ኤርምያስ 4:1-18
ኤርምያስ 4:1-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እስራኤል ወደ እኔ ቢመለስ ይመለስ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ርኵሰቱንም ከአፉ ቢያስወግድ፤ ከፊቴም የተነሣ ቢፈራ፥ ሕያው እግዚአብሔርን! ብሎ በእውነትና በቅንነት፤ በጽድቅም ቢምል፥ አሕዛብ በእርሱ ይባረካሉ፤ በኢየሩሳሌምም እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ። እግዚአብሔር ለይሁዳ ወንዶችና ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እንዲህ ይላልና፦ ልባችሁን አድሱ በእሾህም ላይ አትዝሩ። እናንተም የይሁዳ ሰዎች በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፥ ስለ ሥራችሁ ክፋት ቍጣዬ እንደ እሳት እንዳይወጣ የሚያጠፋውም ሳይኖር እንዳይነድ ለአምላካችሁ ተገረዙ፤ የልባችሁንም ሸለፈት አስወግዱ። በይሁዳ ዘንድ ተናገሩ፤ በኢየሩሳሌምም ላይ አውሩና፦ በሀገሪቱ ላይ መለከት ንፉ በሉ፤ ጮኻችሁም፦ ሁላችሁ ተሰብሰቡ፤ ወደ ተመሸጉትም ከተሞች እንግባ በሉ። ከሰሜን ክፉ ነገርንና ጽኑ ጥፋትን አመጣለሁና ዓላማችሁን አንሡ፤ ወደ ጽዮንም ሽሹ፥ ፍጠኑ፥ አትዘግዩ። አንበሳ ከጕድጓዱ ወጥቶአል፤ አሕዛብንም ሊያጠፋቸው የሚዘርፍ ተነሥቶአል፤ ምድርሽን ባድማ ያደርግ ዘንድ፥ ከተሞችሽንም ሰው እንዳይኖርባቸው ያፈርሳቸው ዘንድ ከስፍራው ወጥቶአል። የእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ ከእኛ ዘንድ አልተመለሰምና ማቅ ልበሱ፤ አልቅሱም፤ ዋይም በሉ። በዚያም ቀን ይላል እግዚአብሔር፤ የንጉሡና የመኳንንቱ ልብ ይጠፋል፤ ካህናቱም ይደነግጣሉ፤ ነቢያቱም ያደንቃሉ። እኔም፥ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! አንተ ሰይፍ እስከ ሰውነታቸው ድረስ እስክትደርስ ሰላም ይሆንላችኋል” ብለህ ይህን ሕዝብና ኢየሩሳሌምን እጅግ አታለልህ አልሁ። በዚያ ጊዜ ለዚህ ሕዝብና ለኢየሩሳሌም እንዲህ ይሏቸዋል፦ በምድረ በዳ የሚያስት ጋኔን አለ፤ የሕዝቤ ሴት ልጅ መንገድም ለንጽሕና ወይም ለቅድስና አይደለም። አሳች ጋኔን ይመጣል፤ አሁንም እኔ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ። እነሆ! እንደ ደመና ይወጣል፤ ሰረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ ናቸው፤ ፈረሶቹም ከንስር ይልቅ ፈጣኖች ናቸው። ተዋርደናልና ወዮልን። ኢየሩሳሌም ሆይ! ትድኚ ዘንድ ልብሽን ከክፉ ነገር እጠቢ። ክፉ አሳብ የሚኖርብሽ እስከ መቼ ነው? የወሬ ነጋሪ ድምፅ ከዳን ይመጣል፥ ከኤፍሬምም ተራሮች መከራ ይሰማል። ለአሕዛብ አሳስቡ፥ “እነሆ፥ መጡ! ጠላቶች ከሩቅ ሀገር ይመጣሉ፤ በይሁዳም ከተሞች ላይ ይጮኻሉ ብላችሁ በኢየሩሳሌም ላይ አውጁ። በእኔ ላይ ዐመፀኛ ሆናለችና በዙሪያዋ ከብበው እንደ እርሻ ጠባቂዎች ሆነውባታል” ይላል እግዚአብሔር። መንገድሽና ክፉ ሥራሽ ይህን አድርጎብሻል፤ ይህ ክፋትሽ መራራ ነው፤ ወደ ልብሽም ደርሶአል።
ኤርምያስ 4:1-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“እስራኤል ሆይ፤ ብትመለስ፣ ወደ እኔ ብትመለስ” ይላል እግዚአብሔር፤ “አስጸያፊ ነገሮችህን ከፊቴ ብታስወግድ፣ ባትናወጥ ብትቆምም፣ በእውነት፣ በቅንነትና በጽድቅ፣ ‘ሕያው እግዚአብሔርን!’ ብለህ ብትምል፣ አሕዛብ በእርሱ ይባረካሉ፤ በእርሱም ይከበራሉ።” እግዚአብሔር ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም ሰዎች እንዲህ ይላል፤ “ዕዳሪውን መሬት ዕረሱ፤ በእሾኽም መካከል አትዝሩ። እናንተ የይሁዳ ሰዎች፣ የኢየሩሳሌምም ነዋሪዎች፤ ለእግዚአብሔር ተገረዙ፤ የልባችሁንም ሸለፈት አስወግዱ፤ አለዚያ ስለ ሠራችሁት ክፋት፣ ቍጣዬ እንደ እሳት ይንበለበላል፤ ሊገታውም የሚችል የለም። “ ‘በምድሪቱ ሁሉ መለከትን ንፉ’ ብላችሁ፤ በይሁዳ ተናገሩ፣ በኢየሩሳሌም ዐውጁ፤ ጩኹ፤ እንዲህም በሉ፤ ‘በአንድነት ተሰብሰቡ፤ ወደ ተመሸጉት ከተሞች እንሽሽ!’ ወደ ጽዮን ለመግባት ሰንደቅ ዐላማ አንሡ፤ ቶሎ ሸሽታችሁ አምልጡ፤ ከሰሜን መቅሠፍትን፣ ታላቅ ጥፋትን አመጣለሁና።” አንበሳ ከደኑ ወጥቷል፤ ሕዝብንም የሚያጠፋ ተሰማርቷል፤ ምድርሽን ባዶ ሊያደርግ፣ ከስፍራው ወጥቷል። ከተሞችሽ ፈራርሰው ይወድቃሉ፤ ያለ ነዋሪም ይቀራሉ። ስለዚህ ማቅ ልበሱ፤ ዕዘኑ፤ ዋይ በሉ፤ የእግዚአብሔር አስፈሪ ቍጣ፣ ከእኛ አልተመለሰምና። “በዚያ ቀን” ይላል እግዚአብሔር፤ “ንጉሡና ሹማምቱ ወኔ ይከዳቸዋል፤ ካህናቱ ድንጋጤ ይውጣቸዋል፤ ነቢያቱም ብርክ ይይዛቸዋል።” እኔም፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ሰይፍ ዐንገታቸው ላይ ተቃጥቶ ሳለ፣ ‘ሰላም ይሆንላችኋል’ ብለህ ይህን ሕዝብና ኢየሩሳሌምን ለምን እጅግ አታለልህ?” አልሁ። በዚያን ጊዜ፣ ለእዚህ ሕዝብና ለኢየሩሳሌም እንዲህ ተብሎ ይነገራል፤ “ለማበጠር ወይም ለማጥራት ሳይሆን፣ ከዚያ የበረታ የሚጠብስ ደረቅ ነፋስ በምድረ በዳ ካሉት ባድማ ኰረብቶች ወደ ወገኔ ሴት ልጅ በእኔ ትእዛዝ ይነፍሳል፤ እንግዲህ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ።” እነሆ፤ እንደ ደመና ይንሰራፋል፤ ሠረገሎቹ እንደ ዐውሎ ነፋስ ይመጣሉ፤ ፈረሶቹም ከንስር ይፈጥናሉ፤ መጥፋታችን ነውና ወዮልን! ኢየሩሳሌም ሆይ፤ እንድትድኚ ከልብሽ ክፋት ታጠቢ፤ እስከ መቼ ክፉ ሐሳብ በውስጥሽ ይኖራል? ድምፅ ከዳን ይሰማልና፤ ከኤፍሬም ተራሮችም ጥፋትን ያውጃል። “ይህን ለሕዝቦች አሳውቁ፤ ለኢየሩሳሌምም እንዲህ ብላችሁ በይፋ ንገሩ፤ ‘ከብበው የሚያስጨንቁ ከሩቅ አገር ይመጣሉ፤ በይሁዳ ከተሞችም ላይ ይደነፋሉ፤ ሰብል እንደሚጠብቁ ሰዎች ይከቧታል፤ በእኔ ላይ ዐምፃለችና፤’ ” ይላል እግዚአብሔር። “የገዛ መንገድሽና ተግባርሽ፣ ይህን አምጥቶብሻል፤ ይህም ቅጣትሽ ነው፤ ምንኛ ይመርራል! እንዴትስ ልብ ይሰብራል!”
