሙር ያን ጊዜ እራት ሲበሉ ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ፣ “ጌታ ሆይ፤ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ያለው ነበር።
ዮሐንስ 21:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በጥብርያዶስ ባሕር አጠገብ ለደቀ መዛሙርቱ እንደ ገና ተገለጠላቸው፤ እንዲህም ተገለጠ። ስምዖን ጴጥሮስና ዲዲሞስ የሚባለው ቶማስ ከገሊላ ቃና የሆነ ናትናኤልም የዘብዴዎስም ልጆች ከደቀ መዛሙርቱም ሌሎች ሁለት በአንድነት ነበሩ። ስምዖን ጴጥሮስ፦ “ዓሣ ላጠምድ እሄዳለሁ” አላቸው። እነርሱም፦ “እኛም ከአንተ ጋር እንመጣለን” አሉት። ወጥተውም ወደ ታንኳይቱ ገቡ በዚያችም ሌሊት ምንም እላጠመዱም። በነጋም ጊዜ ኢየሱስ በባሕር ዳር ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም። ኢየሱስም፦ “ልጆች ሆይ፥ አንዳች የሚበላ አላችሁን?” አላቸው። “የለንም” ብለው መለሱለት። እርሱም፦ “መረቡን በታንኳይቱ በስተ ቀኝ ጣሉት ታገኙማላችሁ” አላቸው። ስለዚህ ጣሉት፤ በዚህም ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ ሊጐትቱት አቃታቸው። ኢየሱስ ይወደው የነበረውም ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን፦ “ጌታ እኮ ነው” አለው። ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ጌታ መሆኑን በሰማ ጊዜ ዕራቁቱን ነበረና ልብሱን ታጥቆ ወደ ባሕር ራሱን ጣለ። ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ግን ከምድር ሁለት መቶ ክንድ ያህል እንጂ እጅግ አልራቁም ነበርና ዓሣ የሞላውን መረብ እየሳቡ በጀልባ መጡ። ወደ ምድርም በወጡ ጊዜ ፍምና ዓሣ በላዩ ተቀምጦ እንጀራም አዩ። ኢየሱስም፦ “አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ አምጡ” አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም ወደ ጀልባይቱ ገብቶ መቶ አምሳ ሦስት ታላላቅ ዓሦች ሞልቶ የነበረውን መረብ ወደ ምድር ጐተተ፤ ይህንም ያህል ብዙ ሲሆን መረቡ አልተቀደደም። ኢየሱስም፦ “ኑ፥ ምሳ ብሉ” አላቸው። ከደቀ መዛሙርቱ አንድ ስንኳ፦ “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ሊመረምረው የደፈረ አልነበረም፤ ጌታ መሆኑን አውቀው ነበርና። ኢየሱስም መጣና እንጀራ አንሥቶ ሰጣቸው፥ እንዲሁም ዓሣውን። ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲገለጥላቸው ይህ ሦስተኛው ጊዜ ነበረ። ምሳ ከበሉ በኋላም ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን፦ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን?” አለው። “አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። “ግልገሎቼን አሰማራ” አለው። ደግሞ ሁለተኛ፦ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን?” አለው። “አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። “ጠቦቶቼን ጠብቅ” አለው። ሦስተኛ ጊዜ፦ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን?” አለው። ሦስተኛ፦ “ትወደኛለህን?” ስላለው ጴጥሮስ አዘነና፦ “ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም፦ “በጎቼን አሰማራ። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ አንተ ጕልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ፥ ሌላውም ያስታጥቅሃል ወደማትወደውም ይወስድሃል” አለው። በምን ዓይነት ሞት እግዚአብሔርን ያከብር ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት ይህን አለ። ይህንም ብሎ፦ “ተከተለኝ” አለው። ጴጥሮስም ዘወር ብሎ ኢየሱስ ይወደው የነበረውን ደቀ መዝሙር ሲከተለው አየ፤ እርሱም ደግሞ በእራት ጊዜ በደረቱ ተጠግቶ፦ “ጌታ ሆይ፥ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ያለው ነበረ።
