ኤርምያስ 29:7-13
ኤርምያስ 29:7-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በእርስዋ ሰላም፥ ሰላም ይሆንላችኋልና ወደ እርስዋ ላስማረክኋችሁ ሀገር ሰላምን ፈልጉ፥ ስለ እርስዋም ወደ እግዚአብሔር ጸልዩ።” የእስራኤልም አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፥ “በመካከላችሁ ያሉት የሐሰት ነቢያቶቻችሁና ምዋርተኞቻችሁ አያታልሉአችሁ፤ ሕልም አላሚዎች አለምንላችሁ የሚሉአችሁን አትስሙ፥ በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ይናገሩላችኋልና፤ እኔም አልላክኋቸውም፥” ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ሰባው ዓመት በባቢሎን በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ፥ ወደዚህም ስፍራ እመልሳችሁ ዘንድ መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ። ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ ይላል እግዚአብሔር፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። እናንተም ትጠሩኛላችሁ፤ ሄዳችሁም ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፤ እኔም እሰማችኋለሁ። እናንተ ትሹኛላችሁ፤ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ።
ኤርምያስ 29:7-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ተማርካችሁ ለሄዳችሁባት ከተማ ሰላምና ብልጽግናን እሹ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸልዩላት፤ ምክንያቱም እርሷ ብትበለጽግ እናንተም ትበለጽጋላችሁ።” የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በርግጥ እንዲህ ይላልና፤ “በመካከላችሁ ያሉት ነቢያትና ጠንቋዮች አያታልሏችሁ፤ የሚያልሙላችሁንም ሕልም አትስሙ፤ በስሜ ሐሰተኛ ትንቢት ይነግሯችኋል እንጂ እኔ አልላክኋቸውም” ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሰባው ዓመት የባቢሎን ቈይታችሁ በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ፤ ወደዚህም ሥፍራ ልመልሳችሁ የገባሁላችሁን መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ። ለእናንተ ያለኝን ዕቅድ እኔ ዐውቃለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ዕቅዱም ፍጻሜው ያማረና ተስፋ የሚሰጥ፣ እናንተንም የሚጠቅም እንጂ የሚጐዳ አይደለም። እናንተም ትጠሩኛላችሁ፤ ቀርባችሁ ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፤ እኔም እሰማችኋለሁ። እናንተ ትፈልጉኛላችሁ፤ በፍጹም ልባችሁም ከፈለጋችሁኝ ታገኙኛላችሁ፤
ኤርምያስ 29:7-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በእርስዋ ሰላም ሰላም ይሆንላችኋልና ወደ እርስዋ ላስማርክኋችሁ ከተማ ሰላምን ፈልጉ፥ ስለ እርስዋም ወደ እግዚአብሔር ጸልዩ። የእስራኤልም አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ በመካከላችሁ ያሉት ነቢያቶቻችሁና ምዋርተኞቻችሁ አያታልሉአችሁ፥ እናንተም የምታልሙትን ሕልም አትስሙ። በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ይናገሩላችኋልና፥ እኔም አልላክኋቸውም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ሰባው ዓመት በባቢሎን በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ፥ ወደዚህም ስፍራ እመልሳችሁ ዘንድ መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ። ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፥ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። እናንተም ትጠሩኛለችሁ፥ ሄዳችሁም ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፥ እኔም እሰማችኋለሁ። እናንተ ትሹኛላችሁ፥ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ።
ኤርምያስ 29:7-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ተማርካችሁ ሄዳችሁ እንድትኖሩባቸው ላደረግኋቸው ከተሞችም ዕድገት መልካም ነገርን ተመኙ፤ ስለ እነርሱም መልካም ኑሮ ወደ እኔ ጸልዩ፤ እነርሱ መልካም ኑሮ ቢኖሩ እናንተም መልካም ኑሮን ትኖራላችሁ። እኔ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ በመካከላችሁ በሚኖሩ ነቢያት ወይም የወደፊቱን ሁኔታ እናውቃለን በሚሉ ሰዎች ሁሉ እንዳትታለሉ አስጠነቅቃችኋለሁ፤ ለሕልሞቻቸውም ትኲረት አትስጡአቸው። እነርሱ በእኔ ስም የሚነግሩአችሁ ትንቢት ሁሉ ሐሰት ነው፤ እኔ ከቶ አላክኋቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።’ ” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በባቢሎን የምትኖሩበት ሰባው ዓመት ከተፈጸመ በኋላ እንደገና እናንተን በምሕረት እጐበኛለሁ፤ ወደ አገራችሁ እንድመልሳችሁ የገባሁትን ቃል ኪዳን እፈጽማለሁ፤ ስለ እናንተ ያለኝን ዕቅድ የማውቅ እኔ ነኝ፤ ይህም ዕቅድ ክፋትን ሳይሆን ሰላምን በማስገኘት እናንተ በተስፋ የምትጠብቁት መልካም ነገር የሚፈጸምበት ነው፤ ከዚያን በኋላ እናንተ ትጠሩኛላችሁ፤ ወደ እኔም ቀርባችሁ ትጸልያላችሁ፤ እኔም እሰማችኋለሁ፤ ትፈልጉኛላችሁ፤ የምትፈልጉኝም በሙሉ ልባችሁ ከሆነ ታገኙኛላችሁ፤
ኤርምያስ 29:7-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በእርሷ ሰላም ሰላም ይሆንላችኋልና እናንትን አስማርኬ ያፈለስኩባትን ከተማ ሰላም ፈልጉ፥ ስለ እርሷም ወደ ጌታ ጸልዩ። የእስራኤልም አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላልና፦ በመካከላችሁ ያሉት ነብዮቻችሁና ምዋርተኞቻችሁ አያታልሉአችሁ፥ እናንተም የምታልሙትን ሕልም አትስሙ። በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ለእናንተ ይናገራሉ፤ እኔም አላክኋቸውም፥ ይላል ጌታ። “ጌታ እንዲህ ይላልና፦ ሰባው ዓመት በባቢሎን በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ፥ ወደዚህችም ስፍራ እናንተን በመመለስ መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ። ለእናንተ የማስበውን አሳብ እኔ ጠንቅቄ አውቃለሁ፥ ይላል ጌታ፤ ለወደፊት የሠመረ ጊዜና ተስፋ ልሰጣችሁ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። እናንተም ትጠሩኛለችሁ፤ ሄዳችሁም ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፤ እኔም እሰማችኋለሁ። እናንተ ትሹኛላችሁ፥ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ።