ትንቢተ ኤርምያስ 29

29
በባቢሎን ምርኮ ላሉት የነቢዩ ኤርምያስ ደብዳቤ
1 # 2ነገ. 24፥12-16፤ 2ዜ.መ. 36፥10። ነቢዩ ኤርምያስ ተማርከው ወደ ተረፉት ሽማግሌዎች፥ ወደ ካህናቱም፥ ወደ ነቢያቱም፥ ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ማርኮ ወዳፈለሰውም ሕዝብ ሁሉ ከኢየሩሳሌም የላከው የደብዳቤው ቃላት ይህ ነው። 2ይህም የሆነው ንጉሡ ኢኮንያን እናቱም እቴጌይቱና ጃንደረቦቹም፥ የይሁዳና የኢየሩሳሌምም አለቆች፥ ጠራቢዎችና ብረት ሠራተኞችም ከኢየሩሳሌም ከወጡ በኋላ ነው። 3ኤርምያስ የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወደ ናቡከደነፆር ወደ ባቢሎን በላካቸው በሳፋን ልጅ በኤልዓሣና በኬልቅያስ ልጅ በገማርያ እጅ ደብዳቤውን ላከው፤ እንዲህም የሚል ነበር፦ 4የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ላስማረክኋቸው ምርኮኞች ሁሉ እንዲህ ይላል፦ 5ቤቶችን ሠርታችሁ ተቀመጡ፤ አታክልትም ትከሉ፤ ፍሬዋንም ብሉ፤ 6ተጋቡ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ውለዱ፤ ሴቶች ልጆቻችሁንም ለወንዶች ልጆቻችሁ አጋቡ፥ እነርሱም ወንዶችንና ሴቶችን ልጆች ይውለዱ፤ በዚያም ተባዙ ጥቂቶችም አትሁኑ። 7በእርሷ ሰላም ሰላም ይሆንላችኋልና እናንትን አስማርኬ ያፈለስኩባትን ከተማ ሰላም ፈልጉ፥ ስለ እርሷም ወደ ጌታ ጸልዩ። 8የእስራኤልም አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላልና፦ በመካከላችሁ ያሉት ነብዮቻችሁና ምዋርተኞቻችሁ አያታልሉአችሁ፥ እናንተም የምታልሙትን ሕልም አትስሙ። 9በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ለእናንተ ይናገራሉ፤ እኔም አላክኋቸውም፥ ይላል ጌታ። 10#2ዜ.መ. 36፥21፤ ኤር. 25፥11፤ ዳን. 9፥2።“ጌታ እንዲህ ይላልና፦ ሰባው ዓመት በባቢሎን በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ፥ ወደዚህችም ስፍራ እናንተን በመመለስ መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ። 11ለእናንተ የማስበውን አሳብ እኔ ጠንቅቄ አውቃለሁ፥ ይላል ጌታ፤ ለወደፊት የሠመረ ጊዜና ተስፋ ልሰጣችሁ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። 12እናንተም ትጠሩኛለችሁ፤ ሄዳችሁም ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፤ እኔም እሰማችኋለሁ። 13#ዘዳ. 4፥29፤ ጥበ. 6፥12፤13።እናንተ ትሹኛላችሁ፥ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ። 14ከእናንተም ዘንድ ታገኙኛላችሁ፥ ይላል ጌታ፤ ምርኮአችሁንም እመልሳለሁ፥ ከአሕዛብም ሁሉ ዘንድ እናንተንም ካሳደድሁበት ስፍራ ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ፤ እናንተንም ለምርኮ ካፈለስሁበት ስፍራ እመልሳችኋለሁ።