ዮሐንስ 21:1-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በጥብርያዶስ ባሕር አጠገብ፥ ለደቀ መዛሙርቱ እንደገና ተገለጠ፤ የተገለጠውም እንደሚከተለው ነው፤ ስምዖን ጴጥሮስ፥ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ፥ የቃና ዘገሊላው ናትናኤል፥ የዘብዴዎስ ልጆችና ሌሎች ሁለት ደቀ መዛሙርት አብረው ነበሩ። ስምዖን ጴጥሮስ “ዓሣ ለማጥመድ መሄዴ ነው” አላቸው። እነርሱም “ከአንተ ጋር እንሄዳለን” አሉት፤ ወጥተውም ሄዱና ወደ ጀልባ ገቡ፤ ነገር ግን በዚያች ሌሊት አንድ ዓሣ እንኳ አልያዙም። ሲነጋ ኢየሱስ በባሕሩ ዳር ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም። ኢየሱስም “ልጆች ሆይ! አንዳች ዓሣ አላችሁን?” አላቸው። እነርሱም “ምንም የለንም” አሉት። እርሱም “መረቡን ከጀልባው በስተቀኝ በኩል ጣሉና ታገኛላችሁ” አላቸው። ስለዚህ መረቡን በባሕሩ ውስጥ ጣሉት፤ ብዙ ዓሣም ከመያዛቸው የተነሣ መረቡን መጐተት አቃታቸው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ የሚወድደው ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን “ጌታ ነው እኮ!” አለው። ስምዖን ጴጥሮስ “ጌታ ነው” ማለትን በሰማ ጊዜ ለሥራ ብሎ ልብሱን አውልቆ ስለ ነበረ ወዲያው ልብሱን ለበሰና ወደ ባሕሩ ዘሎ ገባ። ሌሎች ደቀ መዛሙርት ግን ከምድር የራቁት መቶ ሜትር ያኽል ብቻ ስለ ነበረ ዓሣ የሞላበትን መረብ እየሳቡ በጀልባ መጡ። ከጀልባው በወረዱ ጊዜ ዓሣ በላዩ የነበረበት የከሰል ፍምና እንጀራ አዩ። ኢየሱስም “አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ አምጡ” አላቸው። ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ወደ ጀልባው ገብቶ መቶ ኀምሳ ሦስት ትልልቅ ዓሣዎች የሞሉበትን መረብ ወደ ምድር ጐተተ፤ ይህን ያኽል ብዙ ዓሣ ቢይዝም መረቡ አልተቀደደም። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ፦ “ኑ ብሉ” አላቸው። ጌታ ኢየሱስ መሆኑን ሁሉም ዐውቀው ስለ ነበር፥ ከደቀ መዛሙርቱ አንድ እንኳ፥ “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ሊጠይቀው የደፈረ አልነበረም። ከዚያም ኢየሱስ መጣና፤ እንጀራውንና ዓሣውን አንሥቶ ሰጣቸው። ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ ወዲህ ደቀ መዛሙርቱ ሲያዩት ይህ ሦስተኛ ጊዜ ነበር። ቊርስ ከበሉ በኋላ ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን፥ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! እነዚህ ከሚወዱኝ ይበልጥ ትወደኛለህን?” አለው። እርሱም “አዎ፥ ጌታዬ ሆይ! እኔ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም “ግልገሎቼን መግብ” አለው። ሁለተኛ ጊዜም “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! ትወደኛለህን?” አለው። እርሱም “አዎ፥ ጌታዬ ሆይ! እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም “ጠቦቶቼን ጠብቅ” አለው። ሦስተኛ ጊዜም “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! ትወደኛለህን?” አለው። ሦስተኛ ጊዜ “ትወደኛለህን?” ስላለው ጴጥሮስ አዘነና “ጌታ ሆይ! አንተ ሁሉን ታውቃለህ፥ እኔ እንደምወድህም ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “በጎቼን አሰማራ፤ እውነት፥ እውነት እልሃለሁ፤ አንተ ጐልማሳ ሳለህ ቀበቶህን በገዛ እጅህ ታጥቀህ ወደ ፈለግኽበት ትሄድ ነበር፤ በሸመገልክ ጊዜ ግን አንተ እጆችህን ትዘረጋና ሌላ ሰው ያስታጥቅሃል፤ ወደማትፈልግበትም ይወስድሃል።” ይህንንም ያለው ጴጥሮስ በምን ዐይነት ሞት እግዚአብሔርን ማክበር እንዳለበት ሲያመለክት ነው፤ ከዚህ በኋላ ጴጥሮስን “ተከተለኝ!” አለው። ጴጥሮስ ዘወር ብሎ ኢየሱስ የሚወድደው ደቀ መዝሙር ሲከተለው አየ፤ ይህ ደቀ መዝሙር በእራት ጊዜ ወደ ኢየሱስ ተጠግቶ፥ “ጌታ ሆይ፥ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ብሎ የጠየቀው ነው።