ኤርምያስ 4:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እስራኤል ሆይ፥ ብትመለስ፥ ወደ እኔ ተመለስ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ርኵሰትህንም ከፊቴ ብታስወግድ፥ ባትናወጥም፥ ሕያው እግዚአብሔርን! ብለህም በእውነትና በቅንነት በጽድቅም ብትምል፥ አሕዛብ በእርሱ ይባረካሉ በእርሱም ይመካሉ። እግዚአብሔር ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም ሰዎች እንዲህ ይላልና፦ ጥጋቱን እርሻ እረሱ በእሾህም ላይ አትዝሩ። እናንተም የይሁዳ ሰዎች በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሆይ፥ ስለ ሥራችሁ ክፋት ቍጣዬ እንደ እሳት እንዳይወጣ የሚያጠፋውም ሳይኖር እንዳያቃጥል፥ ለእግዚአብሔር ተገረዙ፥ የልባችሁንም ሸለፈት አስወግዱ። በይሁዳ ዘንድ ተናገሩ በኢየሩሳሌምም ላይ አውሩና፦ በአገሪቱ ላይ መለከት ንፉ በሉ፥ ጮኻችሁም፦ ሁላችሁ ተሰብሰቡ ወደ ተመሸጉትም ከተሞች እንግባ በሉ። ከሰሜን ክፉ ነገርንና ጽኑ ጥፋትን አመጣለሁና ወደ ጽዮን ዓላማን አንሡ፥ ሽሹ፥ አትዘግዩ። አንበሳ ከጭፍቅ ዱር ወጥቶአል፥ አሕዛብንም የሚዘርፍ ተነሥቶአል፥ ምድርሽን ባድማ ያደርግ ዘንድ ከስፍራው ወጥቶአል፥ ከተሞችሽም ሰው የሌለባቸው ፍርስራሾች ይሆናሉ። የእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ ከእኛ ዘንድ አልተመለሰምና ማቅ ልበሱ፥ አልቅሱም ዋይም በሉ። በዚያም ቀን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የንጉሡና የመኳንንቱ ልብ ይጠፋል፥ ካህናቱም ይደነቃሉ ነቢያቱም ይደነግጣሉ። እኔም፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ፥ አንተ ሰይፍ እስከ ነፍስ ድረስ በደረሰ ጊዜ፦ ሰላም ይሆንላችኋል ብለህ ይህን ሕዝብና ኢየሩሳሌምን እጅግ አታለልህ አልሁ። በዚያ ጊዜ ለዚህ ሕዝብና ለኢየሩሳሌም፦ ለማበጠር ወይም ለማጥራት ሳይሆን የሚያቃጥል ነፋስ በምድረ በዳ ካሉ ከወናዎች ኮረብቶች ወደ ወገኔ ሴት ልጅ ይመጣል፥ ስለ እኔ ጽኑ የሆነ ነፋስ ከእነዚህ ይመጣል ይባላል። አሁንም እኔ ደግሞ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ። እነሆ፥ እንደ ደመና ይወጣል፥ ሰረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ፥ ፈረሶቹም ከንስር ይልቅ ፈጣኖች ናቸው። ጠፍተናልና ወዮልን። ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ትድኚ ዘንድ ልብሽን ከክፉ ነገር እጠቢ። ክፉ አሳብ የሚኖርብሽ እስከ መቼ ድረስ ነው? የተናጋሪ ድምፅ ከዳን ዘንድ ይናገራልና፥ ከኤፍሬምም ኮረብቶች መከራን ያወራልና። ለአሕዛብ አሰሙና፦ እነሆ፥ ጠባቂዎች ከሩቅ አገር ይመጣሉ፥ በይሁዳም ከተሞች ላይ ይጮኻሉ ብላችሁ በኢየሩሳሌም ላይ አውሩ። በእኔ ላይ ዓመፀኛ ሆናለችና በዙሪያዋ ከብበው እንደ እርሻ ጠባቂዎች ሆነውባታል፥ ይላል እግዚአብሔር። መንገድሽና ሥራሽ ይህን አድርጎብሻል፥ ይህ ክፋትሽ መራር ነው፥ ወደ ልብሽም ደርሶአል።
