የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መሳፍንት 6:11-27

መሳፍንት 6:11-27 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም መል​አክ መጥቶ በኤ​ፍ​ራታ ባለ​ችው ለኤ​ዝሪ አባት ለኢ​ዮ​አስ በነ​በ​ረ​ችው ዛፍ በታች ተቀ​መጠ፤ ልጁም ጌዴ​ዎን ከም​ድ​ያ​ማ​ው​ያን ለማ​ሸሽ በወ​ይን መጭ​መ​ቂ​ያው ውስጥ ስንዴ ይወቃ ነበር። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም መል​አክ ለእ​ርሱ ተገ​ልጦ፥ “አንተ ጽኑዕ ኀያል ሰው! እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከአ​ንተ ጋር ነው” አለው። ጌዴ​ዎ​ንም፥ “ጌታዬ ሆይ! እሺ፥ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረ​ሰ​ብን? አባ​ቶ​ቻ​ች​ንስ፦ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከግ​ብፅ አው​ጥ​ቶ​ናል ብለው ይነ​ግ​ሩን የነ​በረ ተአ​ም​ራት ወዴት አለ? አሁን ግን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ትቶ​ናል፤ በም​ድ​ያም እጅም አሳ​ልፎ ሰጥ​ቶ​ናል” አለው። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም መል​አክ ወደ እርሱ ተመ​ለ​ከ​ተና፥ “በዚህ በጕ​ል​በ​ትህ ሂድ፤ እስ​ራ​ኤ​ል​ንም ከም​ድ​ያም እጅ ታድ​ና​ቸ​ዋ​ለህ፤ እነሆ፥ ልኬ​ሃ​ለሁ” አለው። እር​ሱም፥ “ጌታ ሆይ! እሺ፥ እስ​ራ​ኤ​ልን በምን አድ​ና​ለሁ? ወገኔ በም​ናሴ ነገድ ዘንድ ጥቂ​ቶች ናቸው፤ እኔም በአ​ባቴ ቤት የሁሉ ታናሽ ነኝ” አለው። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም መል​አክ፥ “እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከአ​ንተ ጋር ነው፤ ምድ​ያ​ም​ንም እንደ አንድ ሰው አድ​ር​ገህ ታጠ​ፋ​ለህ” አለው። ጌዴ​ዎ​ንም፥ “በፊ​ትህ ሞገ​ስን ካገ​ኘሁ፥ የም​ት​ና​ገ​ረ​ኝም አንተ እንደ ሆንህ ምል​ክት አድ​ር​ግ​ልኝ፤ ወደ አን​ተም እስ​ክ​መ​ለስ ድረስ፥ መሥ​ዋ​ዕ​ቴ​ንም አም​ጥቼ እስ​ካ​ቀ​ር​ብ​ልህ ድረስ፥ እባ​ክህ፥ ከዚህ አት​ሂድ” አለው። እር​ሱም፥ “እስ​ክ​ት​መ​ለስ ድረስ እቈ​ያ​ለሁ” አለው። ጌዴ​ዎ​ንም ሄደ፤ የፍ​የ​ሉ​ንም ጠቦት፥ የኢፍ መስ​ፈ​ሪ​ያም ዱቄት የቂጣ እን​ጎቻ አዘ​ጋጀ፤ ሥጋ​ው​ንም በሌ​ማት አኖረ፤ መረ​ቁ​ንም በም​ን​ቸት ውስጥ አደ​ረገ፤ ሁሉ​ንም ይዞ በዛፍ በታች አቀ​ረ​በ​ለት። ሰገ​ደ​ለ​ትም። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም መል​አክ፥ “ሥጋ​ው​ንና የቂ​ጣ​ውን እን​ጎቻ ወስ​ደህ በዚህ ድን​ጋይ ላይ አኑር፤ መረ​ቁ​ንም አፍ​ስስ” አለው። እን​ዲ​ሁም አደ​ረገ። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም መል​አክ በእጁ ያለ​ውን በት​ሩን ዘር​ግቶ ሥጋ​ዉ​ንና የቂ​ጣ​ዉን እን​ጎቻ አስ​ነካ፤ እሳ​ትም ከድ​ን​ጋዩ ውስጥ ወጥታ ሥጋ​ዉ​ንና የቂ​ጣ​ዉን እን​ጎቻ በላች። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም መል​አክ ከዐ​ይ​ኖቹ ተሰ​ወረ። ጌዴ​ዎ​ንም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መል​አክ እንደ ሆነ ዐወቀ። ጌዴ​ዎ​ንም፥ “አቤቱ! አም​ላኬ ሆይ! ወዮ​ልኝ፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን መል​አክ ፊት ለፊት አይ​ቻ​ለ​ሁና” አለ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም፥ “ሰላም ለአ​ንተ ይሁን፤ አት​ፍራ፤ አት​ሞ​ትም” አለው። ጌዴ​ዎ​ንም በዚያ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መሠ​ዊያ ሠራ፤ ስሙ​ንም እስከ ዛሬ ድረስ “የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሰላም” ብሎ ጠራው። እር​ሱም እስከ ዛሬ ድረስ ለኤ​ዝሪ አባት በሆ​ነ​ችው በኤ​ፍ​ራታ አለ። እን​ዲ​ህም ሆነ፤ በዚ​ያች ሌሊት እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር፥ “የአ​ባ​ት​ህን በሬ፥ ሰባት ዓመት የሆ​ነ​ውን ሁለ​ተ​ኛ​ውን በሬ ውሰድ፤ የአ​ባ​ትህ የሆ​ነ​ው​ንም የበ​ዓል መሠ​ዊያ አፍ​ርስ፤ በእ​ር​ሱም ዙሪያ ያለ​ውን የማ​ም​ለ​ኪያ ዐጸድ ቍረጥ፤ በዚ​ያም ተራራ አናት ላይ ለአ​ም​ላ​ክህ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መሠ​ዊያ አሳ​ም​ረህ ሥራ፤ ሁለ​ተ​ኛ​ዉ​ንም በሬ ውሰድ፤ በዚ​ያም በቈ​ረ​ጥ​ኸው በማ​ም​ለ​ኪያ ዐጸዱ እን​ጨት ላይ የሚ​ቃ​ጠ​ለ​ውን መሥ​ዋ​ዕት አቅ​ርብ” አለው። ጌዴ​ዎ​ንም ከባ​ሪ​ያ​ዎቹ ዐሥራ ሦስት ሰዎ​ችን ወስዶ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዳ​ለው አደ​ረገ፤ የአ​ባ​ቱ​ንም ቤተ ሰቦች፥ የከ​ተ​ማ​ዉ​ንም ሰዎች ስለ​ፈራ ይህን በቀን ለማ​ድ​ረግ አል​ቻ​ለም፤ ነገር ግን በሌ​ሊት አደ​ረ​ገው።

መሳፍንት 6:11-27 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የእግዚአብሔር መልአክ ዖፍራ ወደምትባል መንደር መጥቶ፣ በአቢዔዝራዊው በኢዮአስ ዕርሻ ውስጥ በሚገኝ በአንድ የባሉጥ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፤ የኢዮአስም ልጅ ጌዴዎን፣ ምድያማውያን እንዳያዩበት ደብቆ በወይን መጭመቂያው ስፍራ ስንዴውን ይወቃ ነበር። የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ፣ “አንተ ኀያል ጦረኛ እነሆ፤ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው” አለው። ጌዴዎን መልሶ፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ሁሉ እንዴት ሊደርስብን ቻለ? ‘እግዚአብሔር ከግብፅ ምድር አውጥቶናል’ በማለት አባቶቻችን የነገሩን ታምራት የት አለ? አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል፤ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል” አለው። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ወደ እርሱ ዘወር ብሎ፣ “ሂድ፤ ባለህ ኀይል እስራኤላውያንን ከምድያማውያን እጅ ነጻ እንድታወጣ የምልክህ እኔ አይደለሁምን?” አለው። ጌዴዎንም፣ “ጌታ ሆይ፤ የእኔ ጐሣ ከምናሴ ነገድ እጅግ ደካማ ነው፤ ከቤተ ሰቤም እኔ የመጨረሻ ነኝ፤ ታዲያ እንዴት እኔ እስራኤልን ላድን እችላለሁ?” አለ። እግዚአብሔርም፣ “በርግጥ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ ምድያማውያንንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታቸዋለህ” አለው። ጌዴዎን እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “አሁን በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ በርግጥ የምታነጋግረኝ አንተ ራስህ ለመሆንህ ምልክት ስጠኝ፤ ተመልሼ እስክመጣ፣ መሥዋዕቴንም አምጥቼ በፊትህ እስካቀርብ ድረስ እባክህ አትሂድ።” እግዚአብሔርም፣ “እስክትመለስ እጠብቅሃለሁ” አለው። ጌዴዎን ወደ ቤቱ ሄደ፤ የፍየል ጠቦትም ዐረደ፤ አንድ ኢፍ መስፈሪያ ዱቄት ወስዶ እርሾ ያልገባበት ቂጣ ጋገረ። ሥጋውን በቅርጫት፣ መረቁን በምንቸት ይዞ በመምጣት በባሉጥ ሥር ለተቀመጠው አቀረበለት። የእግዚአብሔር መልአክ፣ “ሥጋውንና ዕርሾ ያልገባበትን ቂጣ ወስደህ፣ በዚያ ዐለት ላይ አኑር፤ መረቁንም በሥጋውና በቂጣው ላይ አፍስስ” አለው፤ ጌዴዎንም እንደ ታዘዘው አደረገ። መልአኩም በያዘው በትር ጫፍ ሥጋውንና ቂጣውን ነካ፤ ከዐለቱም እሳት ወጥቶ ሥጋውንና ቂጣውን በላ፤ ከዚያም የእግዚአብሔር መልአክ ተሰወረ። ጌዴዎን ያየው የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን ባወቀ ጊዜ፣ “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና ወዮልኝ” አለ። እግዚአብሔርም፣ “ሰላም ለአንተ ይሁን፤ አትፍራ፤ አትሞትም” አለው። ጌዴዎንም በዚያ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ ስሙንም “እግዚአብሔር ሰላም ነው” ብሎ ጠራው፤ ይህ መሠዊያ የአቢዔዝራውያን ይዞታ በሆነው በዖፍራ ዛሬም ቆሞ ይታያል። በዚያች ሌሊት እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “ከአባትህ መንጋ ሰባት ዓመት የሆነውን ሁለተኛውን ወይፈን ውሰድ፤ አባትህ ለበኣል የሠራውን መሠዊያ አፍርስ፤ በአጠገቡ የአሼራን ዐምድ ሰባብረህ ጣል። በዚህ ፍርስራሽ ጕብታ ላይ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የሚገባውን መሠዊያ ሥራ። ሰባብረህ በጣልኸው የአሼራ ምስል ዐምድ ሁለተኛውን ወይፈን ወስደህ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ አቅርበው።” ጌዴዎን ከአገልጋዮቹ ዐሥር ሰዎች ወስዶ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ቤተ ሰቡንና የከተማውን ሰው ስለ ፈራ ይህን ያደረገው ቀን ሳይሆን ሌሊት ነበር።

መሳፍንት 6:11-27 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

የእግዚአብሔርም መልአክ መጥቶ በዖፍራ ባለችው ለአቢዔዝራዊው ለኢዮአስ በነበረችው በአድባሩ ዛፍ በታች ተቀመጠ፥ ልጁም ጌዴዎን ከምድያማውያን ለመሸሸግ በወይን መጠመቂያው ውስጥ ስንዴ ይወቃ ነበር። የእግዚአብሔርም መልአክ ለእርሱ ተገልጦ፦ አንተ ጽኑዕ ኃያል ሰው፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው አለው። ጌዴዎንም፦ ጌታዬ ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረሰብን? አባቶቻችንስ፦ እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶናል ብለው ይነግሩን የነበረ ተአምራቱ ወዴት አለ? ወዴት አለ? አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል፥ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል አለው። እግዚአብሔርም ወደ እርሱ ዘወር ብሎ፦ በዚህ በጉልበትህ ሂድ፥ እስራኤልንም ከምድያም እጅ አድን፥ እነሆ፥ ልኬሃለሁ አለው። እርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ እስራኤልን በምን አድናለሁ? ወገኔ ከምናሴ ነገድ ከሁሉ ይልቅ የተጠቃ ነው፥ እኔም በአባቴ ቤት የሁሉ ታናሽ ነኝ አለው። እግዚአብሔርም፦ በእርግጥ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ ምድያምንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታለህ አለው። እርሱም፦ በአንተ ዘንድ ሞገስ ካገኘሁ፥ የምትናገረኝም አንተ እንደ ሆንህ ምልክት አሳየኝ፥ ወደ አንተም እስክመለስ ድረስ፥ ቁርባኔንም አምጥቼ እስካቀርብልህ ድረስ፥ እባክህ፥ ከዚህ አትላወስ አለው። እርሱም፦ እስክትመለስ ድረስ እቆያለሁ አለ። ጌዴዎን ገባ የፍየሉንም ጠቦት የኢፍ መስፈሪያም ዱቄት የቂጣ እንጎቻ አዘጋጀ፥ ሥጋውን በሌማት አኖረ፥ መረቁንም በምንቸት ውስጥ አደረገ፥ ሁሉንም ይዞ በአድባሩ ዛፍ በታች አቀረበለት። የእግዚአብሔርም መልአክ፦ ሥጋውንና የቂጣውን እንጎቻ ወስደህ በዚህ ድንጋይ ላይ አኑር፥ መረቁንም አፍስስ አለው። እንዲሁም አደረገ። የእግዚአብሔርም መልአክ በእጁ ያለውን የበትሩን ጫፍ ዘርግቶ ሥጋውንና የቂጣውን እንጎቻ አስነካ፥ እሳትም ከድንጋዩ ውስጥ ወጥቶ ሥጋውንና የቂጣውን እንጎቻ በላ። የእግዚአብሔርም መልአክ ከዓይኑ ተሰወረ። ጌዴዎንም የእግዚአብሔር መልአክ እንደ ሆነ አየ፥ ጌዴዎንም፦ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ ወዮልኝ፥ የእግዚአብሔርን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና አለ። እግዚአብሔርም፦ ሰላም ለአንተ ይሁን፥ አትፍራ፥ አትሞትም አለው። ጌዴዎንም በዚያ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፥ ስሙንም፦ እግዚአብሔር ሰላም ብሎ ጠራው። እርሱም እስከ ዛሬ ድረስ ለአቢዔዝራውያን በምትሆነው በዖፍራ አለ። እግዚአብሔርም በዚያ ሌሊት፦ የአባትህን በሬ፥ ሰባት ዓመት የሆነውን ሁለተኛውን በሬ፥ ውሰድ፥ የአባትህ የሆነውንም የበኦል መሠዊያ አፍርስ፥ በእርሱም ዙሪያ ያለውን የማምለኪያ ዐፀድ ቍረጥ፥ በዚያም ኮረብታ አናት ላይ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር መሠዊያ አሳምረህ ሥራ ሁለተኛውንም በሬ ውሰድ፥ በዚያም በቈረጥኸው በማምለኪያ ዐፀዱ እንጨት ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቅርብ አለው። ጌዴዎንም ከባሪያዎቹ አሥር ሰዎችን ወስዶ እግዚአብሔር እንዳለው አደረገ፥ የአባቱን ቤተ ሰቦች የከተማውንም ሰዎች ስለ ፈራ ይህን በቀን ለማድረግ አልቻለም፥ ነገር ግን በሌሊት አደረገው።

መሳፍንት 6:11-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ “ዖፍራ” ተብላ ወደምትጠራው መንደር መጥቶ ከአቢዔዜር ጐሣ የተወለደው የኢዮአስ ንብረት በሆነው የወርካ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፤ የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን ምድያማውያን እንዳያዩት ተሸሽጎ በወይን መጭመቂያው ስፍራ የስንዴ ነዶ ይወቃ ነበር። በዚያም የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና “አንተ ኀያልና ብርቱ ሰው! እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው” አለው። ጌዴዎንም እንዲህ አለው፦ “ጌታዬ ሆይ! ታዲያ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ሁሉ ችግር እንዴት ሊደርስብን ቻለ? አባቶቻችን እንደ ነገሩን እግዚአብሔር ያደርገው የነበረ ድንቅ ሥራ ሁሉ ዛሬ የት አለ? ከግብጽ እንዴት እንዳወጣቸውም ነግረውን ነበር፤ ዛሬ ግን እግዚአብሔር እኛን በመተው እንደ ፈለጉ ያደርጉን ዘንድ ለምድያማውያን አሳልፎ ሰጥቶናል።” ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “ሂድ፤ በዚህ ባለህ ብርቱ ኀይል ሁሉ በመጠቀም እስራኤላውያንን ከምድያማውያን እጅ ነጻ አውጣ፤ እነሆ እኔ ራሴ ልኬሃለሁ” ሲል አዘዘው። ጌዴዎንም “ታዲያ እኔ እንዴት አድርጌ እስራኤልን ላድን እችላለሁ? ወገኔም ከምናሴ ነገድ መካከል እጅግ ደካማ ነው፤ እኔም ከቤተሰቤ መካከል በጣም አነስተኛ ነኝ” ሲል መለሰ። እግዚአብሔርም “እኔ ስለምረዳህ ይህን ማድረግ ትችላለህ፤ ምድያማውያንንም እንደ አንድ ሰው ያኽል አድርገህ ታደቃቸዋለህ” አለው። ጌዴዎንም “በአንተ ዘንድ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፥ አንተ በእርግጥ እግዚአብሔር መሆንህን የሚያስረዳ ምልክት ስጠኝ፤ ምግብ የሚሆን ቊርባን እስካመጣልህም ድረስ እባክህ ከዚህ ስፍራ አትሂድ” አለው። እግዚአብሔርም “አንተ እስክትመለስ ድረስ እቈያለሁ” አለው። ጌዴዎንም ወደ ቤት ገባና የፍየል ጠቦት ዐርዶ አዘጋጀ፤ ዐሥር ኪሎ የሚያኽልም ዱቄት ወስዶ እርሾ ያልገባበት እንጀራ ጋገረ፤ ሥጋውን በመሶብ፥ መረቁን በምንቸት አድርጎ በወርካው ሥር ለተቀመጠው ለእግዚአብሔር መልአክ ወስዶ አቀረበለት። መልአኩም “ሥጋውንና እንጀራውን በዚህ አለት ላይ አስቀምጠህ መረቁን በላዩ አፍስስበት” ሲል አዘዘው፤ ጌዴዎንም እንደታዘዘው አደረገ። የእግዚአብሔር መልአክ ቀረብ ብሎ በያዘው በትር ጫፍ ሥጋውንና እንጀራውን ነካ፤ እሳትም ከአለቱ ላይ ተነሥቶ ሥጋውንና እንጀራውን በላ፤ ከዚያም በኋላ መልአኩ ተሰወረ። ጌዴዎን ያየው የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን በተገነዘበ ጊዜ “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! የአንተን መልአክ ፊት ለፊት አይቼአለሁ ወዮልኝ!” አለ። እግዚአብሔር ግን “ሰላም ለአንተ ይሁን፤ አይዞህ አትፍራ፤ አትሞትም” አለው። ጌዴዎንም በዚያ መሠዊያ ሠርቶ “እግዚአብሔር የሰላም አምላክ ነው” ብሎ ሰየመው፤ (ይህም መሠዊያ እስከ ዛሬ የአቢዔዜር ጐሣ ይዞታ በሆነችው በዖፍራ ቆሞ ይገኛል።) በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “የአባትህን ኰርማና ሰባት ዓመት የሞላው አንድ ሌላ ኰርማ ውሰድ፤ አባትህ ለባዓል የሠራውን መሠዊያ አፍርስ፤ በአጠገቡ ያለውን ‘አሼራ’ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላክ ምስል ሰባብረህ ጣል፤ በዚያም የፍርስራሽ ጒብታ አናት ላይ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በደንብ የተስተካከለ መሠዊያ ሥራ፤ ከዚያን በኋላ ሁለተኛውን ኰርማ ውሰድ፤ ሰባብረህ የጣልከውንም የአሼራን ምስል ስብርባሪ በማንደድ ኰርማውን በሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ አቅርብ።” ጌዴዎንም ከአገልጋዮቹ ዐሥሩን ወስዶ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ቤተሰቡንና የከተማይቱን ኗሪዎች ከመፍራቱም የተነሣ ይህን ያደረገው ቀን ሳይሆን በሌሊት ጨለማ ለብሶ ነበር።

መሳፍንት 6:11-27 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

የጌታ መልአክ ዖፍራ ወደምትባል መንደር መጥቶ፥ በአቢዔዝራዊው በኢዮአስ ዕርሻ ውስጥ በሚገኝ በአንድ የባሉጥ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፤ የኢዮአስም ልጅ ጌዴዎን፥ ምድያማውያን እንዳያዩት ተደብቆ በወይን መጭመቂያው ስፍራ ስንዴውን ይወቃ ነበር። የጌታ መልአክ ተገልጦለት “አንተ ኃያል ጦረኛ! እነሆ፥ ጌታ ከአንተ ጋር ነው” አለው። ጌዴዎን መልሶ፥ “ጌታዬ ሆይ ጌታ ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ሁሉ እንዴት ሊደርስብን ቻለ? ‘ጌታ ከግብጽ ምድር አውጥቶናል’ በማለት አባቶቻችን የነገሩን ታምራት የት አለ? አሁን ግን ጌታ ትቶናል፤ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል” አለው። በዚህ ጊዜ ጌታ ወደ እርሱ ዘወር ብሎ፥ “ባለህ ኃይል ሂድ፤ እስራኤውያንን ከምድያማውያን እጅ ነጻ እንድታወጣ የምልክህ እኔ አይደለሁምን? አለው” ጌዴዎንም፥ “ጌታ ሆይ የእኔ ጐሣ ከምናሴ ነገድ እጅግ ደካማ ነው፤ ከቤተሰቤም እኔ የመጨረሻ ነኝ፤ ታዲያ እንዴት እኔ እስራኤልን ላድን እችላለሁ?” አለ። ጌታም፥ “በእርግጥ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ ምድያማውያንንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታቸዋለህ” አለው። ጌዴዎን እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “አሁን በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ በእርግጥ የምታነጋግረኝ አንተ ራስህ ለመሆንህ ምልክት ስጠኝ፤ ተመልሼ እስክመጣ፥ መሥዋዕቴንም አምጥቼ በፊትህ እስካቀርብ ድረስ እባክህ አትሂድ።” ጌታም፥ “እስክትመለስ እጠብቅሃለሁ” አለው። ጌዴዎን ወደ ቤቱ ሄደ፤ የፍየል ጠቦትም ዐረደ፤ አንድ ኢፍ መስፈሪያ ዱቄት ወስዶ እርሾ ያልገባበት ቂጣ ጋገረ። ሥጋውን በቅርጫት፥ መረቁን በምንቸት ይዞ በመምጣት በባሉጥ ሥር ለተቀመጠው አቀረበለት። የጌታ መልአክ፥ “ሥጋውን እርሾ ያልገባበትን ቂጣ ወስደህ፥ በዚያ ዐለት ላይ አኑር፤ መረቁንም በሥጋውና በቂጣው ላይ አፍስስ” አለው፤ ጌዴዎንም እንደ ታዘዘው አደረገ። መልአኩም በያዘው በትር ጫፍ ሥጋውንና ቂጣውን ነካ፤ ከዐለቱም እሳት ወጥቶ ሥጋውንና ቂጣውን በላ፤ ከዚያም የጌታ መልአክ ተሰወረ። ጌዴዎን ያየው የጌታ መልአክ መሆኑን ባወቀ ጊዜ፥ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ የጌታን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና ወዮልኝ” አለ። ጌታም፥ “ሰላም ለአንተ ይሁን፤ አትፍራ፤ አትሞትም” አለው። ጌዴዎንም በዚያ ለጌታ መሠዊያ ሠራ፤ ስሙንም “ጌታ ሰላም ነው” ብሎ ጠራው፤ ይህ መሠዊያ የአቢዔዝራውያን ይዞታ በሆነው በዖፍራ ዛሬም ቆሞ ይታያል። በዚያች ሌሊት ጌታ ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “ከአባትህ መንጋ ሰባት ዓመት የሆነውን ሁለተኛውን ወይፈን ውሰድ፤ አባትህ ለበኣል የሠራውን መሠዊያ አፍርስ፤ በአጠገቡ የአሼራን ዐምድ ሰባብረህ ጣል። በዚህ ፍርስራሽ ጉብታ ላይ ለአምላክህ ለጌታ የሚገባውን መሠዊያ ሥራ። ሰባብረህ በጣልኸው የአሼራ ምስል ዐምድ ሁለተኛውን ወይፈን ወስደህ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ አቅርበው።” ጌዴዎን ከአገልጋዮቹ ዐሥር ሰዎች ወስዶ ጌታ እንዳዘዘው አደረገ፤ ቤተሰቡንና የከተማውን ሰው ስለ ፈራ ይህን ያደረገው ቀን ሳይሆን ሌሊት ነበር።