ዮሐንስ 21:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በጥብርያዶስ ባሕር አጠገብ ለደቀ መዛሙርቱ እንደገና ተገለጠላቸው፤ እንዲህም ተገለጠ። ስምዖን ጴጥሮስና ዲዲሞስ የሚባለው ቶማስ፥ ከገሊላ ቃና የሆነው ናትናኤልም፥ የዘብዴዎስ ልጆችና ከደቀ መዛሙርቱም ሌሎች ሁለት በአንድነት ነበሩ። ስምዖን ጴጥሮስ “ዓሣ ላጠምድ እሄዳለሁ” አላቸው። እነርሱም “እኛም ከአንተ ጋር እንመጣለን” አሉት። ወጥተውም ወደ ታንኳይቱ ገቡ፤ ነገር ግን በዚያች ሌሊት ምንም አላጠመዱም። በነጋም ጊዜ ኢየሱስ በባሕር ዳር ቆመ፤ ደቀመዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም። ኢየሱስም “ልጆች ሆይ! አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?” አላቸው። “የለንም” ብለው መለሱለት። እርሱም “መረቡን በታንኳዪቱ በስተ ቀኝ ጣሉትና ታገኛላችሁ” አላቸው። ስለዚህም ጣሉት፤ በዚህም ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ መረቡን መጎተት አቃታቸው። ኢየሱስ ይወደው የነበረውም ደቀመዝሙር ጴጥሮስን “ጌታ እኮ ነው” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም ጌታ መሆኑን በሰማ ጊዜ ዕራቁቱን ነበረና ልብሱን ታጥቆ ወደ ባሕር ዘለለ። ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ግን ከምድር የራቁት ሁለት መቶ ክንድ ያህል ብቻ ስለ ነበር ዓሣ የሞላውን መረብ እየሳቡ በጀልባ መጡ። ወደ የብስ በወጡ ጊዜ ዓሣ በላዩ የተቀመጠበት ፍምና እንጀራ አዩ። ኢየሱስም “አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ አምጡ” አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም ወደ ጀልባይቱ ገብቶ መቶ አምሳ ሦስት ታላላቅ ዓሦች ሞልቶ የነበረውን መረብ ወደ ምድር ጐተተ፤ ይህንንም ያህል ብዙ ዓሣ ይዞ መረቡ አልተቀደደም። ኢየሱስም “ኑ፤ ብሉ” አላቸው። ከደቀ መዛሙርቱ አንድ እንኳን “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ሊጠይቀው የደፈረ አልነበረም፤ ጌታ መሆኑን አውቀው ነበርና። ኢየሱስም መጣና እንጀራ አንሥቶ ሰጣቸው፤ እንዲሁም ዓሣውን። ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲገለጥላቸው ይህ ሦስተኛው ጊዜ ነበረ። ከበሉ በኋላም ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! ከእነዚህ ይበልጥ ትወደኛለህን?” አለው። “አዎን ጌታ ሆይ! እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ፤” አለው። ኢየሱስም “ግልገሎቼን አሰማራ፤” አለው። ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! ትወደኛለህን?” አለው። “አዎን ጌታ ሆይ! እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም “ጠቦቶቼን ጠብቅ፤” አለው። ለሦስተኛ ጊዜም “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! ትወደኛለህን?” አለው። ለሦስተኛ ጊዜ “ትወደኛለህን?” ስላለው ጴጥሮስ አዘነና “ጌታ ሆይ! አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም “በጎቼን አሰማራ። እውነት እውነት እልሃለሁ፤ አንተ ጎልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ቦታ ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ፤ ሌላ ሰውም ያስታጥቅሃል፤ ወደማትወደውም ይወስድሃል” አለው። በምን ዓይነት ሞት እግዚአብሔርን እንደሚያከብር ሲያመለክት ይህንን ተናገረ። ከዚያም “ተከተለኝ፤” አለው። ጴጥሮስም ዘወር ሲል ኢየሱስ ይወደው የነበረውን ደቀመዝሙር ከበስተኋላው አየ፤ እርሱም በእራት ጊዜ ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ “ጌታ ሆይ! አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ያለው ነበረ።