15“እናንተም፦ ‘ጌታ በባቢሎን ነቢያትን አስነሥቶልናል’ ብላችኋልና፤ 16በዳዊት ዙፋን ላይ ስለ ተቀመጠው ንጉሥ፥ ከእናንተም ጋር ተማርከው ስላልሄዱት ወንድሞቻችሁ፥ በዚህች ከተማ ስለሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ፥ ጌታ እንዲህ ይላልና፦ 17‘የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ሰይፍንና ራብን ቸነፈርንም በመካከላቸው እልክባቸዋለሁ፥ ከክፋቱም የተነሣ ሊበላ እንደማይችል እንደ ተበላሸ በለስ አደርጋቸዋለሁ። 18በሰይፍም በራብም በቸነፈርም አሳዳድዳቸዋለሁ፤ ባሳደድኋቸውም አሕዛብ ሁሉ መካከል ለመረገሚያና ለመሣቀቂያ ለማፍዋጫም ለመሰደቢያም ይሆናሉ፤ በምድር መንግሥታትም ሁሉ ዘንድ ለድንጋጤ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ። 19ይህም የሆነው ቃሎቼን ስላልሰሙ ነው፥ ይላል ጌታ፤ በማለዳ ተነሥቼ ባርያዎቼን ነቢያትን ወደ እነርሱ በተደጋጋሚ ላኩኝ፤ እናንተ ግን አልሰማችሁም፥ ይላል ጌታ።’ 20ስለዚህ እናንተ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ያፈለስኋችሁ ምርኮኞች ሁሉ ሆይ! የጌታን ቃል ስሙ፦ 21‘በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ስለሚነግሩአችሁ፥ ስለ ቆላያ ልጅ ስለ አክዓብና ስለ መዕሤያ ልጅ ስለ ሴዴቅያስ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፥ በዐይኖቻችሁም ፊት ይገድላቸዋል። 22ከእነርሱም የተነሣ በባቢሎን ያሉ የይሁዳ ምርኮኞች ሁሉ ይህን እርግማን ይጠቀማሉ፥ እንዲህም ይላሉ፦ “የባቢሎን ንጉሥ በእሳት እንደ ጠበሳቸው እንደ ሴዴቅያስና እንደ አክዓብ ጌታ ያድርግህ፥” 23በእስራኤል ዘንድ አሳፋሪ ነገር አድርገዋልና፤ ከባልንጀሮቻቸውም ሚስቶች ጋር አመንዝረዋልና፤ ያላዘዝኋቸውንም ቃል በስሜ በሐሰት ተናግረዋልና፤ እኔም አውቀዋለሁ ምስክርም ነኝ፥ ይላል ጌታ።’ ”
የሸማያ ደብዳቤ
24ለኔሔላማዊው ለሸማያ እንዲህ በል፦ 25“የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ በኢየሩሳሌም ወዳለው ሕዝብ ሁሉ፥ ወደ ካህኑም ወደ መዕሤያ ልጅ ወደ ሶፎንያስ፥ ወደ ካህናቱም ሁሉ ደብዳቤዎችን በስምህ እንዲህ ስትል ልከሃል፦ 26‘በጌታ ቤት አለቃ ሆነህ እያበደ ትንቢት የሚናገርን ሰው ሁሉ በመንቈርና በዛንጅር#29፥26 የአንገት ሰንሰለት አስረህ እንድታኖረው ጌታ በካህኑ በዮዳሄ ፋንታ ካህን አድርጎሃል። 27አሁንስ ትንቢት የሚነግራችሁን የዓናቶቱን ሰው ኤርምያስን ለምን አልገሠጽከውም? 28እርሱ፦ “ለረጅም ጊዜ በምርኮ ስለምትቆዩ ቤቶችን ሠርታችሁ ተቀመጡ፥ አታክልትንም ተክላችሁ ፍሬዋን ብሉ” ብሎ ወደ እኛ ወደ ባቢሎን ልኮአልና።’ ” 29ካህኑም ሶፎንያስ ይህን ደብዳቤ በነቢዩ በኤርምያስ ጆሮ አነበበው። 30የጌታም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 31“ወደ ተማረኩት ሁሉ እንዲህ ብለህ ላክ፦ ‘ስለ ኔሔላማዊው ስለ ሸማያ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ እኔ ሳልልከው ሸማያ ትንቢት ተናግሮላችኋልና፥ በሐሰትም እንድትታመኑ አድርጎአችኋልና፥ 32ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ኔሔላማዊውን ሸማያንና ዘሩን እቀጣለሁ፤ በጌታ ላይ ዓመፅን ተነናግሯአልና ከእርሱ ዘር በዚህ ሕዝብ መካከል ተቀምጦ፥ እኔ ለሕዝቤ የማደርገውን መልካም ነገር የሚያይ ማንም አይኖርም፥ ይላል ጌታ።’ ”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