ኤርምያስ 4:1-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ወደ እኔ ለመመለስ ከፈለጋችሁ እነዚያን አጸያፊ ጣዖቶችን አስወግዳችሁ ለእኔ ብቻ ታማኞች ብትሆኑ፥ በእውነትና በቅንነት ‘ሕያው እግዚአብሔርን’ ብላችሁ ብትምሉ ሕዝቦች ይባረካሉ፤ በዚህም ይመካሉ።” እግዚአብሔር ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም ሕዝብ እንዲህ ይላል፦ “እዳሪውን መሬት እረሱ፤ ዘራችሁን በሾኽ መካከል አትዝሩ! እናንተ የይሁዳ ሕዝብና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሆይ! የልባችሁን ክፋት ገርዛችሁ አእምሮአችሁን በማንጻት ሁለንተናችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ፤ ይህን ባታደርጉ ግን በክፉ ሥራችሁ ምክንያት ቊጣዬ እንደ እሳት ይነዳል፤ ቊጣዬም ከነደደ ማንም ሊያጠፋው አይችልም።” በምድሪቱ ሁሉ ላይ መለከት ንፉ! ድምፃችሁንም ከፍ አድርጋችሁ ጩኹ! የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ወደተመሸጉ ከተሞች እንዲሸሹ ንገሩአቸው። ለጽዮን መንገዱን አመልክቱአት! ሳትዘገዩ የደኅንነት ዋስትና ወደሚገኝበት ስፍራ ሽሹ! እግዚአብሔር ከሰሜን በኩል መቅሠፍትና ታላቅ ጥፋት ሊያመጣ ነው። አንበሳ ከተሸሸገበት ደን እንደሚወጣ፥ ሕዝብን ሁሉ የሚያጠፋ ይነሣል፤ እርሱም ይሁዳን ለማጥፋት ይመጣል፤ የይሁዳ ከተሞች ይፈራርሳሉ፤ የሚኖርባቸውም አይገኝም። የእግዚአብሔር ብርቱ ቊጣ ከይሁዳ ስላልተለየ፥ ማቅ ለብሳችሁ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በዚያን ቀን ንጉሡና ባለሟሎቹ ፍርሀት ያድርባቸዋል፤ ካህናት ይንቀጠቀጣሉ፤ ነቢያትም ይደነግጣሉ።” እኔም፥ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ማታለል አይሆንብህምን? ‘ሰላም ይሆንላችኋል’ ብለሃቸው ነበር፤ እነሆ አሁን ሰይፍ በአንገታቸው ላይ ተቃጥቶአል” አልኩ። በዚያን ጊዜ ለዚህ ለኢየሩሳሌም ሕዝብ እንዲህ ተብሎ ይነገራቸዋል፥ “በሕዝቤ ላይ የሚያቃጥል ነፋስ በበረሓ ካሉት ኰረብቶች ተነሥቶ ይነፍስባቸዋል፤ ይህም የሚያበጥር ወይም የሚያጠራ ነፋስ አይደለም። በእግዚአብሔር ትእዛዝ የሚመጣ ነፋስ ስለ ሆነ ከሁሉ የበረታ ነው፤ ይህን ፍርድ በሕዝቡ ላይ የሚያስተላልፍ ራሱ እግዚአብሔር ነው።” “እነሆ የጠላት ሠራዊት እንደ ደመና አንዣቦአል፤ የጦር ሠረገሎቹ እንደ ዐውሎ ነፋስ ፈጣኖች ናቸው፤ ፈረሶቹም ከንስር ይበልጥ ይበራሉ፤ ለእኛ ወዮልን! ጠፍተናል! “ኢየሩሳሌም ሆይ! መዳን ከፈለግሽ ክፋትን ሁሉ ከልብሽ አጥበሽ አስወግጂ፤ ለመሆኑ የኃጢአት ሐሳብ ከአእምሮሽ የማይጠፋው እስከ መቼ ነው? “ከዳን ከተማና ከኤፍሬም ኰረብቶች ክፉ አዋጅ የሚያውጅ ድምፅ ይሰማል፤ በይሁዳ ከተሞች ላይ ጦርነትን እያወጁ ወራሪዎች ከሩቅ አገር በመምጣት ላይ መሆናቸውን ለሕዝቦች አሳውቁ! ለኢየሩሳሌም ሕዝብም ንገሩ! ሕዝብዋ በእግዚአብሔር ላይ ስለ ዐመፁ፥ እንደ መከር እህል ጠባቂ ኢየሩሳሌምን ጠላት ይከባታል፤” ይህን የተናገረ እግዚአብሔር ነው። ይሁዳ ሆይ! ይህ ሁሉ የደረሰብሽ በአካሄድሽና በክፉ ሥራሽ ምክንያት ነው፤ ይህም ሁሉ የመረረ መከራ የመጣብሽ በኃጢአትሽ ምክንያት ስለ ሆነ ወደ ሰውነትሽ ዘልቆ ልብሽን አቊስሎታል።
ኤርምያስ 4:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“እስራኤል ሆይ! ብትመለስ፥ ወደ እኔ ተመለስ፥ ይላል ጌታ፤ ርኩሰትህንም ከፊቴ ብታስወግድ፥ ባትናወጥም፥ ‘በሕያው ጌታ እምላለሁ!’ ብለህም በእውነትና በቅንነት በጽድቅም ብትምል፥ አሕዛብ እራሳቸውን በእርሱ ይባርካሉ በእርሱም ይመካሉ።” ጌታ ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም ሰዎች እንዲህ ይላልና፦ “ያልታረሰ መሬታችሁን እረሱ በእሾህም ላይ አትዝሩ። እናንተም የይሁዳ ሰዎች በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሆይ! ስለ ሥራችሁ ክፋት ቁጣዬ እንደ እሳት እንዳይወጣ የሚያጠፋውም ሳይኖር እንዳያቃጥል፥ ለጌታ እራሳችሁን ግረዙ፥ የልባችሁንም ሸለፈት አስወግዱ።” በይሁዳ ላይ ተናገሩ በኢየሩሳሌምም ላይ አውጁ፦ “በአገሪቱ ላይ መለከት ንፉ በሉ፤ ጮኻችሁም፦ ‘ሁላችሁ ተሰብሰቡ ወደ ተመሸጉትም ከተሞች እንግባ’ በሉ። ከሰሜን ክፉ ነገርንና ጽኑ ጥፋትን አመጣለሁና ወደ ጽዮን ዓላማን አንሡ፤ ሽሹ፥ አትዘግዩ። አንበሳ ከችፍግ ዱሩ ወጥቶአል፥ አሕዛብንም የሚያጠፋ ተነሥቶአል፤ ምድርሽን ባድማ ለማድረግ ከስፍራው ወጥቶአል፥ ከተሞችሽም ሰው የሌለባቸው ፍርስራሾች ይሆናሉ። የጌታ ጽኑ ቁጣ ከእኛ ላይ አልተመለሰምና ማቅ ልበሱ፥ አልቅሱም ዋይም በሉ።” “በዚያም ቀን፥ ይላል ጌታ፥ የንጉሡና የመኳንንቱ ልብ ይጠፋል፥ ካህናቱም ይሣቀቃሉ ነቢያቱም ይደነግጣሉ።” እኔም፦ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ወዮ፥ አንተ በእውነት ሰይፍ እስከ ነፍስ ድረስ በደረሰ ጊዜ፦ ‘ሰላም ይሆንላችኋል’ ብለህ ይህን ሕዝብና ኢየሩሳሌምን እጅግ አታለልህ” አልሁ። በዚያ ጊዜ ለዚህ ሕዝብና ለኢየሩሳሌም፦ “ለማበጠር ወይም ለማጥራት ሳይሆን የሚያቃጥል ነፋስ በምድረ በዳ ካሉ ከተራቈቱ ኮረብቶች ወደ ወገኔ ሴት ልጅ ይመጣል፤ ስለ እኔ ጽኑ የሆነ ነፋስ ከእነዚህ ይመጣል ይባላል። አሁንም እኔ ደግሞ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ።” እነሆ፥ እንደ ደመና ይወጣል፥ ሰረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ፤ ፈረሶቹም ከንስር ይልቅ ፈጣኖች ናቸው። ጠፍተናልና ወዮልን! ኢየሩሳሌም ሆይ! እንድትድኚ ልብሽን ከክፉ ነገር እጠቢ። ክፉ ሐሳብ በውስጥሽ የሚኖርብሽ እስከ መቼ ድረስ ነው? የተናጋሪ ድምፅ ከዳን ይናገራልና፥ ከኤፍሬምም ኮረብቶች መከራን ያውጃል። ለአሕዛብ አሳውቁ፦ “እነሆ፥ ጠባቂዎች ከሩቅ አገር ይመጣሉ፤ በይሁዳም ከተሞች ላይ ይጮኻሉ ብላችሁ በኢየሩሳሌም ላይ አውጁ። በእኔ ላይ ዓመፀኛ ሆናለችና በዙሪያዋ ከብበው እንደ እርሻ ጠባቂዎች ሆነውባታል፥ ይላል ጌታ። መንገድሽና ሥራሽ ይህን አድርጎብሻል፤ ይህ ክፋትሽ መራር ነው፥ ወደ ልብሽም ደርሶአል።”