ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ “ዖፍራ” ተብላ ወደምትጠራው መንደር መጥቶ ከአቢዔዜር ጐሣ የተወለደው የኢዮአስ ንብረት በሆነው የወርካ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፤ የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን ምድያማውያን እንዳያዩት ተሸሽጎ በወይን መጭመቂያው ስፍራ የስንዴ ነዶ ይወቃ ነበር። በዚያም የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና “አንተ ኀያልና ብርቱ ሰው! እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው” አለው። ጌዴዎንም እንዲህ አለው፦ “ጌታዬ ሆይ! ታዲያ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ሁሉ ችግር እንዴት ሊደርስብን ቻለ? አባቶቻችን እንደ ነገሩን እግዚአብሔር ያደርገው የነበረ ድንቅ ሥራ ሁሉ ዛሬ የት አለ? ከግብጽ እንዴት እንዳወጣቸውም ነግረውን ነበር፤ ዛሬ ግን እግዚአብሔር እኛን በመተው እንደ ፈለጉ ያደርጉን ዘንድ ለምድያማውያን አሳልፎ ሰጥቶናል።” ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “ሂድ፤ በዚህ ባለህ ብርቱ ኀይል ሁሉ በመጠቀም እስራኤላውያንን ከምድያማውያን እጅ ነጻ አውጣ፤ እነሆ እኔ ራሴ ልኬሃለሁ” ሲል አዘዘው። ጌዴዎንም “ታዲያ እኔ እንዴት አድርጌ እስራኤልን ላድን እችላለሁ? ወገኔም ከምናሴ ነገድ መካከል እጅግ ደካማ ነው፤ እኔም ከቤተሰቤ መካከል በጣም አነስተኛ ነኝ” ሲል መለሰ። እግዚአብሔርም “እኔ ስለምረዳህ ይህን ማድረግ ትችላለህ፤ ምድያማውያንንም እንደ አንድ ሰው ያኽል አድርገህ ታደቃቸዋለህ” አለው። ጌዴዎንም “በአንተ ዘንድ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፥ አንተ በእርግጥ እግዚአብሔር መሆንህን የሚያስረዳ ምልክት ስጠኝ፤ ምግብ የሚሆን ቊርባን እስካመጣልህም ድረስ እባክህ ከዚህ ስፍራ አትሂድ” አለው። እግዚአብሔርም “አንተ እስክትመለስ ድረስ እቈያለሁ” አለው። ጌዴዎንም ወደ ቤት ገባና የፍየል ጠቦት ዐርዶ አዘጋጀ፤ ዐሥር ኪሎ የሚያኽልም ዱቄት ወስዶ እርሾ ያልገባበት እንጀራ ጋገረ፤ ሥጋውን በመሶብ፥ መረቁን በምንቸት አድርጎ በወርካው ሥር ለተቀመጠው ለእግዚአብሔር መልአክ ወስዶ አቀረበለት። መልአኩም “ሥጋውንና እንጀራውን በዚህ አለት ላይ አስቀምጠህ መረቁን በላዩ አፍስስበት” ሲል አዘዘው፤ ጌዴዎንም እንደታዘዘው አደረገ። የእግዚአብሔር መልአክ ቀረብ ብሎ በያዘው በትር ጫፍ ሥጋውንና እንጀራውን ነካ፤ እሳትም ከአለቱ ላይ ተነሥቶ ሥጋውንና እንጀራውን በላ፤ ከዚያም በኋላ መልአኩ ተሰወረ። ጌዴዎን ያየው የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን በተገነዘበ ጊዜ “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! የአንተን መልአክ ፊት ለፊት አይቼአለሁ ወዮልኝ!” አለ። እግዚአብሔር ግን “ሰላም ለአንተ ይሁን፤ አይዞህ አትፍራ፤ አትሞትም” አለው። ጌዴዎንም በዚያ መሠዊያ ሠርቶ “እግዚአብሔር የሰላም አምላክ ነው” ብሎ ሰየመው፤ (ይህም መሠዊያ እስከ ዛሬ የአቢዔዜር ጐሣ ይዞታ በሆነችው በዖፍራ ቆሞ ይገኛል።) በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “የአባትህን ኰርማና ሰባት ዓመት የሞላው አንድ ሌላ ኰርማ ውሰድ፤ አባትህ ለባዓል የሠራውን መሠዊያ አፍርስ፤ በአጠገቡ ያለውን ‘አሼራ’ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላክ ምስል ሰባብረህ ጣል፤ በዚያም የፍርስራሽ ጒብታ አናት ላይ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በደንብ የተስተካከለ መሠዊያ ሥራ፤ ከዚያን በኋላ ሁለተኛውን ኰርማ ውሰድ፤ ሰባብረህ የጣልከውንም የአሼራን ምስል ስብርባሪ በማንደድ ኰርማውን በሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ አቅርብ።” ጌዴዎንም ከአገልጋዮቹ ዐሥሩን ወስዶ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ቤተሰቡንና የከተማይቱን ኗሪዎች ከመፍራቱም የተነሣ ይህን ያደረገው ቀን ሳይሆን በሌሊት ጨለማ ለብሶ ነበር።
መጽሐፈ መሳፍንት 6 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መሳፍንት 6:11-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos